Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከ40 ልጆች እስከ 850 ሺህ ስደተኞች

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከ40 ልጆች እስከ 850 ሺህ ስደተኞች

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ ነው ይባላል። በእርግጥም እንግዳ ተቀባይ ነው። እንግዳ ተቀባይነቱ ጥቅም በሚያስገኙለት ቱሪስቶች የተገደበ አይደለም። ቱሪስትንማ ማን ይጠላል፤ ገንዘብ አለውና። የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት፣ በችግር ምክንያት ምንም ሳይኖራቸው ከሃገራቸው ወጥተው መጠጊያ የሚፈልጉ ስደተኛ እንግዶችንም ነው።  በአሁኑ ጊዜ ከ850 ሺህ በላይ የኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ ስደተኞች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ልብ በሉ።

ይህ እንግዳ ተቀባይነት የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ መለያ አይደለም። ድሮም የነበረ የህዝቡ ባህል ነው። የጥንቱን እንተወውና ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ያሉትን እናስታውስ። በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1915 ዓ/ም የቱርክ መንግስት በግዛቱ የነበሩ ከ2 ሚሊየን በላይ አርመኖች ላይ የዘር ማጥፋት ጥቃት ፈጽሞ ነበር። ታዲያ በዚህ የዘር ማጥፋት ጥቃት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህል አርመኖች እንደተገደሉ ይገመታል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሃገራቸውን ለቀው ተሰድደው ነበር። አርመኖች ተሰደው ከሄዱባቸው ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ አርመኖች ወደኢትዮጵያ መጥተው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅት እየሩሳሌምን ለመጎብኘት ሄደው በእዚያ ያገኙዋቸውን 40 ወጣት (40 ልጆች) አርመናውያን ወደኢትዮጵያ አምጥተዋቸዋል። እነዚህ አርመናውያን በኢትዮጵያ እንደሃገራቸው መኖረ የሚችሉበት እድል አግኝተዋል ። በተለይ 40 ልጆች በመባል የሚታወቁ ወጣቶች ውስጥ የኢትዮጵያን ሙዚቃ እመርታዊ መሻሻል እንዲያመጣ ያደረጉት  የነረሲስ ናልባንዲያንን ቤተሰብ ያፈራው የመጀመሪያ ትውልድ ይገኝበታል።

40 ልጆችም ሆኑ ሌሎቹ አርመኖች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደስደተኛ ባይተዋር ተደረገው አልነበረም የኖሩት። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፈቀዱት ስራ ላይ ተሰማርተው፣ ሃብት አፍርተው፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተዛምደው ነበር የኖሩት። ትውልደ አርመናውያኑም እንደሃገራቸው በኖሩባት ኢትዮጵያ በስነጥበብ፣ በምህንድስና በኢኮኖሚና በሌሎችም የሞያ መስኮች አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ነርሲስ ናባንዳያን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ግዙፍ የጫማ ፋብሪካ ያቋቋመው ዳርማር፣ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘውን አረቄ ፋብሪካ ያቋቋመው ኤልያስ ፓፓ ሲኖስ፣ አርሾ የህክምና ላብራቶሪ ወዘተ በትውልደ አርመን ኢትዮጵያውያን ከተመሰረቱ ተቋማት መሃከል ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው። ትውልደ አርመኖቹ በኢሉ አባቦር፣ ወለጋና ሌሎችም የሃገሪቱ አካባቢዎች መሬት ተሰጥቷቸው ኢትዮጵያዊውን መሰለው፣ ተጋብተው፣ ወልደው ኖረዋል።

ከአርመናውያን በተጨማሪ በተለያየ አጋጣሚ ወደኢትዮጵያ የመጡ ግሪኮችና ጣሊያኖችም ኢትዮጵያ ውስጥ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ሲኖሩ እንደነበር ይታወቃል።

ሌላው የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነት አጉልቶ የሚያሳየው፣ ምናልባት ከ1930ዎቹ በኋላ ይመስለኛል በኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት በብዛት ወደኢትዮጵያ ለፈለሱ የመናውያን የተደረገው አቀባበል ነው። የመናውያን ማንም ከየት መጣህ፣ አባትህ ማነው . . . ሳይላቸው በመላ ሃገሪቱ በተመቻቸው ቦታ በንግድ ስራ ተሰማርተው ኖረዋል። የችርቻሮ መደብርንና ሻይ ቤትን ለኢትዮጵያውያን ያስተዋወቁት እነዚህ የመናውያን ናቸው። የችርቻሮ መደብር አረብ ቤት ይባል የነበረው በእነዚህ የመናውያን ምክንያት ነው። የመናውያኑ ማንም ፓስፖርት ሳይጠይቃቸው፣ እንደባእድ ሳይገፉ ከህዝቡ ጋር ተቀላቀለው፣ ተጋብተው፣ ወልደው ሃብት አፍርተው ነው የኖሩት። እስከአሁንም ድረስ ዘራቸው ኢትዮጵያዊ ሆኖ በመላው ሃገሪቱ ይገኛሉ።

እርግጥ የወታደራዊው ደረግ መንግስት ወደስልጣን ሲመጣ፣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሃብታቸውን ወርሶ  ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጦ ስለነበረ በተለይ የተሻለ ሃብት አፍርተው የነበሩት ትውልደ አርመን ኢትዮጵያውያን  ወደውጭ ሃገር ሸሽተው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሆነው ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ አለ።

የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት ለማሳየት አሁን ያለው ትውልድ የሚያውቀውን አንድ እውነታ ልጨምር። ከ1982 ዓ/ም ጀምሮ ሶማሊያ በእርስ በርስ ግጭት መንግስት አልባ ስትሆን፣ በርካታ ሶማሌያውያን ወደኢትዮጵያ ሸሽተዋል። ጠረፍ አካባቢ ወዳሉ ከተሞችና የሰደተኛ ጣቢያዎች ከገቡት በተጨማሪ፣ በርካቶቹ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው አዲስ አበባ ገብተዋል። በአዲስ አበባ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤት ተከራይተው፣ ከህዝቡ ጋር ተቀላቅለው ኖረዋል። በርካቶቹ በ1980ዎቹ መጀመሪያ አዲስ መንደር በነበረው ቦሌ ሚካኤል በመባል በሚታወቀው አካባቢ ነበር የሰፈሩት። እነደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሱቆች ከፍተው፣ የሚችሉትን ስራ እየሰሩ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ተቀላቀለው ነው የሚኖሩት። እዚያ ሰፈር ተወልደው ያደጉ ልጆች ከሶማሌያውያኑ ልጆች ጋር አብረው ስላደጉ ሶማሊኛ ቋንቋ ይናገራሉ። እአነዚህን ሶማሌያውያን ወዳጅ ከማድረግ ውጭ ማንም እንደባይተዋር ገፍቷቸው አያውቅም።

የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት የሚያረጋግጡ ሌሎችም ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለማሳያነት ያህል እነዚህ ይበቁናል።

ኢትዮጵያ አሁንም ስደተኞችን በመቀበል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ እስከ አስር ከሚገኙት ሃገራት አንዷ ነች። በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት፣ በኤርትራ ባለው ለከት ያጣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በሶማሊያ ባለው አስተማማኝ ሰላም እጦትና ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት ሳቢያ 850 ሺህ ያህል ስደተኞች ወደኢትዮጵያ ሸሽተዋል። ኢትዮጵያ እነዚህን ስደተኞች ሃገራቸው እንደሚኖሩ ያህል እንዲሰማቸው በሚያደርግ ሁኔታ ተቀብላ እያስተናገደቻቸው ትገኛለች።

ያለንበት ወቅት፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አጋጥሞ የማያውቅ  ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለስደትና ከመኖሪያ አካባቢ ለመፈናቀል የተዳረጉበት ነው። በአሁኑ ጊዜ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ሃገራቸውን ለቀው የተሰደዱና በሃገራቸው ውስጥ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 65 ነጥብ 6 ሚሊየን እንደሚደርስ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል። በዚህ የዓለማችን የወቅቱ ፈተና ከሆነ የስደተኞች ቁጥር ውስጥ የአብዛኞቹ መነሻ፣ በእርስ በርስ ግጭትና በሃያላኑ ሃገራት የእጅ አዙር ጦርነት የምትታመሰው ሶሪያ ነች። 12 ሚሊየን ያህል ሶሪያውያን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቀለዋል። 5 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑት የሃገራቸውን ድንበር ተሻገረው ወደጎረቤት ሃገራትና አውሮፓ ተሰድደዋል። በስደተኞችና በተፈናቃዮች ቁጥር ቀጣዩን ደረጃ የያዘችው ደቡብ ሱዳን ነች። በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ከተቀሳቀሰ በኋላ ባሉት ዓመታት 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎቿ ከመኖያቸው ተፈናቀለዋል። 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ሃገራቸውን ለቀው ተሰደዋል።

እነዚህን ዓለምን ያጥለቀለቁ ስደተኞችን ተቀበሎ በማስተናገድ ከፍተኛውን ድርሻ ከተሸከሙት አስር ሃገራት መሃከል አብዛኞቹ መካከለኛና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ናቸው። ከበለጸጉት ሃገራት በአስሩ ተርታ የገባችው ጀረመን ብቻ ነች። ስደተኞችን ተቀብሎ በማሰተናገድ ቀዳሚዋ ሃገር ቱርክ ነች። ኢትዮጵያ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ 850 ሺህ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያ ስደተኞች ባይተዋርነት ሳይሰማቸው እንደሃገራቸው እንዲኖሩ የማደረግ የቆየ ባህል ያላት ሃገር ነች። በዚህ ምክንያት ከፍቷቸው ከሃገራቸው የወጡ ስደተኞች በኢትዮጵያ መጽናናትን ያገኛሉ። በተለይ ከሃያ ስድስት ዓመት በፊት አብረን የነበረንውና የጋራ ባህል ያለን የኤርትራ ሰደተኞች ሃገራቸው የሚኖሩ ያህል ነው የሚሰማቸው። ሰደተኞች በኢትዮጵያ ሲኖሩ እሰከ ፒ ኤች ዲ ዲግሪ ደረስ የነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ከህዝቡ ጋር ተቀላቀለው እንዲኖሩ ተፈቀዶላቸዋል። የመስራት እድልም ተሰጥቷቸዋል።

ታዲያ ይህን የኢትዮጵያ  የስደተኞች አቀባበልና አያያዝ፣ እንዲሁም ሃገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን የላቀ የዲፕሎማሲ ሚና መነሻ በማደረግ 17ኛው የዓለም ስደተኞች ቀን ሰኔ 13፣ 2009 ዓ/ም በኢትዮጵያ ተከብሯል፤ በተባባሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ውሳኔ። በጋምቤላ በጉኝየል የስደተኞች ጣቢያ በተከበረው በዚህ ዕለት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ፣ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እንዲሁም ሌሎች  ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ  ለስደተኞች በሯን ክፍት በማድረግ ምሳሌ የምትሆን አገር ናት። ኢትዮጵያ የጎረቤት አገር ስደተኞችን  ከማስተናገድ በተጨማሪ  ሥልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ በማስቻል  ስደተኞች  የወደፊት ህልማቸውን እውን  እንዲያደርጉ እገዛ  እያደረገች ነው ብለዋል። ኮሚሽነሩ ከበአሉ በኋላ በአዲሰ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣  ኢትዮጵያ በልማት ስራ ላይ ተጠምዳ እንዲሁም ድርቅ እያጠቃትም ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድበት መንገድ ሊበረታታ ይገባል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ ለስደተኞች ለምታደርገውን እንክብካቤና የስራ እድል ፈጠራ ፖሊሲ እውቅና ሊሰጥ፣ ድጋፍም ሊያደርግ ይገባል። ኢትዮጵያ ስደተኞችን የምታስተናግድበት ፖሊሲ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መልካም ፍላጎት የመነጨ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው ተወያየተዋል። ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአንዳንድ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ወደ ጎረቤት የሚሰደዱ ዜጎች ዘላቂ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል በሚያስችል ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር።

እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ ሸሽተው የተጠጓትን ሰደተኞች እንደሃገራቸው እንዲኖሩ የማደረግ ነባር ባህል ያላት ሃገር ነች። ይሁን እንጂ አሁን ያለውን ወደአንድ ሚሊየን የመጠጋ ሰደተኛ የስራ እድል እንዲያገኙ አድርጋ ማኖር ከአቅሟ በላይ ነው። በመሆኑም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ያስፈልጋታል።

በዚህ ረገድ ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የሚውል 200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሊያበድር መሆኑ ተነግሮ ነበረ። ይህ ጉዳይ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባላውቅም፣ በብድር በሚገኘው ገንዘብ የሚገነቡ የኢንደስትሪ ፓርኮች፣ በሃገሪቱ ከሰፈሩ ስደተኞች መካከል ለ30 ሺህ ያህሉ የስራ እድል እንዲፈጥሩ እንደሚደረግ ነበር የተነገረው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከተጠለሉ ስደተኞች መካከል ለ100 ሺህ ስደተኞች በኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ መኖሩም እንዲሁ ተነገሮ ነበር። 100 ሺህ ሰደተኞች የስራ እድል እንዲያገኙ የማድረግ አጠቃላይ 500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ፣ የአለም ባንክ፣ ብሪታንያና ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ተጨማሪውን ወጪ እንደሚሸፍኑ ተገልጾ ነበር። ይህ የተቀደሰ ሃሳብ ነው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለተፈፃሚነቱ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በአጠቃላይ ሰሞኑን በኢትዮጰያ የተከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በጦርነትና በሰብአዊ መብት ጥሰት ሳቢያ ከመኖሪያ አካበቢያቸው ለተፈናቀሉና ከሃገራቸው ለተሰደዱ ወገኖች ያለንን አጋርነት የምንገልጽበት ነው። ኢትዮጵያ፣ ከአርመናውያኑ 40 ልጆች ጀምራ እስከ አሁን በእንግዳ ተቀባይነት ባህል፣ ሸሽተው ለተጠጓት ወገኖች አጋርነቷን በተግባር ያረጋገጠች ሃገር ነች። አሁን ተሰደው የተጠጓትን ወገኖች እንደቤታቸው ሰረተው ከህዝቡ ጋር እንዲኖሩ ለማድረግ ዓለም አቀፉ ማህበረስብ ድጋፍ ሊያደርግላት ይገባል። ከዚህ በተረፈ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ ምክንያት የሆኑ የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች እንዳይቀሰቀሱ፣ የተቀሰቀሱትም ተቀልብሰው ሰላም እንዲሰፍን መስራት አለበት። አሁን ያለንበት የዓለማችን ሁኔታ የአንዱ ሃገር ችግር የሌላውም መሆኑን በተጨባጭ አረጋገጧል። ስለዚህ የመፈናቀልና የስደት መንስኤዎችን በጋራ እንከላከል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy