Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወደ ሀገር መመለስ ክብር ነው!

0 263

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወደ ሀገር መመለስ ክብር ነው!

                                                        ታዬ ከበደ

የሳዑዲ መንግስት በህገ ወጥነት ለፈረጃቸው የውጭ ዜጎች የሰጠው የምህረት ጊዜ እየተገባደደ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ወገኖቻችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መንገስት ጥረቶችን አድርጓል። ግን ተመላሾቹ በሚፈለገው መጠን እንዳልመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እርግጥ የተሰጠው የ90 ቀናት የምህረት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት በዚህ ብያኔ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። የምህረት ጊዜውን አክብረው የሚወጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ የኢሚግሬሽን ፅህፈት ቤቶች የመውጫ ቪዛ ያገኛሉ።

አሊያ ግን ሃብትና ንብረታቸው ተቀምቶና የተጣለባቸውን ቅጣት በመክፈል ጭምር ከሳዑዲ እንዲወጡ ይደረጋል። በመሆኑም በህገ ወጥ መንገድ በሳዑዲ የሚኖሩ የሀገራችን ዜጎች መንግስት ያመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም ወደ ሀገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። በምንም ዓይነት መልኩ የህገ ወጥ ደላሎችን መደለያ ቃላት መስማት የለባቸውም።

እርግጥ በዚያች ሀገር በህገ ወጥነት የሚኖሩት የሀገራችን ዜጎች ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ የዳረጓቸው ህገ ወጥ ደላሎች ናቸው። እነዚህ ደላሎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ እንደላኳቸው ስለሚያውቁ፤ ዜጎችን ‘ዝም ብላችሁ ኑሩ፣ የሚመጣባችሁ ችግር የለም’ በማለት ሊያዘናጓቸው ይችላሉ። ዕውነታው ግን እንዲያ አይደለም። የተሳሳተ ነው። ሃቁ መንግስት የሚለውና የምህረት ጊዜውን መጠቀም ብቻ ነው።

ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሳዑዲ መንግስት የጉዞ ሰነድን ከመቀማት አንስቶ “ቅጣት ናቸው” ያላቸውን ማናቸውንም ጉዳዩች ይፈፅማል። ይህን በጥሞና ማገናዘብ ይገባል። በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የገቡ የሀገራችን ዜጎች ምክንያታቸውን ወደ ጎን በማድረግ የኢፌዴሪ መንግስትና የሪያድ መንግስት እያከናወኑ ያሉትን ትክክለኛ መንገድ በመከተል ወደ ሀገራቸው መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። በርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት የሚታወቅ ቢሆንም፤ የችግሩ መንስኤ ግን ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም። ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻለና ሰርተው መበልፀግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ ወጥ አዘዋዋሪ ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን በዓይናችን የምናየውና በጆሯአችን የምንሰማው ሃቅ ስለሆነ ነው።

ለነገሩ ማንም ሰው በላቡ ጥሮና ግሮ ህይወቱን ለማሻሻል የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ለዚህ አባባሌ መላው ህዝባችንና መንግስት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያታቸው ለዜጎች ብልፅግና እና ኑሮ መሻሻል መሆኑን በአስረጅነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

በመሆኑም ዜጎች የሳዑዲ መንግስት ያቀረበውን የምህረት ጊዜ ቢጠቀሙ ተገቢውን ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ። አንድም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት አሻራቸው በሪያድ አስተዳደር ስለማይወሰድ ተመልሰው ሊሄዱ ይችላሉ። ሁለትም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተካሄዱ ባሉት የልማት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ሊያድጉ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ።

እርግጥም እዚህ ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ ይቻላል። የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር።

በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊው ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸው የትናንት ትውስታችን መሆኑ የሚካድ አይመስለኝም።

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት፣ ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው። እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም። በአሁኑ ወቅትም በተለይ ወጣቶች መንግስት ካዘጋጀው የ10 ቢሊዩን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። እነዚህ ሁኔታዎችም የሀገራችን መንግስት ምን ያህል የዜጎቹን ሀይወት በመለወጥ ተግባር ላይ መሰማራቱን የሚያሳዩ ናቸው።

ተመላሾቹ ባለፉት 15 አምስት ዓመታት በአስተማማኝ ሰላም፣ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጎዳና ላይ ልትተም መቻሏን ማወቅ አለባቸው። ዛሬ ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ከልማቱ በየደረጃው እየተጠቀሙ ነው። የታገሉለትን ሁለንተናዊ መብቶችንም ዕውን ማድረግም ችለዋል። ለሌሎች ጎረቤት ህዝቦችም የሰላም አለኝታ፣ በልማት የመስተሳሰርና አብሮ የማደግ ተምሳሌቶች ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ ከመሆኑም በላይ መስራት ለሚፈልግ ሰው የተመቻቸ ነው። በሳዑዲ መንግስት በህገ ወጥነት ተፈርጀው የሚኖሩ ዜጎች የዘጠና ቀናቱን የምህረት ጊዜ ገደብን ተጠቅመው ባለው ጊዜ ውስጥ መምጣት አለባቸው። ንብረታቸውን ከመወረስ በማዳን ከፈለጉ ዳግም ወደ እዚያች ሀገር በህጋዊ መንገድ ተመልሰው ሊሰሩ ይችላሉ። መንግስት ይህን ሀኔታ አመቻችቷል።

ይጅ ሁኔታም ተመላሾቹ ሀገራቸው ውስጥ እንዲሰሩና ህይወታቸውን እንዲለውጡ የሚያደርግ ነው። ተመላሾቹ ከመንግስት ድጋፍ በተጨማሪ ያለቻቸውን ጥሪት ከቆጠቡ ህይወታቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ። እንደሚታወቀው ዛሬ የተቀመጠ ገንዘብ ከመንግስት ብድር የሚያላቅቅና በሁለት እግር ለመቆም የሚያስችል ነው፡፡ ወጣቶቹ ዛሬ ከመንግስት የሚወስዱት ገንዘብ ነገ በቁጠባ አድጎ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርጋቸው መሆኑ ርግጥ ነው፡፡

ይህን የቁጠባ ባህል እውን ማድረግ ደግሞ በሂደት ኢንቨስትመንትን ያሰፋል፡፡ ኢንቨስትመንት በየትኛውም ደረጃ ሲሰፋ ደግሞ ለዜጎች የስራ ዕድልን ይፈጥራል፤ ምጣኔ ሃብትንም ያደረጃል፡፡ የስራ ዕድል ሲፈጠርና ምጣኔ ሃብት ሲደረጅ ሀገራችን የጀመረችው የልማት ጉዞ ይጠናከራል፡፡

በጋራ ሰርቶ አብሮ የማደግ ትልምም ይበልጥ እውን ይሆናል፡፡  ታዲያ እነዚህ ሁሉ ጉዳዩች የሚከናወኑት በሀገር ነው። ሁሉም የሚያምረው በሀገር ነው፡፡ ተመላሾቹ እንኳንስ በማደግ ላይ ያለች ሀገር እያላቸው ቀርቶ ሌላም ቦታ ቢሆን ከስጋት ራሳቸውን ነፃ ማድረግ አለባቸው። በመሆኑም ሀገራቸው የምታኮራ ስለሆነች ወደ ምቹዋ ምድር መመለስ ለእነርሱም ቢሆን ኩራት ነው። እናም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ማቅማማት አይኖርባቸውም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy