Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣቶች ተደራጅታችሁ ስሩ   

0 571

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣቶች ተደራጅታችሁ ስሩ   

                                ይነበብ ይግለጡ

ወጣቱ ተሰባስቦ ተደራጅቶ በሰራ ቁጥር ብዙ አይነት ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የልማትና የእድገት ስራዎችን ለመከወን ይችላል፡፡ውጤታማም ይሆናል፡፡በተናጠል የሚሰሩ ስራዎች በብዙ መልኩ ለውጤት አይበቁም፡፡ወጣቱ ትኩስ ኃይል፤ ትኩስ ጉልበትና ትኩስ አእምሮ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ መጠን ሀገሪቷ በያዘቻቸው ሰፊ የልማት አጀንዳዎች ውስጥ ዋናውና ግንባር ቀደም ተሳታፊው የሚሆን  አካል ነው፡፡

የአንድ ሀገር ትልቁ ተስፋ የመጪው ዘመን ባለቤት የሀገሩን እድገት አስቀጣይ ሀገሩንም ጠባቂና ተከላካይ ወጣቱ ነው፡፡የብዙ ሙያዎች የፈርጀ ብዙ እውቀቶች ባለቤት ሀገርን ወደ አዲስ እድገት ምእራፍ የመለወጥና የማሸጋገር ሙሉ አቅም ጉልበት ያለው ነው፡፡

ከቀደመው ትውልድ ከአባቶቹ የሀገር ፍቅርና የስራ ፍቅርን ለሀገር በእውነት መቆምን በስነምግባርና በጨዋነት ታንጾና ዳብሮ መገኘትን ተምሮ ነገ እሱም በተራው ለሚፈጥራቸው ልጆች ትልቁ ሊያወርሳቸው የሚችለው እሱም በወጣትነቱ ዘመን እንደ አባቶቹና አያቶቹ የለፋላትንና የደከመላትን ሀገር ብቻ ነው፡፡

ሀገር ከድሕነት ከተረጂነት ተላቃ ቀድሞ የነበረ ክብርና ዝናዋ ተጠብቆ ተተኪው ትውልድ አንገቱን ሳይደፋ ቀና ብሎ የሚራመድባትን የለማችና የበለጸገች ሀገር መፍጠር የዚህ ወጣት ትውልድ ቀዳሚ ታሪካዊ ድርሻ ነው ፡፡ ዛሬ ላይ ያደጉና የበለጸጉ ሀገራት በሙሉ ሀገራቸውን ያለሙት የለወጡት ያሳደጉት ወደላቀ ምእራፍ ያሸጋገሩት በወጣቶቻቸው ትጋት እውቀትና ጉልበት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ ወጣቶች የልማት ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በአንድነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ሲሉ ከሰሞኑ የገለጹት ለዚህ ነው ፡፡የጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፎች የስራ እድል ስለሚፈጥሩና ፍትሀዊ የኃብት ክፍፍልን ስለሚያረጋግጡ ወጣቶች በአንድነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ሰባተኛው የኦሮሚያ ክልል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሽግግርና የሞዴል አንተርፕራይዞች ሽልማት ስነ ስርዓት በተካሄደበት ወቅት በአገሪቷ እስካሁን ድሕነትን ለማቃለል የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከነዚህ መካከል የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለልና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸው፤በተለይ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፎች ተደራጅተው ሕይወታቸውን እንዲቀይሩና ለሌሎችም የሥራ እድል እንዲፈጥሩ መደረጉ በመልካም ተግባርነቱ ተጠቃሽ መሆኑን፤ ዘርፉ ወጭ ቆጣቢ በርካታ ሰዎችን ማቀፍና ፍትሐዊ የኃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በተጨማሪም በከተሞች ያለውን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል ወጣቶችና ሴቶችን በማቀፍ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ወጣቶች ባለቤት ለሆኑ አገሮች ጥቅሙ የጎላ በመሆኑ ወጣቶች ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በአንድነት ማንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ዘርፉ የሥራ እድል ለማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ባለኃብቶች የሚፈጠሩበት መሆኑን፤በክልሉ ያለውን የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል ለጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ፤ዛሬ ወደ መካከለኛ ባለኃብትነት የተሸጋገሩ ወጣቶች ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ አመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ወጣቶች ተለይተው እስካሁን ከዘጠኝ መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑት ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን  የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አወሉ አብዱ በበኩላቸው ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሆኑ ዘርፎችን በመለየት የመሬትና የብድር አቅርቦት በስፋት እያመቻቸ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡በዚሁ መድረክ 968 ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ መሸጋገራቸው ተገልጾል፡፡ይህ ከፍተኛ ሀገራዊ መነቃቃት የሚፈጥር ስራዎችን ሳይንቁ መስራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያበቃ መሰላል መሆኑን ማሳያም ጭምር ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም  ከ87ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዳዲስ  የሥራ እድል  መፈጠሩን  የአዲስ  አበባ  ከተማ  የጥቃቅንና አነስተኛ  ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ሊበረታታ ሊቀጥል የሚገባው መነቃቃትን በሕብረተሰቡ በተለይም በወጣቱ ዘንድ የሚፈጥር ነው፡፡

በዘንድሮ የበጀት ዓመት  በከተማዋ 117 ወረዳዎች የሚገኙ  ሥራአጥ ወጣቶችና ሴቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሠማራት በተደረገው ጥረት 87 ሺህ  ለሚሆኑ  ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ነው የቢሮው ኃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ ለዋልታ  ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የመደበውን የተንቀሳቃሽ ፈንድ በመጠቀም ለተደራጁ ወጣቶችና ሴቶች የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ በማድረግ  በማኑፋክቸሪንግ፤በኮንስትራክሽን፤በንግድ አገልግሎት፤በከተማ ግብርና፤በብረታ ብረትና በእንጨት ሥራ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡ ፈጥኖ ወደ ስራ በመግባት የወጣቱንና የሕብረተሰቡን ጥያቄና የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ያለው ተስፋ ሰጪ ስራ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡የዘገዩ በቀጥታ ወደስራው ያልገቡ ክልሎች ደግሞ ለምን ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡ተጠያቂነትም ይከተላል፡፡

በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች ተመራቂ  ወጣቶችን እንዲሁም  ቤታቸው የነበሩትንና ያለሥራ የተቀመጡ ወጣቶች ጭምር አጭር ሥልጠና ተሠጥቷቸው በሥራ እድል ፈጠራው ተጠቃሚ  እንዲሆኑ መደረጉም ትልቅ ስራ መሰራቱን ያሳያል፡፡ጅምሩ በብዙ ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባዋል፡፡

የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ከብድር ጀምሮ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎች  ተመቻችቷላቸዋል፡፡በአብዛኛው  ወጣቶቹ ሕብረተሰቡን በሚያሳትፉ ሥራዎች  ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ  የበጀት  ዓመቱ  በአጠቃላይ 103ሺህ 576 ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሠማራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ለዋልታ የገለጸ ሲሆን ይህ አፈጻጸም ወደ መሬት ሲወርድ የበለጠ ውጤታማ ስራ በወጣቱና በሕብረተሰቡ ውስጥ ለመስራት የሚያስችል ትልቅ ለውጥም የሚያስገኝ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡በሚዲያውም ሰፊ ሽፋን ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy