Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴ ጉዟችን የስበት ማዕከል!

0 462

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴ ጉዟችን የስበት ማዕከል!

                                               ሰለሞን ሽፈራው

አንድ  ሀገር ዳር ድንበሯ ከውጭ በሚመጣ  ወራሪ ጠላት ሳይደፈርና ሕዝቦቿም ለባዕዳን የቀኝ አገዛዝ ቀምበር ሳይዳረጉ የኖሩበት የነፃነት ታሪክ ስላላት ብቻ ሀገራዊ ክብሯን አስጠብቃለች ማለት ይችላልን? በኢኮኖሚያዊ አቅም እራሳቸውን ያልቻሉ ሀገራት ስለሀገራዊ ክብር መናገራቸው ‹‹ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት›› ከማሰኘት ያለፈ ትርጉም አይኖረው ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች በበርካቶች ዘንድ ሲነሱ ይደመጣል፡፡

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪካቸው ዓለምን ያስደመመ ገናና ስልጣኔ ተቀዳጅተው እንደነበር የሚነገርላቸው፣ ነገር ግን አንድ ወቅት ባጋጠማቸው ታሪካዊ ዕክል ለውድቀት ተዳርገው ሕዝቦቻቸውን መመገብ እስኪያቅታቸው ድረስ በድህነትና በኋላቀርነት የሚማቅቁ ሀገራት ዜጎች ዘንድ ይህ ዓይነቱ ሀገራዊ ክብርን የሚመለከት ጥያቄ በስፋት እየተነሳ የመወያያ አጀንዳ ሲሆን ማስተዋል የተለመደ ነው ማለት ያቻላል፡፡ ለምሳሌ ቻይናውያን  ብንወስድ ከዛሬ ሀምሳ ዓመት በፊት ሀገራቸው የነበረችበትን እጅግ በጣም የከፋ ድህነትና በኋላቀርነት ቀደምት የቻይና ትውልዶች ካለፉበት የጥንታዊ ስልጣኔ ታሪክ ጋር እያነፃፀሩ ሀገራዊ ክብራቸውን ማስመለስ ስለሚችሉበት የህዳሴ መንፈስ አዘውትረው ይመክሩ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከዚያም ቻይናውያን ዳግም የታላቅ ሕዝብነት ክብራቸውን ለመቀዳጀት እጅ ለእጅ ተያይዘው በቁርጠኝነት ከተነሱ፣ ያለሙትን እውን ከማድረግ የሚያግዳቸው ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር አመኑ፡፡ ያመኑበትን የጋራ አጀንዳ ቀርፀው በፈረጀ ብዙው ድህነትና ኋላቀርነት ላይ ዘመቱ፡፡ በዚህ ዘመቻ የአዲሲቷን ቻይና መፈጠር አጭር ሊባል በሚችል ጊዜ ውስጥ ማብሰርም ቻሉ፡፡ በእርግጥም የዛሬዋ ቻይና ለዳግም ልደት የበቃችበት ሁኔታ ለማመን እስኪያዳግት የተፋጠነ መሆኑን ዓለም  ተስማምቶበታል፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም  የቻይና ሕዝብ ሀገራዊ ክብሩን ለማስመለስ ሲል በፍፁም የቁርጠኝነት መንፈስ ድህነትና ኋላቀርነት ላይ በመዝመቱ ነው፡፡

ከዚህ መሰረተ ሃሳብ በመነሳት እያንዳንዱ ቻይናዊ ዜጋ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ የትም ቢሰደድ እንኳን በያለበት ሆኖ ሀገራዊ ክብር የማስመለሱን ተልዕኮ ፈፅሞ መዘንጋት እንደማይኖርበት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ችለዋል ፡፡ እናም በዓለም ዙሪያ ተበትነው እንደየሙያቸው ሥራ ያገኙ ቻይናውያን ሁሉ እያንዳንዱን የዕድገትና የብልፅግና ተሞክሮ ለሀገራቸው የፀረ ድህነት ትግል ወይም የህዳሴ ጉዞ መፋጠን በሚያመች መልኩ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ከማመቻቸት የቦዘነበት አጋጣሚ እንዳልነበረ የቻይና ታሪካዊ እውነታ ያረጋግጣል፡፡

ከዚህ አኳያ በወቅቱ የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ወደ በለፀጉት የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት በተለይም ደግሞ ወደ አሜሪካ ለመሰደድ ከተገደዱ እጅግ በርካታ ቻይናውያን ዜጎች መካከል ጥቂት የማይባሉ በነበሩበት የሥራ መስክ የሀገራቸውን ክብር ለማስመለስ ይረዳል ሚሉትን የዘመኑን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት ሁሉ ‹‹እየኮረጁ›› በመላክ የፈፀሙትን አስደናቂ ገድል እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል፡፡  የዛሬዋ ቻይና እንደ ሀገር  የመጣችበትን የህዳሴ ጉዞ የሚያመለክቱ የታሪክ ሠነዶች እንደሚመሰክሩት፣ የቻይና የዳግም ልደት ጉዞ ያን ያህል ተአምር የሚያሰኝ አመርቂ ውጤት ሊያመጣ የበቃው፣ በዋነኛነት ዩ ኤስ አሜሪካና እንዲሁም በአንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ውስጥ እየኖሩ የተለያየ ሙያ ለመማር የቻሉ ቻይናውያን ዲያስፖራዎች ያለ የሌለ ዕውቀታቸውን አሟጥጠው በመጠቀም ዘመናዊ ሥልጣኔ የፈጠረውን  ቴክኖሎጂ ወደ ሀገራቸው ለማሸጋገር በመቻላቸው ጭምር ነበር፡፡

በዚህ ረገድ የነጃፓንንና ቱርክን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስንመለከትም ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ለምታካሂደው ፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ መሳካት ጠቃሚ ልምዶችን ልንቀስምባቸው የምንችል ሀገራዊ ክብርን የማስመለስ ትግል ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ሶስት ሀገራት (ቻይናን፣ጃፓንንና ቱርክን) ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላቸው እውነታ እናገኛለንና ነው፡፡ ለምሣሌ ጃፓኖች ክብራቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ያላቸው ዝግጁነት ከኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚያመሳስላቸው ታዋቂው የሥነ-ፅሁፍ ሰው አቶ ከበደ ሚካኤል ‹‹ጃፓን እንደምን ሰለጠነች›› በተሰኘ ታሪክ ቀመስ መፅሐፋቸው ላይ ያሰፈሩት ዝርዝር ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ብቻም ሳይሆን ከቱርክና ከቻይና ጋር ጭምር የሚያመሳስላት መሰረታዊ ምክንያት የየሀገራቱ ሕዝቦች ከጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪካቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የታላቅነታቸው መገለጫ ማንነት ወይም የመንፈስ ፅናትና የልብ ኩራት ያልተለያቸው ሆነው መገኘታቸው ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ይህን የአራቱ ሀገራት ሕዝቦች ተመሳስሎ አምኜ እቀበል ዘንድ የረዱኝን የመረጃ ግብአቶች ያገኘሁትም ከላይ የጠቀስኩትን ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል  መፅሐፍ ጨምሮ፤ ማኦ ሴቱንግ የአዲስቷን ቻይና ፅኑ መሰረቶች ስለጣለበት የሀገሩን ብሔራዊ ክብር ከነጥንታዊ ዕሴቶቿ ለመመለስ ያለመ የባህል አብዮትና እንዲሁም የዛሬዋ ቱርክ አባት ተደርጎ የሚቆጠረው ፕሬዝዳንት ከማል አታ ቱርክ ወደ ስልጣን በመጣበት የታሪክ አጋጣሚ ያቺን ሀገር ከመበታተን ለመታደግ ስላደረገው ጥረት ከተፃፉ ድርሳናት ነው፡፡

የእነዚህ ሶስት ሀገራት የወድቆ መነሳት ታሪካዊ ዳራ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ከኢትዮጵያችን ነባራዊ እውነታ ጋር የሚመሳሰልበት ምክንያት የመኖሩ ጉዳይ የሚያከራክር እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ምንም እንኳን የተመሳስሎው ይዘት እንደየሀገራቱ ታሪካዊ ሁኔታ መጠኑም ሆነ ይዘቱ ሊለያይ እንደሚችል መገመት ባያዳግትም፣ መሰረታዊ የሚባሉ ዓለም አቀፍ የወድቆ መነሳት ታሪክ ተወራራሽ ባህሪያትን እንደሚጋሩ ግን የሚያከራክር አይደለም፡፡

በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኝ የማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር ሕዝብ በቀደመ ታሪኩ የገናና ሥልጣኔ ባለቤት እንደነበረና አንድ ወቅት በተከሰተ ታሪካዊ ስህተት ወይም እክል ምክንያት ከታላቅነቱ ከፍታ ላይ ቁልቁል  ወርዶ ሀገራዊ ክብሩን እስከማጣት እንደደረሰ በቅጡ የሚያስገነዝበው መንግስት ያግኝ እንጂ፤ ያኔ እንደ እሳት በሚፋጅ የቁጭት ማዕበል ተነሳስቶ ሀገራዊ ክብሩን ለማስመለስ መዝመቱ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ ይህ የሚሆነውም በሁለት ተያያዥነት ባላቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡

የመጀመሪያው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በቀደም ታሪካቸው የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የነበሩ ሕዝቦች ሁሉ የታላቅነታቸውን ከፍታ ጨርሰው እንዳይዘነጉ የሚያደርጋቸው የመንፈስ ኩራት አይለያቸውም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በተለይም እንደዚህ ዓይነት የታላቅ ማንነት መገለጫ የሆነ መንፈሳዊ ኩራት ያልተለያቸው ሕዝቦች ሀገራዊ ክብራቸውን በድህትና በኋላቀርነት እንደተቀሙ እርግጠኛ የሆኑ ቀን ፈፅሞ እንቅልፍ አይወስዳቸውም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ እናም እውነታው በተገለፀላቸው ልክ እንደህብረተሰብ የፀረ ድህነት ክንዳቸውን አስተባብረው ሀገራዊ ክብራቸውን ለማስመለስ እንደሚዘምቱ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥም ደግሞ ይህን ሃሳብ የሚሰነዝሩ ወገኖች እውነት እንዳላቸው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ከምናየው ሀገራዊ ክብርን ለማስመለስ ያለመ የሕዝብ ቁጭትና ቁጭቱ ከወለደው ፈረጀ ብዙ የህዳሴ ንቅናቄ መረዳት ይቻላል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ በመረረ ቁጭት አቅማችንን ሁሉ አስተባብረን የተያያዝነው የህዳሴ ጉዞ ግቡ ድህነትና ኋላቀርነት  የቆየውን ሀገራዊ ክብራችንን ማስመለስ እንደመሆኑ መጠን፣ እያንዳንዳችን እንደዜጋ ልናበረክት የምንችለውን ገንቢ አስተዋፅኦ ሁሉ ከማዋጣት መቆጠብ የለብንም ፡፡

‹‹አገሬን እወዳለሁ፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ክብር እጨነቃለሁ›› ወዘተ ማለት ብቻውን የዜግነት ግዴታን ለመወጣት በቂ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የዜግነት ግዴታ ማለት ለሀገራዊ ክብር ሲባል ምትክ የለሿን የራስ ህይወት ለመስጠት እስከ መወሰን የሚያደርስ ጥልቅ ትርጉም አለውና ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውን ከላይ እንደተመለከተው የቻይናውያን የዳግም ልደት ገድል ዓይነት ዜግነታዊ ግዴታችንን መወጣትና የሀገራችንን ክብር ወደ ቀድሞው የታላቅነት ከፍታው ለመመለስ በሚደረገው ርብርብ የየራሳንን አኩሪ ታሪክ እየሰራን እናልፍ ዘንድ ይህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይጋብዛልና ልብ ያለው ልብ እንዲል ደግመን- ደጋግመን እንናገራለን፡፡

እንኳን ሀገርን ያህል ነገር እጇን ለምፅዋት ስትዘረጋ ማየት፣ አንድ ወቅት ላይ ጥሮ-ግሮ ባፈራው ሀብት-ንብረት ‹‹ኖሮ-ክብር!›› የሚያሰኝ ስኬታማ ህይወት ሲኖር የምናውቀው ግለሰብ ከጊዜ በኋላ በገጠመው የአግኝቶ ማጣት ዕክል የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ ሲቸገር ማየት ምንኛ ልብን ሊነካ እንደሚችል ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የዚያኑ ያህልም ሰውዬው በቀደመ ታሪኩ ይሰጠው የነበረውን ማህበራዊ ከበሬታ ስለሚያጣ፣ ቢናገር የማይደመጥ፣ ቢጠይቅ ምላሽ የማያገኝና ሲጮህ ውሎ ቢያድር ድምፁ የማይሰማ ምስኪን ፍጡር መሆኑ እንደማይቀር የገሃዱ ዓለም ነባራዊ እውነታ የሚያረጋግጥልን ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን የሚያህል ለሰው ዘር የስልጣኔ ጉዞ ግንባር ቀደም ፋና እንደወጋች የተመሰከረለት ጥንታዊት ሀገርና ኢትዮጵያዊነትን ያህል ለመላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ነፃነት እንደተምሳሌት የሚቆጠር ታላቅ ማንነት፣ ድህነትና ኋላቀርነት በተሰኘ ክፉ ጠላት ክብራቸው ተዋርዶ፣ እንዲሁም  እያየ ጉዳዩ እምብዛም ቁብ የማይሰጠው ‹‹ምሁር›› ዜጋ ‹‹ሀገሬን እወዳለሁ›› ቢል በየትኛው ሞራላዊ ብቃቱ ነው ሊያሳምነን የሚችለው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ህልውናቸውን ለማረጋገጥ የተለሙት ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ አማካኝነት፣ ከፈርጀ ብዙ ድህነትና ኋላቀርነት ጋር የሞት ሽረት ትግል በገጠሙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት እንኳን ነባራዊውን እውነታ አምኖ ላለመቀበል ባለመ የመታበይ መንፈስ ዳር ቆመው መመልከታቸው አልበቃ ብሎ፣ ጭራሽ ከእነርሱ ወዲያ ስለኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነት ክብር የሚጨነቅ እንደሌለ በየአደባባዩ ሲናገሩ የሚደመጡ  ‹‹ምሁራን›› ዜጎች ጥቂት አይደሉምና ነው፡፡ በተረፈ ግን አሁን ላይ ከሳኡዲ ዓረቢያ የስደት ኑሯቸው እየተመለሱ ያሉትን ወገኖቻችንን ጨምሮ፤ ሌሎችም በዓለም ዙሪያ ተበትነው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ ስለ ሀገራዊ ክብር ጥልቅ ትርጉም ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረጉን ጉዳይ የሚመለከተው የመንግስት አካል ሊያስብበት ይገባል ፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy