Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሌ/ጄኔራል ፃድቃን ሃሳቦች ገብቶኛልም፤ አልገባኝምም

0 562

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የሌ/ጄኔራል ፃድቃን ሃሳቦች ገብቶኛልም፤ አልገባኝምም!
ለገሠ ዋቅጅራ
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ግለሰቦችን ሃሳቦች እያንሸራሸረ ነው። እንደ አንድ ለሀገር የዴሞክራሲ ግንባታ የሚተጋ ተቋም፤ ጋዜጣው የሃሳቦች መንሸራሸሪያ መድረክ (forum of discussion) ሆኖ ማገልገሉ ‘በርታ፣ ተበራታ’ የሚያሰኘው ሆኖ አግኝቸቼዋለሁ።

ይህም አዲስ ዘመን በተግባር የህዝብ ጋዜጣ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል። በቅርቡም የቀድሞው የህወሓት ታጋይና ከፍተኛ አመራር እንዲሁም ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ለአስር ዓመታት (ማለትም ከ1983 ዓ.ም እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ) የመከላከያ ሰራዊቱ ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጡረተኛው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይን በፖለቲካ አምዱ ላይ እንግዳው በማድረግ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው፣ በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዩች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል።

እርሳቸውም በእነዚህ ጉዳዩች ዙሪያ የሚያምኑበትን፣ መሆን ነበረበት አሊያም ወደፊት መፈፀም አለበት ያሏቸውን ሃሳቦች ገልፀዋል። በቅድሚያ እርሳቸውና ሌሎች በ1993 ዓ.ም በህወሓት/ኢህአዴግ የመሰንጠቅ አደጋ ወቅት በአንጃነት ተፈርጀው ከድርጅቱም ይሁን ከሰራዊቱ በጡረታ የተሰናበቱ ቀደምት ታጋዮች እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ያፈራቸውና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በተለያዩ ወቅቶች በመገናኛ ብዙሃን ላይ ድምፃቸውን በማሰማት ያሻቸውን መናገራቸው፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን የአመለካከት ብዝሃነት የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ሊጎለብት፣ ሊያድግና ተበረታቶ ሊቀጥል የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ሳልጠቅስ ለማለፍ አልሻም።

እናም ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ያነሱትንና ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዩች ዙሪያ እንደ ማንኛውም ‘በግል የንግድ ስራ’ እንደሚተዳደር ዜጋ ‘የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል’ በማለት በጋዜጣው ላይ ያንሸራሸሯቸውን ሃሳቦች አከብራለሁ። ይሁን እንጂ ሃሳባቸው አደነጋግሮኛል። አንዳንዱ እኔ በግሌ ከማምናቸው ጉዳዮች ጋር የሚመሳሰልና ትክክል ናቸው ብዬ የማምንባቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ትክክለኛና ተገቢ ያልሆኑ፣ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱና ምን ለማለት እንደፈለጉ ማብራሪያ የጎደላቸው ናቸው። ለዚህም ነው — በርዕሴ ላይ ‘…ገብቶኛልም፤ አልገባኝምም’ ያልኩት።
በቅድሚያ ከገቡኝ ሃሳቦቻቸው ልነሳ።

ርግጥ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ካነሷቸው ሃሳቦች ውስጥ የገቡኝ ጉዳዮች ብዙ አይደሉም። ጥቂት ናቸው። የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲው ሲወጣ፤ “…በሙያው ላይ የተለያየ ዕውቀት ያላቸው ሃሳብ ሊሰጡ የሚችሉ የፖሊሲውን ጥልቀትና ስፋት በሚፈለገው ደረጃ ሊያዳብሩ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና ግለሰቦች መሳተፍ አለባቸው። እንዲህ አይነት ሰነድ የቱንም አይነት ችሎታ ቢኖርም በጥቂት ግለሰቦች ሊሰራ አይችልም።…” ያሉት እንዲሁም ፖሊሲው ከወቅታዊ ሁኔታ አኳያ እየታየ መከለስ እንዳለበት፣ የኤርትራ ህዝቦችን ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው ጋር አንድ እንደሆኑ፣ በተዘዋወሪም ቢሆን አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የኤርትራ መንግስት እስካለ ድረስ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሊሻሻል እንደማይችል የገለጿቸውን ሃሳቦች እጋራለሁ።

ከዚህ ውጭ ከላይ እንዳልኩት አብዛኛዎቹ ሃሳቦቻቸው የተሳሳቱ፣ እርስ በርሳቸው የሚጋጩና ራስን ከተጠያቂነት የማሸሽ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው። ርሳቸው በተለይም ፖሊሲውን “…የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ቁምነገር እንዲኖረው አወጣጡ፣ ይዘቱና አስተዳደሩ መስተካከል አለባቸው።…” በማለት ከገለፁበት አግባብ ውስጥ፤ “ቁም ነገር እንዲኖረው…” የሚለው ሐረግ ተገቢ አይመስለኝም። ፖሊሲውንም የሚገልፅ አይደለም። አንድ በስራ ላይ ያለን ጉዳይ “ቁም ነገር እንዲኖረው…” ከተባለ፤ ነገርዬው ‘ቁም ነገር የለውም’ የሚል ግንዛቤን የሚያሲዝ ነው።

ዳሩ ግን ፖሊሲው ቢያንስ በሰነድነት ቀርቦ ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 14 ዓመታት በግልፅ የሚታይና የሚዳሰስ ውጤት አምጥቷል። ራሳቸው ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ስለ ፖሊሲው ወጤታማነት ተጠይቀው “…ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ተቀባይነት በጎረቤቶቻችን እያደገ መጥቷል። በመሰረቱ ፖሊሲው በአገር ውስጥ ላለው ሥራ ደጋፊ እንዲሆን ተደርጎ ተቀርጿል። ከመንግሥት መዋቅር የወጣ መረጃ ባይኖረኝም፤ በውጭ እንደማየው ለውጥ አምጥቷል የሚል እምነት አለኝ።…” እያሉ መልሰው በተቃራኒ አስተሳሰብ “ፖሊሲው ቁም ነገር እንዲኖረው…” በማለት ቁም ነገር ያልፈፀመ አድርጎ ለመተቸት መሞከራቸው አሁን ላይ ቃለ-ምልልሱን መለስ ብለው ቢያዩት ከራሳቸው ጋር እሰጥ-አገባ ውስጥ የሚገቡ ይመስለኛል—ሃሳባቸውን እንዲያው ለመቃወም ብቻ ብለው ካልሰነዘሩት በስተቀር።
በእኔ እምነት በይፋ ተሰንዶ ህዝብ ካወቀው ቢያንስ 14 ዓመታትን የተጓዘችበት የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲ በሀገራችን የገፅታ ግንባታ ላይ ለውጥ ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣናው ሀገሮች፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለይም በኢጋድ አማካኝነት የምታከናውነው ግንባር ቀደም የሰላም፣ የልማት ትስስር፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባሮች ከፃድቃን ገብረተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) የሚሰወር ጉዳይ አይመስለኝም። ምክንያቱም ከህወሓት/ኢህአዴግ የተሃድሶ ማጥራት በኋላ ርሳቸው በአንጃነት በመፈረጃቸው አሜሪካ ድረስ ሄደው በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በፀጥታ ጉዳይ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መስራታቸውን እንዲሁም ማን እንደመደባቸው ባላውቅም ‘ለስምንት ዓመታት የደቡብ ሱዳን የፀጥታ አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ’ በማለት ለጋዜጣው ስለገለፁ ለእውነታው ቅርብ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ስለምገምት ነው።
ጡረተኛው ጄኔራልን የመሳሰሉ ቀደምት ታጋዮችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ውድ ልጆች በከፈሉት መስዋዕትነት እውን የሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ፤ ከራሷ አልፋ የቀጣናው ሀገራትን ሰላም በማስጠበቅ እየተጫወተች ያለችውን ሚናም የሚዘነጉት አይመስለኝም። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለይም ርሳቸው አማካሪ የነበሩባት የደቡብ ሱዳን ወንድም ህዝብ በእርስ በርስ ጦርነት ሲታመስ፣ ሶማሊያዊያን ወንድሞቻችን በአሸባሪው አልሸባብ ሳቢያ የስደት ፅዋን ሲጋቱ ኤርትራዊያን በአምባገነኑ ሻዕቢያ አማካኝነት ሀገራቸውን ጥለው ሲመጡ ተቀብላ ያስተናገደችውና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆት የተቸራት ሀገር መሆኗን ፃድቃን ገብረተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) የማያውቁት ነገር አይደለም።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ከቀጣናው አልፋ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ህዝቦች ድምፅ እስከመሆን መድረሷን ለርሳቸው መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይሆንብኛል። ለዚህም ሀገራችን በአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካዊያንን ፍላጎት በማንፀባረቅ፣ አፍሪካን በመወከል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሀገር ሆና መመረጧን፣ በተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባል መሆኗንና በዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም አማካኝነት ውስብስቡን የዓለም የጤና ችግር ለመፍታት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቦታን መያዟ ፖሊሲው ያስገኛቸው ውጤቶች ናቸው። ምን ይህ ብቻ! ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን “…በመንግስት መዋቅር ባይገለፅም…” ቢሉም፤ ፖሊሲው በወታደራዊና በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ እነ ፃድቃን ገብረ ተንሳይን (ሌ/ጄኔራል) ካሰናበተው ተሃድሶው ማግስት ወዲህ ባሉት ጊዜያት ፖሊሲው ስኬቶችን ማስመዝገቡ ተገልጿል። ያም ሆኖ እነዚህ ስኬቶች ሀገራችን ባከናወነችው ጠንካራ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ አማካኝነት እንጂ በፀሎት የተገኙ አለመሆናቸውን እርሳቸው ይስቱታል ብዬ አላስብም።

የእነዚህ ስኬቶች ባለቤት የሆነው ፖሊሲ በምን ዓይነት ዕይታ “ቁም ነገር እንዲኖረው…፣ ጅምር ነው” ሊባል እንደሚችል የሚያውቁት የሃሳቡ ባለቤት ብቻ ይመስሉኛል።
ፖሊሲው “ጅምር ነው” ከተባለም ምናልባትም እነዚህን ስኬቶች ካለማገናዘብ የመጣ ሊሆን ይችላል።

እንደሚታወቀው ሀገራችን ዛሬ የምትመራበት የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲ በሰነድ መልክ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ የሆነው በ1995 ዓ.ም ቢሆንም፤ ፅንሰ-ሃሳቡ ግን በትጥቅ ትግሉ ወቅት በአህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚታመንበት፣ ከዚያም እርሳቸው የመንግስትና የመከላላከያ ባለስልጣን በነበሩባቸው የሽግግር መንግስቱ ወቅት ጭምር እየተሰራበት የመጣ መሆኑን ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ይዘነጉታል ብዬ አላስብም።

በመሆኑም ጉዳዩን እንደማያውቁት በመምሰል “ከደሙ ንፁህ ነኝ” በማለት “የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት አገራችን የምትመራበት የውጭና የደህንነት ጉዳይ ፖሊሲና ስልት መዘጋጀት እንዳለበት በአንዳንዶቻችን ይነሳ ነበር።…” የሚለው ሃሳባቸው በምንም ዓይነት ስሌት ሚዛን የማይደፋ ብቻ ሳይሆን፤ ተገቢ ያልሆነ ድምዳሜም ጭምር ነው። ምክንያቱም ይህ ሁኔታ መስተካከል ካለበትም ግለሰቡ ዛሬ ላይ ሳይሆን በወቅቱ በማንሳት ከፍ ሲልም የራሳቸውን መነሻ ፖሊሲ በማቅረብ ሊሞግቱ በተገባ ነበር። ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በፀጥታ ጉዳይ ሌላ ሀገር እያማከርኩ ነበር እያሉን፤ የሀገራቸውን ጉዳይ ግን ከ15 ዓመት ዝምታ በኋላ ዛሬ ላይ ለማንሳት መሞከራቸው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። እንዲያውም ‘በፖሊሲው ላይ እኔን የመሳሰሉ ሰዎች ስላልተሳተፉ ትክክል አይደለም’ የሚል አንድምታ ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ርሳቸው ገና ከጥንስሱ ጀምሮ የሚያውቁትን አቅጣጫ አላውቅም ማለታቸው መብታቸው ቢሆንም ቅሉ፤ ከዚያም በኋላ ሀገራችንን የተደማጭነት ማማ ላይ የሰቀላትን ፖሊሲ “መውጣቱ ጥሩ ጅምር ነው” በማለታቸው አንድ ሰው ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን የፖሊሲውን ውጤቶች ለመቀበል አልፈለጉም ብሎ እንዳያስብ፤ መለስ ብለው “…ውጤታማ ነበር” ያሉትን ሲመለከት ሃሳባቸው እርስ በእርሱ የሚጣረስ መሆኑን ያውቃል። ‘ለምን እኔ ከመንግስት ስልጣን ከተሰናበትኩ በኋላ የተዘጋጀን ሰነድ እውቅና እሰጣለሁ’ በማለት ላይ መሆናቸውንም ይገነዘባል። ይሁንና ሀገራችን አሁን ያለችበት የተደማጭነት ደረጃ በራሱ የፖሊሲውን ውጤታማነት አፍ አውጥቶ ስለሚገልፅ በርሳቸው የሚጋጭ አባባል እውነታውን ይስታል ተብሎ አይታሰብም።

ርግጥ ርሳቸውም ይሁኑ እኔ እንደማምነው ማንኛውም ፖሊሲ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር እየታየ እንደየሁኔታው ሊሻሻል ይችላል። ይገባዋልም። ፖሊሲ በሰዎች ስብስብ አማካኝነት የሚወጣ እንጂ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቃል አንድም ቃል የማይቀነስበት፣ አንድም ቃል የማይጨመርበት ተብሎ የማይነካ አይደለም። ዓለማችንና አካባቢያችን በፍጥነት የሚቀያየሩ፣ ትናንት የነበረው የሀገራት ቅርፅ በአንድም ይሁን በሌላ ሁኔታ ሊቀየር መቻሉና የአክራሪነትና የሽብርተኝነት አደጋዎች የዓለማችን ስጋት እየሆኑ መምጣታቸው መንግስታት ያፀደቁትን ፖሊሲዎች እንዲከልሱ ምክንያት ይሆናቸዋል።

ሆኖም በተለይም በፈጣን ልማት ላይ ለምትገኘው ሀገራችን ፖሊሲው ርሳቸው እንደሚሉት በጦርነት የሌላ ሀገርን መንግስት እስከመጣል የሚደርስ መሆን አለበት ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን የኢትዮ-ኤርትራን ጉዳይ ለመፍታት “…ወታደራዊ አቅምን በመጠቀም ጭምር እድሜው የሚያጥርበትን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ ነው።…” በማለታቸው ነው። ርግጥ የአስመራው አስተዳደር ዕድሜ እንዲያጥር የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ የለም—ከሌሎች የሀገራችንን ብልፅግና ከማይሹ ወገኖች ጋር በማበር የኢትዮጰያን ሰላም ላመወክ ያልፈነቀለው ድንጋይ አለመኖሩ ይታወቃልና። ሆኖም የትኛውም የዓለም ህግ ኤርትራንም ሆነ ሌላውን ሀገር በኃይል እንድንወር የሚፈቅድልን እንዳልሆነና የኢፌዴሪ መንግስትም ርሳቸው በሚገርም ሁኔታ “ጅምር ነው” ባሉት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ሀገራችን የሰላም ፖሊሲ የምትከለም መሆኑን ርሳቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ነው።

ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በሚከልስበት ወቅት ማድረግ አለበት ያሉትም ነገር አዲስ ነገር የለውም። ምክንያቱም ምናልባት የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲውን ሲከልስ፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጅነትን ይበልጥ በማቀራረብ የኤርትራ ህዝብ የኢሳይያስ መንግሥት ከአሰባሰባቸው ቡድኖች ተነጥሎ እንዲወጣና ህዝቡም የራሱን የወደፊት ጥቅም የሚያይበትን መንገድ እንዲከተል እንዲሁም እድሜው የሚያጥርበትን መንገድ ማስቀመጥ ያስፈልጋል በማለታቸው ነው። በእኔ እምነት እነዚህ የርሳቸው እምነቶች አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ላለፉት ዓመታት ሲሰሩባቸው የነበሩ ናቸው።

የኢትዮጵያን ህዝብ ወንድሙ ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ለማቀራረብ በኤርትራ መንግስት ከሚደርስባቸው ግፍ ለመታደግ መጠለያ በመስጠት እንዲሁም ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሀገራቸው መሆኗን እንዲያውቁ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የከፍተኛ ትምህርት በነፃ እንዲያገኙ እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም በተግባር የተገለፀ እውነታ ነው። እናም ‘ጀኔራል መኮንኑ ከዚህ አኳያ ያቀረቡት አዲስ ነገር ምንድነው?’ ብዬ ራሴን ስንጠይቅ፤ ምላሹ ‘ምንም’ የሚል ይሆንብኛል። ‘ለምን?’ ቢሉ፤ ርሳቸው ያሉትን ጉዳዮች የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝብ ፖሊሲውን መሰረት አድርገው እየከወኑት በመሆኑ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም የአንድ ሀገር መንግስት ዕድሜው እንዲረዝምም ይሁን እንዲያጥር ወሳኙ የሀገሩ ህዝብ እንጂ፤ በውጭ ኃይሎች እጅ አለመሆኑን ርሳቸው የሚገነዘቡት ይመስለኛል። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን በውጭ ተፅዕኖ አማካኝነት የሚደረግ የመንግስት ለውጥ ርባና እንደሌለው እንደ ዩክሬን ባሉ ሀገሮች ውስጥ በቀለም አብዮት አራማጆች ሳቢያ የተካሄደውና የህዝቡን ሳይሆን የውጭ ሃይሎችን ፍላጎት ሲያስፈፅም የነበረውን መንግስት ለውጥ እውነታን ተመልክተናል።

በተጨማሪም በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የዚያን ሀገር ህዝብ መናቅ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ደግሞ ርሳቸው እንደሚያስቡት ወንድም የሆነውን የኤርትራን ህዝብ የሚንቁ አይደሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክና በደም ትስስር ያለውን ወንድሙን ያከብራል እንጂ አይንቅም። እኔ እስከሚገባኝ ደረስ የኤርትራ መንግስት ለውጥ ጉዳይ የኤርትራዊያን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጉዳይ አይደለም። እናም ምናልባት የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ሊያደርጉ የሚችሉት ወንድማቸው የሆነውን የኤርትራን ህዝብ መርዳት ይመስለኛል።
ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ የደህንነት ፖሊሲው መሻሻል አለበት በማለት ከማኔጅመንት (አስተዳደር) አኳያ በሀገራችን ካለው የፀጥታና የደህንነት ሁኔታ ጋር የማይመጥን መሆኑን ገልፀዋል። ግና አስተዳደሩ ‘እንዲህ ቢሆን ይሻል ነበ’ር በሚል ያቀረቡት አንዳችም መፍትሔ ሃሳብ የለም። ይህም በእኔ እምነት ርሳቸው ለአንጃው በነበራቸው የወገንተኝነት ስሜት ሳቢያ ከሰራዊቱ ኤታማዦር ሹምነት በ1993 ዓ.ም ስለተሰናበቱና ፖሊሲው በ1995 ዓ.ም በይፋ ስለተገለፀ፤ ‘ተሳታፊ ያልሆንኩበት ስለሆነ መቃወም አለብኝ’ የሚል ስሜት ያጫረባቸው ይመስለኛል።

ያም ሆኖ የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ እጅግ ያስገረመኝ የአዲስ ዘመኑ ጋዜጠኛ በፖሊሲው ጉድለት ሳቢያ በሀገራችን ላይ የተፈጠረ ችግር ካለ በማሳያነት እንዲገልፁ ሲጠይቃቸው፤ ርሳቸው “…ለእኔ ግልጽ የሆነውና ቀድሞ የሚመጣው አምና በአገራችን ላይ ተከስቶ የነበረው ብጥብጥና ሁከት ነው።…” በማለት የመለሱት ነው። ርግጥ በሀገራችን አንዳንድ የአማራ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ሁከት መነሻውም ሆነ መድረሻው የመልካም አስተዳደርና ከእርሱ ጋር በተያያዙ የተፈጠሩ ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል። ይህን ችግር በኢፌዴሪ መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጁት ቡድኖች ለኢትዮጵያ በጎ ከማያስቡ ሀገሮች ጋር በመቆራኘት እንዲሁም የሀገራችን ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አንዳንድ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንደሚንቀሳቀሱ የሚገልፁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት ጉዳዩ ላይ እሳት የማርከፍከፍ ሚናን እንደተጫወቱ ግልፅ ነው።

እናም ይህ ጉዳይ እንደምን ከውጭ ጉዳይና ከሀገራዊ ፖሊሲው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚኖረው አይገባኝም። ምናልባት ርሳቸው ‘እዚህ ሀገር ውስጥ የተከሰተውና አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ጠያቂ እንዲሆን ያደረገው የመልካም አስተዳደርና ይህን ሚና የተጫወቱት የሀገራችን አሸባሪዎችና አንዳንድ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ጉዳይ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ውስጥ መካተት ነበረበት’ የሚሉ ከሆነ፤ ይህ ምልከታቸው ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም በውጭ ጉዳይና ሀገራዊ የደህንነት ፖሊሲው ላይ የሰፈሩትና ርሳቸውም “ትክክለኛ አቅጣጫዎች ናቸው” በማለት በተለይ አፅንኦት ሰጥተው “…ዋነኛ ሥራችን አገራችን ውስጥ ያለውን ኋላ ቀርነትና ድህነትን መታገልና ማስወገድ መሆኑን ያስቀምጣል። ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላምና ተከባብሮ መኖር ዋና አቅጣጫ አድርጓል። እያንዳንዱን የጎረቤት አገርንም እየጠቀሰ ምን አይነት ግንኙነት ሊኖረን እንደሚችል ያመላክታል። በአስተሳሰብ ደረጃ የአገር ደህንነት በፖሊሲ መመራት እንዳለበትና ይህን መነሻ አድርጎ በአገሮች መካከል ግንኙነት እንዲኖር መጣር እንደሚገባ አስቀምጧል።…” በማለት የገለጿቸው ሃሳቦች በውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲው ላይ መስፈር የሚገባቸውን ጉዳዩች ስለሚገልፅ ነው። እናም በእኔ እምነት ይህ የጡረተኛው ጄኔራል ‘እኔ ያልነካሁት ነገር ስህተት ነው’ ብሎ ማሰብ፤ እንደ ፃድቃን ገብረተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) ዓይነት በግሌ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ መፈጠር አስተዋፅኦ አድርገዋል ብዬ ከማመሰግናቸውና ከማከብራቸው ታጋይ እንዲሁም ለ10 ዓመታት በመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ላይ ተቀምጦ ከነበረ ሰው የሚጠበቅ አይመስለኝም።

እንዲህ ዓይነቱ ከግል ፍላጎት በመነሳት የሚሰነዘር ሃሳብ እንደ ዜጋ እያንዳንዳንችን ለሀገራችን ማበርከት የሚገባንን ነገር እንድናበረክት የሚያስችለንም አይመስለኝም።
በመጨረሻም ርሳቸው “…እኔ በይበልጥ መናገር የምፈልገው ስለያን ጊዜው አይደለም።…” ስላሉት አስደማሚ ሃሳባቸው ጥቂት ጥያቄዎችን በማንሳት ፅሑፌን ልቋጭ። ይኸውም አንድ ሰው ይበልጥ መናገር ያለበት ስለነበረበትና በጥልቀት ስለሚያውቀው እውነታ ነው ወይስ ‘በመንግስት ስራ ላይ ስለሌለሁ እንዲህ ሲባል እሰማለሁ’ እያለ ስለሚገልፀው ጉዳይ?…ለምሳሌ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ መናገር ያለብኝ እየኖርኩና እያየሁ ስላለሁት የሀገራችን የፀጥታ ጉዳይ ነው ወይስ ፃድቃን ገብረተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) ለስምንት ዓመት በአማካሪነት ሰርቻለሁ ስላሉት ስለ ደቡብ ሱዳን የፀጥታ ጉዳይ?…ርግጥም እኔ ስለ ደቡብ ሱዳን የፀጥታ ጉዳይ ሙያዬም ስላለሆነ በመገናኛ ብዙሃን የሚባለውን አልፎ…አልፎ ከመስማት በስተቀር የማውቀው አንዳችም ነገር የለም። እናም የእርሳቸውን ያህል ቀርቶ ለማለት የምችለው ያህል እንኳን ቅንጣት እውቀት የለኝም። አዎ! መናገር የምችለው በጥልቀት ስለማውቀው የሀገሬ ጉዳይ ነው። እናስ ጡረተኛው ጄኔራል “እኔ ይበልጥ መናገር የምፈልገው ስለ ያኔው አይደለም” ሲሉ ምን ማለታቸው ይሆን?…ያኔ ምን ነበር?፣ ለመናገር የማይፈልጉት ነገር አለ ማለት ነው?…ታዲያ የእነዚህን ጥያቄዎች ምላሾች ለርሳቸው ስተዋቸው ላራመዷቸው የገቡኝም ይሁን ያልገቡኝ ሃሳቦች ያለኝን አክብሮት በድጋሚ በመግለፅ ጭምር ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy