Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ…

0 1,518

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ…

                                                 ደስታ ኃይሉ

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ጠያቂ ህብረተሰብ ተፈጥሯል። ይህ ህብረተሰብ መብትና ግዴታውን በሚገባ እየተገነዘበ መጥቷል። እናም ይህን ግንዛቤ ያጎለበተው በየአካባቢው የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል በየጊዜው የሚደርስበትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፊት ለፊት መታገል ይኖርበታል። ህብረተሰቡ ከእርሱ የሚደበቁ ነገሮች ባለመኖራቸው አሁንም የመፍትሔው አካል ሆኖ ይበልጥ መንቀሳቀስ ያለበት ይመስለኛል።

መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይበልጥ ለመፍታት ግብ ጥሏል። ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገራችን የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ በሚደረገው ጥረት ወሣኙን ምዕራፍ የያዘ ነው። የዜጐችን እኩል የልማት ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመገንባት የላቀ አስተዋፅኦ ያለው ዕቅድ ነው፡፡

ስለሆነም የዕቅዱ ዋና መነሻ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የማሰለፍ ሀገራዊ ራዕይን የነገበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም በቀጣዩ የአምስት ዓመት ዕቅድ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በጥቅሉ ሲታዩ፣ ወደዚሁ ሀገራዊ ራዕይ እንዲያደርሱን ሆነው የተቀረፁ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡

ሁለተኛው ዕቅድ ሀገራዊ የሴክተር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችንም በመነሻነት የያዘ ነው። ሁላችንም እንደምንገነዘበው በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ እንዲሁም በየደረጃው የሕዝቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ ብሎም የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ለመገንባት በሚገባ የተዘረዘሩ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው በመተግበር ላይ ናቸው፡፡

እርግጥ እነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከአንድ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ተሻጋሪ ከመሆናቸውም በላይ፣ እስካሁን ባለው አተገባበር መልካም ውጤቶች እያስገኙና ለህዳሴ ጉዟችን ፅኑ መሠረት እየጣሉ ናቸው። በመሆኑም ቀደም ሲል የጠቀስኩት የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀሞች የዕቅዱ መነሻ ተደርገው ተወስደዋል።

አንድ ዕቅድ ሲዘጋጅ የዕቅዱ ባለቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስማማባቸው ጉዳዩች ታሳቢ ይሆናሉ። በመሆኑም ሀገራችን እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2030 ገቢራዊ የምታደርገው ዘላቂ የልማት ግቦች በዕቅዱ ላይ በመነሻነት እንዲያዝ ምክንያት ሆኗል።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲዘጋጅ የሚሊንየም የልማት ግቦችን (MDG) ማሳካት እንደ አንድ መነሻ ተወሰዶ እጅግ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል። ሀገራችን አብዛኛዎቹን የልማት ውጥኑን ግቦች በማሳካትም አመርቂ ውጤቶችን አግኝታባቸዋለች።

በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን አምስት ዓመታት የሚከናወኑት “ዘላቂ የልማት ግቦችን” (SDG) ለማሳካት ሀገራችን ተነሳሽነቱን በመውሰድ ከዓለም አቀፉ ራዕይ ውስጥ የተወሰኑትን ለማሳካት ትችል ዘንድ በዕቅዱ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጋለች። ታዲያ ልክ እንዳለፈው የልማት ወቅት ሁሉ፣ ሀገራችን በዚህ የዕቅድ ዘመንም መንግስትና ህዝቡ በጋራ ተባብረው የተወሰኑትን እንደምታሳካ እሙን ነው።

ሊያጋጥሙ የሚችሉ ዓለማዊ ሁኔታዎችም የዕቅዱ ታሳቢ ሆነዋል። ባለንበት የሉላዊነት ዘመን ሁሉም ነገሮች በፈጣን ሁኔታ ይለዋወጣሉ። ታዲያ ለውጦቹ ሀገራችንን በመሳሰሉ እየለማ የሚገኝ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም በለውጦቹ ሳቢያ የሚፈጠሩ አዎንታዊና አሉታዊ ጉዳዩች ከግምት ውስጥ ገብተዋል።

በዓለም ላይ የሚከናወኑ ሁሉንም አዝማሚያዎች ግምት ውስጥ አስገብቶ ዕቅድ ውስጥ ማካተት ሊፈጠሩ የሚችሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቋቋም ያስችላል። ለዚህም ነው ይህ ዓለማዊ ሁኔታ በዕቅዱ ውስጥ ታሳቢ እንዲሆን የተደረገው። ይህን ሃቅ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራችን የሚከተሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች በዕቅዷ ውስጥ ገቢራዊ እንዲሆን ተልማለች። እነርሱም በቀጣዩቹ አስር ዓመታት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን፣ የክፍለ-አህጉር የንግድና ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ነፃ በሆነ ሁኔታ የማካሄድ፣ የምጣኔ ሃብታችንን በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት የማሳደግ እንዲሁም ያደጉ ሀገራት አነስተኛ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገሮች የሰጡት እንደ “አጎዋ” ዓይነት ከቀረጥና ከኮታ ነፃ የሆኑ የገበያ ዕድሎችን ይበልጥ በማስፋት ተጠቃሚ መሆንን የሚያካትቱ ናቸው።

  እርግጥ ርዕሰ ጉዳያችን የሆነውን መልካም አስተዳደር ዕውን ለማድረግና ተግዳሮቶችን በብቃት ለማለፍ የሚከተሉት ሁኔታዎች ታሳቢ እንደሚሆኑ መገንዘብ ይገባል። በዕቅድ ዘመኑ የልማታችንና ፈጣን ዕድገታችን የማይተካ አስተዋፅኦ የሚያደርገውና የግብርናው ዘርፍ ዕድገት ዋና ምንጭ ይሆናል፡፡

ከዚህ አኳያ ለውጥ ማምጣት የጀመሩትን የስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች ምርታማነትና ጥራት የበለጠ ከማሳደግ በሻገር የላቀ ዋጋ የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ የልማት ቀጣናን ማዕከል ያደረገ ርብርብ በማድረግ ልዩ ትኩረት አግኝቷል፡፡

በመሆኑም የመስኖ ግብርና የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሥራን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡ በምርት ሂደት ውስጥ ተዋናይ የሆኑ የአርሶ-አደሩና የአርብቶ-አደሩ የቤተሰብ ግብርና ተጠናክሮ የሚቀጥል ሆኖ የአርሶ-አደሩ የተማሩ ወጣቶችና የግል ባለሃብቱ ቅንጅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም በግብርና ልማትና ግብይት ውስጥ ያሉ የሥርዓት ማነቆዎችን በአስተማማኝ ደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ከላይ በዋነኛነት የጠቀስኳቸውን ዋነኛ ስራዎች ማከናወን ከተቻለ የፖለቲካ ኢኮኖሚው ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ከያዘበት ወደ ልማታዊነት የበላይነት ወደ ያዘበት መሸጋገሩ አይቀሬ ነው። በመሆኑም በአንድ ወገን ልማታዊነትን የሚያጐለብቱ ድጋፎችን በጥራት በማቅረብ፣ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምንጭ ሆነው የተለዩትን ጉዳዮች በልዩ ትኩረት በማድረቅ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ልማታዊነት የበለጠ እንዲጐመራና የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ማድረግ ይቻላል። ይህም መልካም አስተዳደርን ዕውን ከማድረግና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እጅግ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል።

ይህ ማለት ግን እስከዛሬ ድረስ አንዳችም ዓይነት የመልካም አስተዳደር ስራዎች ገቢራዊ አልሆኑም ማለት አይደለም። መንግስትና ህዝቡ ችግሩን በሂደት ለመፍታት ሀገር አቀፍ የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በማቋቋምና ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳዳርን ለማስፈን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ህብረተሰቡን በተደራጀ መልኩ የማንቀሳቀስ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ እስሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ቢሆኑም አሁንም ጠንካራ ሥራ መከናወን እንዳለበት አይካድም።

ልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መገንባትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የዛሬ 14 ዓመት ገደማ በተካሄደው የተሀድሶ መስመር ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ታዲያ አሁንም በገጠር ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ያለው እንዲሆንና የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩልም በከተሞች የበላይነት ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቡ ዛሬም ስር የሰደደ መሆኑን ነው። እናም ልማታዊነትን ይበልጥ በማጐልበትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከምንጩ በማድረቅ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ልማታዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር፤ ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበለዓይነትን እንዲይዝ ያደርጋል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy