Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም መሰረት የሆነው የህዝቦች ስርዓት

0 248

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም መሰረት የሆነው የህዝቦች ስርዓት

                                                 ታዬ ከበደ

የትናንቷ ኢትዮጵያ ለብሔሮቿ፣ ብሔረሰቦቿና ህዝቦቿ የሰቆቃ ምድር ነበረች፡፡ ዜጎች ኑሯቸውን በቅጡ እንዳይገፉ የተቸገሩበት፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ግራ የተጋቡበት፣ መቋጫ በሌለው ጦርነት፣ ረሃብና ስደት የሚንገላቱበት ዘግናኝ ወቅት ዳግም ላይመለስ ተሰናብቷል፡፡ በመላው ሀገራችንም እፎይታ ነገሷል፡፡

ዛሬ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ኑሮን ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሰላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለዋል፡፡ ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ውድ የህዝብ ልጆች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሰላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመርን አምጥቷል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም ማድረግም ተችሏል፡፡

እነዚያ አስከፊ የህይወት ጉዞዎች ተገትተዋል፤ ጨቋኙ አምባገነናዊ ስርዓት ምሱን አግኝቶ ዛሬ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጥጦ መንገስ አብቅቷል፤ የመንግሥት ሥልጣን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚረከቡባት አገር መፍጠር ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ሠላምና ዴሞክራሲ መሠረት በማድረግ ከልማቱ በፍትሃዊነትና እኩልነት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የፀና እምነት ተይዟል፡፡ ፍሬውንም መቋደስ፣ ፅዋውንም ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ መነሻ መሠረቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደም ቀለም በተጻፈ ቃል ኪዳን ያፀደቁት ህገ መንግስት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካይነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ 22 ዓመታትን አልፏል፡፡

በእነዚህ ወቅቶች የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡

ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡

የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡ ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ህዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አኃዝ በላይ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አግዟል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የሰፈረው  አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ አሳይቷል፡፡

ብዝኃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነት ምንጭ ሆኗል፡፡ የብዝኃነት አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡ የመደማመጥ፣ መቻቻል፣ መከባበርና አጋርነት ታሪክ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሆነዋል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ ችለዋል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል፡፡

የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በወደቀበት ወቅት የነበሩ የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳንዶቹ ያነገቡት ዓላማ መገንጠልን ነበር፡፡ ሆኖም አብሮ በመኖር ሂደት የተገኘ ጥቅም እያደገና እየሰፋ ስለመጣ የመገንጠል አስተሳሰብ ማኅበረሰባዊ መሠረት እያጣ መጥቷል፡፡

የደርግ መንግሥት በወደቀበት ማግሥት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው ታሪክ መሠረት የሌለው መሆኑን ያለፉት ዓመታት ጉዞ በተግባር አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብዝኃነት አገሪቱ በዓለም ያላትን ገፅታ ቀይሯል፡፡ አንዳንዶች በብሔርና በጎሣ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን የተለየውን ሆኗል፡፡ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ አሳይቷል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት የተረጋጋች ሀገር መሆኗን ብዙዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህ በህዝቦች የተደራጀ የህዝቦች ስርዓት የሰላም መሰረት ሆኗል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy