Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የባቡር መሰረተ ልማትና አገራዊ ጠቀሜታው

0 357

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የባቡር መሰረተ ልማትና አገራዊ ጠቀሜታው

                                                       ታዬ ከበደ

ሀገራችን ዘላቂ ልማትን ለማምጣትና በምጣኔ ሃብት መስክ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላትን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች። የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች በማሳካት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ እየተደረገ ያለው ጥረትም በሁሉም ዘርፍና አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና በተለይም በውጪና ገቢ ንግዳችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ የአገልግሎት መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋትና ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ይገባል።

ይህን ችግር ለመቅረፍም የባቡር መስመር ዝርጋታን የማስፋፋትስራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ባቡር በዋጋ ርካሽ ከመሆኑ፣ከፍተኛ የሆነ ጭነትንም በአንድ ጊዜ ከማጓጓዝ አንፃርና በፈጣንነቱ ተጠቃሽ የሆነ የየብስ ማጓጓዣ ነው።

የባቡር ትራንስፖርት በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚገደብ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራትም ጋር ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከመፍጠር አንፃር ያለው ጠቀሜታ ቁልፍና የጎላ መሆኑም እሙን ነው።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ሁለገብ ጥረት ማፋጠንና የሀገሪቷን የልማትና የንግድ ማዕከላት የሚያስተሳስር እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ገበያና ወደቦች ጋር የሚያገናኝ ዘመናዊ የባቡር መሰረተ ልማት የመዘርጋት ራዕይን ሰንቆ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በዚህም መሰረት በመላ ሀገሪቱ ዘመናዊ የባቡር መሰረተ ልማት  በመገንባት  እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመደገፍና በመላ ሀገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲስፋፋ ብሎም ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲቻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 141/2000 በህዳር ወር 2000 ዓ.ም የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፤ ዋና ዓላማው ተፎካካሪና አቅምን ያገናዘበ የትራንስፖርት አገልግሎት ማረጋገጥ የሚችል የተቀናጀና ከፍተኛ አቅም ያለው የባቡር ትራንስፖርት ስርዓት መዘርጋት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በመሆኑም ያስቀመጠውን ዓላማና ግብ ለማሳካት መንግስት እያከናወነ ካለው የባቡር መስመር ዝርጋታ አቅጣጫ አኳያ የባቡር መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ነድፎ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው።

ቆጣቢ የሆነ የየብስ ትራንስፖርት ስርዓት ለማካሄድ የባቡር መስመር ተመራጭ ነው። ይሁንና የባቡር መስመር አዋጭ የሚሆነው ከፍተኛ ጭነት ወይም መንገደኛ ባለበት እንጂ ውሱን ተጓዥ ወይም ጭነትን በማጓጓዝ ረገድ ይህን ያህል አዋጭ እንደማይሆን ይታመናል።

ዳሩ ግን የኢኮኖሚ እድገታችን በተፋጠነ ልክ ይኸው ፍጥነት ከዚህ በበለጠ እንዲቀጥል ቀልጣፋና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የየብስ ትራንስፖት አገልግሎት እንደሚያስፈልገን እሙን ነው።

ሀገራችን ልትጠቀምባቸው ከምትችለው ዋና ዋና ወደቦች ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ያስፈልገናል፤ በአገር ውስጥም ዋነኛ የትራስፖርት ኮሪደሮችን የሚያገናኝ የባቡር መስመር እንደሚያስፈልገን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።

እንደሚታወቀው ቀደም ባሉት ጊዜያት ለባቡር ትራንስፖርት በቂ ትኩረት ስላልተሰጠውና የሚፈልገውም ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ፋይዳ ያለው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ላይ ደርሰናል። ይሁንና መንግስት ይህንን ሁኔታ ለመቀየር አቅም በፈቀደ መጠን በርካታ ስራዎችን እየከወነ ይገኛል።

እርግጥ አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የመንገድ ትራንስፖርትንና የባቡር ትራንስፖርትን በማቀናጀት ፈጣንና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የትራንስፖርት ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባን አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ይህን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚረዳው የኢፌዴሪ መንግስትም ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት የበለጠ ማረጋገጥ የሚያስችለውን የየብስ ትራንስፖርት ስርዓት ገንብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ይህ ዘርፍ ለሀገራችን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድ እየተኘበት የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር አንዱ ማሳያ ነው።

የዘርፉ ጠቀሜታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ አንጻር የሚጫወተው ሚና የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰዎችን በፍጥነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ማስቻሉም እንዲሁ፡፡ ባቡር በርካታ ስዎችን በአንዴ ከቦታ ቦታ ስለሚያንቀሳቀስ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ አኳያም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

የተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሚገኙባትንና ስብሰባዎች የሚሄዱባትን የመዲናችንን ውበትና ዘመናዊነት በመጨመር ረገድም አስተዋፅኦው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም እንዲሁ፡፡

የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በኤሌትሪክ የሚሰራ በመሆኑ ሀገራችን ለነዳጅ ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለመቆጠብ እንዲሁም የአየር ብክለትን በመከላከል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ በኩልም ጠቀሜታ አለው። በዚህም ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታከናውናቸው መሰል ግንባታዎች የሀገራችን ሰራተኞች የሚቀስሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ሙሉ በሙሉ የመስራት ችሎታቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ የባቡር መስመር ዝርጋታ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ የላቀ ሚና ይጫወታል ሲባል፤ ሽግግሩ ሀገራችን ለወጠነቻቸው የልማት ፕሮግራሞች ማሳኪያ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልጋት ለይቶ መጠቀም ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እናም በቅድሚያ በሂደት መቅዳት፣ መላመድና ማሻሻል  በስተመጨረሻም ቴክኖሎጂውን በማመንጨት የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡

እርግጥ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ለመረዳት እንደሚቻለው የጎንዮሽና የቀጥታ የቴክኖሎጂ ማሸጋገርያ መንገዶች አሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን በመሰሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባው አካሄድ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡት ሀገራት ልምድ በመቅሰም የሚከናወነው የልማት ስራ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

እናም ፈጣን ለውጥ ለማምጣት መሰረታዊ የሚባለው የጎንዮሽ የቴክኖሎጂ ሽግግር በብዙ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የባቡር ዝርጋታ ፕሮጀክት ነው ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እየዋለ የሀገሪቱ ባለሙያዎች ትምህርት ይቀስማሉ፡፡

ለወደፊትም መሰል ፕሮጀክቶች በሀገራችን ሲገነቡ በእኛው መሃንዲሶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ሀገራችን ላለፉት 10 ዓመታት በተከታታይ ያስመዘገበችው የአስራ አንድ በመቶ አማካይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሀገሪቱ በ2025 ልትደርስበት ያሰበችውን የመካከለኛ ገቢ ጎራ ካላቸው ሀገራት የመቀላቀል ዕድልን መደላድል እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይም የሀገራችንን ከተሞች፣ ክልሎችንና አጎራባች ሀገሮችን የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶች ለዚህ ትልም ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡

በኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ እና በባቡር መስመር ዝርጋታ እየተደረጉ ያሉ ሰፊ መሰረት ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ያለ ምንም እንቅፋት እየተከናወኑ ናቸው፡፡ በተለይም በትራንስፖርት ዘርፍ በኩል የባቡር አገልግሎት በፍጥነት ግዙፍ የሆነን ሎጀስቲክካዊ አቅርቦት ወደ ተፈለገበት ቦታ ስለሚያደርስ አገልግሎቱ የአማራጮች ሁሉ ቅድሚያ መሆኑ አይካድም፡፡

መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ የባቡር መስመር ዝርጋታውን አቅም በፈቀደ መጠን እያከናወነ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚዘረጉ የባቡር መስመሮች በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተካተቱ ውስጥ የአዲስ አበባ – ድሬዳዋ- ደዋሌ አንደኛው ሲሆን፤ የስድስት መቶ ሃምሳ ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ የሙከራ ስራውንም ጀምሯል። ሌሎች መስመሮችም ይሳለጣሉ፡፡ የዘርፉ ስራ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳደረው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ስራው ሊጎለብት ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy