Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢሳያስ መዘዝ አላባራም!!

0 380

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 የኢሳያስ መዘዝ አላባራም!!

                                       ይነበብ ይግለጡ  

ሰሞኑን የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ጠቅላይ  ኤታ ማዦር ሹም የነበሩት  ሌተና ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ዘላቂ የሆነ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ተግባራትን እየሰራ መሆኑን አስቀድሞ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ በመግለጽ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር  ሰፊ ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ይህ ቃለ ምልልስ ከፍተኛ ግምትና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያምናል፡፡

 

ጀነራል ጻድቃን በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ያለፉ ኢሕአዴግ በትረመንግስቱን ከጨበጠ በኋላም ባለው ጊዜ የሀገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት በሌተና ጀነራልነት ማእረግ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነት የመሩ ሰው ናቸው፡፡

 

ከመንግስት ስልጣን ከለቀቁም በኃላ አሜሪካን ሀገር በሚገኘው ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ገብተው በአለም አቀፍ ግንኙነትና በጸጥታ ጉዳዮች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙ በመቀጠልም ለስምንት አመታት ያህል በደቡብ ሱዳን የጸጥታ አማካሪ ሆነው የሰሩ ናቸው፡፡፡ዛሬ በግል ስራ ይተዳደራሉ፡፡

 

የኤርትራን ጉዳይ ከመነሻው ጀምሮ የሚያውቁት ጀነራሉ የኢሳያስ መንግስት በስልጣን ላይ እስካሁን ድረስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና ወዳጅነት ሊመሰረት እንደማይችል ይናገራሉ፡፡ሕዝብ ለሕዝብ ያለው ግንኙነት ትላንትም ዛሬም የነበረና የቀጠለ መሆኑን የሚገልጹት ጀነራል ጻድቃን ሁለቱን ሕዝቦች የበለጠ የማቀራረብ ስራ መሰራት እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀድሞ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ጦርነት በድንገት መነሳቱን አስታውሰው ከዚያ በኋላ የውጭ ፖሊሲው መቀረጹን , አሁን ባለበት ደረጃ ከጎረቤቶቻችን ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለን ሆኖም የመስኩን ምሁራን በሰፊው በማሳተፍ  የወደፊቱን የሀገሪቱን መጻኢ የእድገትና ልማት  ከየትኛውም ጥቃት መከላከል በሚችልበት መልኩ አዲስ ሰፋ ያለ ሀገራዊ ጥቅምንና ጉዳትን ያመዛዘነና የፈተሸ  የውጭ ፖሊሲ መዘጋጀት እንዳበት ይገልጻሉ፡፡

 

በትላንት እይታ ሳይሆን ዘመኑን በአግባቡ የሚያነብ በፈጣን ሁኔታ ከሚለዋወጠው የአካባቢያችንም ሆነ የአለም ፖለቲካ ጋር የሚራመድ የሀገራችንን ዘላቂና ቋሚ ጥቅም የሚያስከብር መንግስታት ቢለዋወጡም መሰረታዊ መስመሩን ተከትሎ የሚሄድና በየትውልዱ እንደ አስፈላጊነቱ የሚዳብር የውጭ ፖሊሲ መቅረጽ ማዳበር አስፈላጊ እንደሆነ  ያስረዳሉ፡፡ተገቢና ትክክለኛ አስተያየት ነው፡፡

 

የተቸከለ በአንድ ቦታ ብቻ ተገትሮ የሚቀር በየጊዜው ወቅታዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን የማይተነትን ለወቅቱም ፈጣን ምላሽ የማይሰጥ አዝጋሚ ከሆነ በውጭ ኃይሎች የመቀደም እድሉ ይሰፋል፡፡ይህ እንዳይሆን አስቀድሞ አጠቃላይ ሀገራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ጠላትንና ወዳጅን መለየት አስቀድሞም በብዙ መልኩ መዘጋጀት ግድ ይላል፡፡

 

ጅቡቲ ብሔራዊ ንግዶቻችን የሚስተናገዱበት ለእኛ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ብትሆንም አለም አቀፍ የፖለቲካ ተዋናዮች ቻይና፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ ሌሎችም ኃይላቸውን  እያሰፈሩባት ያለች ሀገር ነች፡፡ሁኔታው ወደፊት ወዴት ሊያመራ ይችላል ብሎ አስቀድሞ ማሰብ ማስላትን ይጠይቃል፡፡

 

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የእኛን ብሔራዊ ጥቅም የምናስጠብቀው በምን መልኩ  መሆን አለበት የሚለው አስቀድሞ ሊሰላ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ተለዋዋጭ ከሆነው የአለም ፖለቲካ አንጸር ለመተንበይ ለመገመትም ይከብዳል፡፡ያዳግታል፡፡ ሁልጊዜም ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ሁሌም ለሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደሕንነት ነው፡፡ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ ለደቡብ ሱዳን እንደ ሀገር መቆም ኢትዮጵያ የከፈለችው መስዋእትነት ግዙፍ ነው፡፡

ዛሬ በደቡብ ሱዳን የውስጥ ፖለቲካ ገብተው ተዋናይ የሆኑት ኡጋንዳና ግብጽ  ናቸው፡፡ለዛውም ከ250 ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናውያንን እንደ ሀገር ተቀብለን ያስጠጋን በስደት ቢመጡም የተቀበልን መሆናችን በሁሉም ወገን ይታወቃል፡፡ግብጽና ኡጋንዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፈጠሩት ወዳጅነት ሽር ጉድ ማለትን ይዘዋል፡፡እኛም በእርጋታ  እያየነው ነው፡፡ሁኔታው ሲበስል ሊከሰት የሚችል ነገር ይኖራል፡፡

ግብጽ ምን ፈልጋ ነው ይሄን በማድረግ ላይ ያለችው የሚለው ጥያቄ ሲነሳ መልሱ ቀላል ነው፡፡ጉዳዩ ከአባይ ወንዝ ጋር የተያያዘ ነው፡የግብጽ የምንጊዜም ከጥንት እስከዛሬ የዘለቀው ስትራቴጂካዊ አላማዋን ኢትዮጵያ ደካማ ሀገር ሆና እንድትኖር መስራት ነው፡፡ቢቻላት እንድትበታትን ማድረግ ነው፡፡ይሄንንም ብዙ ጊዜ ሞክራዋለች፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በዘላቂነት ማቀድ መስራት በገንዘብ መርዳት ኢትዮጵያውያንን እየመለመለች በሀገር ውስጥ ሁከት ብጥብጥ ደም ማፋሰስ እንዲካሄድ ብሔር ብሔረሰቦችን ማጋጨት ማለያየት ማዋጋት መደበኛ ስልትዋ ነው፡፡ ግብጽ በደቡብ ሱዳን፤በሰሜን ሱዳን አስቀድሞ፤በሶማሊያ፤በጅቡቲ ቋሚ የጦር ሰፈር ለመመስረት ቦታ እንዲሰጣት የጠየቀች  በኤርትራ መሬትም የጦር ሰፈር የመሰረተች ሀገር ናት ፡፡እኛም ይሄንን ሚስጥርዋን እናውቃለን፡፡አስቀድመን ስንመክተው ኖረናል፡፡ ዛሬም ወደፊትም ይመከታል፡፡

በኤርትራ ውስጥ የጦር ሰፈር አግኝታ ሠራዊቷን አስፍራለች የሚሉ መረጃዎችም አሉ፡፡የሻእቢያ ጊዜና ዘመን የማይሽረው ጠላትነት ዛሬም በአዲስ መልኩ ቀጥሎአል፡፡የሳኡዲ አረቢያና የገልፉ ሀገራትን ሠራዊት የጦር ሰፈር ሰጥቶ በአሰብ ላይ አስፍሯል፡፡፡በዚህም በሚሊዮኖች ዶላር አግኝቶበታል፡፡እያገኘም ነው፡፡ይህ ደግሞ ለሌላ እብሪት እንደሚጋብዘው ይታወቃል፡፡

አሰብ ላይ የኩዌት የኩዋታር የሳኡዲ ሠራዊቶች ሰፍረው በባሕሩ ላይ መርከቦቻቸውን በሜዳው ደግሞ የጦር ጀቶቻቸውን አስፍረዋል፡፡በየመን ላይ የሚያካሂዱት ድብደባና ዘመቻም መነሻው አሰብ ነው፡፡ይህ ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ዙሪያ ገባውን ያለ በምስጢር የተያዘው ከበባ መጨረሻው ምንድነው ብሎ ማሰብንም ይጠይቃል፡፡አሜሪካ ለግብጽ አመት በአመት ከምታስታጥቃት የመጠቁ የጦር ጀቶችና ታንኮች ሚሳኤሎች ውስጥ ግብጽ ለኤርትራ አትሰጥም አታሻግርም ብሎ ማሰብ የዋህነትም ጅልነትም ነው የሚሆነው፡፡

ሳኡዲም  ሆነች ኩዌትና ኩዋታር አክራሪና ጽንፈኛ የሆነውን የዋሀቢ እስላማዊ እምነትን የሚከተሉና የሚያራምዱ  በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ሲሉም በየአመቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያፈሱ ናቸው፡፡የእንግሊዝ የዜና ምንጭ ቢቢሲ በአንድ ወቅት በዶክመንተሪ ዘገባ አቅርቦታል፡፡

ይህ ባለበት ሁኔታ ውስጥ በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ተዋጊ ሠራዊታቸውን ለማስፈር የበቁት የኢሳያስ አፈወርቂን ጸረ ኢትዮጵያ ሴራና ደባ መሰረት በማድረግ ነው፡፡የሻእቢያ መንግስት ለጊዜውም ቢሆን ከወደቀበትና ከገባበት የኢኮኖሚ ቀውስና ውድቀት የሚታደገው የአረቦች ዶላር አግኝቶአል፡፡፡ሌላ የሚያስጨንቀው ጉዳይ አይኖርም፡፡

የኢትዮጵያን መዳከምና ውድቀት አጥብቆ እንደሚመኝ ለዚህም እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ ዋናው ጥያቄ ኢትዮጵያስ ራስዋን ከዚህ አደጋ ለመከላከል ምን ማድረግ አለባት የሚለው ነው፡፡ጀነራል ጻድቃን እንደሚሉት የኢሳያስ አፈወርቂን መንግስት በፖለቲካውም ሆነ በማንኛውም መስክ የሚከፈለው መሰዋእትነት ተከፍሎ ማስወገድ ካልተቻለ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አደጋ ሆኖ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡

በረዥም ዘመን አደጋ ሊያስከትል የሚችል ተግባር በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ መሆኑን ይገልጻሉ፡፤ጀነራሉ ይህን ጉዳይ ዛሬ ላይ ይግለጹት እንጂ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ኢትዮጵያን በአረብ ሀገራት ሰራዊት በቅርብ ርቀት ድንበርዋ እያስከበባት ያለው ኢሳያስ አፈወርቂ ለቀጣዩ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የሚተርፍ አደጋን እየደቀነ መሆኑን በመግለጽ በርካታ ጽሁፎች ተጽፈዋል፡፡

በኤርትራ ሰራዊት ላይ የተመጠነ በሚል ሲወሰድ የነበረው ኃይል የማዳከም እርምጃ ዘለቄታዊ መፍትሄና ስትራቴጂካዊ ውጤት የማያመጣ ጊዜያዊ ማስተጋሻ ብቻ እንደነበረና እንደሆነም ስንገልጽ ቆይተናል፡፡አዋጪው ችግሩን ለዘለቄታ የሚፈታ ስትራቴጂካዊ መፍትሔ ማስገኘት መቻል ነው፡፡በኤርትራ የሚታገዙት ተቃዋሚዎች በሀገር ክህደት የተሰለፉ መሆናቸውም መታወቅ አለበት፡፡ኢትዮጵያን ለማጥፋት በሚሰራ መንግስት እየተረዱ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አስባለሁ ማለት የከንቱ ከንቱነት ነው::

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy