Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንቨስትመንት መንገዶች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እያመሩ ነው!

0 961

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንቨስትመንት መንገዶች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እያመሩ ነው!

                                                               ዘአማን በላይ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ጎዳናው ምቹ ነው። አይጎረብጥም። እንደ ልብ ያንሸራሽራል። የታጠረ መንገድም የለውም። መንግስት ያዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በደርግ ስርዓት ወቅት ዜጎች ከ500 ሺህ በላይ ብር ሃብት መያዝ እንዳይችሉ ታጥሮባቸው የነበረውን አጥር ያስወገደ፣ የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያ ጠላት ሳይሆኑ የሀገራችን የልማት አጋር እንዲሆኑና መዋዕለ ነዋያቸውን በሀገራችን እንዲያፈሱ ያደረገ ነው።

አዎ! መንግስት እየተከተለ ያለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የኢንቨስመንት መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመሩ ያደረገ ነው። ምቹው ጎዳና ኢንቬስተሮች ከአራቱም የዓለም ማዕዘናት ወደ ሰርቶ ማደግና መለወጥ ወደሚቻልባት “አፍሪካዊቷ ነብር” (African Tiger) ሀገር እንዲተምሙ እያደረገ ነው። ይህ ሁኔታም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) እንዲመጣ አድርጓል።

ርግጥ ‘ይህ ለምን ሆነ?’ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው መልሱ ቀላል ነው። ይኽውም በአንድ ሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ከተፈለገ በዚያች ሀገር ውስጥ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና አስተማማኝ ሰላም ሊኖር የግድ ነው። ከዚህ አኳያ ባለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በፅኑ መሰረት ላይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ሀገሪቱን መለወጥ ያስቻለ ሰላም እውን መሆን ችለዋል።

ሆኖም የዛሬ ዓመት ማብቂያ አካባቢ አንዳንድ ዕንፈኞች ዋስትና ባለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና አስተማማኝ በሆነ ሰላም የተገኘውን ልማት ለመቀልበስ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በበርካታ ኢንቨስትመንቶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ይሁንና መንግስት ለባለሃብቶች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ አድርጓል። ይህም መንግስት እዚህ ሀገር ውስጥ እየሰሩ ያሉ ባለሃብቶች በመንግስት ላይ መተማመንን እንዲፈጥሩና በመንግስትና ህዝብ ላይ ያላቸውን ጽኑ ዕምነት እንዲያጎለብቱ አስችሏል። ይህም በተያዘው ዓመት ውስጥ ብቻ በርካታ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል። ነባር ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ ጭምር።

ታዲያ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ መረጋጋት የራቃትና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የምትተዳደር ሀገር አድርገው በማቅረብ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ  ተግዳሮት እንደተጋረጠበት አድርገው ሲያቀርቡ ነበር። ሆኖም አለመረጋጋት በሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ በማንኛውም ሀገር ውስጥ ሊከሰት ይችላል፤ አዲስ ነገርም አይደለም። የትኛውም ሀገር ቢሆን ለጥቂት ጊዜ በችግር ውስጥ ሊቆይ ይችላል። ዋናው ቁም ነገር ችሩን በዘላቂነት የመፍታት ጉዳይ ነው። መንግስት ደግሞ ከህዝቡ ጋር በመሆን ሁኔታውን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቀይሮ ለሰላም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህም የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አውድን ፈጥሯል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን ማንኛውም ሀገር ጊዜያዊ እክል ሲያጋጥመው ችግሩን እስኪቀለበስ ድረስ የሚያወጣው አዋጅ ነው። ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ግብፅና ሌሎች ሀገራት ችግር ሲግጥማቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት እልባት ሰጥተዋል፤ እየሰጡም ነው። እናም አዋጁ በእኛ ሀገር ውስጥ በመተግበሩ ብቻ እንደ “ጉድ” የሚታይበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።

ያም ሆኖ ሀገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ክለከላዎች በየደረጃው በማንሳት ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች። አዋጁ በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ጉልህ ጫና እንዳያሳድር ጥንቃቄ ተደርጓል። ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ በአዋጁ ሳቢያ የተስተጓጎለ ኢንቨስትመንት አልተከሰተም። እንዲያውም ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ሆና በያዝነው ዓመት ብቻ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች።

በዚህም ሳቢያ ፅንፈኛ መገናኛ ብዙሃኑ እንዳሉት ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን እየሳበች ያለች ሀገር ሆናለች። በእኔ እምነት ይህ ትልቅ ስኬት ነው። የዓለም ባንክም በቅርቡ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚው እንደሚሆን የተነበየውም ኢትዮጵያ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ የግብርና ምርት ዕድገትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋት ውጤታማ ስራዎችን በማከናወኗ ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ነገር፤ የውጭ ባለሃብቶች ሀገራችንን ለኢንቨስትመንት የሚመርጡበት ምክንያት ኢትዮጵያ የምትከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መሆኑን ነው። ፖሊሲው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የተመቻቸ ከመሆኑም በላይ፤ መንግስት በራሱ ወጪ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ባለሃብቶች በቀጥታ ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርታማ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ነው። ይህም ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል።  

እንደሚታወቀው የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ በመዋሉ ሳቢያ ባለፉት 15 ዓመታት ኢንቨስትመንት ወደዚህች ሀገር እንዲተም ምክንያት ሆኗል። በምጣኔ ሃብት ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ተከናውነዋል። ከዚህ በተጨማሪ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት የሚያስችሉ ርምጃዎችን በመውሰድና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ስራዎችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

በኢንቨስተመንቱ መስክ በየጊዜው ከታዩ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ጥንካሬዎቹን የማጎልበት ድክመቶቹን የማረም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩም መጥተዋል። በመሆኑም በህገ መንግሥቱ የተገለፀው ዓይነት ፈጣን ዕድገት ልቅ በሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ብቻ ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ሀገራችን ካለፈው ልምዷ ትምህርት ወስዳለች። በመሆኑም እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓይነት የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎች በመንግስት ተዘጋጀተው የግሉ ባለሃብት እንዲረከባቸው እየተደረገ ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው፤ ልቅ የሆነ የገበያ ሥርዓት ዘላቂና ሰፊ መሰረት ያለው ዕድገት የማምጣት አቅም እንደሌለው እና ይልቁንም የህዝብንና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰማሩ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም በሂደት መንግሥት የማይተካ ልማታዊ ሚና የሚጫወትበት የነፃ ገበያ ሥርዓት መከተል እንደሚገባ ታምኖበት በመስራት ላይ ይገኛል።

በዚህም መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች በመከተል ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት መንግስት በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ነው።

ይህ ሁኔታም የግሉ ባለሃብት መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን በማድረግና በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልፅ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲካሄዱ ተደርጓል።

ከዚህ አኳያ የመሬትና የባንክ አስተዳደር ሥርዓቶቹ እንደታቀደው ልማትን በሚያፋጥንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሟላ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ እየተከናወኑ ነው። የታክስ አስተዳደር ስርዓቱም ፍትሃዊ ውድድርን የሚያሰፍንና ህጋዊ ያልሆነ ጥቅምን የሚዘጋ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም የግል ባሃብቱን በሚያበረታታ መንገድ እየተከናወነ ነው።

በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት መንግስት የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥበብ በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ሂደት ውስጥ ውስን ሃብቱን መሰረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ የልማት ሥራዎች ላይ አውሏል። የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እንዲሁም የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው ብሎም ፍትሃዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገትንና ማህበራዊ ልማትን ማረጋገጥ ችሏል።

ታዲያ እነዚህ ተስፋ ሰጪና አስተማማኝ እውነታዎች ሀገራችን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆንና የኢንቨስትመንት መንገዶች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመሩ አድርገዋታል ማለት ይቻላል። ይህ ከአሁኑ ውጤት ያመጣ ምቹ ምህዳር ወደፊትም ተጠናክሮ ለሀገራችን ህዳሴ መረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ርግጠኛ መሆን የሚቻል ይመስለኛል—“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” ይባላልና።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy