Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዴሞክራሲ  ስርዓታችን ሲጎለብት

0 310

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዴሞክራሲ  ስርዓታችን ሲጎለብት

ልማታችን ይፋጠናል

 

ዮናስ

 

መንግስት የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት የበለጠ እንዲጎለብት ባለው የጸና አቋም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር  እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ያመቻቸ መሆኑ ይታወቃል።  ሰባት ፓርቲዎች በድርድር ሂደት ላይ ሲሆኑ ታዛቢዎችንም  መርጠዋል። በዚሁ መሰረት  አሁን ላይ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድር ላይ ይገኛሉ። ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ሊደራደሩባቸው በሚሿቸው አጀንዳዎች ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ውይይት፤ የምርጫ ህግና ስርአትን በማሻሻል ጉዳይ ላይ ለመደራደር የተስማሙ ሲሆን ኢህአዴግ የ“አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ” ላይ አልደራደርም ማለቱንም የድርድር ኮሚቴውን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ፡፡ “የፍትህ ስርአቱ እንደገና ይዋቀር” በሚለው አጀንዳ ላይ  ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም  በተመሳሳይ፡፡

የድርድር አጀንዳ አደራጅ ኮሚቴውም፤ ከፓርቲዎቹ የቀረቡትን ርዕሰ ጉዳዮች ጨምቆና ተመሳሳዮችን አጠጋግቶ፣ 13 አጀንዳዎች ለድርድር እንዲቀርቡ ባመቻቸው አግባብ
በነዚሁ በተመረጡ 13 አጀንዳዎች ላይ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ባለፈው ረቡዕ መወያየት ጀምረዋል። “የምርጫ ህግ እና ስርአትን ማሻሻል” የሚል አጀንዳ ለቀጣይ ድርድር እንዲቀርብ ከስምምነት ላይ የደረሱት እነዚህ ፓርቲዎች በረቡዕ ውይይት ከአጀንዳዎቹ በ2ኛነት የቀረበውና ፓርቲዎቹ ተነጋግረውበት መቋጫ ሳያበጁለት ለሰኞ ሰኔ 12 በይደር ያቆዩት የተለያዩ አዋጆችን የተመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ስለጉዳያችን እዚህ ጋር ሊነሳ ይገባል፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ስር የፀረ ሽብር አዋጁ፣ የሚዲያ አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅና የታክስ አዋጅ … ድርድር እንዲደረግባቸው የተጠየቀ ሲሆን ኢህአዴግ በአዋጆቹ ላይ ለምን መደራደር እንደፈለጉ ፓርቲዎቹ እንዲያስረዱት ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ 


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለድርድር እንዲቀርብ በሚል ለቀረበው ሃሳብ በሰጠው ምላሽም፤ ‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነን፣ ስለ አዋጁ መደራደር ስለማንችል ለድርድር መቅረቡን አልቀበልም›› ያለው ገዥው ፓርቲ፤ የንግድ ኢንቨስትመንት ህግን በተመለከተ የቀረበው አጀንዳም፤ ህጉ ገና ያልፀደቀ በመሆኑ፣ ፓርቲዎች ሀሳብ ካላቸው ማዋጣት እንደሚችሉ ጠቁሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም ማለቱንም ኮሚቴውን የጠቀሱ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ 


የፀረ ሽብር አዋጁ ለምን ለድርድር ሊቀርብ እንደሚገባ ገዥው ፓርቲ ላቀረበው የማብራሪያ ጥያቄ፤ የኢዴፓ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ይሰረዝ የሚል ጥያቄ የለኝም፤ ነገር ግን በአዋጁ የትርጉም ይዘት የተነሳ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያጋጠመ በመሆኑ ድርድር ሊደረግበት ይገባል›› ማለታቸውን ይፋ ያደረጉት እነዚህ ዘገባዎች፤ የመኢአድ ተወካይ አቶ አዳነ ጥላሁን በበኩላቸው፤ “ህዝባችን በህጉ እየተሳበበ የሚንገላታበትና ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በህጉ ምክንያት የሚታሰሩበት ለስደት የሚዳረጉበት ሁኔታ እንዳለና ለሰብአዊ መብት ጥሰት መነሻ የሆኑ አንቀፆችን በማካተቱ ድርድር ሊደረግበት ይገባል” ማለታቸውንም አመልክተዋል፡፡  

 
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ ተቃዋሚዎች ‹‹ለድርድር ብለን ያቀረብናቸው አጀንዳዎች ተቆርጠው ቀርተውብናል›› የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውንም የተመለከቱ ዜናዎች እየወጡ ሲሆን ፤  ቀርተዋል ተብለው ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከልም ‹‹ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ሳይቀር ብሄራዊ መግባባት ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚለው ሃሳብ አንዱ ነው፡፡ አሁን ያለው ባለአርማ ሰንደቅ አላማ ጉዳይም ህዝብን እያግባባ ባለመሆኑ ድርድር ሊደረግበት ይገባል የሚል መከራከሪያ ቀርቧል፡፡ 


የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን እድሜ ሊገደብ ይገባል፣ ኢህአዴግ በስልጣን ለመቀጠል የህዝብ መተማመኛ ድምፅ ማግኘት አለበት፣ የውጭ ግንኙነታችን መመርመር ያስፈልገዋል፣ የሀገሪቱ አለማቀፍ የድንበር ወሰንን እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት የመንግስት ጣልቃ ገብነት – ለድርድር እንዲቀርቡ ከፓርቲዎች ቢጠየቅም በአጀንዳነት አልተያዙም።   

የመላ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ “የኦሮሞ ህዝብ የመገንጠል ጥያቄ ለህዝብ ውሳኔ መቅረብ አለበት” የሚል ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ ደግሞ “ኢትዮጵያ” የሚለው የሀገሪቱ ስያሜ “ወደ ኩሽ ምድር መቀየር አለበት” የሚል አቋም አንፀባርቋል፡፡ የባህር ወደብ ጉዳይም ለድርድር እንዲቀርብ ተጠይቋል፡፡ የሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብን ወደኛ ማምጣት አለብን ተብሏል፡፡ 

ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት የኢህአዴግ ዋነኛ ተደራዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ‹‹የኦሮሞ ህዝብን ህዝበ ውሳኔ፣ የኢትዮጵያን ስያሜ፣ የሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብን በተመለከተ ፓርቲዎች የመደራደር ስልጣን ስለሌላቸው በአጀንዳው ላይ አንደራደርም›› ማለታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በፓርቲዎቹ የተነሱትና ከላይ የተመለከቱት ጥያቄዎች ለድርድር የቀረቡ ይመስላሉ ወይስ ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አኳያ ቀርነታችንን ለማስተካከል የተሰነዘሩ ናቸው የሚለውን መፈተሽ የዚሀ ተረክ መነሻ ምክንያት ነው፡፡  

ከእነዚህ ፓርቲዎች  ህዝብ የሚፈልገው የአገርንና የህዝብን ፍላጎታ ታሳቢ ያደረጉ አጀንዳዎችን እንጂ የግል ፍላጎታቸውን ይልቁንም ፓርቲዎቹ የሚወክሉትን ማህበረሰብ ፍላጎት እንጂ የፓርቲው መሪ ስለሆኑ ብቻ የግል ፍላጎታቸውን እና አስቀድሞ ድርድሩን ለማክሸፍ የተጠነሰሱ ሴራዎችን እንዳልሆነ በማያጠራጥር አግባብ ይታወቃል።  በእርግጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ልዩነት መኖር ጤናማ አካሄድ ነው። ጤናማ የማይሆነው ከላይ የተመለከቱ ህጋዊ መሰረት የሌላቸውን እና ይልቁንም ከድርድሩ መነሻና አላማ ጋር ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ የልዩነት ሃሳቦችን አንስቶ ለማሳጣት መሞከር ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በድርድር ወቅት ልዩነት መፈጠሩ አዲስ ነገር አለመሆኑና ድርድር እስከሆነ ድረስም የሚጠበቅ ነው። ግን ደግሞ በያንዳንዱ ጉዳይ ተቀራርቦ መነጋገር መቻል ዋንኛ ጉዳይ ነው። በአካሄድ ጉዳዮች ላይ የሚኖር ልዩነትም  መሰረታዊ  ችግር  አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ችግር የሚሆነው ላይመለሱ በህግና ህገመንግስታዊ አግባብ የተቀበሩ አጀንዳዎችን አግበስብሶ እንወያይ ማለትና ለፓርቲዎች ከተሰጠ ስልጣን በላይ ርቆ የህዝብን መብትና ፍላጎት የሚጻረሩ ጉዳዮች ላይ ካልተደራደርን ብሎ አሻፈረኝ ማለት ነው።  

 

ምንም በማያሻማ መልክ ሃገሪቷም ሆነች ህዝቦቿ  በድርድር ወቅት  ከፓርቲዎች  የሚፈልጉት የህዝብንና የአገርን ጥቅም ቀዳሚ አጀንዳቸው  በማድረግ   የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት  ለማጎልበት  ወደሚያስችል አጀንዳ እንዲመጡ ነው።  የዴሞክራሲ ስርዓቱን በማጎልበት  ልማትን ማፋጠን የሚያስችል የመደራደሪያ አጀንዳ እንዲያቀርቡ ነው።  ሁሉም የፖሊቲካ ፓርቲዎች ሰጥቶ መቀበልን እንደመርህ  ሲከተሉ ማየትን እንጂ ያልበላን ቦታ ላይ እንዲያኩልን አይደለም።

ለአገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዕድገት፣ ብልፅግና፣ እንዲሁም ለሕዝብ የተሟላ እርካታ ሲባል ጤነኛ የሆነ ሥርዓት መገንባት መቼም ቢሆን የማይታለፍ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ገዢው ፓርቲ ከላይ የተመለከተውን የእንደራደር ጥያቄ ጨምሮ በርካታ መደላድሎችን  እየፈጠረ መሆኑ በሚታወቅበት በዚህ ወቅት፤ ከዚህ በተቃራኒ የሚከናወኑ ከላይ የተመለከቱ አፍራሽ አጀንዳዎችና ድርጊቶች ደግሞ ለጤና አልባ ሥርዓት መደላድል መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልጋታል ሲባል በዴሞክራሲ መመዘኛ ብቁ የሆነ ቁመና መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ጤናማ የውይይት ሥርዓትን እንጂ ከላይ የተመለከቱ አይነቶችን እያነሱ መጣል  ከመሰረቱ የተበላሸና ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት በስተጀርባ የሚካሄድ ደባ ነው።  

ዜጎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በፈቃዳቸው እንዲመሠረት ዕውቀትን የተመረኮዘ ግንዛቤ ከነዚህ ፓርቲዎች ሲጠብቁ ከላይ የተመለከቱት አይነት አጀንዳዎች እያነሱ መነታረክ ጸረ ህዝባዊነት ነው ፡፡ የሕግ የበላይነት ሲከበር ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና በነፃነት ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ የሚያስችላቸው ዕድል በጣም የሰፋ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ የተቀደሰ ሐሳብ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ደግሞ የፓርቲዎች ሚና ግንባር ቀደም ነው። ሚናቸው የሚለካው ደግሞ  በአሉባልታ ላይ የተመሠረቱ ሳይሆን በመረጃና በማስረጃ የዳበሩ አስተሳሰቦችን ማንሸራሸር ሲችሉ ነው፡፡   ከላይ በተመለከተው መልኩ አሁን የሚሰማውና የሚታየው ደግሞ የሌሎችን አና ለህዝብ ጠቃሚ የሆነውን  ሐሳብ ደፍቆ የራስን ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ማቀንቀን መሆኑ ያሳስባል ፡፡ የሻሩ የዘመናት ቁስሎችን እያነሱ እንደራደርባቸው ማለት የፖለቲካ ውድቀትና ኋላ ቀርነት ነው።  

ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ድርድሩ አሁን እንደሚታየው እና ከላይ በተመለከተው መልኩ የቀልደኞች መጫወቻ ሳይሆን፣ ለአገራቸው ከሚታሰበው በላይ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ወገኖች የሚሳተፉበት መሆን ይገባዋል፡፡ አገራቸውን በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚያገለግሉ ወገኖች በነፃነት ያደራጁዋቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብርታትና ጥንካሬ አግኝተው የሚፈለግባቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ ደጋፊ ወይም አባል መሆን የሚፈልጉ ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ እንዲሳተፉባቸው ሲደረግ የአገሪቱ የወደፊት ተስፋ ይለመልማል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተግባር ሲረጋገጥና በሕግ የተደነገጉ መብቶች ሥራ ላይ ሲውሉ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ቀና መንገድ ላይ መረማመድ የሚቻለው ደግሞ ከቀልደኞች የጸዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ብቻ ነው ።  

በተቃውሞው ጎራ ያሉ አንዳንድ ወይም ከላይ የተመለከቱ የቆሸሹ ሃሳቦች ባለቤት የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አደብ አስገዝተው ለዴሞክራሲ ታዛዥ መሆን አለባቸው ፡፡ ‘ከእኔ በስተቀር…’ የሚባሉ ፉከራዎቻቸውን ፋይል ዘግተው ለሐሳብ ነፃነት መሟገት ይኖርባቸዋል፡፡ በሐሰተኛ ታሪኮችና ድርሳናት ላይ ተንጠልጥለው የሌለ ነገር እያወሩ የጤናማ ሥርዓት ግንባታን እንዲያደናቅፉ ህዝብ መፍቀድ የለበትም ፡፡  

ህዝብ የሚሻው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለአገራቸው ክብር፣ ዕድገትና ብልፅግና አስተዋጽኦ ይኖረናል የሚሉ ሁሉ በቀና መንፈስ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ነው፡፡ በዚህም ለልማታችን መፋጠን ቅድመ ሁኔታ የሆነውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ማጎልበት ይቻላል። ይህንን ማድረግ ሲቻል መቀራረብ፣ መነጋገርና መደራደር ችግር አይሆንም፡፡ እስካሁን ድረስ በሰፊው ሲስተጋቡ የቆዩ ከላይ የተመለከቱ አፍራሽ ሃሳቦች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ልዩነትን እያጦዙ አገርን ለማጥፋት መገዳደር ኋላቀርነት ነው፡፡ አገር የሚጠቅማት ጤናማ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ ለጤናማ ሥርዓት  ግንባታ ደግሞ በድርድር መድረኮቹ ሁሉ ጤናማ ሃሳቦችን እንጂ አቆርቋዥ ሃሳቦችን  ማስወገድ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy