Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጤናው ዘርፍ ውጤቶች

0 301

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጤናው ዘርፍ ውጤቶች

    ዳዊት ምትኩ

ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ መጥተው ዛሬ ላይ ከደረሱት የሀገራችን ዋነኛ ችግሮች ውስጥ አንዱ ስር የሰደደ ድህነት መሆኑ የሚታበይ አይደለም። የአፄውና የደርግ ስርዓቶች የህዝቡ የችግሩ ሁሉ እምብርት የሆነውን ይህን አሳፋሪ ጉዳይ ከባህሪያቸው በመነጨ ከቁብ ሳይቆጥሩት የራሳቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ብቻ ሲያሳድዱ እንደነበር የትናንት ትውስታችን ነው።

ታዲያ ይህን ስር የሰደደ የሀገር ጠላትን ከነ ሁለመናው ባህሪያቱ የተረከበው የኢፌዴሪ መንግስት፤ ‘ድህነትን ድል መንሳት የህልውናችን ጉዳይ ነው’ በማለት በዚህ አንገት አስደፊና አዋራጅ ጉዳይ ላይ ከዘመተ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል።

ይህ ከመንግስታችን ልማታዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ከሁሉም በፊት ለህዝብ ችግር ቅድሚያ የመስጠት ማንነት የመነጨው ቁርጠኛ የፀረ-ድህነት ዘመቻ፤ የችግሮችን ጓዳዎች በየመስኩ እያንኳኳ ውጤት እያስመዘገበ ነው። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባ እና እማ ወራዎች እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች አስከፊውን የድህነት ካባ አሽቀንጥረው እየጣሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው ሚሊኒየሙን በመሻገር ላይ ይገኛሉ።

እርግጥም ሀገራችን ከቻይና እና ከህንድ ቀጥላ በሶስተኛ ፈጣንና ተከታታይ የዕድገት ባለቤት እንድትሆን ያስቻሉት የመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዛሬ ላይ ተዓምር እየሰሩ ነው። እንዲያውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀደም ሲል በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ሊያሳኳቸው ይገባል በማለት ያስቀመጣቸውን “የምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች” ሀገራችን አስቀድማ እንድታሳካ አድርገዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ አድናቆትን አትርፋለች። በተለይም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ሞትን እንዲሁም የእናቶችን ሞት በመቀነስ፣ ድህነትን በግማሽ ብሎም እንደ ቲቢ፣ ወባና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የመሳሰሉ በሽታዎች ስርጭትን በመቀነስ ግቡን ማሳካት ችላለች።

ለዚህ ውጤት መገኘት የአንሳውን ድርሻ የሚወስዱት ልማታዊው መንግስትና ታታሪው የሀገራችን ህዝቦች ናቸው። ሁለቱም አካላት ተቀናጅተውና እጅ ለእጅ ተያይዘው በመስራታቸው ይህን መሰል ወርቃማ ድል ማስመዝገብ ችለዋልና። ውጤቱ በአንድ በኩል ለሀገራችንና ህዝቦችና ለወዳጆቿ ደስታ ሲሆን፤ ጠላቶቿንና ‘ልማት የለም’ እያሉ የሚያላዝኑ ‘ጥቁር ቀለም ቀቢዎችን’ አንገት የሚያስደፋ ነው።

ኢትዮጵያ በተለይም በጤናው መስክ ያገኘችው ውጤት ስኬት ማምጣት የቻሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዋነኞቹ ቢሆም፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረጋቸውም ለተገኘው ውጤት ፋይዳ አለው።

በተለይም በከፍተኛ ደረጃ የሚገለፅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ በጤናው መስክ ያለው ጠንካራ አመራር፣ የባለ ድርሻ አካላት ውጤታማ አደረጃጀት እንዲሁም የአጠቃላይ ማህበረሰቡ በተመሳሳይ ልማታዊ አስተሳሰብ እየተመራ የያዘው ቁርጠኛ አቋምና ያደረገው ተሳትፎ ተጠቃሽ ናቸው።

መንግሥት አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚሠራው ጤነኛ ዜጋ ከመፍጠር ሥራ ተነጥሎ አይታይም በሚል እምነት የጤናን ፕሮግራሞች መተግበሩ ሌላኛው ምክንያት ነው። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የጤናን ፕሮግራም ሰፊውን የገጠርና የከተማ ህዝብ ለማገልገል የተቃኘና በመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ላይ አትኩሮ በመስራቱ እንዲሁም ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረጉ ነው፡፡

የመሠረተ ጤና አገልግሎቱ ራሱ መከላከልን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ መላው ህዝብ ራሱን መሠረት ያደረገ ጤንነትና የማረጋገጥ ስርዓት ዘርግቶ በባለሙያዎች እየታገዘ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ እየተደረገ ነው፡፡ በየቀበሌው ለ5ዐዐዐ ሰው አንድ የጤና ኬላና ሁለት ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን መድቧል።

እንዲሁምለ25ሺ ሰዎች አንድ የጤና ጣቢያ ሂሳብ የጤና ጣቢያዎችን ገንብቷል። የሰው ኃይልና የቁሳቁስ አቅርቦት በማሟላት ረገድም በባለሙያዎቹ ዘንድ የአገልጋይነት አመለካከት ከመፍጠር በተጓዳኝ በአርብቶ አደሩ አካባቢ እንዲስፋፋ በማድረጉና በዚህም በዘርፉ የምዕተ ዓመቱንን ግቦች ለማሳካት ውጤታማ ስራ ማከናወኑ የስኬቱ ተጠቃሽ ምክንያት ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጤናው ዘርፍም ይሁን በአጠቃላይ በህዝቡ ውስጥ መንግስት ሲከተለው የነበረው ጥራት ያለው ፖሊሲና የአመራር ዘይቤ የስኬቱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም።

ይህም ልማታዊው መንግስት ምን ያህል የህዝቡን ችግር በፈጣንና ተከታታይ ሁኔታ እየቀረፈ መሆኑን ነው። እርግጥም ሀገራችን የመሰረታዊ ጤና አገልግሎትን በመላ ሀገሪቱ እንዲዳረስ ያደረገው ዋነኛው ጉዳይ፤ በመንግስት አማካኝነት የጤና አቅርቦቶች ውስጣዊ አደረጃጀታቸው እንዲሟላና ቁጥራቸውም በፈጣን ሁኔታ እንዲጨምር በመደረጉ ነው።

የጤና ኤስቴንሽን ፕሮግራሙ ሰራተኞች በየአካባቢው ከሚገኙ ቀበሌዎች የተመረጡ ወጣት ሴቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁና ተጨማሪ ትምህርት በጤና አጠባበቅ የወሰዱ እንዲሁም ጤናን የማስፋፋት ቁልፍ ሚናን የሚጫወቱ ናቸው።

ወጣቶቹ ሴቶች እንደመሆናቸው መጠን በአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ዋነኛ የእነርሱ ተጠቃሚዎች በሆኑት እናቶች ተሰሚነት አላቸው። በመሆኑም በማህበረሰብ ደረጃ ወደ እናቶችና ልጆች በጥሩ ሁኔታ መድረስ ችለዋል። በዚህም እናቶችን በቅርበት በመከታተል ስለ ቤተሰብ ዕቅድ፣ ስለ ጤናማ ቤተሰብ አኗኗር እንዲሁም ነፍሰ ጡር እናቶች ከመውለዳቸው በፊትና በኋላ በመከታተል እንክባቤ ያደርጉላቸዋል።

ውጤቱም ኢትዮጵያ ትክክለኛ የጤና ፖሊሲ እንዳላት ያረጋገጠ ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን አስመልክተው “የጤና ኤክስቴንሽኑ ፕሮግራም 16 ነጥቦችን የያዘ ነው። በዚህ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አማካይነት በየትኛውም የሶስተኛው አለም ያልታየ ለውጥ እየታየ ነው።

ከጤና አገልግሎት አኳያ በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በአንዳንድ አካባቢዎች በጣም አስገራሚ ውጤት ተገኝቶበታል። የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እየተተገበሩ ካሉ ስራዎች ውስጥም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ማስፋፋት፣ እናቶች በወሊድ ወቅት በሰለጠነ የጤና ባለሙያ እንዲወልዱ ማድረግና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። እነዚህን የዘርፉን ውጤቶች አቅቦ መቀጠል ያስፈልጋል።

የዘርፉን ውጤቶች አቅበን ከቀጠልን በአሁኑ ወቅትእየተከናወነ ያለውን “ዘላቂ የልማት ግቦችን” ማሳካት እንችላለን። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ገቢራዊ እንዲሆኑ የታለሙ የዘርፉን ስራዎችም በተገቢው መንገድ ለማሳለጥ ያስችለናል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy