Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጥልቅ ተሃድሶው ስኬት ለህዳሴው ጉዞ ስምረት ወሳኝ ነው!

0 236

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጥልቅ ተሃድሶው ስኬት ለህዳሴው ጉዞ ስምረት ወሳኝ ነው!

አባ መላኩ

በሁሉም ዘርፍ  በአገራችን  ተጨባጭ ለውጦች እንዲመዘገቡ ኢህአዴግ   የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል።  እንደእኔ ኢህአዴግ “እየሰራ የሚማር” “እየተማረም የሚሰራ”  ጠንካራ ፓርቲ ነው።  በዚህ ውጣውደር ውስጥ  የተፈጠሩ ችግሮች እንደሚኖሩ እርግጥ ነው።   “የሚሰሩ እጆች ይቆሽሻሉ”  እንደሚባለው ይህ ፓርቲ  ባለፉት 26 ዓመታት ባስመዘገባቸው ድሎች ውስጥ  እንከኖችም  የሉበትም  ማለት የዋሀነት ነው።  ምክንያቱም  ባለፈው  የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ወቅት  ህብረተሰቡ እጥረት ያላቸውን  ነገሮች  ለመንግስትም ሆነ ለፓርቲው  ልቅም አድርጎ  አሳይቷቸዋልና ነው።  

ከኢህአዴግ አመሰራረትና አመጣጥ መረዳት እንደሚቻለው ድርጅቱ ራሱን የማየትና  እጥረቶቹን በጥልቀት የመገምገም የቆየና የዳበረ ልምድ ያለው ፓርቲ  መሆኑ አሌ የሚባል ሃቅ አይደለም። ኢህአዴግ በርካታ ደጋፊ ያለው መሰረተ ሰፊ የሆነ የህዝብ ድጋፍ ያተረፈ ጠንካራ ፓርቲ ነው። በቅርቡ በአገራችን  በአንዳንድ አካባቢዎች  በመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳቢያ የተከሰቱ ሁከቶች ድርጅቱ ለህዝብ የገባውን ቃል በተፈለገው ፍጥነትና  ጥራት  አለማቅረቡን  የሚያመላክት ነበር። ፓርቲው  ከህዝብ የተነሱ እጥረቶቹን አምኖ ተቀብሎ የመልካም አስተዳደር ችግሮች  ለማስተካከል   የሚያስችለውን  ተገባራት  በማከናወን ላይ ነው። በጥልቅ ተሃድሶ ሂደት  ህዝብንና መንግስትን ሲያቃቅሩ የነበሩ  የስራ ሃላፊዎችንና ፈጻሚዎችን  በማጋለጥ መንግስትም በየደረጃው  ያለውን አሰራር  በመፈተሽ  እስከ ስራ አስፈጻሚው (ካቢኔ) ድረስ  እንደገና የማዋቀር ስራ ሰርቷል።  ህብረተሰቡም ከመንግስት  ጎን በመቆም ይሻላል የሚለውን አሰራር እንዲተገበር አድርጓል። በማድረግም ላይ ነው።

“ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ’’  እንደሚባለው ኢህአዴግ ይህን ጥልቅ ተሐድሶ የሚያደረገው በቅድሚያ ለራሱ ህልውና ነው፡፡ ይህ ፓርቲ አገራችንን ወደአሰብንበት ከፍታ ለማውጠት ገና ብዙ መስራት ቢጠበቅበትም፤ እስካሁን በአገራችን ለተመዘገቡ ለውጦች ማለትም  ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና ዕኩልነት፣ ለህዝቦች ኑሮ መሻሻል፣    ለአገራችን የኢኮኖሚ  ዕድገት፣ ለአገራችን ገጽታ  መለወጥ፣ ያበረከተው  ጥረት  የሚደነቅና  ሁሌም አንጸባራቂ ናቸው።  ባለፈ ታሪክ የሚኖር የለም። በትላንት ትዝታ አይኖረም፡፡ ትላንት እንዲህ ነበርኩ ማለት  የትም አያደርስም። አገራችንን ወደኋላ የጎተታት ይህ አይነት አካሄድ  ነው።   ያ ትውልድ መልካም ነገር አስቀምጦልን አልፏል።

አገራችን በአንድ ወቅት የአክሱምን ሃውልትን፣ የላሊበላን ውቅር አብያተክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተ መንግስቶችን፣ የሐረር ግንብን አንጻለች በማለት የሚገኝ ነገር የለም። እኛስ ምን እናድርግ?  ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቀው  የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓትና ልማት ማስቀጠል ነው።  የአሁኑ ትውልድ አሻራውን በታሪክ መህደር ላይ ለማስቀመጥ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነው። ይህን አገራዊ ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ ደግሞ  በየትኛውም በኩል ያሉ ችግሮችን መፍታት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።   

ባለፈው በተካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ  ሂደት  ህብረተሰቡ  በመልካም አስተዳደር ረገድ  ይስተካከሉልኝ ያላቸው ነገሮች ተለይተው የሚመለከተው አካልም  ሁሉ ለመፍትሄው በመረባረብ ላይ ይገኛል። ኢህአዴግም ሆነ መንግስት የተጀመረውን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማስቀጠል ቁርጠኝነታቸውን  በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት  አሳይተዋል። በተመሳሳይ  ሁሉም ባለድርሻ አካላት  አገራችንን ወደ ከፍታ ለማውጣት    ራሳቸውን  ማየት እንዳለባቸው አምነው “በጥልቀት በመታደስ” ሂደት ውስጥ  ሁሉም በንቃት ተሳትፏል። ይህ ሂደት እስከታች አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ድረስ  ወርዷል። ለታህድሶው ስኬት የህብረተሰቡ  ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ  እንደከዚህ በፊቱ  ህዝብና መንግስት  በቅርበት በመስራት  ጥገኞችን መመንጠር ይጠበቅባቸዋል። መንግስት የትኛውንም ያህል ቁርጠኝነት ቢኖረው ያለህዝብ አጋርነት የትም ሊደርስ አይችልም። ለዚህ ነው ኢህአዴግ ለእያንዳንዱ ነገር ከህዝብ ጋር መመካከርን የሚመርጠው።

ኢህአዴግ የሚታወቅባቸው መልካም ተሞክሮዎች እንዳሉት ሁሉም ይስማማል።  እነዚህ መልካም ልምዶች አሁንም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ አንድ ፓርቲ  ህዝባዊ ከሚያሰኙት ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው በፓርቲው የውስጥ አሰራር ይሁን በመንግስት ስራ ተጠያቂነትን ማንገስ መቻል ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እንደኢህአዴግ ተጠያቂነትን የሚያነግስ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም።  ኢህአዴግ ተጠያቂነትን በማንገስ  ረገድ   በአፍሪካ  ተወዳዳሪ  ያለው ፓርቲ  አይደለም። ኢህአዴግ ከፍተኛ የሚባሉ  መስራች አባላቱን ሳይቀር በህግ ፊት እንዲገተሩ  አድርጓል። ከቅርብ ጊዜ በፊት እኮ “የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ሲባል እንዳልነበር አሁን ላይ ደግሞ  “ሲሾም ያልበላ…” የሚባለው የዛገ አስተሳሰብ  በበርካታ የፓርቲው አባላት  እንደ ሞቶ  ሲቀነቀን አድምጠናል። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ከፍታ ማምጣት የቻለው ህዝባዊነትን መላበስ በመቻሉ ነው፣ ያ በፓርቲው ውስጥ የተገነባው ህዝባዊ  ባህሪ ዛሬ በጥልቅ በመታደስ ሂደት እንደገና በማበብ (Rejuvenate)  በማድረግ   ላይ ነው።

በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሚሰባሰቡ አባላት ሁሉም ምልዑ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በአንድ  ፓርቲ ውስጥ  ቢያንስ ሶስት አይነት አባላት ይኖራሉ። የመጀመሪያዎቹ  እውነተኛ የህዝብ ልጆች፣ ለህዝብ ጥቅም የቆሙ፣  ህዝብ ሲጠቀም እንጠቀማለን ህዝብ ሲለወጥ እንለወጣላን ብለው የሚያምኑ አባላት ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ  ደግሞ የድርጅትን ስም ተላብሰው የግል ጥቆማቸውን የሚያሳድዱ ፣ የህዝብን አደራ የረሱ፣ የአገር ልማትና ዕድገት የማያስጨንቃቸው እርስ በርሳቸው በጥቅም የተሳሰሩና የሚደጋገፉ አካሎች  ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት  የመድረክ አንበሶች ናቸው።  የተገኘውን መድረክ ሁሉ  ለህዝብና ለድርጅቱ ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት  ይሞክራሉ።  በመድረክ ላይ  ታማኝ መስለው ይቀርባሉ። ገቢራቸው ግን በግልባጩ ነው።  በሶስተኞቹ  ወገኖች ደግሞ ሁሉን ነገር በምናገባኝነት  የሚያልፉ፣  አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ በሁሉም ነገር መስለው ማደር የሚፈልጉ አባላት ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢህአዴግ ቤት እየበዛ ያለው  ምን አገባኝ የሚለው ሶስተኛው አባላት ቁጥር ይመስለኛል። እነዚህ አካላት  በርካቶቹ ድርጅቱን በቅርቡ የተቀላቀሉ ልምድ የሌላቸው በመሆናቸውም የተነሳ የድርጅቱን አላማ በቅጡ አልተረዱትም። በርካቶቹ ወደዚህ አደርባይነት ጎራ የተቀላቀሉት ልምድ ከማጣትና ከፍራቻ  ይመስላል።  እነዚህን በስልጠናና በሌሎች ነገሮች  ማስተካከል ብዙም የሚከብድ አይደለም።   ከላይ በሁለተኝነት ያነሳናቸው በኢህአዴግ ስም የመንግስት የስራ ሃላፊነትን የያዙ አባላት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የግልና የቡድናቸውን ጥቅም  የሚያሳድዱ ህዝብና መንግስትን የሚያራርቁ አከላት  በመሆናቸው በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት ልናራግፋቸው ይገባል።   

እነዚህን የጥፋት ሃይሎች  የማጋለጥ ስራ ኢህአዴግ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጥልቀት መታደስ በሚል የጀመረው ሂደት በርካቶችን ተጠያቂ በማድረግ ላይ ይገኛል። እንደእኔ ኢህአዴግ ካለው ልምድ እነዚህን ጥገኞች  የማበጠርም ሆነ ቆርጦ የመጣል ችግር የለበትም፡፡  ለአብነት  ያህል  የኢህአዴግ መስራች የነበሩ  ከዚያም የመንግስትም  ሆነ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች   ለጥፋታቸው  ተገቢውን  ቅጣት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

 

 

 

አሁንም ኢህአዴግ የጀመረው የጥልቀት ተሐድሶ ሂደት ስንዴውን ከአንክርዳዱ የማጥራት ስራ በሁሉም ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠል መቻል አለበት፡፡ ኢህአዴግ እዚህ የደረሰበትን   ህዝባዊነት ባህሪ  በጥልቀት በመታደስ ሂደት  መተግበር ይኖርበታል። የፌዴራል መንግስቱ የተሻለ አፈጻጸም ያመጣሉ ያላቸውን አስፈጻሚዎች ወደ ከፍተኛ ስልጣን አምጥቷል። በተመሳሳይ ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸው ክልሎች አስፈጻሚያቸውን እንደገና መሰረታዊ በሚያስብል መልኩ ተቀይረዋል። የመንግስት ስልጣን ለህዝብ ማገልገያ መሳሪያ እንጂ  የግል ጥቅም ማሳደጃ  ምቾት መጠበቂያ ሊሆን አይገባውም።  ጥልቅ ተሃድሶው ሂደት  ውጤታማ የሚሆነው ህብረተሰቡ መብቱን የመጠየቅ እንዲሁም  ግዴታውን የመወጣት  ልምዱን ማዳበር ሲችል ብቻ ነው። መንግስትም  አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቹን በቅርበት የመከታተልና አጥፊዎችን በፍጥነት ወደህግ ማቅረብ ይኖርበታል።

ኢህአዴግ የቆየና የዳበረ ልምዱን   ተጠቅሞ ህዝብ ላይ የተጠበቁ የድርጅትን ካባ ለብሰው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አባላቱን ቆርጦ ለመጣል የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡም ሊያግዘው ይገባል። አድረባይነትና መስሎ ማደርም ለአራችን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት አደገኛ አካሄድ ነውና መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በድርጅትም ሆነ በመንግስት  አስተዳድረ ውስጥ  የኔትዎርክ  አሰራር  መዘርጋትና የግል ጥቅምን ማሳደድ   የኢህአዴግን የቆየ ህዝባዊ ባህል የሚሸርሽር በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ “አካፋን አካፋ’’ የማለት የድርጅቱ የቆየ ልመድ አሁንም መተግበር  ይኖርበታል።  

እንደእኔ እንደእኔ ኢህአዴግ በቅድሚያ ራሱን ለማረም ቆርጦ መነሳቱ  ሊያስመሰግነው ይገባል።   ምክንያቱም ኢህአዴግ ከማንኛውም ነገር በላይ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፓርቲ ነው። ለዚህ በቂ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። ለአብነት ኢህአዴግ በአገራችን ለተመዘገቡ መልካም ነገሮች ሁሉ መሰረት ነው፡፡ ለህዝቦች እኩልነትና ነጻነት፣ ለተመዘገበው ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ኢህአዴግ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ህዝቦች ማንነታቸውን እንዲያውቁ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ዜጎች ሃሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ፣ አገራችን በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ተሰሚነት እንዲኖራት፣ ከሁሉም በላይ በአገራችን ህዝቦች መካከል የ”ይቻላል” መንፈስን  እንዲፈጠር አድርጓል። በመሆኑም  የኢህአዴግ  የጥልቅ ተሃድሶ ስኬት የአገራችን የህዳሴ ጉዞ  ስምረት  በመሆኑ ነው።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy