Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ለዴሞክራሲ ግንባታ

0 383

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ለዴሞክራሲ ግንባታ

                                                          ታዬ ከበደ

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 31 ላይ፤ “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት አለው። ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ናቸው” በሚል በተደነገገው መሰረት፣ ማንኛውም ዜጋ ባሻው ማህበር ወይም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታቅፎ መንቀሳቀስ እንዲችል በመደረጉ ሀገራዊ ዴሞክራሲው አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሰፋ ተደርጓል። በዚህም ለዴሞክራሲው መጎልበት ወሳኝ ሚና ያላቸው በርካታ ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

የመደራጀት መብቱን ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ እስከተካሄደው ምርጫ 2007 ድረስ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለአምስት ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች ተወዳድረዋል።

ሆኖም የምርጫ ጉዳይ በመራጩ ህዝብ ፍላጎት በሚሰጥ ድምፅ ላይ የተመሰረተ እንጂ፣ በገዥው ፓርቲ አሊያም መንግስት በሚያደርጉት ችሮታ ላይ የሚከናወን ባለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በአብላጫ ድምፅ ተመራጭ ሊሆኑ አልቻሉም። በእኔ እምነት ሶስት ምክንያቶች ተቃዋሚዎቹ የህዝቡን አብላጫ ድምፅ እንዳያገኙ ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል። አንደኛው፤ ተቃዋሚዎቹ በህገ መንግስቱና በህዝባቸው ከመተማመን ይልቅ በውጭ ኃይሎች የሚዘወር ዴሞክራሲን የሚሹ ሆነው መቅረባቸው ነው።  

ሁለተኛው፤ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠሩ ብሶቶችን ከማራገብና ቅንጭብጫቢ የኒየ-ሊበራሊዝን አስተሳሰብ ከማስተጋባት በስተቀር የህዝብን ቀልብና ልብ ሊገዙ የሚችሉ የነጠሩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ማቅረብ አለመቻላቸው ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ፤ ተቃዋሚዎቹ ራሳቸውን እንደ ፓርቲ ሲመሰርቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን እናጎለብታለን በሚል እሳቤ ይሁን እንጂ፣ ከአወቃቀራቸው ጀምሮ እርስ በርሳቸው የማይተማመኑና “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ስሜታዊ ቁርኝት የተቧደኑ እንዲሁም በጥቅም ሽኩቻ ሳቢያ በምርጫ ሰሞን በአደባባይ ሲፈረካከሱና እርስ በርሳቸውም ሲወነጃጀሉ በመራጩ ህዝብ ዓይን ትዝብት ላይ ስለወደቁ ነው ብዬ አምናለሁ።

ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር እያደረጉ ነው። ታዛቢ መርጠውም በሰላማዊ መንገድ እየተወያዩ ነው። በአሁኑ ወቅት መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል። ተቃዋሚዎችም ይህን ተስፋ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳይከታቸው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል።

እናም ከተቃዋሚዎቹ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች መነሻቸውና መድረሻቸው በግልፅ ተለይተው ሊገለፁና የጋራ ድምዳሜ ሊያዝባቸው ይገባል። ይህ ሲሆንም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ይበልጥ በመግለፅ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል። አሊያ ግን በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የምንሰማቸው እንደ ‘ስልጣን እንጋራ’ ዓይነት የተሳሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመፍጠር በአጠቃላይ ህዝቡ ውስጥ የማይገባ ምስል ሊያሲዙ ይችላሉ። በመሆኑም ለእኔ ከዚህ አኳያ ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ተገቢ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀቱን ለመጨመር በተያዘው ቁርጠኝነት ላይ አንድ ርምጃ መሄድ ጭምርም ነው።

በአንፃሩም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር፤ ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ። ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል።

ዴሞክራሲን ከማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ይህ በገዥው ፓርቲ አማካኝነት የተጠራው የድርድር መድረክ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው። እንዲህ ዓይነት መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የሀገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። እናም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄደው ክርክርና ድርድር ከዚህ ዴሞክራሲያዊ አውድ ብቻ መታየት ያለበት ይመስለኛል።

በመሆኑም በአንዳንድ ፅንፈኛ ወገኖች እንደሚነገረው የሚካሄደው ድርድርና ውይይት ለታይታ አሊያም ከፍራቻ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ይገባል። እንደሚታወቀው ገዥው ፓርቲ ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር ያደረገው መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል የነበረው አንዱ ጉዳይ የዴሞክራሲ እጦት ነው። ደርግን አስወግዶ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን፣ ይህን የህዝቦችን ጥያቄ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት አድርጓል። ገዥው ፓርቲ ገና ከስልጣን መባቻው ወቅት ጀምሮ የታጠቁና ወደ 17 የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማወያየትና በማከራከር ባህሉ የሚታወቅ ነው። ይህም ዴሞክራሲን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማስቻል ክርክርና ድርድር ማድረግ ለገዥው ፓርቲ አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። እናም ሰሞነኛው ለድርድርና ለክርክር የሚሆን ስምምነት በኢህአዴግና በሀገራችን ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማካኝነት ለመካሄድ የተያዘው ውጥን ከታይታ አሊያም ‘ገዥው ፓርቲ ስለ ፈራ ነው’ ከሚለው የፅንፈኞች የተዛባ ምልከታ ጋር ምንም የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

እርግጥ አንዳንድ ፅንፈኞችና የሀገራችን ሰላምና ልማት እንዲሁም ዴሞክራሲያችን በሚፈለገው መጠን እንዳይሰፋና ጥልቀት እንዳይኖረው የሚሹ የውጭ ሃይሎችና ተላላኪዎቻቸው እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውንም ነገር ማጥላላትና ለጉዳዩ ያልተገባ ስም መለጠፍ የተለመደ ተግባራቸው በመሆኑ ተግባራቸው እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም።

ሆኖም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ማናቸውም ዴሞክራሲን የሚያጎለብቱ ተግባራት የህዝቡን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ እንጂ ፅንፈኞችና የውጭ ሃይሎች ተላላኪዎች እንደሚያስወሩት የተዛባ አስተሳሰብ አይደለም።

በመሆኑም እዚህ ሀገር ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚካናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆመ ታስቦ የሚከናወን ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ስለሆነም  በገዥው ፓርቲም ይሁን በመንግስት በኩል የሚከናወኑ ጉዳዩች ሁሉ ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል እንጂ፣ ለታይታ አሊያም ለሌላ ጉዳይ የሚከናወኑ አይደሉም፤ ሊሆኑም የማይቸሉ መሆናቸውን በሰከነ አዕምሮ ግንዛቤ መያዝ ይገባል ባይ ነኝ። ምክንያቱም የሚካሄደው ድርድር ግብ ዴሞክራሲን ስለሚያጎለብት ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy