Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲ የነብር ጅራት ነው

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲ የነብር ጅራት ነው

 

አሜን ተፈሪ

 

የሐገራችን የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በስልጣን በመቆየት ሒሳብ የሚታዩ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እጅግ ውስብስብ ከሆነ እና ስር ከሰደደ ድህነት ለመውጣት የሚያስችሉን ወይም ምቹ የልማት ዕድል የሚጥሩልን መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር፤ ህዝቡ ከዛሬ ነገ ኑሮዬ ይሻሻላል፤ ጥሩ ጊዜ ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረጉን ትቶ፤ መጪው ዕድሉ ሁሉ ጨለማ መስሎ ታይቶት በተስፋ መቁረጥ ላይ የተመሠረተ ጎዳና እንዳይከተል እና ፋይዳ ወደ ሌለው ትርምስ እና ደም መፋሰስ እንዳንገባ የሚጠብቁን፤ ከሐገራዊ ህልውና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ የግጭት እና የጦርነትን ፖለቲካዊ ምንጮች በማድረቅ ለልማት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዙ፤ የልማት፣ የሰላም እና የሐገራዊ ህልውና ዋስትና የሆኑ ክቡር ግቦች ናቸው፡፡

 

ገዢው ፓርቲ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በምን ደረጃ እንደሚመለከታቸው ለመረዳት፤ ከ14 ዓመታት በፊት ይፋ በሆነው የመንግስት የፖሊሲ ሰነድ (በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች፣ 1994) የሰፈረውን ቃል መመልከት በቂ ነው፡፡ ‹‹የዴሞክራሲ እና የመልካም ስርዓት መገንባት ከተሳነን እጅግ ዘግናኝ በሆነ እልቂት ተንጠን ረጅም ባልሆነ ጊዜ ውስጥ እንበታተናለን›› የሚለው ኢህአዴግ፤ ‹‹ህልውናችንን ለማረጋገጥ ከዴሞክራሲ እና ከመልካም አስተዳደር ግንባታ ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ በዚህ ዓላማ ላይ መንሸራተትን፣ ወደ ኋላ መመለስን፣ ሽንፈትን መቀበል አይቻልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሽንፈት ማለት እንኳንስ ለመሸከም ለማሰብም የሚከብድ ጥፋት የሚያስከትል ነገር ይሆናል›› (ገጽ፣ 13)፤ ይላል፡፡

 

ጉዳዩን በዚህ ደረጃ የሚመለከት ድርጅት በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ሊቀልድ አይችልም፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እና በመልካም አስተዳደር ጉድለት ሊታማ አይገባም፡፡ በርግጥ በዚህ ረገድ በኢህአዴግ ላይ የሚቀርበው ትችት መነሻው፤ የሐገራችን የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ እያደር የማሽቆልቆል አዝማሚያ በመከተሉ ሣይሆን በፍጥነት እየመጨመረ ከመጣው የህዝብ ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ ካለመቻሉ ጋር እንደሚያያዝ አምናለሁ፡፡

 

ታዲያ እንዲህ ዓይነት ችግር የተፈጠረው፤ በየደረጃው የተቀመጡት የመንግስት እና የድርጅት የሥራ ኃላፊዎች የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ለሐገራችን ምን ያህል ወሳኝ ጉዳዮች እንደሆኑ ‹‹ባመረዳታቸው›› አይደለም፡፡ ጨርሶ አይደለም፡፡ እንዲያውም የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች የጉዳዩን አጣዳፊነት በተባ አገላለጽ በመድረክ ሲናገሩ በተደጋጋሚ መስማታችን አልቀረም፡፡ ርግጥ ነው፤ አንዳንዴ ችግሩን ‹‹በሰበብ ጋሻ›› ሊመክቱት ሲሞክሩ እናያለን፡፡ በጋሻነት ከሚነሱት ነጥቦች መካከልም አንዳንዶቹ ለችግሮቻችን ሰበብ ሆነው ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ሰበቦቹ ያለ ጥንቃቄ በየአጋጣሚው የሚነሱ ከመሆናቸው እና በስንፍና ለሚፈጠሩ ጉድለቶች ሁሉ ጋሻ ተደርገው የሚጠቀሱ በመሆናቸው የተነሳ፤ የህዝቡን ልብ የማሸነፍ አቅማቸው ተንጠፍጥፏል፡፡ አሁን ህዝቡ ኢህአዴግን የሚመዝነው፤ ድርጅቱ ምን ያህል ከባድ የሆኑ የትግል ምዕራፎችን አልፎ፤ ሐገሪቱን አሁን ከምትገኝበት የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረሱን ከግምት አስገብቶ አይደለም፡፡ አሁን መሪው ድርጅት እና መንግስቱ የሚመዘኑት ሊያደርጉ የሚገባቸውን ነገር በመፈጸም –አለመፈጸማቸው ብቻ ነው፡፡  

 

በሁለት አስርት ዓመታት የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ትግል፤ በንጽጽር ከተነሳነበት ሁኔታ እጅግ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሳችንን በማስታወስ የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ይህን ጉዳይ ከቃል በላይ እርሱ በኑሮው አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በኑሮው የሚገጥሙት ፈተናዎች እንዲወገዱለት ይፈልጋል፡፡ አሁን መሪው ድርጅት እና የመንግቱ የሚመዘኑት እነዚህን ፈተናዎች አርኪ በሆነ ደረጃ መመለስ በመቻላቸው እና ባለመቻላቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ትግሉ ከትናንት ዛሬ ከባድ እየሆኑ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ በዚሁ ልክ የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ወሳኝ የህልውና ጥያቄዎች የመሆናቸው ጉዳይ ተጠናክሮ ይወጣል፡፡

 

ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የተሃድሶ ንቅናቄው ሲጀመር አመራሩን ሲያስጨንቀው የነበረው እና ‹‹በጊዜ የለንም›› መንፈስ ሲያሯሩጠው የነበረው፤ በየጊዜው እንደሚወርድ ናዳ  የቆጠረው ችግር አስጊነቱ አሁንም እንዳለ ቢሆንም፤ በአመራሩ ዘንድ የነበረው ‹‹የጊዜ የለንም››  ጥድፊያ አሁን አይታይም፡፡ ሆኖም የችግሮቹ አጣዳፊነት ይበልጥ እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አይደለም፡፡ በታላቅ ቁርጠኝነት የተጀመረው የዴሞክራሲ እና ልማት እንቅስቃሴ አዳዲስ ፍላጎቶችን እየፈጠረ፤ ማህበራዊ ሽግሽጉ (social mobility) እየተጠናከረ በመሄዱ፤ ዙሩ እየከረረ እንጂ እየረገበ አይደለም፡፡ ትናንት የአርሶ አደር አባቱን ህይወት ተቀብሎ ለማደር ዘግጁ የነበረው የአርሶ አደሩ ልጅ፤ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሲወጣ ከአባቱ የተሻለ ህይወት የሚፈልግ ሰው ይሆናል፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን እየፈጥርን በመሆኑ ሩጫው እየከረረ እንጂ እየረገበ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ በላይ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ የድህነቱ ናዳ እንዳለ ሆኖ፤ አሁን የልማት ናዳው ተጨምሯል፡፡ ትናንት የበጋ መንገድ ይሰራልኝ ይል የነበረው ህዝብ፤ ዛሬ የአስፋልት መንገድ አልተሰራልኝም ብሎ የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ ሩጫው እየከረረ መጥቷል፡፡

 

በመልካም አስተዳደር ረገድ ለሚታዩት ጉድለቶች፤ የመንግስት የማስፈጸም አቅም ደካማ መሆን እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም፤ ይህን ጉዳይ በመናገር የህዝብን ጥያቄ ማስታገስ አይቻልም፡፡ የሚቻለውን መስራት የተሳነው ሰው፤ ከአቅሙ በላይ ለሆኑ ችግሮች የሚያቀርባቸውን ምክንያቶች ተቀባይ አያገኝም፡፡ የነብር ጅራት ይዘናል፡፡ ‹‹ግዳይ እንጥላለን፤ ወይ በነብሩ እንበላለን›› የሚያሰኝ ሁኔታ ውስጥ እገኛለን፡፡ የማስፈጸም አቅማችን ደካማ ሆኖ ሳለ በቁርጠኝነት በተሰማራንበት አካባቢ ምን ዓይነት ሥራ መስራት እንደምንችል የሚያሳዩ የተግባር ተመክሮዎች አሉ፡፡ የህሊናችን ፋና ልናደርጋቸው የሚገባው እንዲህ ያሉትን ስኬቶች እንጂ፤ ሰነፎች እና ኪራይ ሰብሳቢዎች በቀላሉ አንስተው ጋሻ የሚያደርጓቸውን እጥረቶቻችን አይደለም፡፡ ከድህነት አዘቅት ወጥተው ብልጽግናን ማረጋገጥ የቻሉ ጠንካራ ህዝቦች ሁሉ እንደ ሰበብ ሊነሱ የሚችሉ ነገሮችን ተሻግረው መሄድ የቻሉ ናቸው፡፡

 

በፖለቲካው ሆነ በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ የሚታዩ እንከኖች ሁሉ ፌዴራላዊ – ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለቀውስ የሚዳርጉ ችግሮች መሆናቸውን በመረዳት ነቅቶ መታገል ይገባል፡፡ ሃይ ባይ የሌላቸው የፓርቲ እና መንግስት ባለሥልጣናት የኢህአዴግን ፍቅር እየቸረቸሩ፤ ራሳቸው እና ከነሱ የተጠጉ ሰዎች በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚያደርጉትን ሩጫ በቆራጥ ውሳኔ መታገል ይኖርብናል፡፡

 

 

ይህ መንግስት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› በሚል የሚጠቅሰው ችግር ተወግዶ፤  በስራ አስፈፃሚው አካል ውስጥ ያለ ባልሥልጣን የወደደውን ሐብታም የሚያደርግበት፤ የጠላውን በድህነት እንዲኖር ማድረግ የሚችልበት አሰራር እንዳይኖር በማድረግ በየደረጃው ባለው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ አድርባይነት እንዳይነግስ እና መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ በመግባቱ የተነሳ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ የህዝብ ተሳትፎ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህም ጉዳይ መልሶ ወደ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ጉዳይ ያመጣናል፡፡ እናም በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳዳር ዘርፍ ያለውን ችግር በማስወገድ የተስፋው ብርሃን እንዲደምቅ በማድረግ የተጀመረውን ፈጣን የልማት ጉዞ እናስቀጥል፡፡

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy