ድርቅን መቋቋም የቻለ ሀገራዊ አቅም
ቶሎሳ ኡርጌሳ
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለአየር ንብረት ለውጥ የተጋለጠ ነው። በዚህም ሳቢያ በየጊዜው ለድርቅ አደጋ ይጋለጣሉ። ኢትዮጵያም ከዚህ የተፈጥሮ አደጋ ልታመልጥ አልቻለችም። በተለያዩ ወቅቶች ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ ሆና ቆይታለች። ርግጥ ድርቅን መቋቋም የሚያስችል አቅም በኢፌዴሪ መንግስት አማካኝነት በመገንባቱ ሀገራችን ውስጥ ድርቅ ወደ ረሃብ እንዳይቀየር ማድረግ ተችሏል።
እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት በሀገር ውስጥ ባስመዘገበው ዕድገት ሳቢያ ሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋን እየተቋቋመ ነው። ይህ አቅሙም በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የድርቅ አደጋ ሲከሰቱ አደጋው ወደ ረሃብነት እንዳይቀየሩ ማድረግ የቻለ ነው። በአሁኑ ወቅትም ለጋሽ ሀገራት ይህ ነው የማይባል ድጋፍ ሳያደርጉ መንግስትና ህዝቡ በአንድነት በመሆን አደጋውን መቋቋም ችለዋል። ይህም የህዝቡና የመንግስት አቅም እየጎለበተ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ እዚህ ላይ ይህ አቅም እንዴት እንደተገነባ በጥቂቱም ቢሆን ማውሳት አስፈላጊ ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስታችን የምትመራው ሀገራችን ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው ዕድገት ችግሮችን እየተቋቋመች መጥታለች። ወደፊትም በቀየሰችው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አማካኝነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታች ህዳሴዋን ማረጋገጧ አይቀሬ ነው።
ጥቂት ቀደምት ምሳሌዎችን ላንሳ። የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ዕመርታችን የሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዘገቡ ሀገራችን በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና በአፍሪካ ከሚገኙ ሶስት ሀገራት ግንባር ቀደም በመሆን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የድርቅ ችግር የተገኘው ዕድገት ለመቋቋም ችሏል ሲባል ቀደም ሲል የተሰሩ ስራዎች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ መገንዘብ ይገባል። በተለይም የኢፌዴሪ መንግስት በየጊዜው በወሰዳቸው ተከታታይ ድህነትን የመቀነስ ርምጃዎች ድምር ውጤት ለዛሬው ድርቅን ተቋቋሚነታችን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸው የሚካድ አይመስለኝም።
ከ1994 ዓ.ም በፊት የተከናወኑ የኢኮኖሚ መዋቅር ማስተካከያና ማሻሻያ ፕሮግራሞች የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴውን ከማነቃቃታቸው ባሻገር፤ የኋሊት ሲጓዝ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ትክክለኛ አቅጣጫውን ይዞ እንዲጓዝ ያደረጉ መሆናቸውን እየተመዘገቡ ካሉት ዘርፈ ብዙ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቶች መገንዘብ ይቻላል።
ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖር ወሳኝ መሆኑ ስለታመነበት፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የፊስካልና የሞኒተሪንግ ፖሊሲዎችን በማጣጣም እንዲሁም ዝቅተኛ የመንግስት በጀት ጉድለትንና የውጪ አሸፋፈን እንዲኖር በማድረግ ብሎም የገንዘብ እንቅስቃሴው ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዋጋ ዓመታዊ ዕድገት ጋር የተዛመደ እንዲሆንና የውጭ ምንዛሬ ምጣኔዎችን ለማስተካከል ያለሰለሰ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ውጤት ተገኝቷል።
ባለፉት 15 ዓመታት ለሁለት ዓበይት የኢኮኖሚ ዘርፎች (ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ) ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ መቻሉን ነው— በእስከ አሁኑ የተመዘገበው መረጃ የሚያስረዳው፡፡ በድህረ – ማሻሻያ ፕሮግራሙ ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለስራው የሰው ሃይል ልማት በመንግስት የተሰጠው ትኩረት የላቀ በመሆኑ የተገኙ ውጤቶችም አበረታች ሆነዋል፡፡ እርግጥም በመንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም በንጹህ ውኃ አቅርቦት ረገድ የተገኘው መሻሻል አገልግሎቶቹን ለማስፋፋት የጠየቁት ከፍተኛ የፋይናንስና የሙያ ክህሎቶች፤ የተፈራውን ያህል ስራዎቹን ሊያስተጓጉሏቸው አለመቻላቸውን የተገኙት ውጤቶችን አይቶ መመስከር የሚቻል ይመስለኛል።
ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የኢኮኖሚ ዕመርታችን የሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዘገቡ ሀገራችን በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና በአፍሪካ ከሚገኙ ሶስት ሀገራት ግንባር ቀደም በመሆን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ በቅታለች። የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው። እናም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ስርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የቻለ ቢሆንም፤ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን በአመርቂ ሁኔታ መፈፀም ተችሏል። በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚሊዮነር ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል። በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመት አፈፃፀምም አመርቂ እየሆነ ነው።
ርግጥ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ በገጠርም ሆነ በከተማ የምታከናውነው የልማት ርብርብ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እንዲቀየር ማድረጉ አይካድም። እናም አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚተትኑት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቱ በዚሁ ከቀጠለ በሚቀጥሉት አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ባስቀመጠችው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ጎራ ለመሰለፍ ያስችላታል።
ዕድገቱ የዜጎችን የትምህርት፣ የጤናና የንፁህ መጠጥ ውሃ…ወዘተ ተጠቃሚነት የመሳሰሉት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ የማህበራዊ አገልግሎት እንዲዳረሱ በማድረጉ በኩል አስተዋፅኦ አድርጓል። ታዲያ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የቻለ ቢሆንም፤ በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና የዕድገቱ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ መተግበር ከተጀመረ ሁለት ዓመት እየሆነው ነው።
የሀገሪቱ የግብርና መር ፖሊሲ ወደ ኢንዱስትሪ መር በሂደት እንዲሸጋገር እየተደረገ ያለው ጥረትም የሚደነቅ ነው። ባለፉት 15 ዓመታት መንግስትና ህዝብ በጋራ በመሆን ባከናወኑት ሰፊ ጥረት እያስመዘገቡ ያሉት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት አሁንም ግለቱን ጠብቆ በመካሄድ ላይ ነው። እነዚህ ሀገራዊ አቅሞች የመንግስትንና የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም ያጎለበቱ ናቸው። እንደሚታወቀው የሀገራችንን ምጣኔ ሃብት እየመራ ያለው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ነው። ይህም ግብርናውን በፍጥነት በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር እውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ታዲያ ግብርናው በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ኢትዮጵያችንን በኢንዱስትሪ የበለፀገች ለማድግና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማቀላቀል፣ መንግስት በነደፈው በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰፊ ርብርብ እያደረገ ነው። ዕቅዱ በቀሩት ጊዜያት ውስጥም በአጥጋቢ ውጤት እንደሚሳካ ቀደምት ተግባራት ውጤታማነት በመነሳት ለመተንበይ የሚከብድ አይደለም።
ታዲያ እነዚህ ተግባራት ድርቁን ለመቋቋም የሚያስችሉን ቀደምት ስራዎች ናቸው። መንግስትም የተከሰተውን የድርቅ ችግር ብዙም የልማት አጋር ሃይሎች ድጋፍ ሳይኖረው በራስ አቅም ሊቋቋመው ችሏል። ህዝቡም መንግስት በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ድርቁን በመቋቋም ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው። ወደፊትም ማንኛውንም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችል አቅም ተገንብቷል ማለት ይቻላል።