Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርቅን በዘላቂ ልማት

0 629

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድርቅን በዘላቂ ልማት

ብ. ነጋሽ

ድርቅ የሚለውን ቃል ከፊደል ጋር ነው የቆጠርኩት፤ በልጅነቴ የቄስ ትምህርት ቤት እያለሁ። የኔታ ትምህርት ቤት ሀ፣ ሁ . . . ሲያስተምሩኝ ውዬ ወደቤቴ ሰመለስ ዳንቴል ተሸፍኖ የተቀመጠው ሬዲዮ ስለወሎ ድርቅ ያወራል። ሬዲዮው የወሎ ድርቅ፣ የድርቅ ኮሚሽን ምናምን ይላል። ሲዘፍንም ስለረሃብ ነው።  ወሎ ተርቦ እንደዚያ ሲያልቅ፣ በድብቅ ነበር ማንም ሳያውቅ፤ ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ . . . ይላል። እንዲህ ድርቅንና ረሃብን ከፊደል ጋር አወኩት። ይህ በልጅነት ያወኩት ድርቅ የልጅነት ትውስታ ብቻ ሆኖ አልቀረም። ሁሌ የምሰማው፣ ነብስ ካወኩ በኋላ ደግሞ የሚያስጨንቀኝ አስፈሪ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል፤ አሁንም አለ።

ከፊደል ጋር ያወኩት ድርቅና ረሃብ ቀጥሎ የመጣው ከአስር ዓመት በኋላ ነበር፤ በ1977 ዓ/ም። ታዲያ ያኔ “ህዝብ ተርቦ እንደዚያ ሲያልቅ፣ በድብቅ ነበር . . .” ተብሎ ባይዘፈነበትም፣ ወታደራዊው ደርግ ኢሰፓን ለመመሰረትና አስረኛ የአብዮት በአሉን ለማክበር ሽር ጉድ ሲል ደብቆት ቆይቶ፣ የሚችለውን ያህል ሰው እምሽክ አድርጎ ከፈጀ በኋላ ነበር ይፋ የወጣው። ታዲያ ይህ የ1977ቱ ድርቅ ያስከተለው ረሃብ እጅግ አስከፊ ነበር። በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የገደለ አስከፊ ረሃብ።

ከዚህም በኋላም ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱን አላቆመም። ምናልባት የተለየው ነገር ወደረሃብነት ተቀይሮ ሰው አለመፍጀቱ፣ ከመኖሪያ ቂዬ አለማፈናቀሉ ነው። ረሃብ ሰው አለመግደሉ፣ ከመኖሪያ ቂዬ አለማፈናቀሉ ቀላል ነገር ነው እያልኩ እንዳልሆነ እንዲስተዋል እፈልጋለሁ። ድርቅ ተከስቶ፣ ድርቁ የምግብ እጥረት አስከትሎ፣ የምግብ እጥረቱ ወደረሃብነት ተቀይሮ ሰው አለመገደሉ፣ ከመኖሪያ ቂዬ አለማባረሩ እጅግ ትልቅ ስኬት ነው። ይህ ላለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው መንግስት ያስገኘው አዲስ የድርቅ ገጽታ ነው፤ ድርቅና ረሃብ የተፋቱበት ገጽታ።

ድርቅን ማስቆም አይቻል ይሆናል። በተለይ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የሚያጠቃውን ኤል ኒኖ በተሰኘ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ድርቅ ማስቀረት የሚቻል አይመስለኝም፣ አሁን ባለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃ።  እርግጥ የዓለምን የአየር ንብረት የሚያዛቡ ሰው ሰራሽ ድርጊቶችን በመከላከል መጠኑንና የሚከሰትበትን ድግግሞሽ መቀነስ ሳይቻል አይቀርም።

ይሁን እንጂ ድርቅንና በሰዎች ላይ የሚያስከተለውን የምግብ እጥረት ተጽእኖ ዘመቻ በማይፈልግ የዘውትር ስራ መከላከል  ይቻላል። ለምሳሌ የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ውስጥ በአስከፊ ድርቅ ተመትታለች። በዚህ ድርቅ ዝናብ ጠፍቷል፤ የሃይቆችና የግድቦች የወሃ መጠን በጉልህ ቀንሷል። ዘመቻ የሚፈልግ የምግብ እጥረት ግን አልተከሰተም። የግዛቷ ህዝብ ውሃ አላጠረውም። የሚዝናናበት የውሃ አካል አላጣም። የሚገርመው የካሊፎርኒያ ግዛት በእነዚህ የድርቅ ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቧል። የካሊፎርኒያ ግዛት ሰዎች ምግብ አጥሯቸው የሚሸሿት ሳትሆን፣ እንጀራ ፍለጋ የሚጠጉባት ነበረች።

ይህ የሆነው በተአምር አይደለም። ወይም ድርቅ የካሊፎርኒያን ህዝብና የግዛቷን መንግስት ስለሚፈራ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የድርቅን ተጽአኖ መቋቋም የሚያስችል ውሃ ላይ ያተኮረ የልማት ስራ በአግባቡ መከናወኑ፣ ኢኮኖሚው ከድርቅ ተጽእኖ ውጭ በሆኑ የምርት ዘርፎች ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ ወዘተ ምክንያት ነው።

ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ድርቅና ኢትዮጵያ ተጣጥተው አያውቁም። አሁን ድርቅ የሚያጠቃቸው ወይም የድርቅ ተጽእኖ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ታውቀዋል። እነዚህ የሚታወቁ የድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎች ላይ ያተኮረ ልዩ የልማት ስራ ማከናወን ያስፈልጋል። በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት (የገጸና ከርሰ ምድር ውሃ፣ ማዕድን፣ . . .)፣ ነባር የስራ ባህል ወይም የእደጥበብ ክህሎት፣ መገኛ ስፍራ (ለገበያና ለጥሬ ሃብት ያለ ቅርበት ወዘተ) በመለየት ይህን አቅም ወደተጨባጭ ሃብትነት የሚለውጥ የልማት ስራ መከናወን አለበት።

እስካሁን ባለው ሁኔታ እንደታዘብኩት የከረሰ ምድር ውሃ የማውጣት፣ ወንዞችን የመጥለፍ፣ ወሃ የማቆርና የማቀብ ስራዎች ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው በድርቅ ወቅት ወይም የድርቅ ወቅት ባለፈ ማግስት ነው። በድርቅ ወቅትና ማግስት ጥሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ይጀመሩና በጅምር ይቀራሉ። ተቆፍረው አገልግሎት መሰጠት በማይችሉበት ደረጃ ስራቸው የተቋረጠ ጥልቅ የወሃ ጉድጓዶችን፣ ተዘርግተው ዳዋ የዋጣቸውን የወንዝ መጥለፊያ ቦዮችን፣ ተቆፈረው አፋቸውን እንደከፈቱ የቀሩ የወሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን ለዚህ አሰረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ ነባሩን ድርቅ መቋቋም የማያስችለውን የኑሮ ዘይቤ መቀየር ወይም በዚህ ነባር የኑሮ ዘይቤ ላይ ያለውን ጥገኝነት ጉልሀ በሆነ ደረጃ መቀነስ ያስፈልጋል። ድርቅ የሚያጠቃቸው የኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ውሃን ማዕከል ያደረገ የልማት ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህ ውሃና የግጦሽ ሳር ፍለጋ የሚንከራተተውን አርብቶ አደር የለማ ውሃ ያለበት ቦታ ረግቶ እንዲኖር ያደርገዋል። አርብቶ አደሩ የሚንከራተተው፣ መንከራተት እጣ ፈንታው ስለሆነ ወይም ስለሚመርጠው ሳይሆን ውሃ ፍለጋ ነው። በመሆኑም ውሃ ካገኘ አንድ ቦታ ይሰፍራል። ይህ አንደ ቦታ መስፈሩ የመጀመሪያው የኑሮ ዘይቤ ለውጥ ነው።

አርብቶ አደሪ አንድ ቦታ ሰፍሮ ረግቶ መኖር መጀመሩ ሌሎች ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ የኑሮ ዘይቤዎችን ማላመድ የሚያስችል እድል ይፈጥራል። ለምሳሌ አርብቶ አደሩ የውሃ ልማት በተከናወነበት አካባቢ የመስኖ ግብርናን እንዲለማመድ ማድረግ ይቻላል። በለማው ወሃ ላይ የአሳ ማሰገርና መሰል ተጓዳኝ ስራዎችን ማለማመድ የሚቻልበት እድልም አለ። ከዚህ በተጨማሪ ከብቶች ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው በማሰገንዘብ፣ ዝቅተኛ የምርታማነት መጠን ያላቸውን እንስሳት በተሻለና ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በአንድ ስፍራ የሚጠበቁ እንስሳ እርባታ ጋር ማስተዋዋቅ ይሚቻልበት እድል አለ። አርብቶ አደሩ ማህበረሰበ አንድ ቦታ ሰፍሮ መኖሩ፣ የትምህርት አገልግሎትን በማስፋፋት ቀጣዩ ትውልድ በተለየ የስራ መስክ ላይ የተሰማራ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

ለድርቅ ተጋላጭ የሆነ አርሶ አደር መኖሪያ አካባቢም ተመሳሳይ የኑሮ ዘይቤ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ስራዎችን መስራት የግድ አስፈላጊ ነው። ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ የሰብል እርሻ ለድርቅ ተጽእኖ ያለን ተጋላጭነት ይጨምራል። በመሆኑም ከዝናብ ጥገኝነት የመላቀቅ ጉዳይ፣ ለዘለቄታው ከድርቅ ተጽእኖ፣ በዘመቻ ጋጋታ ከሚሰጥ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የመላቀቅ ያለመላቀቅ ጥያቄ ነው። የመስኖ ግብርናን በተለይ ገበያ ተኮር የመስኖ እርሻን ማስተዋዋቅ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። ሌሎች በአካባቢው የተፈጥሮ ስጦታዎችን መሰረት ያደረጉ ስራዎች ላይ ቢያንስ ገሚሱ ማህበረሰብ እንዲሰማራ ማድረግም እንዲሁ የድርቅን ተዕእኖ መከላከያ መንገድ ነው።

የድርቅን ተጽእኖ ለመቋቋም አርሶ አደሩ ወይም አርብቶ አደሩ የግድ በቀጥታ ለምግብ ፍጆታው የሚያውለውን ምርት ማምረት የለበትም። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸውም ጊዜያት አጠቃላይ የሃገሪቱ የሰብል ምርት እድገት እያሳየ ነው። በመሆኑም ሁሉም አርሶ አደር በቀጥታ ለፍጆታ የሚያውለውን ምግቡን ሳይሆን እነደአካባቢው ሁኔታ ገቢ የሚያስገኝ ስራ ላይ ቢሰማራ የምግብ ዋስትናውን ማረጋጋጥ ይቻላል።

እንግዲህ ባለፉ አመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱት ድርቆች ረሃብ አላስከተሉም። ረሃብ ያላስከተሉት ግን አርሶ አደሩ በራሱ አቅም ራሱን መግቦ ሳይሆን፣ በመንግስትና በለጋሾች በወቅቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲያገኝ በመደረጉ ነው። ይህ በአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የድርቅን ተጽእኖ የመከላከል አካሄድም ሊቀየር ይገባል። አርሶ አደሩ በማንኛውም የአየር ንብረት ሁኔታ በምግብ ራሱን እንዲችል የሚያደርገው ገቢ የሚያገኝበት የአሰራር ዘይቤና የስራ አይነት ላይ እንዲሰማራ መደረግ ይኖርበታል። የድርቅን ተጽእኖ በአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለመከላከል የሚመደበውን በጀት፣ በሰላሙ ጊዜ ለዘለቄታ ድርቅን መቋቋሚያ የልማት ስራ መመደብ አይቻል ይሆን? ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል መንግስት 16 ቢሊየን ብር መድቦ የነበረ መሆኑን ልብ ይሏል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy