Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ገፅታ ግንባታና ኢንቨስትመንት

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ገፅታ ግንባታና ኢንቨስትመንት

                                                ዘአማን በላይ

የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ውጤታማ ሆኗል። ይህ ውጤት የተገኘው መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን የሀገሪቱን ገፅታ ለመገንባት ባደረገው ጥረት መሆኑ አይካድም። የገፅታ ግንባታ ስራ የአንድ ጊዜ ተግባር አይደለም። ተከታታይና የረጅም ጊዜ ስራን ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ማግኘት የቻለችው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለረጅም ዓመታት በመከናወኑ ነው።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሀገራችን ውስጥ የስራ ዕድል ይፈጥራል። የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንም ይጎለብታል። ይህ ግኝታችን የሀገር ኢኮኖሚን በማጎልበት ኢትዮጵያ ላለመችው መካከለኛ ደረጃ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያስችላታል። ታዲያ እዚህ ላይ ለኢንቨስትመንት መዳበር ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተውን ፖሊሲ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ህጎችና ደንቦች በአሁኑ ወቅት ተወግደዋል፡፡ በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ በመለወጥ መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በየጊዜው ከታዩ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ጥንካሬዎቹን የማጎልበት ድክመቶቹን የማረም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩም መምጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ የሚፈለገው ዓይነት ፈጣን ዕድገት ደግሞ ልቅ በሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ብቻ ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ካለፈው ትምህርት መውሰዱ ተገቢ ይሆናል።

ልቅ የሆነ የገበያ ሥርዓት ዘላቂና ሰፊ መሰረት ያለው ዕድገት የማምጣት አቅም እንደሌለው እና ይልቁንም የህዝብንና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰማሩ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም በሂደት መንግሥት የማይተካ ልማታዊ ሚና የሚጫወትበት የነፃ ገበያ ሥርዓት መከተል እንደሚገባ ታምኖበት በመስራት ላይ ይገኛል።

መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች በመከተል ላይ ይገኛል። መንግሥት የገበያ ጉድለቶችንና ተያያዥ የኪራይ ምንጮችን ለመዝጋት በመሰረተ ልማት እና በሰው ሃብት ልማት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ርግጥ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ከዕድገት ደረጃችን ጋር ተያይዞ ከሚኖረው የገበያ ጉድለት እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ ሊከሰትና ፈጣን ዕድገቱን ሊያስተጓጉል የሚችለው አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። አደጋውን ለማስቀረት አስቀድሞ የተለየና መፍትሔም የተቀመጠለት ጉዳይ ሆኗል።

የመሬትና የባንክ አስተዳደር ሥርዓቶቹ እንደታቀደው ልማትን በሚያፋጥንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተሟላ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው መንግሥት በፅኑ ያምናል። ማመን ብቻም ሳይሆን፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱም ፍትሃዊ ውድድርን የሚያሰፍንና ህጋዊ ያልሆነ ጥቅምን የሚዘጋ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ማከናወኑንም ቀጥሏል። የመንግሥት ተሳትፎ የባለ ሃብቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል።

የመንግሥት ደጋፊ ተቋማት አቅም ለማሳደግ የፋብሪካዎች የቴክኖሎጂና የማኔጅመንት አቅም ካደገ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከባለሃብቱ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውና ለመፍትሔውም በጋራ መሰለፋቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው እሙን ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት የተፋጠነ ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች፣ በተለይም በግብርና ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ መር አቅጣጫን በቀዳሚነት የገቢ ምርት መተካት ላይ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል። በማዕድንና ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፕሮግራም ላይ የሚፈሰው ገንዘብ በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር አድጓል። ለዚህ ሥራ ይመች ዘንድ በመሰረተ ልማት ዘርፍ የሀገሪቱን የመንገድ አውታር ለማሳደግና ለማሻሻል የሚደረገው ጥረትም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።

እነዚህን የኢንቨስትመንት ጥረቶች በማሳያነት አነሳኋቸው እንጂ፤ መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማሻሻልና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብርቱ ጥረት አድርጓል። ታዲያ ይህ ጥረቱ ዝም ብሎ አልቀረም። ፍሬ አፍርቷል። ዛሬ ሀገራት ሁሉ ዓይናቸውን ወደ ሀገራችን ኢንቨስትመንት እንዲያሳርፉ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያችን የኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል እየሆነች ነው። ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን ይህ የስበት ሁኔታ እንዲቀጥል ሁሉም ዜጋ ስለ ሀገሩ ትክክለኛ ሁኔታ በመናገር ገፅታችንን መገንባት ይኖርበታል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy