Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግብርና፣ የትራንስፎርሜሽኑ ሞተር

0 459

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግብርና፣ የትራንስፎርሜሽኑ ሞተር

ኢብሳ ነመራ

የዘንድሮ በልግ ዘግይቶ ከምግባቱ ውጭ የዝናብ ስርጭቱ ከሞላ ጎደል መልካም እንደነበረ የሚቲዮሮሎጂ መረጃ ያመለክታል። ድርቅ ያጠቃቸው ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎችም ዝናብ አግኝተዋል። በድርቁ ምክንያት በርካታ ከብቶች ያለቁ ቢሆንም፣ የተረፉት ከብቶች እያገገሙ መሆናቸውን አርብቶ አደሮች እየተናገሩ ነው። ለሰው የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ግን መቀጠል ይኖርበታል። አርብቶ አደሩ የዝርያ ከብቶችን ስላስቀረ ይህን እንደእርሾ ተጠቅሞ ማንሰራራት ይችላል። መንግስት በተለይ የቦረና ልዩ ዝርያ ከብቶች እንዳይጠፉ  9 መቶ ሺህ ገደማ ከብቶች በማቆያ አስቀምጧል። ያም ሆነ ይህ ድርቅ ያጠቃውን አርብቶ አደር ወደቀድሞ የኑሮ ሁኔታው እንዲመለስ የመልሶ ማቋቋም ስራ መከናወን ይኖርበታል።

አሁን የሰኔን ወር ልንያያዝ ነው። በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ክረምት የሚጀምረው በሰኔ ወር ነው። እርግጥ ሰኔ በተወሰኑ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች አጨዳና ውቂያ የሚካሄድበት ወር ነው።

በዘንድሮ ክረምት ከመደበኛ ጋር የተስተካከለ ዝናብ እንደሚገኝ ብሄራዊ የሚትዮሮሎጂ አገልግሎት ኤጀንሲ ትንበያ ያመለክታል። በትንበያው መሰረት በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢ መደበኛ ዝናብ ያገኛል። በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር ይችላል። መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የሃገሪቱ ምእራብ አካባቢዎች ናቸው። የሃገሪቱ ሰሜናዊና ደቡባዊ እንዲሁም ምስራቃዊ አካባቢዎችም መደበኛ የክረምት ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በታች ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የሚቲዮሮሎጂ ትንበያው ያመለክታል። እስካሁን የአየር ንብረት መዛባት ሊከሰት ይችላል የሚያስብል ሁኔታ እንደሌለ ያመለከተው ብሄራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ፣ ይሁን እንጂ ክረምቱ መውጫ ላይ የኤልኒኖ ክስተት ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁሟል። በዚህም ክረምቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ቀድሞ ሊወጣ የሚችልበት እድል መኖሩን ኤጀነሲው ጠቁሟል።

ክረምት ከ80 በመቶ በላይ የሃገሪቱ የእርሻ ምርት የሚመረትበት ወቅት በመሆኑ የክረምቱ የአየር ንብረት የተስተካከለ አለመሆን የሃገሪቱ የምግብ ምርት ላይ የጎላ ተጽእኖ ያሳድራል። የዘንድሮው ክረምት ግን የሚያሰጋ አይደለም። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በዘንድሮው ክረምት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶች – ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን አስታውቋል። የማዳበሪያ ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱንም ነው ያስታወቀው። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ዘንድሮ የተሟላ ግብአት ቢያቀርብም፣ በአጠቃለይ የሃገሪቱን የግብርናው ዘርፍ በፍጥነት ከማሳደግ አኳያ ሲመዘን ግን የምርጥ ዘር፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ችግሮች ማነቆ መሆናቸውንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ከ90 በመቶ በላይ በአነስተኛ ማሳ፣ በቤተሰብ ጉልበት፣ ኋላ ቀር በሆነ የእርሻ ቴክኖሎጂ እየታገዘ የሚከናወን ነው። እርግጥ ይህንኑ የእርሻ ስራ ቴክኖሎጂ በአግባቡ ከዘመናዊ ጋር በመከለስ ምርታማነትን የማሻሻል ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል። መሬትን ደጋግሞ አለስልሶ የማረስ፣ በመስመር የመዝራት፣ አሲዳማ መሬቶችን በኖራ የማከም፣ ውሃ የሚተኛበትን ኮቲቻማ መሬት በማጠነፈፍ ለምርት ስራ የማዋል ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው። በቂ የግብአት አቅርቦት መዘጋጀቱን ያስታወቀው የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር፣ አርሶ አደሩ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ መሬቱን በአግባቡ አለስልሶ እንዲያርስ አሳስቧል። ከመደበኛ በታች ዝናብ ሊያገኙ የሚችሉና ክረምቱ ቀድሞ የሚወጣባቸው አንዳንድ አካባቢዎች አርሶ አደሩ የውሃ እቅባ ስራ እንዲያከናውንም አሳስቧል።

የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የዘንድሮን ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የግብአቶች አቅርቦትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መነሻ በማደረግ በ2010 ዓ/ም መኸር 345 ሚሊየን ኩንታል እህል ሊመረት ይችላል የሚል ቅድመ ትንበያ አስቀምጧል። ይህ በዘንድሮ መኸር ከተገኘው የ293 ሚሊየን ኩንታል ምርት ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ያህል ብልጫ ይኖረዋል። ግብርና በሃገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ 40 በመቶ ድርሻ አለው። ይህ ሰፊ ድርሻ ነው። በመሆኑም የመጪው መኸር የግብርና ምርት እንደታሰበው 17 በመቶ እድገት ካስመዘገበ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ ከአስር በመቶ በላይ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።

እርግጥ ይህ የ345 ሚሊየን ኩንታል የመጪው መኸር ትንበያ የተጋነነ ይመስላል።  ይሁን እንጂ ከባለፈው ዓመት ቅድመ ትንበያ ጋር ሲወዳደር ሊሳካ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። የባለፈው ዓመት መኸር የማሳ ላይ ትንበያ 320 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ የሚያመለክት ነበር። እርግጥ ይህ ቅድመ ምርት ትንበያ አልተሳካም፤ ቀደም  ሲል እንደተጠቀሰው ባለፈው መኸር የተገኘው ምርት 293 ሚሊየን ኩንታል ነው። የማሳ ላይ ትንበያው በዚህ መጠን የቀነሰው፣ በተለይ በታህሳስ ወር ተከስቶ በነበረው ውርጭ ምክንያት ነው። በማሳ ላይ የነበረውን ለአጨዳ የደረሰ ሰብል ያጠፋው ውርጭ የምግብ ተረጂዎች ቁጥር እንዲጨምር እስከማድረግ የደረሰ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ ነበር። እናም የአየር ንብረት ሁኔታው የተስተካከለ ከሆነ የታቀደው በ2010 መኸር ይመረታል ተብሎ የታሰበው የ345 ሚሊየን ኩንታል  የሰብል ምርት ሊገኝ ይችላል።

የግብርናው ዘርፍ ከ1993 ዓ/ም ጀምሮ ያስመዘገበው እድገትም የመጪው መኸር ቅድመ ትንበያ ሊሳካ እንደሚችል ያመለክታል። ከ1993 እስከ 2002 ዓ/ም ተግባራዊ በተደረጉ ሁለት የዓምስት ዓመት ገጠርና ግብርና ላይ ያተኮሩ የልማት እቅዶች ትግበራ ግብርናው በአማካይ የ9 በመቶ እድገት አሳይቷል። በዚህም በ1993 ዓ/ም 60 ሚሊየን ኩንታል ገደማ የነበረውን የሃገሪቱን የሰብል ምርት 2002 ዓ/ም ላይ 191 ሚሊየን ኩንታል ማድረስ ተችሏል።

ከ2003 እስከ 2007 ዓ/ም ተግባራዊ በተደረገው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አምስት ዓመታት አጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ 10 ነጥብ 1 አማካይ እድገት ማስመዝገብ ሲችል፣  የግብርናው ዘርፍ የ6 ነጥብ 6 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። የግብርናው ዘርፍ እድገት 20 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ካስመዘገበው የኢንደስትሪና 10 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ካስመዘገበው የአገልግሎት ዘርፍ ጋር ሲነጻጻር አነስተኛ ቢመስልም፣ ግብርናው በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ካለው 40 በመቶ ገደማ ድርሻ አኳያ ሲታይ ለአጠቃላይ እድገቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።    

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያው ዓመት፣ ማለትም በ2008 ዓ/ም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ዘመን 6 ነጥብ 6 በመቶ አማካይ እድገት አስመዝግቦ የነበረው ግብርና በ2 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ነበር ያደገው። የዚህ ምክንያት በ2007 ያጋጠመው የኤልኒኖ የአየር ንብረት መዛባት ክስተት ያስከተለው ድርቅ ነበር። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ግብርናው በአጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ከ1993 እስከ 2007 ተግባራዊ በተደረጉ ሶስት ተከታታይ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ልማት እቅዶች ሲመዘገብ የቆየው ባለሁለተ አሃዝ አጠቃላይ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ወደአንድ አሃዝ ዝቅ ብሎ  8 በመቶ እንዲሆን አድርጓል።

በእድገትና ተራንስፎረሜሽን እቅድ ትግበራ የኢኮኖሚ መሪነቱን ከግብርና ወደኢንደስትሪ ለማሸጋጋር የታቀደ ቢሆንም፣ የግብርናውም ዘርፍ ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብ የማድረጉም ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል። የግብርናው ዘርፍ ከ80 በመቶ በላይ የሃገሪቱ የሰው ሃይል የተሰማራበት በመሆኑ የዘርፉ እድገት የህዘቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው። ከዚህ ባሻገር የግብርናን ምርታማነት በማሻሻል የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ በሃገሪቱ ትልቅ የገበያ አቅም ይፈጥራል። ይህ ትልቅ የገበያ አቅም የኢንደስትሪውና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ትርፋማነታቸው እንዲያድግ ያደርጋል። ይህ ገቢው ካደገ ሰፊ አርሶ አደር በትርፍ መልክ ወደኢንደስትሪና የአገልግሎት ዘርፉ የሚተላለፍ ሃብት፣ በባለሃብቶቹ ዘንድ የኢንቨስትመንት አቅም ይፈጥራል። ይህ የኢንቨስትመንት አቅም ነው የኢንደስትሪውና የአገልግሎት ዘርፉን በማሳደግ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ማደረግ የሚያስችለው። በመሆኑም ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት አሁንም የግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ግብርናው የትራንስፎርሜሽኑ ስኬት ሞተር መሆኑ በአርሶ አደሩም በየደረጃው በሚገኙ አስፈጻሚዎችም ሊታወስ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy