Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥልቅ ተሃድሶውና ለውጦቹ

0 255

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥልቅ ተሃድሶውና ለውጦቹ

                                                          ታዬ ከበደ

ሀገራችን በጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ውስጥ ናት። በዚህ ሂደት በርካታ ጉዳዩችን አልፋለች። የወጣቶች ተጠቃሚነትን በማረጋገጥና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን በመፍታት ተገቢውን ርቀት ተጉዛለች። ይህም ጥልቅ ተሃድሶው በጥልቀት የሀገራችንን ችግሮች ፈትሾ የመጀመሪያ ደረጃ ዘላቂ ለውጦች ማምጣቱን የሚያሳይ ነው።

በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት መንግስትና ገዥው ፓርቲ ከህዝባቸው ጋር በመሆን በጥልቅ ለመታደስ የገቡትን ቃል በየደረጃው ዕውን ለማድረግ እያከናወኑ ያሉት ተግባር ነው። እነዚህ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን በሁለንተናዊ የዕድገት ጎዳና የመለወጥ ፍላጎትን አንድም የውጭ ሃይሎች ተላላኪ ሆነው፣ ሁለትም ከራሳቸው የከሰረ ፖለቲካ ተነስተው ለማጥላላትና በጭፍን ጥላቻ ላይ በመመርኮዝ ሐሰትን የሚደርቱ ፅንፈኛ ሃይሎች፤ ጥልቅ ተሃድሶውን ‘ምንም ውጤት አያመጣም፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገር የለውም፣ ህዝቡን ለማደናገር ነው…ምንትስ’ የሚሉ የአሉባልታ ድረታዎችን ያስደምጣሉ—ዕውነታው “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉት ዓይነት ቢሆንም።

እናም እኔም የእነዚህን ፅንፈኛ ሃይሎች የውሸት ድርሰትን ለመዳሰስ በፅሑፌ ርዕስ (ራስጌ) ላይ ‘የጥልቁ ተሃድሶ ጥልቀት—እስከ የት?’ የሚል ጥያቄን አንስቻለሁ። ለጥያቄዬ ምላሽ ይሆንኝ ዘንድም በጥልቅ ተሃድሶው ውይይቶች አማካኝነት የተገኙ ውጤቶችን ለማሳየት እሞክራለሁ። ማንኛውም እዚህ ሀገር ውስጥ የሚኖር ሰው እንደሚያውቀው፤ በሀገራችን ውስጥ የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት በየደረጃው ውይይትና ግምገማ እየተካሄደበት ነው። በሚካሄዱት ውይይቶችም ፐብሊክ ሰርቫንቱም ሆነ ህዝቡ ተሳታፊ ሆነዋል። ተሳትፎው ግልፅ፣ አሳታፊና ዴሞክሲያዊ ነው።

ሃሳቦች በየመድረኩ በነፃነት ተንሸራሽረዋል፤ እየተንሸራሸሩም ነው። ፐብሊክ ሰርቫንቱም ይሁን ህዝቡ የሚሰማቸውንና ለመልካም አስተዳደር እመርታ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዩችን እየለዩ ፊት ለፊት ገልፀዋቸዋል። በዚህም የሀገራችን ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ እየተካሄዱ ባሉት የውይይትና የግምገማ መድረኮች የመንግስትን ባለስልጣኖች ከሃላፊነታቸው አንስቷል። ከዚህ አኳያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ህዝቡ በግምገማው ያካሄደውን ሹም ሽር በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ይህም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመታደስ ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት እያመጣ እንጂ፣ አንዳንድ ፅንፈኞች እንደሚሉት ውጤት አልባ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ጥልቅ ተሃድሶው ዋጋ ያለውና የሀገሪቱን ችግሮች በመግባባት እየፈታ ነው።

እርግጥ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

ለነገሩ የኢፌዴሪ መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች በመጠኑም ቢሆን እየቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ተገኝቷል ማለት አይቻልም። እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ። በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም። በሰጪም ይሁን በተቀባይ መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሆነውም ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ብሎም ልማቱ የፈጠራቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስለኛል።

ፐብሊክ ሰርቪሱ ምንም እንኳን በሀገራችን ውስጥ ለተገኘው ልማት የበኩሉን ድርሻ ቢያበረክትም ከዚህ ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ ውጪ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ስልጣን የህዝብ ማገልገያ ሳይሆን የራስ መገልገያ ሊሆን ችሏል። ይህን አመለካከት ለመለወጥ ደግሞ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የአስፈፃሚነት ስራን የሚከውኑት የፐብሊክ ሰርቪሱ አካላት በአመለካከት ብሎም በአደረጃጀት ለውጦች ውስጥ ማለፍ የግድ ይላቸዋል። የእነርሱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ በማለፋቸውም የተጠያቂነት መንፈስ ተፈጥሯል፤ እየተፈጠረም ነው።

ተግባሩን በአግባቡ ያለመወጣት ዝንባሌ ያለው ማንኛውም የፐብሊክ ሰርቪሱ አባል በህዝቡ ይገመገማል፤ ለፈፀማቸው የተሳሳቱ ስራዎችም ተጠያቂ በመሆንም ከያዘው የኃላፊነት ቦታ ይነሳል፤ በተጨባጭ ማስረጃዎችና መረጃዎች ላይ ተመርኩዞም አስተዳደራዊ ርምጃ ሊወሰድበት ይችላል። ታዲያ ይህ በጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ውስጥ መንግስትና ህዝቡ እያከናወኑት ያለው ተግባር ከተጠያቂነት ጋር የተያያዘ መሆኑን እየታወቀ፤ የሀገራችንን መለወጥና የተጀመረው ሁለንተናዊ ዕድገት እንዳይቀጥል የሚመኙ ፅንፈኛ ኃይሎች ግን በተቃራኒው በማሰብ ተሃድሶውን እንደምን “ተጠያቂነት የሚባል ነገር የለውም” እንዳሉ ለማንም ግልፅ አይደለም።

በሁሉም መድረኮች እየተከናወነ ባለው በዚህ የጥልቅ ተሃድሶ ቁርጠኛ አቋም ዋነኛ ተዋናዩ ህዝብ ነው። ህዝብ የትኛው አካል ትክክል የሆነ ስራ እንደፈፀመ፣ የትኛው ደግሞ ስልጣንን ለራሱ ጥቅም በማዋል በህዝቡ እየተገለገለ ተገቢውን አገልግሎት እንዳልሰጠ ያውቃል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ነገር የለም። የሀገራችን ህዝብ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ የልማትና የፖለቲካ ጉዳዩች ግንባር ቀደም ኃይል እንጂ፤ ነገሮችን በባይተዋርነት የሚመለከት አካል አይደለም። እናም ህዝቡ ሁኔታውን በመገንዘቡ በቀጣይ በጥልቅ የመታደሱን ሂደት ያሳልጠዋል።

ይህ ሁኔታ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ተሳታፊነት ከማሳየት በስተቀር፤ ከማደናገር ጉዳይ ጋር ምን እንደሚያገናኘው የሚያውቁት ውጭ ሆነው የውሸት ድርሳን እየከተቡ የሚያነበንቡት ተላላኪ ፅንፈኞች ይመስሉኛል።

እርግጥ ፅንፈኞቹ እነዘ ሀገር ውስጥ የሚከሰቱ ማናቸውም ጉዳዩች ለምን እንደማይጥሟቸው ግልፅ ነው። ይኸውም ሀገራችን ውስጥ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩች ከተፈፀሙና ሀገራችን የአስተማማኝ ሰላም አብነት ከሆነች የተላላኪነታቸው እንጀራ ገመድ ስለሚበጠስ ነው። ወትሮም የሀገሩንና የህዝቡን ተጠቃሚነት አሳልፎ ለባዕዳን የሰጠ ማንኛውም አካል፤ ከራሱ ጥቅም በስተቀር የሚታየው ነገር ስለማይኖር የጥልቅ ተሃድሶውን ውይይትና ግምገማ ለማጠልሸት መሞከሩ የሚደንቅ ጉዳይ አይመስለኝም—የሚጠበቅ ነውና።

ያም ሆነ ይህ ግን የጥልቅ ተሃድሶው ጥልቀት በቅድሚያ የአስተሳሰብ ልዕልናን ከማረጋገጥ እስከ አደረጃጀት ለውጥ ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። በውይይቶቹና በግምገማዎቹ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ከተቻለ መልካም አስተዳደርን በሂደት ማስፈን ይቻላል። መልካም አስተዳደር በሂደት ከሰፈነ ደግሞ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄደው የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎች ይተገበራሉ። የልማትና የዴሞክራሲ ስልጠቶችም የተጀመረውን ሁለንተናዊ ዕድገት ያሳልጣሉ። ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያቀደችውን ትልም ያሳካሉ። በጥልቀት መታደስ የሂደት ጉዳይ በመሆኑ እስካሁን የተገኙትን ወሳኝ ለውጦች አቅቦ መጓዝ ይገባል። ለውጦቹን በሂደት እያጠናከሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉትን ችግሮች በተቻለ መጠን መቅረፍ ያስፈልጋል። በተገኙት ለውጦች በመበረታታትም በቀጣይ ከህዝቡ ጋር በመሆን አሁንም በጥልቀት መታደስ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy