Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥያቄ ውስጥ የገባው የመሬት ባለቤትነት መብት F

0 1,447

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተሞች የመሬት ሊዝ ሽያጭ ዋጋ ማሻቀቡ እየተገለፀ ነው፡፡ ይህም መሬት በውስን ሰዎች እጅ ውስጥ ገብቶ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ያደርጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪ መሬት የመንግሥት ነው በሚል በገጠርም ሆነ በከተማ ዜጎች ከኖሩበት አካባቢ እየተነሱ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ሳቢያ መሬት የህዝብ ነው የሚለው ሃሳብ ተግባር ላይ አልዋለም በማለት ሃሳባቸውን የሚገልፁ ተበራክተዋል፡፡ በእርግጥ በህግም ሆነ በተግባር በኢትዮጵያ የመሬት ባለቤት የማን ነው?

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር በላቸው ይርሳው እንደሚናገሩት፤ ህገመንግሥትን መሰረት በማድረግ መሬት የህዝብና የመንግሥት ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ በኢትዮጵያ መሬት የመንግሥት ብቻ ነው በማለት የሚሞግቱ አመራሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ይህ ህጉን ካለመረዳት የመጣ ነው፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር ያሉ ተነሺዎችን መሬት የመንግሥት ነው በሚል ሳያሳምኑ፤ መሬቱ በትክክል ለልማት እንደሚውል ሳያስገነዝቡ፤ ሰዎቹ ያላቸውንም መብት ማዕከል ሳያደርጉ፤ በማስገደድ የሚያስነሱበት ሁኔታ አለ፡፡ይህ ትክክል አይደለም፡፡ በህግ እንደተቀመጠው መሬት የመንግሥትና የህዝብ ነው፡፡ በማለት የተፈጠሩትን ክፍተቶች አስታውሰዋል።

በእርግጥ አሁን ላይ መሬት በምሪት የሚገኝበት ዕድል ተመናምኗል፡፡ ይልቁንም መሬትን ሃብት ያላቸው ሰዎች በሊዝ በስፋት በመግዛት ላይ ናቸው፡፡ ሻጩም መንግሥት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የመሬቱ ባለቤት መንግሥት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ይህ የሊዝ ፖሊሲው ያመጣው ክፍተት ነው፡፡ ፖሊሲው የሊዝ ሽያጩ ላይ ገደብ ሊያስቀምጥ ይገባ ነበር፡፡ አንድ ሰው ምን ያህል መሬት ሊገዛ እንደሚችል ማስቀመጥ ሲኖርበት ያ አልሆነም፡፡ ይህም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖርና ልዩነቱ የበለጠ እንዲለጠጥ እያደረገ ይገኛል። በማለት ህጉ መሬት የመንግሥትና የህዝብ ነው ቢልም በተግባር የመንግሥት ብቻ በሚያስመስል መልኩ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የዲፕሎማሲ፣ የግጭት አፈታትና ሌሎች ትምህርቶችን የሚያስተምሩት ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህም በዶክተር በላቸው ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ ጥቂት ሰዎች ነፃ የገበያ ውድድር በሚል አስር እና ሃያ መሬት ሲይዙ ሌሎች አንድ እንኳን የሚያጡበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህ የዜጎች እኩል ተጠቃሚነትን አደጋ ውስጥ የሚጨምር በመሆኑ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሬት በግለሰቦች እጅ ከሆነ መንግሥት መንገድ እንኳ መሥራት የማይችልበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት የመሬት ባለቤት መሆኑ መልካም ነው፡፡ እንደፈለገ የልማት ሥራን ማከናወን ያስችለዋል፡፡ ነገር ግን የእኩል ተጠቃሚነት መዘንጋት የለበትም፡፡ በተጨማሪ መሬት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የህዝብም መሆኑን ማወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

የቀድሞ የኢዴፓ ፓርቲ አመራርና አሁን ከፓርቲ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ መሬት የህዝብ ቢሆንም በመንግሥት መተዳደር እንዳለበት አይካድም፡፡ በህገመንግሥቱ መሬት የህዝብና የመንግሥት ነው በሚል አሻሚ በሆነ መልኩ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ መንግሥት መሬት ያለ አግባብ በማንም እንዳይወረር እንዲያስተዳድር የተሰጠውን ስልጣን አንሻፎ መሬቱን እንደራሱ ንብረት ወስዶት ባልተገባ መልኩ ወደ ባለቤትነት ዘልቋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን መሬት ያለምንም ጥያቄ የህዝብ ብቻ ነው፡፡ በማለት ከሁለቱም ሃሳብ ሰጪዎች የተለየ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

መሬት አላቂ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ ማከፋፈልና አግባብ ላለው የህዝብ አገልግሎት እንዲውል ማድረግ ላይ ክፍተት አለ፡፡ መንግሥት መሬትን እንደፈለገው ለራሱ በጀት መደጎሚያ አድርጎታል፡፡ ቤት የሌለው ሰው ቤት መገንባት ከቻለ መሬት በነፃ የሚያገኝበት ሁኔታ ሊመቻችለት ይገባ ነበር፡፡ ማንኛውም ዜጋ በአገሩ ቤት እንዲኖረው መብት ያለው ቢሆንም መንግሥት ከህዝቡ መብት ይልቅ የራሱን ጥቅም ብቻ በማስጠበቅ ሙሉ ለሙሉ የመሬት ባለቤትነትን መብት ተቆጣጥሮታል የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመሬትና ሌሎች ተዛማጅ ህጎችን የሚያስተምሩት ዶክተር ሙራዱ አብዶ በበኩላቸው፤ መሬት የመንግሥት ሳይሆን የህዝቡ የጋራ ሃብት ነው በማለት፤ ከዶክተር በላቸው እና ከዶክተር የሺጥላ ጋር የመሬት ባለቤት የመንግሥት እና የህዝብ ነው በማለት ያነሱትን ሃሳብ ይቃረናሉ፡፡ መሬት የህዝብ መሆኑን በመግለፅ የአቶ ሙሼን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡

በህገመንግሥቱ የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ የተገለፀው ሃሳብ ግራ ቢያጋባም ሲጠቃለል የመሬት ባለቤትነት የህዝብ የጋራ ሃብት መሆኑን አስቀምጧል ይላሉ፡፡ አንቀፅ 40 ንዑስ አንቀፅ 3 እና 4 ላይ የተፈጥሮ ሃብትም ሆነ የመሬት ባለቤትነት የመንግሥትና የህዝብ ብቻ ነው የሚለው ይታይና መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው የሚለው ሃሳብ ይዘነጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በአንቀፅ 52 እና በአንቀፅ 89 ላይ የቀረቡ ሃሳቦችም ይረሳሉ፡፡ ህገመንግስቱ መንግስት የመሬት ባለቤት ሳይሆን ህዝብን በመወከል የሚያስተዳድር ነው፡፡ ብሎ እንዳስቀመጠው በመግለፅ የመሬት ባለቤትነትን ጉዳይ ያብራራሉ፡፡ከህገመንግሥቱ በኋላ የወጡ አዋጆችና ደንቦች መሬት የህዝብና የመንግሥት ነው በማለት ከህገመንግስቱ የሚጣረስ ሃሳብ ቢይዙም መሬት የህዝብ የጋራ ሃብት ብቻ መሆኑ አከራካሪ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግለሰቦችና ተቋማት በህጋዊ መንገድ መሬት ሲሰጣቸው የመሬት ባለቤት ሳይሆኑ በመሬት የመጠቀም መብት ያገኙ ይሆናሉ፡፡ የመጠቀም መብታቸውን መሸጥና ማከራየት ይችላሉ፡፡ መንግሥትም መሬት የመጠቀም መብትን ለባለሃብቶች መስጠት ይችላል፡፡ ይህ በህገመንግሥቱ ተቀምጧል፤ በማለት የመሬቱ ባለቤት መንግሥት አይደለም፤ ሽያጩም ሆነ ስጦታው ከመሬት ባለቤትነት ጋር የማይያያዝ እና በመሬት ከመጠቀም መብት ጋር ብቻ የሚቆራኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

«ሃብት ያላቸው ሰዎች መሬት የመጠቀም መብትን የመጠቅለል አዝማሚያ አለ፡፡ ይህ መብት በተወሰኑ ግለሰቦች እጅ ውስጥ መውደቁ የሃብት ክፍፍሉን ፍትሃዊ እንዳይሆን ያደርጋል» የሚለውን ሃሳብ ይስማሙበታል። ነገር ግን የችግሩ ምንጭ ህገመንግሥቱ ሳይሆን እየተሄደበት ያለው አቅጣጫ፣ የፍላጎቱ አለመመጣጠንና ሌሎችም ክፍተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሙራዱ፤ አብዮቱ ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ መሬት የህዝብ የጋራ ሃብት ነው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ደግሞ በመሬት የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ ሙሼም ሆኑ ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች በፊት ዜጎች መሬት የሚያገኙበት የተሻለ ዕድል እንደነበር ይስማማሉ፡፡ አሁን ላይ ከመሬት ባለቤትነት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለማቃለል መፍትሄ የሚሉትን ይጠቁማሉ፡፡

ዶክተር በላቸው ውጤታማ የአሰራር ስርዓትን ማስፈን፤ የነገውን መገመት የሚችል ብቃት ያለው ሙያተኛን በአመራርም ሆነ በሠራተኛ ደረጃ ማስቀመጥ፤ ፖሊሲውን በማየት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችል ማሻሻያ ማድረግ መፍትሄ ያመጣል ብለዋል፡፡

ዶክተር የሺጥላም መንግሥት መሬትን በራሱ ዕጅ ሊይዝ ቢችልም ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የጋራ ሃብት በማድረግ መሬት የህዝብም ጭምር መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ መሬት የህዝብና የመንግሥት ነው ቢባልም አፈፃፀሙ ላይ የስትራቴጂ ለውጥ መምጣት ያስፈልጋል በማለት መፍትሄ የሚሉትን ጠቁመዋል፡፡ ሰፊ አቅምና ቦታ ቢኖርም ውስን ከተሞች ላይ መታጨቅ በመኖሩ፤ ስትራቴጂ ይዞ የከተሞችን ቁጥር ማብዛትን እንደአማራጭ መያዝ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሼ በበኩላቸው መንግሥት መሬት የህዝብ መሆኑን ተገንዝቦ መሬትን በመሸጥ ከሚያገኘው ገቢ በላይ የዜጎችን ቤት የማግኘት መብትን ማረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሙራዱ እጅግ ደካማ የሆነውን የከተማ አስተዳደሮችን አቅም ማሳደግ፤ የሰውን እውቀት እና ህጉን ማሻሻል የሚያስፈልግ መሆኑን ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ካልሆነ ግን አደጋው በቀላል የሚታይ ባለመሆኑ ያሉትን አዝማሚያዎች ማስተዋል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር በላቸውም በትክክል መሬትን መጠቀም ከተቻለ ብልፅግና ይኖራል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ የተወሰነው ሰው ብቻ በገንዘብ ሃይል ሰብስቦ የሚይዝበት ሁኔታ በዚሁ ከዘለቀ መሬት ትልቅ የግጭትና የድህነት ምንጭ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው፡፡

ዶክተር የሺጥላም መሬትን ወደ ግል ላለማስተላለፍ የሚቀርበው የመንግሥት ሃሳብ ብዙሃኑ ህዝብ ይደኸይና ከመሬት አቅርቦት ይገለላል የሚል ነበር፡፡ አሁንም ይህኛውአስተሳሰብ ከዘለቀ መሬት በጥቂቶች እጅ ሆኖ ዘመናዊ ፊውዳል ይመጣል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ አክለውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ለውጦች የመጡት ከመሬት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ነውና ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ምህረት ሞገስ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy