Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራሊዝም እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ

0 527

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራሊዝም እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ

                         ሰለሞን ሽፈራው

እንደ ህዝብ የፆታ ወይም የእድሜ ልዩነት ሳይኖር፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ንቅል ብሎ ከየቤቱ እየወጣ የፖለቲካ አቋሙን በሚገልጽ ስሜት ለስርነቀል የሥርዓት ለውጥ የሚታገሉ ተራማጅ ኃይሎችን ሲደግፍ የታዘባችሁበት አጋጣሚ አለን? ይህን ስል ግን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስተዳደራዊ ዘይቤ የምዕት ዓመታት ታሪክ ባስቆጠረ ጥረት ወይም ሂደት አልፎ የፖለቲካ ባህላቸው እጅግ በጣም እንደገና በአስተሳሰብ እኛን አፍሪካውያንን የትየለሌ ጥለውን እንደሔዱ በሚነገርላቸው የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ህብረተሰብ ውስጥ ማለቴ እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቁንስ “የፖለቲካና ኮረንቲን በሩቅ ነው” የተሰኘ አጉል ፈሊጥ በወለደው ፍርሃት የተሸበበ ህብረተሰብ በሚኖርባት የድህረ አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ በትረ ስልጣን የመጨበጥ ጉዳይ የፈጣሪ መልኮታዊ ፀጋ ካልታከለበት ፈጽሞ የማይቻል ተደርጎ ሲቆጠር በቆየባት ሀገራችን አንድ ጥግ ላይ እንደዚህ ዓይነት ህዝብ ገጥሟቸው ያውቃል ወይ?

በዚህ መሠረተ ሃሳብ ከተግባባን በአንድ ወቅት በታሪክ አጋጣሚ ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል አቅንቼ በተለይም የኢትዮጵያ ሶማሌ የተመለከትኩትንና ባስታወስኩት ቁጥር የሚያስገርመኝን ትዕይንት ዛሬ በትዝታ ላወጋችሁ ፈልጌ ነው ፡፡  ከዛሬ 26 ዓመት በፊት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአፈና አገዛዝ ቁም ስቅል ያሳያቸው የነበረው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት መንኮታኮቱን ተከትሎ፣ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ለተንቀሳቀሰው የኢህአዴግ ሰራዊት፣ በተለይም የሶማሌ ክልል ህዝብ፣ ያደረገለትን ልዩ ድምቀት የተላበሰ የጀግና አቀባበል፣ በጥሞና ወደ ታዘብኩበት ታሪካዊ አጋጣሚ አልፋለሁ፡፡

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ህዝቦች የተገኘው ታሪካዊ ድል የደርግ አምባገነናዊ ስርዓት ግብዓተ – መሬቱ እንደተፈጸመ ካረጋገጠልን በኋላ ሳይውል ሳያድር ሀገርን ወደ ማረጋጋት ስራ የተሰማራው የኢህአዴግ ሰራዊት፣ በተለይም ወደ ምስራቅና ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ያደረገው እንቅስቃሴ ማውሳት ይቻላል፡፡ ይህ  ትውስታም  ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች በወቅቱ ያሳዩንን ፍቅር ነው፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1983 ዓ.ም ማለዳ ላይ፣ ከአፋር ሚሌ አካባቢ ተነስቶ ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተነቃነቀው የኢህአዴግ ሰራዊት፤ የማዘዣ ጣቢያውን ሐረር ከተማ ውስጥ አድርጎ፤ ከአዋሽ ወንዝ እስከ ኦጋዴን ጠረፋማ አካባቢዎች ያለውን ሰፊ መሬት ይቆጣጠር በነበረው የምስራቅ እዝ ስር የሚመደቡ የደርግ ወታደሮች፤ አጉል ለመላላጥ ያህል የሚያደርጉትን ማንገራገር ሁሉ፤ ብዙም ደም ባላፈሰሰ መልኩ እየፈታ ጉዞውን ቀጥሎ ጅግጅጋ የገባው ግንቦት 25 ቀን ረፋዱ ላይ ነበር፡፡ እናም የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች፤ በአጀብ ተሰልፈው፤ ከፍጹም የደስታ ስሜት በመነጨ እልልታቸውን እያቀለጡ  አቀባበል አደረጉ፡፡

የዛሬዋ የኢትዮጵያ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው ጂግጂጋ ውስጥ ለጥቂት ቀናት ቆይተን፤ ጉዟችንን ወደፊት ስንቀጥል፤ በቁጥር የሚበዛው የክልሉ አርብቶ አደር ህዝብ በሚኖርባቸው የኦጋዴን ዞኖች፤ የጠበቀን እውነታም ተመሳሳይ ድባብ እንደነበረው ትዝ ይለኛል፡፡ በተለይም የደጋ ሐቡርና የቀብሪድሃር ከተሞች ነዋሪ ህዝብ፤ በወቅቱ ለሰራዊታችን ያደረጉለት የጀግና አቀባበል ከሁሉም በላይ ደማቅ ከመሆኑ የተነሳ፤ አብዛኛውን ታጋይ ያስፈነደቀ የደስታ ስሜት ፈጥሮብን ነበረ ፡፡

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ያኔ በሀገራችን ውስጥ ከተካሄደው ስር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ምን ያህል ተጠቃሚ ሆኗል? ማግኘት ያለበትን ሕገ – መንግስታዊ መብቶች ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የተደረገው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት በተጨባጭ ሲመረመርስ እውን ሚዛን ይደፋል ወይ? ህዝቡ የራሱን ክልልዊ መንግስት ከመሰረተ ጀምሮ መስተዳደሩን ሲፈታተኑት የተስተዋሉ ልዩ ልዩ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ ግን ደግሞ በርካታ መልካም ተግባራት እንደተከናወኑ የሚካድ ጉዳይ አይደለም ባይ ነኝ ፡፡ እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልል ካስመዘገባቸው መሰረታዊ ለውጦች ይበልጥ ጎልተው የሚታዩት የትኞቹ ናቸው? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የራሴን ግለሰባዊ ምልከታ መነሻ አድርጌ ጥቂት ነጥቦችን ለማከል እሞክራለሁ፡፡

በዚህ  መሰረት እውነታውን ከሞላ ጎደል ስገመግመው በእርግጠኝነት ምስክርነቴን እንድሰጥ የሚያስገድደኝ ጉዳይ ሆኖ የሚታየኝ ድል ብዙ ነው፡፡ በተለይም ከደርግ ውድቀት ማግስት የብሔራዊ መብት ጥያቄ ዛሬ ላይ ተረት ወደ መሆን ስለመቃረቡ ፈጽሞ ማስተባበል እንደማይቻል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ አሁን የሚመራበትን ክልላዊ የመንግስት አወቃቀር በቅርበት ለመታዘብ የቻለ ማንኛውም ሰው ሊገነዘብ የሚችለው ጥሬ ሃቅ ቢኖር ነው፤ ያ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት ለሶማሌ ወጣት ፈጽሞ የማይቻል ጉዳይ መስሎ ይታየው የነበረውን የወታደራዊ ማዕረግ ጉዳይ ብንወስድ አሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፤ እስከ ከፍተኛው የመኮንንነት ደረጃ ትከሻቸው ላይ ጭነውት፤ ሲወጡ ሲወርዱ ማየት የተለመደ የዕለት ተዕለት ትዕይንት ሆኗል፡፡ በሌሎቹ የክልል መስተዳደሮች ከምናውቀው የፖሊስ ኃይል አደረጃጀት በተጨማሪ፤ የክልሉን ነባራዊ እውነታዎች፤ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ፤ አሰልጥኖ ያስታጠቃቸውና የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ተክተው የሚሰሩ፤ የአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ልጆች “ልዩ ፖሊሲ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው፤ እንደሚንቀሳቀሱም ጭምር አውቃለሁ፡፡ ከዚህ ባሻገር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መዋቅር ውስጥ የሶማሌ ብሔራዊ ክልል ህዝብ በሀገሩ ሁለንተናዊ ጉዳይ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ያስቻለውን እድል ስለማስገኘቱ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

ለዚህ ደግሞ እስከ ሚኒስቴርነትና ሚኒስቴር ዴኤታነት በሚደርስ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ተመድበው ለኢትዮጵያ የሕዳሴ ጉዞ መሳካት የድርሻቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በመወጣት ላይ የሚገኙትን የክልሉ ተወላጆች ማየት በቂ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልል ህዝብ ግንቦት1983 ዓ.ም ለኢህአዴግ ሰራዊት ያደረገው እጅግ ደማቅ አቀባበል ያለ ምክንያት እንዳልነበረ የሚያረጋግጥ እውነታ መኖሩን መረዳት አያዳግትም፡፡ ክልሉ አሁን የደረሰበትን ተጨባጭ እውነታ ስንመለከትም የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ፤ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ተፈጥሮአዊ ሃብቱን ጥቅም ላይ አውሎ የፍትሐዊ ልማት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥበት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረለት መገንዘብ ይቻላል፡፡

እንዲሁም ደግሞ ኢትዮጵያ ሶማሌዎች ሀገራችን ለተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ መሳካት መጫወት የሚጠበቅባቸውን ታሪካዊ ሚና እንዳይጫወቱ የሚያግዳቸው ምንም ምክንያት እንደማይኖር ጭምር እያረጋገጡልን ስለመሆናቸው ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለዚህም እንደ እኔ ፌዴራሊዝማችን ህዝቦችን ለጋራ ልማት የሚያሰልፍ እንጂ፤ ሀገሪቷን ለብተና አደጋ ያጋለጠ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ ግን ኢትዮጵያ ሶማሌዎች ወዳጆቼን እንኳን ለ26ኛው የግንቦት 20 ድል በዓል አደረሳችሁ እያልኩኝ እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy