Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍርድ ቤቱ በአቶ ስማቸው ከበደ ላይ የስድስት አመት ጽኑ እስራት ቅጣት አስተላለፈ

0 910

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው ባለሀብቱ አቶ ስማቸው ከበደ ላይ የስድስት አመት ጽኑ እስራት ቅጣት አስተላለፈ።

ችሎቱ በግለሰቡ ቅጣቱን የጣለው ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም የፍሬ ግብርና ተጨማሪ እሴት ታክስ ከ15 ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ በወቅቱ አሳውቀው ባለመክፈላቸው የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የመሰረተባቸውን ሁለት ክሶች ተከትሎ ነው።

ችሎቱ ቀደም ሲል በነዚህ ሁለት ክሶች ላይ ያስተላለፈባቸውን ፍርድ ተከትሎ አቶ ስማቸው ከበደን በስድስት አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ይህ ንግድ የሚንቀሳቀስበት ድርጅታቸው ዲ ኤች ሴሜክስ ላይ የአንድ መቶ ሺህ ብር ቅጣት ጥሏል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት በግለሰቡ ላይ የ16 አመት የቅጣት መነሻ ቢይዝም አቶ ስማቸው ያቀረቧቸው አምስት የቅጣት ማቅለያዎች ውሳኔው ስድስት አመት እንዲሆን አድርጎታል።

ችሎቱ በግለሰቡ ላይ ያስተላለፈው ቅጣት እጃቸው ከተያዘበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ እንዲሆንም ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ በሶስት መዝገቦች እየታዩ ካሉ ክሶች፣ ችሎቱ  141354 እየተባለ በሚጠራው የክስ መዝገብ ላይ የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮችን እስከሚቀጥለው ሁለት ሳምንት ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።

141352 እና 56 እየተባሉ የሚጠሩ ሁለት የክስ መዝገቦችን ከአዲሱ የበጀት አመት ጀምሮ መከታተል እንደሚጀምር ከፍርድ ቤቱ መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

ሪፖርተር:-ጥላሁን ካሳ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy