Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፓርቲዎቹ የመደራደሪያ አጀንዳዎቻቸውን የማጽደቅ ተግባር አጠናቀቁ

0 337

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገርአቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደሪያነት ያዘጋጇቸውን አጀንዳዎች የማጽደቅ ተግባር አጠናቀቁ፡፡

የዛሬው ውይይት ቀደም ባሉት ውይይቶች ኢህአዴግ ያልተቀበላቸውን አጀንዳዎች እንዲቀበል ለማሳመን ታቅዶ የተካሄደም ነው፡፡

ኢህአዴግ በአጠቃላይ ለመደራደሪያነት ከተዘጋጁት 13 አጀንዳዎች መካከል “የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ስለመኖራቸው፣ የመሬት ስሪት፣ ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ኃይሎች በድርድሩ  ተሳታፊነት ሁኔታ፣ ሕገ መንግስት ማሻሻልና የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የድንበር ወሰኖችን” ከሚመለከቱት  ውጪ ያሉትን አጀንዳዎች  ለድርድር  እንዲቀርቡ ተስማምቷል፡፡

በተጨማሪም ለመደራደሪያነት ከተቀበለውና በልዩ ልዩ ህጎችና አዋጆች ውስጥ ከተዘረዘሩ ንዑስ አጀንዳዎች መካከል ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደማይደራደር ገልጿል፡፡

የፓለቲካ እስረኞች ስለመኖራቸው እና  የፌዴራሊዝም አወቃቀርን የሚመለከቱ ሃሳቦች ሰፋ ባለ ሁኔታ  ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በውይይቱ ወቅት፤ በአገሪቷ ውስጥ የፖለቲካ የህሊና እስረኞች እንዳሉና መፈታት እንደሚገባቸው በመግለጽ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ኢህአዴግ በበኩሉ፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአገሪቷ ውስጥ እንደሌሉ ጠቁሞ፤ ነገር ግን ወንጀል ሳይሰሩ የታሰሩ ማናቸውም ዜጎች ካሉ በተዘረጋው ህጋዊ የአሰራር ሥርዓት መሰረት መጠየቅ እንደሚቻል ገልጿል፡፡

የፌዴራሊዝም አወቃቀርን በሚመለከት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገሪቷ የምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት የግጭት ምክንያት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ኢህአዴግ በበኩሉ እንደገለጸው፤ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ተራማጅና ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳደሩ እድል የሰጠ ነው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ተነሱ የተባሉ ግጭቶችም ቢሆኑ በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁሞ፤ በተለይ አገሪቷ በአሃዳዊ ስርዓት ወቅት የከፋ ግጭት ውስጥ  እንደነበረች አስታውሷል።

በፓርቲዎቹ ተጠቃለው የጸደቁ አጀንዳዎች ለድርድር በሚመች መልኩ በቅደም ተከተል ተደራጅተው ለሁሉም ፓርቲዎች እንዲደርሱ ለድርድር መሪዎች ኃላፊነት ሰጥተዋል።

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ድርድሩ ምን መምሰል እንዳለበት እና የድርድሩ አጀንዳዎችን ለመለየት ከጥር 5 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከአስር ጊዜ በላይ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ በሚኖራቸው ግንኙነት ቀጥታ ወደ ድርድር ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy