Artcles

ሁነቶችን ታሳቢ ተደርገው የተፈጠሩ የገበያ ትስስሮች በመደበኛነት ቢቀጥሉስ?

By Admin

June 05, 2017

ሁነቶችን ታሳቢ ተደርገው የተፈጠሩ የገበያ ትስስሮች በመደበኛነት ቢቀጥሉስ?

አባ መላኩ

የሚሰራ እጅና  እግር ይዘን፣   የሚያስብ  ጭንቅላት  ይዘን፣  በቀላሉ  ሊለማ  የሚችል መሬት  ይዘን  ስንዴ  እየለመንን  መኖር  የለብንም  በማለት ነበር   በአንድ   ወቅት   ታላቁ መሪ አቶ   መለስ   ዜናዊ   ለህዝባቸው በመስቀል አደባባይ  መልዕክታቸውን  ያስተላለፉት። የመጀመሪያውና ትልቁ ጠላታችን ድህነት መሆኑን እኛ ኢትዮጵያዊያን ከስምምነት ልንደርስ ይገባል። አዎ  በሁላችንም  ወስጥ ድህነት የፈጠረብን መልካም ያልሆኑ ነገሮች ቁጭት ሊፈጥሩብን ይገባል።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በበርካቶች  ዘንድ  ድህነት የጋራ ጠላታችን መሆኑን ከስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ይመስለኛል። ድህነት የችግሮቻችን ቁንጮ ነው። ድህነትን ማስወገድ  ቢከብደንም  መቀነስ  ከቻልን ግን የአገራችን ችግሮች ሊፈቱ አይችሉም።  ምክንያቱም ጥበትና ትምክህት  በራሳቸው አንዱ የድህነትና የኋላቀርነት መገለጫዎች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንቆች  ናቸው።  ድህነትን ማሸነፍ የሚቻለው ደግሞ አሉባልታን  በማራገብ ሳይሆን በተሰማራንበት መስክ በቅንነትና ታማኝነት በማገልገል ብቻ ነው።

ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግስታት ልዩነትን ማስተናገድ ባለመፍቀዳቸው ህዝቦች የህይወትና የአካል መሰዋዓትነትን  ከፍለዋል። ለዕኩልነትና ነጻነት በተደረገ ትግል በርካቶች ክቡር ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረዋል። የዛሬው ነጻነትና ዕኩልነት  ነጻነት ደም እንደተከፈለበት  አጥንት እንደተከሰከሰበት ስንቶቻችን አስበነው እናውቃለን? ዛሬ ላይ ለነጻነትና እኩልነት ተብሎ የሚከፈል የህይወትም ሆነ የአካል  መሰዋዓትነት የለም። በአገራችን ዛሬ ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ስርዓት መገንባት ተችሏል።

በዴሞክራሲያዊ መንገድ ልዩነትን ማራመድ እየተቻለ አገርን ለማወክ መሯሯጥ የግል ጥቅምን ፍለጋ ካልሆነ በስተቀር  ለህዝብና ለወገን በማሰብ እንዳልሆነ መገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። አሁን ላይ ለአገርና ለወገን አስባለሁ የሚል  ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድ በሙሉ መረባረብ ያለበት ድህነትን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት በተከፈተው ጦርነት ላይ እንጂ  በሃሰት መረጃ  ህዝባችንን  ወደእርስ በርስ ጦርነት የሚያስገቡ  አካሄዶች  መሆን የለበትም።      

መንግስት ድህነትን ለመዋጋት የተለያዩ ፓኬጆችን ቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል። መንግሥት  ለድህነት  ቅነሳና  ለሥራ  ፈጠራ  ልዩ  ትኩረት  በመስጠቱ  በከተማና  በገጠር  በተጨባጭ ልዩነትን  ሊፈጥሩ  የሚችሉ አነስተኛና  ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን  በማልማት ላይ ይገኛል።  በከተሞችም ሆነ በገጠር ዜጎች በጥቃቅንና  አነስተኛ  ተቋማት  ተደራጅተው  ራሳቸውን  እንዲለውጡ  ልዩ ልዩ  ድጋፎችን  አድርጓል። በማድረግም ላይ ነው። በዚህም ተጨባጭ ለውጦች በመመዝገብ ላይ ነው።   

ዜጎች  በጥቃቅንና  አነስተኛ  ዘርፍ  በመደራጀት ራሳቸውን ለድጋፍ አመቺ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ፈረስ ያደርሳል እንጂ … እንደሚባለው ዜጎች በተለይ  ወጣቶች ሁሉን ነገር መንግስት እንዲያደርግላቸው ከመንግስት ብቻ  መጠበቅ የለባቸውም።  መንግስት ወጣቶች  ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርገው   በመጀመሪያ  ወጣቱ  በፍቃደኝነት  ሲደራጅ ነው።  አንዳንድ ግለሰቦች  የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ጥቅም በአግባብ ያለመረዳት ችግር ይስተዋልባቸዋል። ለአብነት አንዳንድ  አካሎች   ሲያነሷቸው  ከነበሩ   ጥያቄዎች መካከል  “ወጣቶች ከተደራጁ  የመንግስት (የኢህአዴግ) መጠቀሚያ ትሆናላችሁ” የሚል መያዣ መጨበጫ የሌለው  ነገር ነው።  

ፖለቲካና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን  የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው።  ማንም የፈለገውን  አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ (ደጋፊም ሆነ ተቋዋሚ) የሚያራምድ ወጣት  በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የመደራጀት መብቱ የተጠበቀ ነው።  እንዚህ ተቋማት  ከፖለቲካ አስተሳሰብ ወይም ጫና ውጭ መሆናቸውን መታወቅ ይኖርበታለ። ማንም በፖለቲካ አስተሳሰቡ የሚያገኘውም ሆነ የሚያጣው ነገር አይኖርም።   

በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ  ለተደራጁ አካላት   ሰሞኑን ለግንቦት ሃያ ህዝባዊ የድል ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ  የሚገኙ  በተለያዩ ክፍለ ከተሞች  አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው ተመልክቻለሁ።    ትናንት  በየመንገዱ ላይ  ተሰብስበው  ወጪ  ወራጁን  ሲተነኩሉ  የነበሩ ወጣቶች  በመሃበር በመደራጀት የተለያዩ ስራዎቻቸውን ይዘው  በባዛሮች ላይ ታድመው ስመለከት ደስታን ፈጥሮብኛል።  

የጥቃቅንና   አነስተኛና፣   የሥራ   ፈጠራ   ተግባራት   ውጤታማ  የሚሆኑት  በፍላጎት   ላይ  የተመሰረቱ ሲሆኑና ተገቢው  የመንግስት ድጋፍ ሲያገኙ ብቻ ነው የሚለውን አስተሳሰብ እውነትነት በዚህ ባዛር ላይ ተምልክቻለሁ። በርካታ ዜጎች በተለይ  ወጣቶችና ሴቶች በባዛሮች ላይ ይዘዋቸው የቀረቡት  የስራ ውጤቶቻቸው እጅግ የሚያኮሩ ነበሩ። እኛ ሸማቾችም በጥራትም ይሁን በዋጋ ተጠቃሚ መሆን ችለናል። ይሁንና እንዲህ ያሉ ባዛሮች  እንደመስቀል ወፍ  ጥፍት ባይሉ መልካም ነው። ምክንያቱም እነዚሀ ባዛሮች ጥቅም  ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ብቻ ሳይሆን  ለሸማቾችም  ጥቅማቸው የላቀ  በመሆኑ  ቀጣይነት ቢኖራቸው ተገቢ ነው።    

የፌዴራልና የክልል መንግስታት  በያዝነው ዓመት ብቻ በርካታ ገንዘብ በመመደብ  ለወጣቶች አዳዲስ የስራ ዕድል ለመፍጠር በመስራት ላይ ነው።   መንግስት ወጣቶችን  ወደ  ሥራ  ለመግባት  የመለለየት፣ የማደራጀት   ፋይናንስ የመመደብ፣ የሙያ ስልጠና የመስጠት፣ የስራ ቦታና የምርት መሸጫ ቦታዎች የማመቻቸት፣ ከሚያገኙት ገቢ ላይ   የቁጠባ  ባህላቸውን  እንዲያዳብሩ   የሚያስችሉ  ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል። ቁጠባ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት እስትንፋስ ነው። ቁጠባን የማያውቅ ተቋም ሊለወጥ አይችልም። በመሆኑም ጀማሪ ስራ ፈጣሪ የሆኑት  በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ  ግለሰቦች  ይቅርና ትላልቅ ኩባንያዎች ውጤታማ የሚሆኑት  ቁጠባን ተግባራዊ ሲያደርጉ ብቻ ነው።

የጥቃቅንና  አነስተኛ  ዘርፍ  ችግር  ከሚባሉት ውስጥ  የገበያ ትስስር በቀዳሚነት የሚነሳ ጉዳይ ነው። የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ መንግስት እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ  መልካም የሚባል ቢሆንም በቀጣይ ከዚህ የበለጠ ሊያጎለብተው ይገባል ባይ ነኝ። እስካሁን እንዳየሁት መንግስት ኢቨንቶችን እየጠበቀም ቢሆን አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ከህብረተሰቡ ጋር እንዲገናኙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይሁንና ኢቨንቶችን ከመጠበቅ ባሻገር  እንዲህ ያሉ ባዛሮችን በየክፍለ ከተማው ብቻ ሳይሆን በየቀበሌው ማደራጀት ብዙ የሚከብድ ጉዳይ አይደለም።  

መንግስት  በቀጣይ ለወጣቶች  የስራ ዕድል እንዲፈጠር ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ሸማቹ ሃይል  ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች  ውጤት ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎችን መስራት ይኖርበታል።  አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን  ምርቶቻቸውን  እንዲያስተዋውቁና  ዕርስ  በርስ  እንዲደጋገፉ  አመቺ  ሁኔታዎችን  መፍጠር ለመንግስት ብቻ የሚተው ስራ መሆን የለበትም። ሁሉም  ትላልቅ  ኩባንያዎች ከአነስተኛና ጥቃቅን ጋር በመቀናጀት መስራት የሚችሉበት ሁኔታ  ማጎልበት ይኖርባቸዋል። መስፍን ኢንጂነሪንግ ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት እየፈጠረ ያለው የገበያ ትስስር መልካም ጅምር  ነው። ሌሎችም ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ይህን አካሄድ መከተል እንደጀመራችሁ ይታወቃል። ይሁንና አጠናክሮ መቀጠል፤ ከዚህ በተሻለ በማጎልበት የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን አቅም በማሳደግ  ድህነትን መቀነስ ይቻላል።