Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተመቻቸ ምህዳር

0 577

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተመቻቸ ምህዳር …

 

አባ መላኩ

በዓለም ባንክ ብያኔ መሠረት መልካም አስተዳደር ማለት ሊተነበይ የሚችልና በነጠረ ፖሊሲ አወጣጥ የተካነ እንዲሁም በሙያው ሥነ-ምግባር የሚታገዝና በሚወስዳቸው ርምጃዎች ተጠያቂ ሊሆን የሚችል መንግሥትና በመንግሥታዊ ጉዳዮችም በንቃት የሚሳተፍ ኅብረተሰብ ያለበት ሆኖ፤ ሁሉም አካላት በህግ የበላይነት አምነው የሚንቀሳቀሱበት ሥርዓት ነው።


እርግጥ በዚህ ትርጓሜ ውስጥ ያሉት አባባሎች ለመልካም አስተዳደር ጠቃሚ መሆናቸው አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ አባባሎቹ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታቸውን ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመት በፊት መስርተው በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚባሉት ምዕራባውያንም እንኳን ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ አድርገዋቸዋል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ከእኛ አገር የ25 ዓመት ታዳጊ ዴሞክራሲ አኳያም፤ ተግባሩ ተቃዋሚዎች “መንግሥት ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳደርን አላሰፈነም” እያሉ እንደሚያስወሩት ሳይሆን የራሱን ሂደት ጠብቆ በጊዜ ዑደት ውስጥ የሚገነባ ሆኖ እናገኘዋለን።


እናም ከመልካም አስተዳደር አኳያ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ፤ ተግባሩ በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር የሚመጣ አለመሆኑን ነው። ምዕራባውያንም ቢሆኑ ዛሬ ለደረሱበት የመልካም አስተዳደር ተግባር ለዚያውም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባላደረጉበት ሁኔታ ረጅም ጊዜ የወሰደባቸው መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጀማሪ የዴሞራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ አራማጅ አገር፤ ተግባሩን “በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ካላመጣች” ብሎ እሪታን ማሰማትና በጭፍን መሞገት ግራ ያጋባል።  

እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት ነው። ስለሆነም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም። ታዲያ ይህን እውነታ በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥትም፤ ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።

 

ስለሆነም በቅንጭብጫቢ የኒዩ ሊበራል እሳቤ ከወዲያ ወዲህ የሚላጉት “ተቃዋሚ” ተብዬዎችም ሰሚ ያገኙ ይመስል “መንግሥት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ተስኖታል” እያሉ ያላዝናሉ።  ተግባሩን በአንዲት ጀንበር ከሰማይ እንሚወርድ መና ቆጥሮ መጠበቅ ቆጥረው ‘የግድ አሁኑኑ መፈፀም አለበት’ ብሎ ማሰብ ከእውቀት አጠርነት በስተቀር ሌላ ሥያሜን አያሰጥም። ይህ የአላዋቂነት ጩኸት ከዚህ አኳያ መታየት አለበት።


መንግሥትና ገዥው ፖርቲ መልካም አስተዳደር ጊዜ ስለሚወስድ ተግባሩን ላለማከናወን በዝምታ አልተቀመጡም። ይልቁንም ላለፉት 26 ዓመታት መልካም አስተዳደር በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ዘርፈ ብዙ ጥረት አድርገዋል። በመሆኑም ለመቃወም ብቻ የሚሰነዘሩ ሃሳቦች እነዚህን ጥረቶች ለመወከል አቅም የላቸውም።  

 

ባለፉት 26 ዓመታት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ አጥጋቢ ውጤቶችም ተገኝተዋል። የአገራችን ዴሞክራሲ ሥር መስደድ ይችል ዘንድ በሁሉም ደረጃዎች የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲቋቋሙና እንዲጠናከሩ፣ የዳበረ የፍትህ ሥርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት፣ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት አካላት ውስጥ የግልፅነት፣ የተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት መርህ እንዲሰፍንና የተግባር መመሪያ እንዲሆን ብሎም በሁሉም መስኮች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ብርቱ ጥረት ተደርጓል።

ይሁንና የተከናወኑ በጎ ተግባሮችን ግምት ውሰጥ ሳያስገቡ በጭፍን ጥላቻ የህግ አስፈፃሚውን አካል በደፈናው ለማውገዝ መሯሯጥ ከትዝብት ውጪ የሚያተርፍለት አንዳችም ነገር የለም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መጎልበት አንድም ስንዝር ወደፊት ሊገፋው አይችልም። ለምን ቢሉ ጭፍን ጥላቻ ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን እንጂ ዴሞክራሲያዊነትን ሊወልድ አይችልምና።


ይሁንና አንዳንድ በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ወገኖች የአገሪቱ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ያከናወኑትን ተግባራት ሳይገነዘቡ በደፈና ተቃውሞ እየተመሩ መልካም አስተዳደርን አሁኑኑ ውለዱ በማለት በየሚዲያው የጥላቻ ዲስኩር ሲያሰሙ ይስተዋላል።


እነዚህ ወገኖች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መንግሥትንና ገዥውን ፓርቲ ለማብጠልጠል ሁሉንም አማራጮች አሟጠው ለመጠቀም የሚያደርጉት አግባብነት የሌለው የመከራከሪያ ነጥብ ግን ውኃ አይቋጥርም። የአገራችን የህግ አስፈፃሚ አካል ተቃዋሚዎቹ እንደሚያስደምጡን የጥላቻ አሉባልታ ዲስኩር ሳይሆን፤ በህግና በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚመራና የሚሰራ ነው።


መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግስት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል መሆኑ ነው። ማንኛውም ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልምና።

 

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑት ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል። በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው። መንግስት ምንም እንኳን ግዴታው ቢሆንም ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዜጎች አቤቱታ የሚደመጥበት እንዲሁም ተገቢው ምላሽ የሚሰጥበት የእንባ ጠባቂ ተቋምን አቋቁሟል።


ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ሊመሰገንና ሊደገፍ ይገባል እንጂ፤ ያለ አንዳች በቂ ማስረጃ በመንግሥትና በተቋማቱ ላይ በደፈና ጥላቻ እየታገዙ የውርጅብኝ መዓት ማውረድ ተገቢ አይደለም።  ክንዋኔዎችን በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከሚያይ ፓርቲ የሚጠበቅም አይደለም።


የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎችን አስተዳደራዊ በደል ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ በርካታ ስራዎቸን በማከናወን ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ እየታወቀ፤ በስሜት ብቻ እየተገፋፉ የተቋሙን ስም ለማጥፋት መሯሯጥ እንዲሁም የመንግስት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ታፍኖ ላለመቀበልና ለማጣጣል መሞከር “ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ” ዓይነት በመሆኑ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ራሱ ተቃዋሚ ነኝ ባዩ አካልም ቢሆን አመለካከቱ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ በእንዲህ ዓይነቱ ጭፍን እሳቤ ጉዞው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ አሜኬላ እሾህ መሆኑ አይቀርም።


መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የአገራችን ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy