Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹ለአክሰስ ሪል ስቴት የማቀርበው የመፍትሔ ሐሳብ ለሌላ ዓላማ ውሎ ነው እንጂ ተግባራዊ ቢደረግ ይኼ ሁሉ ችግር በቀላሉ ይፈታ ነበር››

0 1,037

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ የአክሰስ ሪል ስቴት ማኅበር መሥራችና ባለድርሻ

አክሰስ ሪል ስቴት በመባል የሚታወቀው የአክሲዮን ማኅበር በ2001 ዓ.ም. ቁጥራቸው 634 በሆነ አባላትና በ34 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ነው፡፡ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አውጥቶ የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት በአዲስ አበባ ከተማ የሊዝና የግለሰብ ይዞታ የሆኑ ነባር መሬቶችን አብሮ በማልማትና በመግዛት በተለያዩ ቦታዎች ሳይቶችን በማቋቋም፣ ከቤት ገዢዎች ጋር ውል በመዋዋል፣ የግንባታ ጊዜውን የርክክብ ሁኔታዎችንና የክፍያ አፈጻጸሞችን ሁሉ በተቀናጀና በተደራጀ መልክ በአጭር ጊዜ በማስተባበር ስኬታማ ሥራ ለመሥራት ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው፡፡ በወቅቱ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አመራሮች በየኃላፊነት ደረጃዎቻቸው ጉልህ ሚና የነበራቸው ቢሆንም፣ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ማኅበሩ ከፍተኛ የሕዝብ ኃላፊነትን ተቀብሎ ጉዳዮችን መምራት ተስኖት ቤት ገዥዎች ለከፈሉት ገንዘብ የውል ባለመብት የሆኑበት ሀብታቸው ላይ ሥጋት ያሳደረ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱን ያቋቋሙትና የቦርድ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲሠሩ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ61 ዓመታት በፊት የተወለዱት አቶ ኤርሚያስ ያደጉትና አፋቸውን የፈቱት ግብፅ ውስጥ በዓረብኛ ቋንቋ ነው፡፡ ከግብፅ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በማቅናትም የእንግሊዝኛና ስዋህሊኛ ቋንቋዎችን ተናጋሪ ሆነዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአሜሪካ ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል በማጠናቀቅ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለአንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደው ኑሯቸውን እዚያው አድርገው ቆይተዋል፡፡ ባለ ትዳርና የስድስት ልጆች አባት የሆኑትን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን፣ በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት በችግር ውስጥ የሚገኘውንና እሳቸውንም እስከማሳሰር የደረሰውን አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበርን በሚመለከት ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ የተለያዩ ድርጅቶችን ከፍተው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከድርጅቶቹ ውስጥ አንዱ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ ይህ ድርጅት ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው እርስዎን የሕግ ተጠያቂ ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ ማኅበሩ እንዴት እንደተመሠረተና አሁን ስላለበት ሁኔታ ቢነግሩን?

አቶ ኤርሚያስ፡- አክሰስ ሪል ስቴት ከተመሠረተ ስምንት ዓመታት ሊያልፈው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከአራት ዓመት በላይ ሥራ እየሠራ አይደለም፡፡ በሥራ ላይ የነበረበት ጊዜ ደግሞ ለአራት ዓመታት ነው፡፡ አክሰስ ሪል ስቴትን ልጀምር የቻልኩት በገበያው ውስጥ የነበረውን ትልቅ ክፍተት አይቼ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመጣሁ 22 ዓመታት ሊሞላኝ ነው፡፡ ከመጣሁ ጀምሮ ከ20 በላይ ድርጅቶች በራሴ ገንዘብ አቋቁሜያለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተዘጉም የተሸጡም ድርጀቶች አሉ፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት የመጨረሻው ድርጅቴ ነው፡፡ ይህንንም ድርጅት ላቋቁም የቻልኩት አስቤበት ሳይሆን አክሰስ ካፒታል በሚባለው ሌላው ድርጅቴ አማካይነት ነው፡፡ በአክሰስ ካፒታል ውስጥ የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት ለመንግሥት ተቋማት፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለሌሎችም የውጭ ድርጅቶች እንበትን ነበር፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፖርት ሠርተን እንሰጣለን፡፡ ለምንሠራቸው ጥናቶች አናስከፍልም፡፡ ለአገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ጠቃሚ መረጃ እናቀርብ ነበር፡፡ ጥናታችን አካዴሚክ ሳይሆን ከኢንቨስትመንት ጋር የተገናኘ ነበር፡፡ ኢንቨስትመንት ያለመረጃ አይሆንም፡፡ ቢደረግም ውጤታማ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱና ዋናው ችግር ማንኛውም ነገር የሚደረገው ያለመረጃና በአሉባልታ ማለትም መረጃ ከሌለው ሰው በሚገኝ ምክር ነው፡፡ ይህንን የምናገረው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፖርት እንደምንሠራው ሁሉ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ሴክተሮች ላይ የተሟላ ጥናት እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ በባንኮች ላይ እንሠራለን፡፡

ያ ማለት ድርጅታችን ቁጭ ብሎ የሚገኘውን መረጃ የሚተነትን፣ የሚያቀነባብርና የሚጽፍ ክፍል ነበረው፡፡ በግብርና ላይ፣ በማኑፋክቸሪንግና በተለያዩ ሴክተሮች ላይ ትንታኔ እንሠራለን፡፡ በሪል ስቴት ላይም ሪፖርት ሠራን፡፡ የሪል ስቴት ሪፖርታችን (ጥናታችን) የተሠራው 40 ዓመታት ወደኋላ ሄደን፣ የሕዝብ ብዛት ሁኔታና አሁን የተደረሰበትን የሕዝብ ብዛት ያካተተ ነበር፡፡ ሕዝብ በመብዛቱ የመኖሪያ እጥረት አለ፡፡ መንግሥት ለሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው ተመዝግቧል፡፡ ይህ ሁሉ ሰው ቤት ይፈልጋል፡፡ መንግሥት ከሚነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ውጪ ሪል ስቴቶችም እየገነቡ ነው፡፡ ሪል ስቴቶቹ ከአዲስ አበባ ወጣ ወጣ እያሉ ሰፋፊ ቦታዎችን ወስደዋል፡፡ ሕዝቡ ግን ሥራ የሚሠራው መሀል ከተማ ላይ ነው፡፡ እየተመላለሰ ለመሥራት የትራንስፖርት እጥረት ስላለበት ይቸገራል፡፡ በመሀል ከተማ ላይ የሚሠሩት ቤቶች ወይም የተሠሩት ቤቶች በሰፋፊ ቦታ ላይ ሆኖ ቪላዎች ናቸው፡፡ የቤቶቹ ባለቤቶች ደግሞ ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡ ባይኖርበትም አከራይቶት ይሄዳል፡፡ ይህንን ሁሉ ያረጋገጥነው ባደረግነው ጥናት ነው፡፡ አሜሪካ የኢንቨስትመንት ባንከር ሆኜ ስሠራበት የቆየሁት ሴክተር ኢንቨስትመንት ላይ ነበር፡፡ እኔ አማክራቸው የነበሩ ድርጅቶች በዓመት አሥር ሺሕና አሥራ አምስት ሺሕ ቤቶችን ሲገነቡ አይቻለሁ፣ አውቃለሁም፡፡ ስለዚህ በዚህ አገር ያለውን ክፍተት በመረዳቴ ወደ ሪል ስቴት ለመግባት ወሰንኩ፡፡ ቀደም ብዬ የመሠረትኩት አክሰስ ካፒታል ስለነበር በሥሩ አክሰስ ሪል ስቴትን መሠረትኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ሪል ስቴቱን ከመሠረቱ በኋላ ቤቶቹን የመገንቢያ ቦታና ቤት ገዢዎችን ያገኙት እንዴት ነበር?

አቶ ኤርሚያስ፡- ትልቁ ነገር አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩና ሥራቸውም አዲስ አበባ ውስጥ የሆኑ ሰዎች የገቢ መጠናቸው የሚፈቅድላቸውን ቤት ያመዛዘነና ጥሩ የሆነ ቤት ይዤ መቅረብ እንዳለብኝ ገምቼ ነው ወደ ሴክተሩ የገባሁት፡፡ የኅብረተሰቡን ገቢ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ ይዤ በመቅረቤ ገበያው እንደ ባህር እንደሚሆንም እርግጠኛ ነበርኩኝ፡፡ በከተማው ውስጥ በቂ ቤት ባለመሠራቱ ፈላጊዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በመሀል ከተማ ለሚኖር ሰው ቪላ ሳይሆን አፓርትማ መገንባት አዋጭ ነው፡፡ ኒውዮርክ ቢሊየነሮች የሚኖሩት በአፓርትማ ውስጥ ነው፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ባንደርስም ሒደቱ እንደዚያው ነው፡፡ በመሆኑም በቀለበት መንገዶች ውስጥ አፓርትመንቶችን በገፍ መሥራት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ቤቶችን በገፍ (በብዛት) መሥራት ከተቻለ በትንሽ ዋጋ በመሸጥ ትርፋማ መሆን ይቻላል፡፡ እኔም ብዙ ሕንፃዎችን በመሥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ ትርፋማ ለመሆን ተንቀሳቀስኩኝ፡፡ የቻይናን ኢኮኖሚ ብንወስድ ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ሥራ ፈጣሪም ነው፡፡ አነሳሳችን ይህንን ይመስል ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለብቻቸው ድርጅት ለማቋቋም የሚያስችል ገንዘብ ባይኖራቸውም፣ ከሌሎች ጋር በመቀናጀት በማኅበር ተደራጅተው መሥራት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በመሆኑም ሪል ስቴቱን ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በማካተት አክሲዮን ማኅበር አደረግነው፡፡ የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢና ሥራ አስኪያጅ እኔ ሆንኩኝ፡፡ የሚገርመው ነገር በተመሳሳይ ሁኔታ የአክሰስ ካፒታልና የዘመን ባንክም ቦርድ ሰብሳቢና ሥራ አስኪያጅም ነበርኩ፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበርን ሐሳቡን በመንደፍ ያቋቋምኩት እንዳሰብኩት ይሄዳል ብዬ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ላሰቡት የሪል ስቴት ግንባታ ቦታ እንዴት እንዳገኙና አብዛኞቹ ቤት ገዢዎች ዳያስፖራ እንዴት ሊሆኑ እንደቻሉ ቢነግሩን?

አቶ ኤርሚያስ፡- ሪል ስቴት ግንባታ ውስጥ ለመግባት ሳስብ ቤት ገዢዎች ዳያስፖራዎች ይሆናሉ የሚል ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ አሥር በመቶ እንኳን ለዳያስፖራ እንሸጣለን የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ የአገር ውስጥ ቤት ፈላጊዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው ወደ ሥራው የገባነው፡፡ ሁለት ሺሕ ቤቶችን ነው መጀመሪያ ለመገንባት ያሰብነው፡፡ ከሁለት ሺሕ ቤቶች ውስጥ አንድ ሺሕ የሚሆኑት ቤቶች ሊገነቡ የታሰበው ወይም ግንባታ የተጀመረው በሦስት ሳይቶች ላይ ነው፡፡ ኒያላ ሞተር አካባቢ፣ ሲኤምሲና አያት በሚገኙ ሳይቶች ላይ ግንባታ ተጀመረ፡፡ ኒያላ ሞተር አካባቢ ያለውን በካሬ ሜትር 6,000 ብር፣ ሲኤምሲ ያለውን ደግሞ በ8,000 ብር ነው የሸጥነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ  150 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን አፓርትማ በዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር ነው የሸጥነው፡፡ ይህንን ያደረግነው ደግሞ ኅብረተሰቡ ያለውን ገቢ ያማከለ ዋጋ እንዲሆን ነው፡፡ በእርግጥ በርከት ያሉ ዳያስፖራዎችም ገዝተዋል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ ገንዘብ ዘርዝረው ስለከፈሉ፣ ዳያስፖራው የገዛው ይህንን ያህል ነው ወይም አገር ውስጥ የሚኖረው የገዛው ይህንን ያህል ነው ልልህ አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በሪል ስቴት ሴክተር ሲሰማሩ መሬቶችን ያገኙት በሊዝ ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- አይደለም፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ መሬት በሊዝ ወስጄ እንዳልሠራ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ አንደኛ የእኔ ትልቁ ዓላማዬ ከተማ ውስጥ ለመሥራት ነወ፡፡ እኔ ሥራውን ስጀምር ለሊዝ የሚቀርቡ መሬቶች አልነበሩም፡፡ እኔ የምፈልጋቸው አካባቢዎች ባሉ መሬቶች ላይ ሊዝ አይወጣም ነበር፡፡ በዓለም ላይ ጭምር ለሪል ስቴት ግንባታ የቦታ አቀማመጦች (ሎኬሽንስ) በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ ሁሉም ቤት ፈላጊ የመጀመሪያ ጥያቄው የቦታው አቀማመጥ ነው፡፡ እኔም የመጀመሪያ ምርጫዬ በከተማው ውስጥ በጥሩ አቅጣጫ ላይ ያሉ መሬቶችን መፈለግ ነበር፡፡ የመጀሪመሪያዎቹ ሳይቶች የተገነቡባቸው ቦታዎች ቀደም ብሎ በሌሎች ሰዎች በሊዝ የተወሰዱ ናቸው፡፡ እነዚህ መሬቶች ላይ በእሽሙር (ጆይንት ቬንቸር) መሥራት ጀመርን፡፡ በቀጣይ የቤት ፈላጊዎች ቁጥርም እየጨመረ በመምጣቱ የምንፈልገውን ግንባታ በምንፈልገው ቦታ ላይ ለመሥራት በግድ ወደ ግል ገበያው መግባት ነበረብን፡፡ የግል ቪላ የተገነባባቸውና ስፋታቸው እስከ 1,500 ካሬ ሜትር የሚደርሱ ቦታዎችን ከግለሰቦች በመግዛት መሥራት ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል መሬቶችን ገዛችሁ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ከመንግሥት ምንም ዓይነት መሬት አልወሰድኩም፡፡ በሊዝ የተወሰዱ የግል ይዞታዎችና በድርጅቶች ተወስደው በዕዳ የተያዙ መሬቶችን ነው የገዛነው፡፡ በግል ድርጅቶች የተወሰዱትን አክሲዮኖች ነው የገዛነው፡፡ በድምሩ ወደ 43 የሚደርሱ ቦታዎችን ገዝተናል፡፡ አሁን ግን ያሉት 20 ቦታዎች ብቻ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀሪዎቹ ከ23 በላይ ቦታዎች ምን ሆኑ?

አቶ ኤርሚያስ፡- እንደነገርኩህ ሥራውን የጀመርነው በሰፊው ነበር፡፡ በሰፊው የጀመርነውም ሁሉንም እንደየፍላጎቱ ለማዳረስ ነበር፡፡ መርካቶ ሥራ ያለው በመርካቶ አካባቢ እንዲኖር፡፡ ፒያሳ የሚሠራ በዚያው አካባቢ እንዲኖርና ሥራንና መኖሪያን በማቀራረብ የሕዝቡን ኑሮ የተስማማ ለማድረግ ነበር፡፡ በሁሉም አካባቢ ማለትም ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ የቀድሞ አውሮፕላን ማረፊያ፣ መገናኛ፣ ሲኤምሲ፣ አያትና ሌሎችም አካባቢዎች መሬቶችን ገዝተን ነበር፡፡ ካዛንቺስ፣ ቦሌና መሀል አካባቢ የገዛናቸውን ቦታዎች ማለትም ከ20 በላይ የሚሆኑትን አትርፈን ሸጠናቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕዝቡ ትንሽ ወደድ ስላሉበት ሊገዛቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ቀድመን የገዛነው የቦታዎቹን ተፈላጊነት አጥንተን ቢሆንም፣ የሕዝቡን አቅም ቀድመን ማጥናት ባለመቻላችን ፈላጊ በማጣታቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ አክሰስ ሪል ስቴት በድምሩ ስንት ካሬ ሜትር ቦታ አለው?

አቶ ኤርሚያስ፡- በአሁኑ ጊዜ 300,000 ሜትር ካሬ ቦታ አለው፡፡ ይህ ቦታ በቤት ገዢዎች ተመርጦ የተገዛ ነው፡፡ ሕዝቡ ማወቅ ያለበት ሁለት ሺሕ ቤት ገዢዎች ግዢ     ፈጽመዋል ቢባልም፣ ያልተሸጡ 2,000 ቤቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ክፍያው የገዢውን አቅም የገናዘበ ስለሆነ፣ አቅም ላለው ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡ ቤት ከገዙት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ክፍያ የፈጸሙት ከ20 በመቶ አይበልጡም፡፡ የክፍያ ጊዜ የምንሰጠው እስከ አምስት ዓመት ድረስ ነበር፡፡ ግን አላደረግነውም፡፡ አንድ ነገር መታወቅ ያለበት ቤት ገዝተው የተወሰነ ክፍያ የከፈሉ ቢኖሩም፣ ቤቱ እየተሠራ የሚፈጸም 500 ሚሊዮን ብር ያልተከፈለ ገንዘብ ነበረን፡፡ አሁን ግንባታ ብንጀምር ይህ ገንዘብ መከፈል አለበት፡፡ ሙሉ ክፍያ የከፈሉ ቢኖሩም 100 ሺሕ ብርና 200 ሺሕ ብር የከፈሉም አሉ፡፡ ቤቱን መሥራት ስንጀምር ይህ ሁሉ ብር ይሰበሰባል፡፡ 500 ሚሊዮን ብር ቀላል አይደለም፡፡ የአምስት ዓመታት የክፍያ ጊዜ ሰጥተን የነበረው ፋይናንሳችንን በጅምላ ስለምናንቀሳቅስ ነበር፡፡ የሪል ስቴቶች ችግር ቤቶችን በገቡት ኮንትራት መሠረት ሠርተው አለማስረከብ መሆኑን በጥናታችን በማረጋገጣችን፣ አዲስ ቴክኖሎጂን ማለትም በፋብሪካ የተሠሩ ቤቶችን በማቅረብ በአጭር ጊዜ ገጣጥሞ ለመስጠት ነበር፡፡ ለቤት ገዢዎችም እናደርጋለን ያልነውን ፈጽመን ማሳየት እንዳለብንም እምነት ሰንቀን ተነስተን ነበር፡፡ እንጠቀማለን ያልነው አዲስ ቴክኖሎጂ በውጭው ዓለም ተግባራዊ የሆነና ለውጥ ያመጣ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ከደቡብ አፍሪካ ከመጣ ድርጀት ጋር በእሽሙር (ጆይንት ቬንቸር) የሚሠራ አገር በቀል ድርጅት መሥራት በመጀመሩ ከእሱ ጋር ኮንትራት ገባን፡፡ ድርጀቱ ሙሉ በሙሉ በብረት የተገነባ ግድግዳና ጣሪያ አምርቶ ሊያስረክበን ተስማማን፡፡ ቤት ገዢዎቹ ከእኛ ጋራ ውል ሲገቡ፣ በገባነው ውል መሠረት በቀኑ ካላስረከብናቸው በየወሩ 5,000 ብር እንደምንቀጣ ውል ገብተናል፡፡ ወይም ቤት ገዢው በፈለገ ጊዜ ብሩ እንዲመለስለት ከፈለገ፣ ብሩን ከተቀበልንበት ጊዜ ጀምሮ 15 በመቶ ወለድ አስበን እንደምንመልስም በውሉ ተገልጿል፡፡ ይህንን ያደረግነው ሥራውን ጠንክረንና ተገደን እንድንሠራ ስለሚያደርገን ነው፡፡ ብዙ ቤት ገዢዎች ተማምነው ውል የፈጸሙት እኔን ዓይተው ነው፡፡ ቀደም ብዬ የመሠረትኳቸውን ድርጅቶችና እኔን በማማከር ድርጅት የመሠረቱ ሰዎች ውጤታማ መሆናቸውን ስላዩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደገለጹት ከቤት ገዢዎች ጋር በገቡት ውል መሠረት ቤቶቹን ገንብቶ ለማስረከብ ጊዜ ቆርጣችሁ ውል ብትፈጽሙም፣ በሌሎች ሪል ስቴት አልሚዎች የተለመደው ጊዜ ማራዘም በአክሰስ ሪል ስቴትም ታይቷል፡፡ ተጨማሪ አስገዳጅ ውሎችን በመፈጸማችሁም መጨረሻው እርስዎን እስከማሳሰር ተደርሷል፡፡ እስቲ ስለሁኔታው ይንገሩን?

አቶ ኤርሚያስ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ለሁሉም ግራ የሚገባ ነገር ነው፡፡ አንደኛው ጥያቄ እንዴት በገባችሁት ግዴታ መሠረት ማስረከብ አቃታችሁ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ይህንን የሚያህል ፕሮጀክት እንዴት በአንድ ጊዜ ብትን ሊል ይችላል? የሚል ጥያቄ ነው፡፡ በማንኛውም ዓይነት ሥራ ትልቁ ሥራ ገበያ ማግኘት ነው፡፡ ሰው ማሳመንና ፋይናንስ ማመቻቸት ነው፡፡ ያንን ከባድ ሥራ በጥሩ ፋይናንስ ሠርተነዋል፡፡ እዚህ አገር አዲስ ቴክኖሎጂ መኖሩን ስለማላውቅ ኒያላ ሞተርስ ጋ ያለውን ሳይት በተለመደው የሕንፃ ግንባታ አሠራር መሥራት ጀመርን፡፡ በሒደት ግን የቤቶችን ግድግዳዎችና ጣሪያ የሚሠራ ቴክኖሎጂ መኖሩን ሳረጋግጥ፣ ይህንን ትልቅ የቤት ገዢዎች ሮሮ በተፋጠነ ሁኔታ ለመቅረፍ የመጀመሪያውን ሳይት በሲኤምሲ ጀመርኩ፡፡ የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ በውጭ አገር ተሠርቶና ጣጣው አልቆለት የሚመጣ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር 50 ኮንቴይነር የሕንፃ መገጣጠሚያ እስካሁን ጂቡቲ ተቀምጦ ቀርቷል፡፡ ከኒያላ ሞተርስ ሳይት በስተቀር ሲኤምሲና አያት ሳይትን በአዲሱ ቴክኖሎጂ ጀምረን በጥሩ ሁኔታ እየሠራን ነበር፡፡ መሬቶቹ በሊዝ የተያዙ ስለነበሩ በእሽሙር (ጆይንት ቬንቸር) ገብተን ነው የያዝናቸው፡፡ ቤቶቹን በገባነው ውል መሠረት ለማድረስ ደፋ ቀና ስንል ‹‹ግንባታ አቁሙ›› የሚል ደብዳቤ ተጻፈልን፡፡

ሪፖርተር፡- ማነው ደብዳቤ የጻፈላችሁ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ከማዘጋጃ ቤት መሬት አስተዳደር ነው የተጻፈልን፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታ እንድታቆሙ የተደረጋችሁት ለምንድነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ለምን እንደሆነ ስንጠይቅ ያላግባብ በሊዝ የተሰጡ መሬቶች ስላሉ መጣራት አለበት የሚል ምላሽ ተሰጠን፡፡ መንግሥት ለሰባት ወራት ያህል እያንዳንዱን ሳይት ካጣራ በኋላ ጀምሩ አለን፡፡ የሲኤምሲና የአያት ሳይቶች ከላይ እንደገለጽኩት በአዲሱ ቴክኖሎጂ የሚገነቡ ናቸው፡፡ ሕንፃዎቹን ለመገጣጠም የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ ማዘዝ የሚቻለው የሕንፃው መሠረት ከመሠራቱ በፊት ነው፡፡ መሠረቱ ከወጣ በኋላ ቢታዘዝ ጊዜ ስለሚወስድ ሥራ ስለሚያስፈታ ነው፡፡ በመሆኑም ቴክኖሎጂውን ለሚያቀርበው ድርጅት በአንድ ጊዜም ባይሆን ትልቅ ገንዘብ ተከፍሎ ታዞ መጥቶ ነበር፡፡ ግንባታውን በድንገትና ባልታሰበ ሁኔታ አቁሙ ሲባል ድርጅቱ ብረቱን ለሌላ ሥራ አዋለው፡፡ ከሰባት ወራት በኋላ ሥራ ጀምሩ ሲባል ብረቱ የለም፡፡ ድርጅቱን ስንጠይቅ የሸጠለት ድርጅት ገንዘብ ስላልከፈለው እኛ በጠየቅንበት ወቅት ሊያደርስልን አልቻለም፡፡ መጀመሪያ ያንገዳገደንና ለብዙ ችግር የዳረገን ባላሰብነው ሁኔታ ግንባታ አቁሙ መባላችን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ግንባታው እየተጓተተ መጣ፡፡ ቤት ገዢው ደግሞ በገባነው ውል መሠረት ይፈጸምልን ማለት ጀመረ፡፡ የተለያየ ሰበብ እየሰጠሁ ነገሮችን ለማሳካት ጥረት ባደርግም ሊሳካ አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ የቤት ገዢዎች እምነት መሸርሸር ጀመረ፡፡ ቀስ ቀስ እያለ ቤት ገዢው ‹‹በውሌ መሠረት ቤቴን ልታስረክበኝ ስላልቻልክ ብሬን መልስልኝ›› ማለት ጀመረ፡፡ እኔም መክፈል ጀመርኩኝ፡፡ ችግሮች እየተፋፋሙ መጡ፡፡ ገንዘብ እያጠረኝ መጣ፡፡ ምክንያቱም ለኮንትራክተር፣ ለቴክኖሎጂና ለተለያየ ነገር ወጪ በመደረጉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከቤት ገዢዎች 1.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡ ሁሉንም ገንዘብ ነው የከፈሉት?

አቶ ኤርሚያስ፡- ልክ ነህ 1.4 ቢሊዮን ብር ሰብስበናል፡፡ ማወቅ ያለብን ግን የተሰበሰበው ሁሉ በእኛ ካዝና ውስጥ ብቻ ይገባል ማለት አይደለም፡፡ ከተሰበሰበው ገንዘብ ላይ ወደ 200 ሚሊዮን ብር ቫት ተከፍሏል፡፡ ምክንያቱም የሸጥንበት ዋጋ ቫትን ያካተተ ስለነበር ነው፡፡ እኛ ጋ የቀረው 1.2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ለኮንትራክተሮች 500 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል፡፡ ግን የ500 ሚሊዮን ብር ሥራ አልተሠራም፡፡ 500 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለመሬት መግዣ ውሏል፡፡ ለአማካሪ ድርጅቶችና ለተለያዩ ወጪዎች ደግሞ 200 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል፡፡ በውሉ መሠረት ቤታቸው ላልተሰጣቸው ቤት ገዢዎች ደግሞ 80 ሚሊዮን ብር ከፍለናል፡፡ ግንባታው በወቅቱ ካልደረሰ በየወሩ 5000 ብር ቅጣት እንከፍላለን ብለን በተስማማነው መሠረት መቶ ለሚሆኑ ቤት ገዢዎች 20 ሚሊዮን ብር ከፍለናል፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ነገሮች ቀስ ብሎ የተጀመረው ነገር ቀስ እያለ እያበጠ መጣ፡፡ ሁሉም ቤት ገዢ በኮንትራቱ መሠረት ቤቱን መረከብ ባለመቻሉ ገንዘቡ እንዲመለስለት ፈለገ፡፡ ይህ ደግሞ መብቱ ነው፡፡ የአክሰስ ሪል ስቴትን ጉዳይ በምሳሌ ላስረዳ፡፡ የአገር ውስጥ ሳይሆን የውጭ ባንክን እንውሰድ፡፡ አንድ የውጭ ባንክ ካሉት ደንበኞች መካከል አሥር በመቶ የሚሆኑት በድንገት ወደ ባንኩ ሄደው ያላቸውን ገንዘብ በአንድ ቀን ቢያወጡ፣ ባንኩ ኪሳራ ላይ ይወድቃል፡፡ ባንኩ ገንዘቡን የሰበሰበ ቢሆንም ገንዘቡን የሰበሰበው ሊቀመጥበት አይደለም፡፡ አበድሮታል ወይም በሥራ ላይ አውሎታል፡፡ ጊዜ ተሰጥቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ መልስ ቢባል ግን የሰጠውን ብድርና ወለድ ሰብስቦ ሊከፍል ይችላል፡፡ የአክሰስም ተመሳሳይ ነው፡፡ በአንድ ቀን ባይሆንም በድምሩ ‹‹ብሬን መልስልኝ›› ብለው ያመለከቱት 400 ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም ቢሆን ፋይናንስ አመቻችቼ ለመክፈል ጫፍ ላይ ደርሼ እያለሁ ነገሮች ሁሉ ተበለሻሹ፡፡ በሥራ ላይ የዋለን ገንዘብ በአንድ ጊዜ መጥቶ ክፈለኝ ማለት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ጊዜ ቢሰጠኝ ከገዛኋቸው ቦታዎች ግማሹን እንኳን ብሸጥ አይደለም የጥቂቶችን የሁሉንም መክፈል እችል ነበር፡፡ በመሬቶቹ ላይ (300 ሺሕ ሜትር ካሬ) ትልቅ ገንዘብ ወጪ ስለተደረገ ማኅበሩ እስካሁን ትርፋማ እንጂ ኪሳራ የሚባል ነገር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደሚሉት የቤት ገዢዎች ገንዘብ በመሬቶች ላይ ከዋለና እስካሁንም ማኅበሩ ትርፋማ ከሆነ፣ እርስዎን እስከማሳሰር የደረሱ ችግሮች እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ከቤት ገዢዎች ጋር የገባሁት ውል መፈጸም አለበት፡፡ ውል መከበር አለበት፡፡ ነገር ግን ገንዘቡን በሥራ ላይ አውዬው ስለበር የሁሉንም ጥያቄ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ አልቻልኩም፡፡ ጥያቄው ፋታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ የነበረውን ገንዘብ ሰጥቼ ስጨርስ ነገሮችን አስተካክዬ ለሁሉም ገንዘባቸውን እስከምሰጥ ድረስ ቼክ እየጻፍኩ ሰጠሁ፡፡ ለ80 ቤት ገዢዎች ቼክ ጻፍኩኝ፡፡ ቼክ የጻፍኩት ቼክ የሚያመጣውን ሕጋዊ ተጠያቂነት ሳላውቅ ቀርቼ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ገንዘብ የማገኝበት አንድ ነገር ላይ በመደራደር ላይ ስለነበርኩ ለአጭር ጊዜያት መተማመኛ እንዲሆን በማለት ነበር፡፡ ሌሎች ግማሽ ክፍያ የፈጸሙና ቀሪ 500 ሚሊዮን ብር ያለባቸው ቤት ገዢዎችም እንቅስቃሴ ሳይጀመር አንከፍልም አሉ፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ ፕሮግራም ውስጥ የነበረና ገቢ መደረግ የነበረበት ነው፡፡ በዚህ መሀል አንድ ቤት ገዢ የጻፍኩለት ቼክ ብር እንደሌለው በማረጋገጥ አስመትቶ እንድታሰር ወደ ፖሊስ ጣቢያ አስወሰደኝ፡፡ የእሱን ገንዘብ ከዚያምም ከዚህም ብዬ ከፈልኩ፡፡ በመቀጠል ቤት ገዢው ሁሉ ወደ ቢሮ መምጣት ጀመረ፡፡ ይህንን ነገር ማረጋጋት ስለነበረብኝ በድንገት ብድግ ብዬ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በጻፉት ደረቅ ቼክ ምክንያት ታስረው ሲፈቱ የሄዱት ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አልነበረም?

አቶ ኤርሚያስ፡- አይደለም፡፡ ወደ አሜሪካ በቀጥታ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው የወጣሁት፡፡ ነገር ግን ብዙ ነገር ሰምቻለሁ፡፡ በጁባ ወጣ፣ በጂቡቲ ወጣ መባሉን ሰምቻለሁ፡፡ እኔ የአሜሪካ የረጅም ጊዜ ቪዛ ስለነበረኝ ነገሮችን ለማረጋጋት ነው የወጣሁት፡፡ እኔ እስር ቤት ከገባሁ ሁሉም ነገር ይበተናል፡፡ ነገር ግን ወጣ ብዬ ነገሮችን ማስተካከል ስለነበረብኝ አሜሪካ ካለው ቢሮዬ ሆኜ ሥራውን መከታተልና መምራት ጀመርኩኝ፡፡ ለሁለት ወራት፡፡ ተመልሼ ነገሮችን ማስተካከል እንደምችል ስለማውቅ ነገሮችን ሁሉ ግልጽ አድርጌ በመግለጽ በጻፍኳቸው ቼኮች ምክንያት ለእስር እንዳልዳረግ መንግሥት ዋስትና እንዲሰጠኝ በደብዳቤ ጠየቅኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ለጻፉት ደብዳቤ የመንግሥት ምላሽ ምን ነበር?

አቶ ኤርሚያስ፡- የመንግሥት ምላሽ የተፈጠረው ችግር ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደቻለና በቀጣይስ እንዴት ሊስተካከል እንደሚችል የሚያሳይ ሰነድ ሰርቼ እንድልክ የሚገልጽ ነበር፡፡ በመንግሥት ምላሽ በመደሰቴ ከ30 ገጽ በላይ የሚሆን ሰነድ ጽፌ ላኩኝ፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ በመወሰን መመለስ እንደምችል የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ይህ የሆነው በስድስት ወራት ውስጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት እንዲመለሱ የሚገልጽ ደብዳቤ ሲልክልዎት ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም፡፡ ለምን ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሄዱ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ወደ ዱባይ የሄድኩት የቀንና ሌሊት ፈረቃ (Sleep Time) ለማስተካከል ለጥቂት ቀናት ነበር፡፡ የአፈጻጸም ችግር እንዳለ ስለተገለጸልኝ 14 ወራት በዱባይ ለማሳለፍ ተገደድኩኝ፡፡ ከኢትዮጵያ የወጣሁት እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 18 ቀን 2013 ሲሆን ተመልሼ የመጣሁት ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 18 ቀን 2015 ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የሰጠዎት ዋስትና ምንና እስከ መቼ የሚቆይ ነበር? አስገዳጅ ሁኔታዎችን የያዘ ነበር?

አቶ ኤርሚያስ፡- የመጀመሪያው ጥያቄ ‹‹ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ በሌላ አገር ያለህን ንብረት አስመዝግብ›› የሚል ነው፡፡ ቀጥሎ በአክሰስ ሪል ስቴት ላይ የተፈጠረው ችግር አንተ እንደጻፍከው ከሆነና መፍትሔ መስጠት የምትችል ከሆነ መንግሥት ከለላ ይሰጥሃል የሚል ነው፡፡ የተጭበረበረ፣ የተሰረቀና የጠፋ ነገር ካለም በግልጽ ተናገር የሚልም ነበረበት፡፡ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው እኔ ከአክሲዮን ድርሻዎች ውጪ በየትም ቦታ ቤት  የለኝም፡፡ በባንክም ገንዘብ የለኝም፡፡ መኪናም የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ኢንቨስተር ነዎት፡፡ በውጭው ዓለም በታዋቂ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሠሩና ትልቅ ተከፋይ ከሚባሉት ግለሰቦች አንዱ ነበሩ፡፡ ቤት፣ መኪናና ገንዘብ በባንክ የለኝም ሲሉ ምን ማለት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- እውነት ነው፡፡ እኔ በውጭ አገርም ሆነ እዚህ ምንም ትርጉም ያለው ገንዘብ የለኝም፡፡ ማለቴ በባንክ ውስጥ፡፡ ገንዘብ ሳገኝ ማስቀመጥ አልወድም፡፡ ገንዘብ ሳገኝ ወዲያውኑ ኢንቨስትመንት ላይ አውለዋለሁ፡፡ ገንዘብ ቢኖረኝ ኖሮ ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው እኔ ነበርኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የሚያገኙትን ገንዘብ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ እያዋሉ ምንም ገንዘብ የለኝም ማለት ይቻላል?

አቶ ኤርሚያስ፡- አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ለእኔ ትርጉም ስለሌለው ነው፡፡ ሰው ጉራ ወይም ሌላ ነገር ሊመስለው ይችላል፡፡ አሜሪካ የሰው ልጅ ሊኖር የሚችለውን ኑሮ ኖሬያለሁ፡፡ በአሜሪካ ደረጃ እላይ ጫፍ ላይ ኖሬያለሁ፡፡ በአሜሪካ ስምንት ሺሕ ካሬ ሜትር ግቢ ያለው መኖሪያ ቤት ነበረኝ፡፡ የኖርኩትን ኑሮ ማውራት አልፈልግም፡፡ አንድ ነገር መታወቅ ያለበት እኔ ብር ብፈልግ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አልመጣም ነበር፡፡ ይህንን የምነግርህ ከዛሬ 22 ዓመት በፊት የነበረ ታሪክ ነው፡፡ አሜሪካ ዎልስትሪት ኢንቨስትመንት ባንክ ምን እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ በዓለም ላይ ለሙያ (ፕሮፌሽን) ዋጋ የሚከፈልበት ተቋም ቢኖር እሱ ነው፡፡ እዚያ ስሠራ በዓመት አገኝ የነበረውን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ኢንቨስት የማደርገው ከየት አምጥቼ ነው? ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ አሜሪካ ባለንብረት ነበርኩኝ፡፡ ሀብታምም ነበርኩኝ፡፡ ያ ትርጉም ቢሰጠኝ ኖሮ እዚያው እቀመጥ ነበር፡፡ የከሰርኩት እዚህ መጥቼ ነው፡፡ አሁን እኔ አንድ ክፍል ውስጥ ወይም ቤተ መንግሥት ውስጥ ብኖር ለእኔ ስሜት አይሰጠኝም፡፡ ስለ ሀብት ንብረት ማሰብም አልፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ እጅግ ሀብታም ከሚባሉ ሰዎች እኩል ጫፍ የደረሰ ኑሮ ኖረዋል፡፡ ሀብታምም ነበሩ፡፡ ነገር ግን በሀብት ላይ እየሠሩ ካልጨመሩበት የነበረው ሀብት እየተመናመነ መጥቶ ማጣትም ሊከተል ይችላል፡፡ እርስዎም ይህንን ስለሚያውቁ ይመስለኛል ወደ ኢንቨስትመንት የገቡት፡፡ ይህ ካልሆነ የግል ነፃነትዎን ጭምር የሚያሳጣ ሥራ ውስጥ የገቡት ለምንድነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ልክ ነህ፡፡ እኔ አልዋሽህም፡፡ መልዓክ አይደለሁም፡፡ የአገር ስሜትም ይዞኝ አይደለም፡፡ እኔ በቀውጢው የፖለቲካ ጊዜ ማለትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኒቨርሲቲ ኮሌጅ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲደረግ ለእኔ ምንም አይገባኝም ነበር፡፡ እኔ ለእንደዚህ ዓይነት ነገር አልተፈጠርኩም፡፡ ነገር ግን ደፋር ነኝ፡፡ ‹አድቬንቸር› እወዳለሁ፡፡ የተረጋጋ ነገር አይጥመኝም፡፡ ሁልጊዜ አዲስ ነገር ማድረግ እወዳለሁ፡፡ ትምህርትም ቢሆን ኢኮኖሚክስ፣ ፖለቲካል ሳይንስና ፍልስፍና ተምሬያለሁ፡፡ እዚህ ላይ አዕምሮዬ ተከፍቷል፡፡ ከሁሉም በላይ በአሜሪካን  የሠራሁበት ደረጃ የመጨረሻ ግዙፍ የሚባሉ ተቋማት ውስጥ ነው፡፡ ከ100 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ሠራተኞች ባሏቸው ኩባንያዎች ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ በቢሊዮኖች የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች አማካሪ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ የድርጅቶቹ የፋይናንስ ምንጭ በሆኑ ኢንዱስትሪዎችም ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ስሠራ ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ሆነብኝ፡፡ አዲስ ነገር ማየት አልቻልኩም፡፡ ገንዘብ ማግኘትና ጥሩ ኑሮ መኖር ብቻ ሆነብኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ወደ ኢትዮጵያ በአጋጣሚ መጣሁ፡፡ የመጣሁበት ምክንያት ደግሞ ባለቤቴ ነች፡፡ ኢሕአዴግ እንደመጣ ባለቤቴ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ሦስት ወራት ቆይታ ወደ አሜሪካ ስትመለስ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ እንዳለብኝ ስታሳምነኝ መጣሁ፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ግን ቤቴ የገባሁ መሰለኝ፡፡ ግራ የሚገባ ስሜት ተሰማኝ፡፡ ደስ የሚል ስሜት፡፡ በቆየሁባቸው ቀናት እየተዟዟርኩኝ ከተማውን ስጎበኝ አዲስ ነገር አየሁ፡፡ ለአንድ ሳምንት ብዬ ብዙ ነገሮችን አቁሜ መጥቼ ከወር በላይ ቆየሁ፡፡ ወደ አሜሪካ ስመለስ ኢትዮጵያ ተመልሼ መኖር እንዳለብኝ ወስኜ ስለነበር እየተመላለስኩ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ጀመርኩኝ፡፡ የምሠራቸው ሥራዎች ግን አትራፊ አልነበሩም፡፡ በጣም የሚገርምህ ነገር ለሠራተኛ የምከፍለው ገንዘብ አጥቼ መኪናዬን ሸጫለሁ፡፡ ለእኔ የሚያስደስተኝ ውጣ ውረዱና ተግዳሮቶቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድን ሥራ ስሠራው እንደምወጣው በመተማመን ነው፡፡ ምክንያቱም የማውቀውን ሥራ ስለምጀምር ነው፡፡ አክሰስ ሪል ስቴትም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ በቀላሉ ልፈታው የምችለው የሥራ ዓይነት ነበር፡፡ ደግሞም እፈታዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራዎችን የሚሠሩት ለትርፍ ሳይሆን ‹አድቬንቸር› ስለሚወዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የመሠረቷቸው ድርጅቶች ገንዘብ የሚያስገኙና መሠረታቸውን በትርፍ ላይ ያደረጉ ናቸው፡፡ እርስዎ ገንዘብ አልፈልግም ከሚሉት ጋር አይጋጭም?

አቶ ኤርሚያስ፡- እኔ ውጤት እወዳለሁ፡፡ ማሸነፍና ለውጥ ማምጣት እወዳለሁ፡፡ አሜሪካ ሆኜ ዓለምን የሚያንቀሳቅስ ሞርጌጅ ባንክስ ሴኪዩሪቲ ሲፈጠር እዚያ ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ እኔ ራሴ የፈጠርኩት ነገርም ነበር፡፡ አሜሪካ ባንከር መጽሔት ፊት ገጽ ላይ ወጥቼ የነበረውም ለዚያ ነው፡፡ ማለት የፈለግኩት ከበፊትም አንድ ነገር ዓይቶ የመቀየር ችሎታ እንደነበረኝ ለመግለጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እየነገሩኝ ካለው ነገር መገመት የሚቻለው አክሰስ ሪል ስቴትን ሲመሠርቱ በውጭ አገር ሲሠሩ እንደነበሩባቸው ተቋማት ውጤታማ ለማድረግ ቢሆንም፣ ከመጓጓት የተነሳ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ መፈጸም የማይችሉትን ሥራ ጀምረዋል ማለት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- አክሰስ ሪል ስቴት በተጀመረበት ሁኔታ የተሳካ ሥራ መሥራት ይቻል ነበር፡፡ ሥራውን ያደናቀፈው ተራ ነገር ነው፡፡ ባልታሰበና በድንገት ‹‹ግንባታ አቁሙ›› ባይባል ኖሮ ሥራው ቀጥ ብሎ ይሠራ ነበር፡፡ ውጤታማም እንሆን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ሲነገር የነበረው አቶ ኤርሚያስ ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ ስላላቸው ሕዝቡን በማሳመን ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ከፍተኛ ገንዘብ የሰበሰቡ ቢሆንም፣ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ባለመቻላቸው በተለይ ለቤት ገዢዎች የገቡትን ቃል ባለማክበራቸውና ለሕዝቡ የሚመልሱት ገንዘብ በእጃቸው ላይ ስላልነበር ከአገር ስለመውጣታቸው ነው፡፡ እርስዎ ደግሞ የሚሉት ተገድጄ ግንባታ እንዳቆም በመደረጉ ነው ይላሉ፡፡ እውነቱ የትኛው ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- እውነቱ ከላይ የነገርኩህ ነው፡፡ እንዳልከው ብዙ ብዙ ነገር ተብሏል፡፡ ሁሉም ትንበያ እውነታ አይደለም፡፡ እንደተባለው ቢሆን ኖሮ ለምን ልመለስ ብዬ ጠየቅኩኝ? ሌላው ደስ ያለኝ ነገር ጊዜ ቢፈጅም ድርጅቱን የመንግሥት ኦዲተር ኦዲት እንዲያደርገው ተደርጎ ዝርዝር ውጤቱን ባላየውም ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ ኦዲት መደረጉ ጥቅሙ ምንድነው፣ ገንዘቡን አጠፋው፣ ንብረቱን ወዲህ ወዲያ አደረገውና ሌሎች ከአሉባልታ የማይዘሉ ነገሮችን ይዘጋቸዋል፡፡ ሕዝቡም እውነቱን ይረዳዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቤት ገዢዎች ከማኅበሩ ጋር በገቡት ውል መሠረት ቤታቸውን መረከብ ባለመቻላቸው እርስዎን እስከ ማሳሰር ደርሰዋል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ከአገር እንደወጡ ተሰማ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ድርድር በተለይ በጻፏቸው በቂ ስንቅ የሌላቸው ቼኮች ምክንያት እንዳይታሰሩ ዋስትና (ኢሚዩኒቲ) እንዲሰጥዎ ጠይቀው በቀድሞው ፍትሕ ሚኒስትር የተፈረመ ዋስትና አግኝተው ተመልሰው መጥተዋል፡፡ ከውጭ እንደተመለሱ በሰጡት መግለጫ፣ በአክሰስ ሪል ስቴት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ማግኘት እንደሚችል፣  ቤት ገዢዎች ቤቱን የማይፈልጉ ከሆነ በገቡት ውል መሠረት ገንዘባቸውን መውሰድ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር፡፡ ነገር ግን እርስዎ የገቡት ቃል ሳይፈጸም እርስዎም በመንግሥት የተገባልዎት ዋስትና ታልፎ ታስረው ነበር፡፡ አሁንም ያሉት በዋስትና ነው፡፡ ምክንያቱ ምን ነበር?

አቶ ኤርሚያስ፡- እሺ፡፡ ዋናው ሕዝብ መስማት የሚፈልገው ጥያቄ ይህንን ነው፡፡ አንድ  መታወቅ ያለበት ነገር፣ ማንም የሚያውቀኝም ሰው ቢሆን መገመት የሚችለው ከመንግሥት ጋር ተነጋግሬ ወደ ኢትዮጵያ መመለሴ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ነው፡፡ የሚፈራው ነገር እንደሌለና የሚደብቀው ነገር ስለሌለው ነው እንደሚባል እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔ የምፈራው ነገር ቢኖር፣ የፈጸምኩት ወንጀልና በደል ቢኖር፣ የሰው ገንዘብ አጥፍቼና ተጠቅሜበት ቢሆን ኖሮ ወይም መክፈል እንደማልችል ባውቅ ኖሮ ዎልስትሪት ኢንቨስትመንት ባንክ ገብቼ ባልሠራም (ቀደም ብለው ሠርተውበታል) ጥገኝነት ጠይቄ መኖር አያቅተኝም ነበር፡፡ እኔ ግን ገና ከአገር እንደወጣሁ ነው መንግሥትን ደብዳቤ በመጻፍ መመለስ እንደምፈልግ የጠየቅኩት፡፡ ምክንያቱም የፈጸምኩት ነገር እንደ ወንጀል የሚታይ እንዳልሆነ ውስጤ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ሪል ስቴቱ ትልቅ ሀብት እንዳለውና ቤት ገዢውም ቤቱን ማግኘት እንደሚችልም ስለማውቅ ነው፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ ሙሉ አቅሙም ነበረኝ፡፡ መንግሥት በዚህ ችግር ውስጥ የገባው 2,000 ሕዝብ ስለተንጫጫ እንጂ የወንጀል ተግባር ተፈጽሟል የሚል እምነት ኖሮት አይደለም፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ከጥንስስ እስከዚህ ያደረስኩት ውስብስብ የሚመስለውን ችግር መፍታት ያለብኝም እኔ መሆኔን ስላመነበትም ነው፡፡ ደግሞም ዝም ብሎ ሳይሆን፣ እኔ በጻፍኩት ደብዳቤ መሠረት ሁሉን ነገር ዓይቶና መርምሮ ችግር እንደሌለብኝ ስላመነ ነው ዋስትና ሰጥቶኝ የተመለስኩት፡፡ ከተመለስኩ በኋላ ከመንግሥት ጋር ቁጭ ብዬ ተነጋገርኩኝ፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ስለነበር በወቅቱ፣ ከነበሩት ሚኒስትርና ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተወያየን፡፡ በተመለስኩ በአንድ ወር ውስጥ በተለይ ተጀምረው የተቋረጡትን መገናኛ ኒያላ ሞተርስ አጠገብ የሚገኘውን ሳይትና በሲኤምሲና በአያት ያሉትን ሳይቶች በማስጀመር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጡን ማሳየትትና ጨርሶ ማስረከብ ነበር፡፡ ይህንን ሥራ ለማከናወን ደግሞ ከኮንትራክተሩ ጋር ተነጋግሬ የጨረስኩት ወደ አገር ቤት ከመመለሴ በፊት ዱባይ ነበር፡፡ ወደ አገር ቤት ተመልሼ ከመንግሥት ጋር ከተወያየሁ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት ከኮንትራክተሩ ጋር ለመፈራረም እንቅስቃሴ ስጀምር፣ ቦርዱ በድንገት ተነስቶ ፊርማ መፈራረም ያለበት የሪል ስቴቱ ወይም የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ነው አለ፡፡

ሥራ አስኪያጅ የተባለው ሰው እኔ ቀደም ብዬ ያስቀመጥኩት ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው እንዲፈርም ቦርዱ ሲወስን ችግር የለም ይፈርም ብዬ ተስማማሁ፡፡ ግለሰቡ የጥበቃ ሠራተኞችን የሚያሰማራ ድርጅት ያለው በመሆኑና ለአክሰስ ሪል ስቴትም የጥበቃ ሠራተኞችን የሚያቀርብ መሆኑን ገልጾ፣ ‹‹የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር ማኅበሩ የኮንስትራክሽን ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ያልተከፈለኝ 22 ሚሊዮን ብር ስላለኝ በቅድሚያ ይከፈለኝ›› አለ፡፡ እኔ በወቅቱ ግራ ገባኝ፡፡ እንዴት ይህንን ያህል ገንዘብ ሊኖርብን ይችላል ብዬ ሒሳብ ክፍሎችን ባነጋግርም የተወሰነ ገንዘብ ሊኖር ቢችልም፣ ይህንን ያህል የተጋነነ ገንዘብ ሊኖር እንደማይችል ገለጹልኝ፡፡ ነገር ግን ነገሮችን ሳጣራ ግለሰቡ ያላሰማራቸውን በወር 540 ሰዎች እንዳሰማራ አስመስሎ ሲያስፈርም እንደነበር ደረስኩበት፡፡ ይህንን ለቦርዱ ሪፖርት አደረግኩኝ፡፡ ነገር ግን ቦርዱ ሰውየው ያቀረበውን ሰነድ ፈርሞና አጽድቆ ክፍያው ላይ ተደራደር አለኝ፡፡ እንዴት ይሆናል ብዬ ብከራከርም ምላሽ የሚሰጠኝ አጣሁ፡፡ ግለሰቡም የቦርዱን ድጋፍ በማግኘቱ ግንባታውን ማስጀመር የሚችለውን ፊርማ አልፈርምም አለ፡፡ የሚሰማኝ ሳጣ ያለውን ነገር ዘርዝሬና ማስረጃውን አባሪ አድርጌ ለቴክኒክ ኮሚቴው በደብዳቤ አሳወቅኩኝ፡፡ የሚገርመው ነገር ቦርዱ ‹‹አቶ ኤርሚያስ የመክሰስ መብት የለውም›› ብሎ ለግለሰቡ ተከራከረለት፡፡ ቦርዱ ሰባት አባላት አሉት፡፡ በወቅቱ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው አምስቱ ተማክረው እኔን ከቦርድ ሰብሳቢነት አወረዱኝ፡፡ በዚህ ጊዜ በቦርዱ ላይ ግልጽ ችግር እንዳለ ገባኝ፡፡ ቦርዱ ቀጠለና የድርጀቱን ሰነድ እንዳላይ ከለከለኝ፡፡ በመቀጠልም ወደ ድርጅቱ እንዳልገባ ዕግድ ጣለብኝ፡፡ ሁሉም ነገር በማስረጃ የተደገፈና መንግሥት የሚያውቀው ነው፡፡ ቦርዱና ሥራ አስኪያጁ እጅና ጓንት ሆነው ድርጅቱን ተቆጣጠሩት፡፡ የሚያሳዝነው ግን ቤት ገዢው ይህንን ሁሉ ድራማ አያውቅም፡፡ ቤት ገዢው ስድስት አባላት ያሉት ዓብይ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡  ሦስቱ ቤት ገዢ ሲሆኑ ሦስቱ ቤት የገዙ አይደሉም፡፡ ተወካዮች ናቸው፡፡ ዋናው የኮሚቴው ሰብሳቢና ነገሮቹን ሆን ብሎ በማምታታት፣ የሆነ ያልሆነውን ለቤት ገዥው በመንገር ውዥንብር የፈጠረው ግለሰብ ወኪል እንጂ ቤት ገዢ አይደለም፡፡ ደመወዝ ስለሚከፈለውና መኪና ስለተሰጠው ማንኛውንም ነገር ማለቴ ቤት ገዢዎችንና እኔን የማያስማማ ነገር ለመፍጠር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ በመሆኑም መሬቱን እንረከብና ቤቱን እንገንባ የሚል እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ እኔ ግን እዚህ አገር ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት አድርጎ ከሚሠራ ድርጅት ጋር ተነጋግሬ ጨርሼ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቱን ገንብቶ ሊያስረክብ ወይም ገንዘቡን ለሚፈልግ ከነወለዱ ሊከፍልና አክሲዮን መሸጥ የሚፈልግም ካለ አትርፎ ሊገዛ የሚችል ድርጅት ነበር፡፡ ያ ድርጅት አሁንም አለ፡፡ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ሊከፍልና ወደ ሥራ ሊገባ ተስማምተን ያስፈረምኩትን ሰነድ ሁሉ ለቦርዱ አቅርቤለት ነበር፡፡ ነገር ግን ሊስማሙና ሊፈርሙ አልቻሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ጋር የተፈራረመው የውጭ ኩባንያ ማንና የየት አገር ድርጅት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ትልቅ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በትልልቅ የኮንስትራክሽን ዘርፎች የተሰማራ ታዋቂ ኩባንያ ነው፡፡ ቦርዱ ተረጋጋቶ እንዲያጤነው ሳስረዳ፣ ‹‹ይህ ነገር ውስብስብ ፋይናንስ ስለሆነ፣ ያቀረበው ነገር ጥሩ ይሁን አይሁን መገመት ስለማንችልና ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ይህንን መንግሥት ይወስንበት›› አሉ፡፡ ነገር ግን ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ሳይሆን ተንኮል ነው፡፡ መንግሥት ብዙ ሥራ አለበት፡፡ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ገብቶ ‹‹ይህንን ፋይናንስ አድርግ፡፡ ይህንን አታድርግ›› ሊል እንደማይችልም ያውቁታል፡፡ ሆን ብለው ነገሩን ለማወሳሰብና እነሱ የጀመሩት ሴራ እንዳይጋለጥ የሚያደርጉት አካሄድ በመሆኑ፣ ሁሉንም ነገር ገልጬ ለመንግሥት (ቴክኒክ ኮሚቴው) በቃለ ጉባዔ አስረድቻለሁ፡፡ መንግሥት የሰጠኝ መልስ ግን ‹‹መንግሥት በግል ድርጅት አሠራር ውስጥ ገብቶ ሊወስን አይችልም፡፡ ማድረግ የሚችለው የድርጅቱ ንብረት (መሬት) እንዳይወሰድ ማድረግና ድርጅቱ እንዳይበተን ማድረግ ነው፤›› የሚል ነው፡፡ ቦርዱ ‹‹አልገባኝም›› ያለውን ነገር በመሀል ገብቶ ይኼንን አድርግ ሊለው አይችልም፡፡ ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት እኔ ከመንግሥት ጋር ተነጋግሬ ስመለስ፣ እንደዚህ ዓይነት ችግር ቢገጥመኝ በራሴ መፍትሔ እንዳለኝ ተናግሬ ነበር የመጣሁት፡፡ ቦርዱ ካስቸገረ የባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶና ያለውን ችግር በማስረዳት አዲስ ቦርድ እንዲመርጥ ማድረግ ነበር፡፡ በንግድ ሕጉ መሠረት በአክሲዮን ማኅበር ውስጥ አሥር በመቶ ድርሻ የያዙ ባለድርሻዎች፣ በማንኛውም ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ማስጠራት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ለእኔ  ውክልና የሰጡኝን ሰዎችና ድርጅቶች ጨምሮ 23 በመቶ ድርሻ አለኝ፡፡ ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ እንድናደርግና አዲስ ቦርድ በመሰየምና ሥራ አስኪያጅ በመለወጥ ወደ ሥራ እንድንገባ በደብዳቤ ስጠይቅ፣ መንግሥት ያቋቋመውና በንግድ ሚኒስቴር አንድ ኃላፊ የሚመራው ቴክኒክ ኮሚቴ የሰጠኝ ምላሽ ‹‹ስብሰባ መጥራቱ ይቆይ፡፡ ተግባብታችሁ ሥሩ፡፡ ችግሩን እንፈታዋለን፤›› የሚል ነው፡፡ ሰብሳቢው ይኼንን መልስ የሚሰጡት ከሚኒስትሮቹ ጋር ተመካክረው ይሁን ወይም በግላቸው አላውቅም፡፡ በተደጋጋሚ ስጠይቃቸው ምላሽ የሚሰጡኝ ግን በቃላቸው ነው፡፡ እኔ ግን የጠየቅኳቸው በደብዳቤ ነው፡፡ በግልባጭ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች አሳውቄያለሁ፡፡ ቦርዱ ግን የሚያየው በመሬቶቹ ላይ ያለውን ትርፍ በመሆኑ፣ ቦታው ከተሰጠው በተወሰኑት ቦታዎች ላይ ለቤት ገዢዎች ግንባታ በማድረግ ቀሪውን ለመውሰድ በመሆኑ ችግሮቹን ከመፍታት ይልቅ እየተባባሰ እንዲሄድ አደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ያቀዱትን ሥራ እንዳያከናውኑ ያደረገዎት ቴክኒክና ዓብይ ኮሚቴው ነው ማለት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ትክክል፡፡ በዋናነት የችግሩ ምክንያት የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢና የተወሰኑ እንደ ሥራና ገቢ ምንጭ የያዙት የዓቢይ ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡ ሌላው ነገሩን ሁሉ ውኃ የደፉበት ቦርዱና ሥራ አስኪያጁ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለአክሰስ ሪል ስቴት ትልቅ እንቅፋት የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም ነገር እኔ ነኝ የማውቀው በማለት ፈላጭ ቆራጭ ይሆናሉ፡፡ ሁሉንም ነገር የሚያሽከረክሩት እሳቸው ናቸው የሚሉ አሉ እኮ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ትክክል፡፡ ይኼንን ነገር እኔም ሰምቼዋለሁ፡፡ ፈላጭ ቆራጭ ነው፡፡ እሱ ያለው ካልሆነ ሰው ያለውን አይሰማም፡፡ ግትር ነው እንደሚባል ሰዎች ነግረውኛል፡፡ እኔ የማደርገው የተለየ ነገር የለም፡፡ የምመራው ድርጅት እስከሆነ ድረስ ስለምሠራው ሥራ አስረዳለሁ፡፡ ሲያምኑበት አቅጣጫ አስይዛለሁ፡፡ ማሳመን ፈላጭ ቆራጭ መሆን አይደለም፡፡ ለተንኮል ሲነሱ ሴራ ጠንስሰው ከቦርድ አነሱኝ፡፡ እውነት እኔ የእነሱን ፈቃድ ጥሼ፣ እነሱን ደብቄ እንቅስቃሴ ባደርግ እኮ ሁለት አማራጭ አላቸው፡፡ እኔን ከኃላፊነት ማውረድ ወይም እነሱ ጥለው መሄድ፡፡ ነገር ግን በቦርድ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምንም አይሉም ነበር፡፡ ብዙ የሚያወራው ውጭ ያለው ሰው ነው፡፡ እኔ እያለሁ ችግር አልነበረም፡፡ እኔ ከአገር ስወጣ ግን ክፍተት ተፈጠረ፡፡ በዚህ ክፍተት ውስጥ የቤት ገዢ ዓብይ ኮሚቴ የሚባል ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ ኮሚቴ ገባ፡፡ ምንም የማያውቅ አዲስ ቦርድ እንዲመረጥ በማድረግ እነሱ (ኮሚቴው) የሚላቸውንና የሚፈልጋቸውን መሥራት ጀመሩ፡፡ ከመንግሥትና ከቤት ገዥዎች የተውጣጣ ጥምር የቴክኒክ ኮሚቴ ሲቋቋም ከላይ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እየተከታተለው፣ የንግድ ሚኒስቴር ተወካይ የቴክኒክ ኮሚቴውን መምራት ጀመሩ፡፡ መንግሥት አምኖበት ችግሩ መፍትሔ እንደሚያገኝ በማረጋገገጥ ዋስትና ሰጥቶኝ ከመጣሁ በኋላ፣ የተፈጠሩ ችግሮችን ከሥር ከሥር አንድም ሳይቀር ሪፖርት ሳደርግ ጣልቃ ገብቶ ማስቆም ነበረበት፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ ‹‹ቆይ እኛ እንፈታዋለን፤››  እያሉ ጊዜ ወሰዱ፡፡ ነገሮች ሕገወጥ በሆኑ የቤት ገዢ ዓብይ ኮሚቴ ነን ባዮች እየተበላሹ መሆኑን በተደጋጋሚ ባሳውቅም ምላሽ የሚሰጠኝ ጠፋ፡፡ በጣም የሚያሳዝነውና የሚገርመው ነገር እኔ በየቀኑ እያንዳንዱን ነገር በደብዳቤ ሳሳውቃቸው ‹‹ቆይ እኛ እንፈታዋለን፣ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል፣ ይስተካከላል፣ ተረጋጋ፣ ቀላል ነው. . .›› ሲሉኝ የቆዩት የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢው የመንግሥት ተወካይ፣ ‹‹ኤርሚያስ ነባሮቹን ሊፈታቸው አልቻለም፡፡ መሬቶቹ ለቤት ገዢዎቹ ይሰጡ፤›› የሚል አቋም ያዙ፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር እኚሁ ሰብሳቢ እኔ ከመታሰሬ አንድ ወር በፊት ‹‹ኤርሚያስ ይታሰራል፤›› የሚል ወሬ ሲያስወሩ እንደነበር እሰማው የነበረውን ነገር እንዳስታውስና ከበስተጀርባዬ የሆነ ነገር ይሠሩ እንደነበር ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ዋስትና የሰጠዎት መንግሥት ነው፡፡ የተመለሱት ደግሞ የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ከሕዝብ ጋር የገቡትን ውል ለመፈጸም ነው፡፡ የመጡባቸው ሥራዎች በቴክኒክ  ኮሚቴ ሰብሳቢው ጭምር ሲደናቀፍ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል (ሚኒስትሮች) ለምን አላሳወቁም?

አቶ ኤርሚያስ፡- እያንዳንዱን ነገር ገልጬ ለቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በደብዳቤ ስገልጽ፣ ለሚመለከታቸው ሁሉ በግልባጭ አሳውቄያለሁ፡፡ መስማት ለማይፈልግ ሰው ምንም አታስረዳውም፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢም ያደረጉት ያንን ነው፡፡ እኔ በየቀኑ በደብዳቤ የምገልጽላቸውን ዝም ብለው ይዘው ከርመው ‹‹ችግሩን ኤርሚያስ ስለማይፈታው መሬት ለቤት ገዢዎች ይሰጥ›› የሚል ሪፖርት አቀረቡ፡፡ በመቀጠልም ጠቅላላ ጉባዔ ይደረግ የሚል ጥሪ አቀረቡ፡፡ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ በደንብ አስረድቼ የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት ተረዱኝ፡፡ ይዤ የተመለስኩትን ሐሳብም ተቀበሉት፡፡ በዕለቱ ቤት ገዢዎችን ሰብስበን ጠዋት ላይ ለቦርዱ ያቀረብኩት ከሰዓት በኋላ ለማስረዳት በስብሰባው ላይ ተገኘሁኝ፡፡ ነገር ግን የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ መድረኩን ሲከፍቱ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተስማማንበትን ወደ ጎን በመተው ‹‹የአቶ ኤርሚያስ መፍትሔ ስላልሠራ ወደ ሌላ መፍትሔ እንሄዳለን›› የሚል ንግግር ተናገሩ፡፡ የሚገርመው ነገር የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢና የቤት ገዢዎች አሰባሳቢ ዓብይ ኮሚቴ አስበውበትና በደንብ ተደራጅተው ወደ ስብሰባው ስለገቡ እየተነሱ እኔንም መንግሥትንም መሳደብ ጀመሩ፡፡ እውነት ለመናገር በዕለቱ ቅንብሩ፣ የመድረኩ አከፋፈት፣ ቦታ ቦታ የያዙና ተልዕኮ የተሰጣቸው ሰዎች የሚናገሩትን ስመለከት በልዩ ጥናት የተሠራ ፊልም ነው የመሰለኝ፡፡ አንድ ጊዜ እንኳን ለመናገር ዕድል አልተሰጠኝም፡፡ በዕለቱ የነበሩት ሚኒስትሮች ጭምር ያልገመቱትና ያልጠበቁት ነገር በመከሰቱ ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ ሌላ ችግር እንደሚፈጠር የገባቸው ባለሥልጣናቱ እኔን የፀጥታ ሰዎች ይዘውኝ እንዲሄዱ አደረጉ፡፡ በአጭሩ ታሰርኩኝ፡፡ አራት ወራት ማዕከላዊ ታስሬ ተፈታሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ችግሩን መፍታት ቢችሉ አራት ዓመታት ምን ሲሠሩ ነበር? እኔ የተለያዩ መፍትሔዎች ይዤ ስቀርብ አንፈልግም ይላሉ፡፡ ምንድነው የሚፈልጉት? ቤት ገዢዎች የሚፈልጉት ቤት እንጂ የማኀበሩ ባለድርሻዎችን ውጣ ውረድ አይፈልጉም፡፡ ኮሚቴዎቹ ግን ቤት ገዢዎችን ወክለናል በማለት ለሥራ ማስኬጃ እያሉ ከቤት ገዢዎች ከእያንዳንዳቸው 5,000 ብር በድምሩ አምስት ሚሊዮን ብር ተቀብለው ነገሮችን በማምታታት የእኔ መፍትሔ እንዳይተገበር በሮች ያዘጋሉ፡፡ የእነሱ ዋና ዓላማ የነበረው ‹‹ማኅበሩ ከስሯል፣ ሊቀጥል አይችልም፤›› በማለት ለመዝጋት ነበር፡፡ ድርጅቱ ከተዘጋ ደግሞ እነሱ ከተጠያቂነት ይድናሉ፡፡ ይኼ ነው ሐሳባቸው፡፡ ግን አይሆንም፡፡ ይዋል ይደር እንጂ እውነታው ይወጣል፡፡ ማንም ከተጠያቂነት አይድንም፡፡

ሪፖርተር፡- አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር በመንግሥት ትዕዛዝ ኦዲት ተደርጓል፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ውጤቱን አላየሁትም፡፡ ግን ኦዲት ተደርጎ ተጠናቋል፡፡ ድርጅቱ ትልቅ ሀብት አለው፡፡ እንደ ድርጅት ጥሩ አመራር ቢያገኝ መቀጠል ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከፍተኛ የአመራር ችግር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ማኅበሩ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የሚያውቁት  ነገር አለ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ማንንም አነጋግሬም አላውቅም፡፡ በአካባቢውም ደርሼ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ሪል ስቴቱን በሚመለከት ከመንግሥት ጋር የተነጋገሩት ወይም ሌላ የሚያስቡት የመፍትሔ አቅጣጫ አለ?

አቶ ኤርሚያስ፡- አዎ አለኝ፡፡ መቼም ቢሆን ከመጠየቅ አላቆምም አላቆምኩም፡፡ ለምሳሌ በቅርብ የአክሰስ ካፒታል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ባለድርሻዎችን በንግድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጠርቻቸው ተሰባስበን ነበር፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ካደረግን አምስት ዓመታት ሆኖን ነበር፡፡ ያለውን ነገር ሁሉ አስረድቼና ተማምነን አዲስ ቦርድ እንዲመርጥ አድርገናል፡፡ ስለተማመኑብኝ እኔን ቦርድ ሰብሳቢ በማድረግና በጎደሉ የቦርድ አባላት ምትክ ሌሎች ሁለት ሰዎች ተጨማሪ በመሾም፣ በቀጣይ እንዴት መሥራት እንዳለብን ተስማምተን ተለያየን፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበርንም የጠየቅሁት፣ ይህንን ዕድል እንዲሰጡኝና ያሉትን ችግሮች ላስተካክል የሚል ነው፡፡ ባለድርሻዎቹ ተሰብስበው ቢሰሙኝ አዲስ ቦርድ ይመረጣል፡፡ ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ አሁን ግን መንግሥትም እጁን ስላስገባና ኦዲት እንዲደረግ በማድረጉ ውጤቱን ይፋ አድርጎ ቀጥል እስከሚለኝ እየጠበቅኩኝ ነው፡፡ ቀደም ብለው ተመድበው የነበሩ የመንግሥት ተወካዮች መፍትሔ ያመጣሉ እንጂ አፍራሽ ይሆናሉ የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ ላይ የመንግሥት አቋም ምንድነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- የመንግሥት አቅጣጫና አቋም አንድ ብቻ ነው፡፡ ቤት ገዢዎች ቤታቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ በተደጋጋሚ የተለያዩ ደብዳቤዎች እያስገባሁ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ እኔም ባለመናገሬ ማለትም ሕዝቡ በመገናኛ ብዙኃን መረጃ እንዲደርሰው አላደረግኩም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የቴክኒክ ኮሚቴውና ዓብይ ኮሚቴው በጋራ ሆነው ‹‹ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳትሰጥ›› አሉኝ፡፡ ሁሉም ነገር ሲያልቅ ከእነሱ ጋር በጋራ እንደሚሰጥ ነግረው አስጠነቀቁኝ፡፡ እኔም መንግሥት በወኪሉ በኩል አትናገር ብሎኛል ብዬ ያለኝን ዕቅድ በጽሑፍ አስገባሁ፡፡ ጥሩ ነው ስለተባልኩኝ ዝም ብዬ በመጠበቅ ላይ እያለሁ መጨረሻዬ እስር ቤት መግባት ሆነ፡፡ ለአክሰስ ሪል ስቴት በዋናነት ተጠያቂዎቹ ቦርዱ፣ ዓብይ ኮሚቴው፣ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢና ሥራ አስኪያጁ ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ቤት ገዢዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር ያለውን ድራማ አያውቁም፡፡ ማወቅም የለባቸውም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ቤት ማግኘት ብቻ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን እኔን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ማኅበሩን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ ቡድን አለ፡፡ ‹‹መሬቱን ስጡንና ሠርተን እናስረክባችሁ፤›› እያለ ቤት ገዢዎችን የሚማፀን ቡድን አለ፡፡ ነገር ግን የሚሳካላቸው አይመስለኝም፡፡ አሁን ግን በግሌ ‹‹ኤርሚያስ አመልጋ›› በሚል ደብዳቤ ለመንግሥት እየጻፍኩ ያሉኝን ሦስት አማራጮች እያሳወኩኝ ነው፡፡ አንድ የአውሮፓና አንድ ቻይና ድርጅቶች ከማኅበሩ ድርሻ በመግዛት ቤቱን ሊገነቡ እንደሚችሉ አስረድቻለሁ፡፡ ሌላው ከቤት ገዢዎችም ሆነ ከውጭ ኢንቨስተር አምስት ሳንቲም ሳንጠይቅ ሥራውን አስጀምሬና ጽሕፈት ቤቱን ከፍቼ ሥራውን ለማከናወን ሁኔታዎችን ማመቻቸቴንም አሳውቄያለሁ፡፡ አሁን በሚሊዮን ብር የምናወራለት አክሰስ ሪል ስቴት ሲጀምር የነበረው ካፒታል 34 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ከተሠራ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ በብልጠት ሳይሆን ድርጅቱ ትልቅ ሀብት አለው፡፡ ሀብት ይዞ መሥራት አልቻልኩም ማለት ሥራ አታውቅም ማለት ነው፡፡ ተራራ የሚመስለው ነገር በጣም ቀላልና ሊፈታ የሚችል ነው፡፡ አሜሪካ በቅርቡ እንኳን ሪል ስቴት ላይ ምን ያህል ኪሳራ እንደደረሰ ታይቷል፡፡ አንድ ድርጅት ከከሰረ ከሰረ ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን ሌብነት ወይም ማጭበርበር አይደለም፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት ግን ከዚህ ሁሉ ውጪ ነው፡፡ ሀብት አለው አልከሰረም፡፡ እንኳን ሳይከስርም ቢከስር ምንም ማለት አይደለም፡፡ ሰው የሚማረው ከውድቀት ነው፡፡ በንግድ ዓለም ሳይከስር የሚቀጥል በመሰለኝ የሚኖር ሰው ብቻ ነው፡፡ በማኅበሩ ላይ ምንም የተጭበረበረ ነገር የለም፡፡ ለአክሰስ ሪል ስቴት የማቀርበው የመፍትሔ ሐሳብ ለሌላ ዓላማ ውሎ ነው እንጂ ተግባራዊ ቢደረግ ይኼ ሁሉ ችግር በቀላሉ ይፈታ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ሀብት የሚሉት የገዙትን መሬት ነው፡፡ መሬት ደግሞ የሕዝብና የመንግሥት ስለሆነ አይሸጥም አይለወጥም፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ልክ ነው የሊዝ መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ንብረት ያለባቸው ናቸው፡፡ እነሱን ደግሞ የመሸጥ መብት አለን፡፡ የምንሸጠው ቤት ነው፡፡ ትልቁ ችግር በተለይ ቤት ገዢው መረጃ የለውም፡፡ እኔም አትናገር ስለተባልኩ ዝም ማለቴ ለአጀንዳ ጠላፊዎች ተመችቷቸዋል፡፡ የሆነ ያልሆነውን ወዲያ ወዲህ በማለት መንግሥትንና ሕዝብ ለማለያየት የሚሯሯጡ ዋጋቸውን ካላገኙ፣ በእኛ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ነገ ጠዋት በሌሎች ላይ የማይደርስበት ምክንያት የለም፡፡ የእኔ ዓላማ ስሜ የጠፋበትን ፕሮጀክት አስተካክዬ ማሳየትና ለቤት ገዢዎች በገቡት ውል መሠረት ቤታቸውን ሠርቼ ማስረከብ ነው፡፡ የሌላው ዓላማ ሌላ ሆነና ችግሩ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ አጀንዳው ሌላ መስመር እንዲይዝ ያደረጉት የቤት ገዢዎች ዓብይ ኮሚቴና መንግሥት በሰፊው የተሳተፈበት ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሠሩትን መንግሥት ተመልክቶ መፍትሔ ይሰጠኛል የሚል እምነት ይዤ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy