Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለፅንፈኞች አሉባልታ ላለመጋለጥ!

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለፅንፈኞች አሉባልታ ላለመጋለጥ!

                                                       ዘአማን በላይ

የፅንፈኞች ሴራ ብዙ ነው። ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። እነዚህ ሃይሎች የጥበትና የትምክህት ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንዲሁም የአንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎችን ተልዕኮ በመቀበል እዚህ ሀገር ውስጥ ስላለው ሁኔታ የማያስወሩት ነገር የለም። ተጨባጭ ሁኔታውን በመካድ ኢትዮጵያ ሰላም የራቃት ሀገር አስመስለው በማቅረብ የሚያናፍሱት አለሉባልታ የትየለሌ ነው። ሆኖም ለእንዲህ ዓይነቱን የ“በሬ ወለደ” ድርሰት ቦታ መስጠት አይገባም። ለተራ ወሬም ራስን ማጋለጥ ተገቢ መስሎ አይሰማኝም። በተለይም ወጣቱ ለእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ ምንም ቦታ መስጠት የለበትም።

እንደሚታወቀው እነዚህ ሃይሎች የሚሰነዘረው አሉባልታ ከአዋጁ መንፈስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል—የአዋጁ ዓላማ የሰላሙ ባለቤት ለሆነው ህዝብ ተጨማሪ ጉልበት ለመስጠት እንጂ፣ እነዚህ አካላት እንደሚሉት የህዝቡን የመንቀሳቀስ መብት ለመገደብ አይደለም። እርግጥ የእነዚህ አካላት ፍላጎት ለሀገራችን ከማሰብ የመነጨ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እንዲያውም ከመንግስትና ከህዝቡ በላይ ለዚህች ሀገር አሳቢ ሆነው በመቅረብ በተዘዋዋሪ አዋጁን ለማጥላላት የሚሰነዝሩት አባባል መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

ያም ሆኖ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እነርሱ ከሚሉት ጋር የሚጣረስ ነው። ይጋጫል። ይኸውም የአዋጁ ግብና ዓላማ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የፀጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ብሎም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ስለሆነ ነው። በተለይም አዋጁ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነት ዋነኛ ምክንያቶችን በመግታት፤ ሀገራችንና ህዝቦቿ ወደ ነበሩበት አስተማማኝ ሰላም እንዲመለሰሱ ያስቻለ ነው። ከመብት ግደባ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ጉዳይ የለም።

ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ‘የሰላም ተምሳሌት’ ተብላ ስትጠቀስ ኖራለች። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ አብረውን ለማደግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ።

ሆኖም ላለፈው አንድ ዓመት ያህል ሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው የመረጋጋት ችግር ወደ ነበርንበት የተረጋጋ ቦታችን ለመመለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ለስድስት ወራት ተግባራዊ ሆኗል። አሁንም በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቅ ጥልም እያሉ የሚስተዋሉ ችግሮች በመኖራቸው አዋጁ ለአራት ወራት እንዲራዘም የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ወስኖ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ይሁንና አዋጁ ላይ የሰፈሩት ጉዳዩች በሂደት እየታዩ እንዲነሱ ተደርጓል። እንዲያውም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ያለች ሀገር አትመስልም።

ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የአፍሪካን ኢኮኖሚ እንደምትመራ ተተንብዩዋል። ሀገሪቱ የውጭ ኢንቨስተሮችን እየሳበችም ነው። ይህም በህዝቡ ባለቤትነት እውን በሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት የተገኘ ነው።

ርግጥ ይህ ሰላም ላለፉት 26 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ እንደ ደንቡሽት ቤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈራርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው። ይህም ወደ ሀገራችን መምጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች አስተማማኝ ዋስትናን ይሰጣል።

ኢንቬስተሮችም በአዋጁ ዋስትናቸው በአስተማማኝ ሁኔታ እየተረጋገጠ ነው። በስራቸው ላይ የሚፈጥረውም ተፅዕኖም የለም፤ አይኖርምም። አዋጁ በእስካሁን ትግበራው ሰላምን ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ ኢንቬስተሮች መዋዕለ ነዋያቸውን ይበልጥ እንዲያፈሱ አድርጓቸዋል። ይህ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የዓለም ሀገራት ኢንቬስተሮችን ቀልብ መሳብ ችላለች።

የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ግን ይህን ሃቅ ለመመለከት ዓይናቸውን በመሃረብ ይሸፍናሉ። ሀገር ቤት ያለውን እውነታው በመካድም ጉዳዩን አጣሞ በማቅረብ አንዴ አዋጁ የዜጎችን መብት ይጥሳል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢንቨስትመንትን ይጎዳል በማለት አሉባልታ ያወራሉ።

ወጣቶች በባህሪያቸው ሁሉንም ነገር የማወቅ ፍላጎት አላቸው። ይህ ባህሪያቸውም ለጥበትና ትምክህት ሃይሎች አሉባልታ ሊያጋልጣቸው ይችላል። አሉባልታዎቹ ወጣቶቹን ወዳልተፈለገ ጉዳይ የሚመራቸው ነው። ይህ ደግሞ ስራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ ያደርጋቸዋል። ስራቸውን በአግባቡ ካልከወኑ ደግሞ እንደ ዜጋ በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፋቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ የራሳቸውን፣ የዜጎችንና የሀገርን ሁለንተናዊ ጥቅም የሚጎዳ ነው። የጥፋት ሃይሎቹ እኩይ ሴራ እዚህ ድረስ የዘለቀ በመሆኑ ወጣቶች ለእነዚህ ሃይሎች አሉባልታዎች በር መክፈት የለባቸውም።

ወጣቶች የእነዚህ የጥፋት ሃይሎች መንገድ የሰላም ሳይሆን የሁከት፣ የልማት ሳይሆን የድህነት፣ የነፃነት ሳይሆን የባርነት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ሳይሆን የፀረ-ዴሞክራሲያዊነት በመሆኑ ልንታገለውና አስተሳሰባቸውንም ልንኮንነው ይገባል። ይህን መፈፀምም በአሁኑ ወቅት ሀገራችን እያከናወነች ያለችውን ሁለተኛውን የልማት ዕቅድ በሁለንተናዊ መንገዱ እንዲሳካ ድጋፍ ማድረግ ብቻ አይደለም። የራስንና የሀገርን ጥቅም ማስከበርም ጭምር ነው።

ወጣቶች በፅንፈኝነት የሚታመሱት የጥበትና የትምክህት ሃይሎች የትላንት ገዥ መደቦች በህዝቦች ላይ የፈፀሙትን በደል ሁሉ የአንድ ብሔረሰብ አባላት እንደፈፀሙት አድርገው የጥላቻ መርዝ በመርጨት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂት ሲፈጥር ለማየት የሚሹ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠላቶች መሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል።

እነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች በተለያዩ ወቅቶች ‘እገሌ የተባለውን ብሔረሰብ አባል ከክልልህ አባረው ወይም አጥፋው’ በማለት የማያቋርጥ ስብከታቸውን ሲያሰሙ ነበር። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በሰፈነባትና ሁሉም ብሔር በእኩልነትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እየሆነ ባለባት ሀገር ውስጥ “የአንድ ብሔር የበላይነት አለ” በማለት የውሸት ዲስኩራቸውን ሲያሰሙም አድምጠናል። ዓለም ኢትዮጵያ በፈጣን የልማት ሂደት ውስጥ መሆኗም ሲመሰክር እነርሱ “ኢትዮጵያ ውስጥ ልማት የለም” እያሉ የሚለፍፉት። ሆኖም ሃቁን እዚህ ሀገር ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች በሚገባ ያውቁታል። እናም ለፅንፈኞች አሉባልታ አንዳችም ዓይነት ቦታ ሊሰጡ አይገባም። እንዲያውም ለእነርሱ አሉባልታ ባለመጋለጥ ለሌሎች ወጣቶችም ትምህርት መስጠት ይኖርባቸዋል እላለሁ።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy