Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መታደስ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም!

0 270

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መታደስ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም!

                                  ታዬ ከበደ

የተሃድሶ ወይም የህዳሴ ተግባር በአንድ ወቅት ተጀምሮ በዚያው የሚጠናቀቅ አይደለም። በተለይም ጉዳዩ ጥልቅ ተሃድሶ በሚሆንበት ወቅት ክንዋኔውን በአጭር ጊዜ ለመለካት የሚያስቸግር ይሆናል። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖረው ህዝብም ለተሃድሶ ተግባር ለመዘጋጀት፣ ተግባሩን ለመከወንና ከፍፃሜው ለማድረስ የሚወስደው ጊዜ ከፍ ያለ ነው።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለና ያለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች የተለያዩ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችን ጥለው ባለፉባት አገር ውስጥ ማንኛውም የለውጥ ሂደት አልጋ በአልጋ ሊሆን አይችልም። ይህ ሁኔታ ብቻውን የተሃድሶ ሂደት የአጭር ጊዜ ሳይሆን ለረጅም ወቅት የሚወጠን ስራ መሆኑን የሚያስረዳ ይመስለኛል።

ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት ያለፉ 15 ዓመታትን የተሃድሶ ጎዞን በሚገባ ገምግመዋል። በግምገማቸውም መላው የሀገራችን ህዝቦች በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተሰባስበው በገጠርና ከተማ በልማት፣ በዴሞክራሲና ሰላም አንፀባራቂ ድሎችን በማስመዘገብ የተሃድሶ መሰመሩን ህያው ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

እንደሚታወቀው የመጀመሪያው የተሃድሶ መስመር በገጠር ብቻ ሳይወሰን በጥቃቅና አነስተኛ ስትራቴጂ የከተማ ህዝብ ኑሮ ለመቀየር ተስፋ የሚሰጥ ለውጥ አስመዝግቧል። በዚህም ብዙ የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም በርካታ ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተግባራዊ ሆነዋል። እንዲሁም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይም በትምህርትና በጤና የዕድገቱን መሰረት ለመጣል የሚያስችል ስራም ተከናውኗል።

ያም ሆኖ ገዥው ፓርቲና መንግስት የነበሩትን ችግሮች ከመግለፅም አልተቆጠቡም። ሀገራችን እየተከተለች ባለችው ልማታዊና ዴሞክራሰያዊ መስመር በህዝቡ ተሳትፎ እነዚህ ድሎች ቢመዘገቡም፤ የተጀመረውን ለውጥ ወደ ኋላ የሚመልሱ፣ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የአመራር ጉድለት መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል። እነዚህ ችግሮች በህዝቡ ውስጥ ተስፋ ቆራጭነት እንዲያቆጠቁጥ ከማድረግ ባሻገር እስከ አመፅ የሚያደርስ ሁኔታን መፍጠራቸውንም አልካዱም። አያይዘውም የችግሮቹ መንስኤ ናቸው በማለትም ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገበው ድል የፈጠራቸው ተጨማሪ ፍላጎቶችን በአግባቡ መልስ መስጠት አለመቻሉ፣ በመጀመሪያው በተሃድሶው ወቅት የተለዩትና የሥርዓቱ አደጋዎች መሆናቸው በግልፅ የተቀመጡት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በፅናት በመመከት ከምንጩ ለማድረቅ የተከናወኑት ስራዎች አናሳ መሆናቸውን ለይቷል።

በተለይም የመንግስት ስልጣንን የግል ኑሮ ማደላደያ የማድረግ ፍላጎትና ተግባር መከሰቱ የችግሩ መንስኤ እንደነበር ተገልጿል። በዚህም ሳቢያ ገዥው ፓርቲና መንግስት በጥልቀት እንታደሳለን በማለት የተለያዩ ስራዎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን አከናውነዋል። ህዝቡን እስከ ታች ድረስ ወርደው በማወያየትም በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን በመገምገም ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ አድርገዋል። ይህ ተግባራቸውም ውጤትም የተገኘበት ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የሚያካሂደው ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝብ ጉያ ውስጥ ያደገ፣ የህዝቡን ጥያቄዎችን የሚያዳምጥና የመፍታት ባህልን ያዳበረ እንዲሁም የህዝብን ፍፁም የበላይነት ከመገንዘብ መንፈስ እንጂ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የተፈጠረውን ችግር ፈርቶ አይመስለኝም።

ለነገሩ ገዥው ፓርቲ የህዝብን አመኔታ ተቀብሎ ሀገሪቱን የማስተዳደር ኮንትራት የወሰደው ከህዝቡ በመሆኑ ህዝቡን ቢፈራው ምንም የሚደንቅ ነገር ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ህዝቡ የሰጠውን የኮንትራት ውል በፈለገው ጊዜ ሊነጥቀው ስለሚችል ነው።

ገዥው ፓርቲና መንግስት የሚከተሉት መስመር ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ነው። ሀገራችን በዚህ መስመር ስር ተጉዛ ላለፉት 15 ዓመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት አስመዝግባለች። ህዝቧም ከዕድገቱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ከተገኘው ዕድገት ጋር የተፈጠሩ ፍላጎቶችን በማርካት ረገድ የሚቀር ነገር ሊኖር ይችላል።

ያም ሆኖ ግን ይህ ዓለም የመሰከረለት ዕድገትና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ምሳሌ መሆን የቻለ ዕድገት እዚህ ሀገር ውስጥ ተመዝግቧል። ይህም በተለያዩ ወቅቶች የተካሄዱ የመታደስ ሂደቶች ውጤት መሆኑን መካድ አይቻልም።

እንደሚታወቀው በ1993 ዓ.ም ከተካሄደው ተሃድሶ ኢህአዴግ ውጤታማነትን አትርፏል። ይህ ውጤት ግን አሁንም በሂደት ሊጎለብቱ በሚችሉ ጉዳዩች ሳቢያ በብዙ ጥረቶች መታጀብ ይኖርበታል። ዛሬም እንደ ትናንቱ የመንግስት ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌና አስተሳሰብ ብሎም የህብረተሰቡን እርካታ ያለመፍጠር ችግር ብርቱ ችግር ሆነዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ገዥው ፓርቲ በጥልቅ ተሃድሶ መስመር የመጓዙ ትክክለኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም። እናም ከ15 ዓመት በኋላ ጥልቀት ባለው ሁኔታ እታደሳለሁ ማለቱ ከሂደት እንደሚማርና ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቅ ይመስለኛል።

ኢህአዴግ ዳግም በመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ ነው። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት “አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ” ዓይነት አይደለም።

መንግስት ከህዝቡ ጋር የሚያካሂዳቸው የውይይት መድረኮች ለዚህ ትግበራ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ መድረኮች መንግስትንና ህዝቡን በቀጥታ ፊት ለፊት የሚያገናኙ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ከዋነኛ ተዋናዩ ማግኘት የሚያስችሉ በመሆናቸው ለስር ነቀል አፈታቱ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ሆነዋል።

የችግሮቹን ትክክለኛ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ ለማወቅ፣ አውቆም ለመረዳትና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት መንግስት ወደ ታች ወደ ህብተሰቡ ውስጥ የሚያወርዳቸው መድረኮችም መጠናከር ያለባቸው ይመስለኛል። የውይይቶች መጠናከር ደግሞ የተጀመረውን የረጅም ጊዜ የመታደስ ንቅናቄ ከግቡ የሚያደርሱ ናቸው። ከተቃዋሚዎች ጋር የሚካሄዱት የውይይትና የድርድር ተግባሮችም የጥልቅ ተሃድሶው አካል ናቸው። እናም እነዚህም ውይይቶች ይበልጥ እየሰፉና ጥልቀት እየኖራቸው ሊሄዱ ይገባል።

ታዲያ ውይይቶቹና ድርድሮቹ ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የራስ ምታት ይሆናሉ። እናም ውይይቶቹንና ለውይይቶቹ መነሻ የሆነውን ጥልቅ ተሃድሶ በሁከት ሃይሎቹ አማካኝነት “አይሳካም” በማለት የሚነዛው አሉባልታ ብዙም የሚደንቅ አይሆንም። ያም ሆኖ የሁከት ኃይሎቹ በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ በመንዛት ውይይቶቹን ለማደናቀፍ ለመጣር ቢሞክሩም ህዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ለቅጥፈታቸው ቦታ አልሰጣቸውም።

በእኔ እምነት ገዥው ፓርቲ ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው ተሃድሶ በውጤት የሚታጀብ መሆኑን ማስረዳት የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ዕውነታም ለህዝቡ በጥልቅ ተሃድሶው ውይይትች ላይ በግልፅ መብራራት ያለበት ይመስለኛል። የሁከትና የትርምስ ኃይሎች የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ሃይሎች እንጂ ከየትኛውም ብሔርና ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑንም ህዝቡ አሁን ካለው ግንዛቤ በላይ ይበልጥ ማስረፅ ያስፈልጋል። መታደስ የአንድ ጀንበር ተግባር አለመሆኑንና ጥልቅ ተሃድሶው በዚህ ሳያቆም የሚቀጥል እንደሆነ ማስገንዘብም ያሻል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy