Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መወያየት መልካም ነው

1 540

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መወያየት መልካም ነው

 

ለመምህር ሓጎስ ኣረጋይ (PhD) የተሰጠ ጥቆማ

ተኮላ መኮንን

tekolamekonen@yahoo.com

በአዲሱ የሰላምታ አሰጣጥ ሰላም ነው? ልበልና ልጀምር። ቃሉን በጣም እወደዋለሁ። አንዳንዶቹ ባለፈው እንዳልኩት እግዚአብሔር ይመስገን፡ እንዳንል የተፈጠረ ቃል ነው ይላሉ። ለምን? ሲባሉ፣ ሰላም ነው? ሲባል መልሱ ሰላም ነው፡ ይሆናልና። እንዴው ለጥቆማ ያክል ሰላም ነው? ስትባሉ እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም ነገር ሰላም ነው ብላችሁ ከመለሳችሁ ችግሩ የሚፈታ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ሄጄ መጣሁ። ቆይታዬ ለትንሽ ቀናት ነበርና ሳልጠግበው ቀኑ አለቀብኝ። ባለፈው ሄጄ የነበረው በግርግሩ ወቅት ነበርና አሁን ሰላም ሰፍኖ ሳይ ከምንም በላይ ደስተኛ ሆንኩ። የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉ ለማየት እድል ገጥሞኛል። መወያየት መልካም ነውና ውይይት በመለመዱ ደስ ተሰኘሁ። ማንም ሰው ከተወያየ ለምንም ነገር መፍትሄ ማግኘት ይችላል ብዬ አምናለሁና። በምንም ነገር መካረር የሚመጣው ካለመደማመጥና ካለመነጋገር ነው ብዬ ስለማስብ እንደውይይት የሚያረካኝ ነገር የለም። ደጋግሜ እንዳልኩት የበሰለ ሰው ይወያያል እንጂ አይሰዳደብም። የሚሰዳደብ ሰው የአስተሳሰብ ድሃ የሆነ ብቻ ነው። የሚል አመለካከት ካደረብኝ ውሎ አደረ።

በአገር ቤት ቆይታህ ያበሳጨህ ነገር ነበር ወይ? ብላችሁ ብትጠይቁኝ አዎ ብዙ ነገር ነገር አለ ማለት እችላለሁ። ጥሩው ነገር ከመጥፎው ማየሉ ግን ተስፋዬን እንዳጎላው ደጋግሜ ልንገራችሁ። የብጫ ወረቀት ለማሳደስ የወሰደብኝ ጊዜ አንዱ ያናደደኝ ጉዳይ ነበር። ያንን በሚቀጥለው ጊዜ በሰፊው እገልጸዋለሁ። ለዛሬው በየድህረ ገጾች ላይ እየተጻፉ ያሉትን የተለመዱ መጣጥፎች እንድዳስስ ፍቀዱልኝ። ምንም ይሁን ምን አገራችን ላይ ያለውን ሁኔታ መቃወም አለብን የሚለውን ቡድን እንዳለ ልተውና፣ የመንግሥት ደጋፊ ነን ወደሚሉት ደገፍን የሚሉትን መንግሥት እየጎዱ ወዳሉት ተችዎች ፊቴን በማዞር የተሰማኝን ልግለጽ። ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ቡድን፣ ማንም ከየትም ብሔር ይሁን ሃገር ቤት ደግ ነገር አለ ብሎ ከተናገረ አንድም “ሆዳም” ካልሆነም “ጠባብ” ከባሰ ደግሞ “ጸረ ኢትዮጵያዊ” ነው ብለው በግለሰቦች ላይ ቃጭል ማንጠልጠል ይወዳሉና እነሱን ልቦና ይስጣቸው በማለት ልለፋቸው። እንደታዘብኩት ይህንን ስድብ ፈርቶ ወደ እነሱ ጎራ የተቀላቀለ በግል የማውቀው አርቆ አሳቢ ግለሰብ አላጋጠመኝም። በስድብ ሰውን ማናደድ ይቻል ካልሆነ በስተቀር ተጋዳይ ማድረግ ይቅርና ጓደኛም ማድረግ እንደማይቻል ግን የሕይወት ተመክሮ ያስረዳናል ብዬ አምናለሁ። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ጥበቃ ሹም ሆኑ ሲባል ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ አይደለም አፍሪካዊ ቢኖር አሁንም ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ክፍል አባል ብቻ ይመስለኛል። ታዲያ ዶክተሩ የተወዳደሩት በራሳቸው ስምና ችሎታ ሆኖ እያለ ድርጅት ወክለው የተወዳደሩ ይመስል ከአለው መንግሥት ጋር ተያይዞ የቀረበባቸው ክስ አሳዝኖኛል። እሳቸው በመመረጣቸው አፍሪካውያን ብሎም የኤርትራ መንግሥት ሳይቀር ባንድ በመሰለፍ ለአህጉሩ የተደረገ ትልቅ አስተዋጽኦ መሆኑን መቀበል አለብን ሲሉ እየሰማን ኢትዮጵያዊ ሆነን እንዴት እንቃወማለን? በሚመጣው ዓመት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ከአፍሪካ ቢቻል ከኢትዮጵያ ቢሆን ደስተኛ እንሆናለን እንጂ እንዴት ተከፊ እንሆናለን። በዚህ አጋጣሚ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምን እንኴን ደስ አለዎ እያልኩ የልጅነት ትዝታ ቀስቅሼ ደብረብርሃን ላንሳላቸውና ባይማሩበትም የኃይለማርያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትን ለማደስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለሆነ የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ልጠይቃቸው ነው።

ይህንን በዚህ ከቋጨን በኌላ በውጭ ያሉ የመንግሥት ደጋፊ የተባሉ ድህረ ገጾች ስለ ዶክተሩ መመረጥ የሰነዘሩትን ግን ሌላውን በተቃወምኩበት መንገድ ልቃወማቸው ተነሳሁ። ዶክተሩ የተመረጡት በትግራውያን ትግልነው ብሎ ማለት ከስተትም ስህተት ይሆናል እላለሁ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ያገለገሉትን ዶክተር፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን እንጂ የውልደት ሰፈራቸውን ማጉላቱ የሚሰጠው ጥቅምም አልታይ አለኝ። ከዚህ በፊት ሎንዶን ላይ የዶክትሬት ዲግሪ የተቀበሉትን የኢሕአዴግ አመራር አባል በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ውጤት ተመረቁ ተብሎ በዚሁ ድሕረ ገጽ ላይ የተለጠፈውን ጽሑፍም አስታወሰኝ። አባባሉን የተጻፈላቸው ዶክተርም እራሳቸው የሚቀበሉት እንደማይሆን በጊዜው ተናግሬ ነበር። በነገራችን ላይ ይህ እራስን ከመውደድ የመጣ አመለካከት ነው ብዬ ማሰቤ አልቀረም። ነገርን ነገር ያነሳዋል ይባል የለ? ትዝ ይላችሁ ከሆነ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሬ የውጊያ ጀቱን በዓባይ ድልድይ ሥር አሳለፈው። ተብሎ ይነገር የነበረውን አፈ ታሪክ ለብዙ ጊዜ በየዋህነትና በልጅነት መንፈስ አምኜው እንደ ነበር ዛሬ ልናዘዝ። ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት ነች የሚባለውን አባባል እንዲሁ እስከ ወሎ እረሃብ ድረስ አምኜው እንደ ነበር ማለቴ ነው። ታዲያ ማንም ይሁን ምን ዶክተር ቴዎድሮስ ያሸነፉት በተወሰነ የብሔራቸው ህብረተሰብ ድጋፍ ነውና እኛ የክልሉ ደጋፊዎቻቸው ልንመሰገን ይገባል ብሎ ማለት ግለሰቡን ማጥበብ እንጂ ጠቀሜታው አልታይ አለኝ። የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩትን ቀደም ሲል ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የነበሩትን ዶክተር የሠሩት ሥራ ሁሉ የትግራይ ክልል ተወላጅ ስለሆኑ ነው ማለት ሌሎች “ኢትዮጵያዊነትን ማቃለል የትግራይ ልጆች መፈክር ሆኗል” የሚለውን አባባል ማጉላት ይመስለኛል። እኔ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የሚወድ ለእምነቱና ለባንዲራው የሚሞት መሆኑን አውቃለሁ። ሌላውን ለማናደድ በሚል የሚሰነዘሩ ወንዝ የማያሻግሩ አስተሳሰቦችን አደባባይ አለማውጣት ብልህነት እንጂ ሽንፈት አይደለም። አንድ ግለሰብ ሌላውን “ለምንድነው ማርያምን ሰው ሁሉ የሚፈራት?” ቢለው ”ወዶ መሰለህ ከግንድ የሚያጋጭ ልጅ ስላላት ነው“ አለ እንደሚባለው አይነት ማለቴ ነው። ማርያም የምትከበረው ማርያም ስለሆነች መሆኑን እንቀበል።

ሌላው ነጥብ ላነሳው የምወደው እንዲሁ በዚሁ የደጋፊ ድሕረ ገጽ እየተለጠፉ ያሉትን የተለያዩ ትግራይን የሚመለከቱ ጽሁፎች ሳነብ እየገረመኝ የመጣውን ጉዳይ ነው። “ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ማነው? ህወሓት ወይስ ሁሉም የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች?” በሚል በሓጎስ ኣረጋይ (PhD) የተጻፈ 12 ገጽ ትምህርታዊ ጽሑፍ አነበብኩ። ትምህርታዊ ያልኩት የጸሐፊውን ምሑርነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። የጸሐፊውን መንደርደሪያ ሳነብ ደግሞ ስለእውነት ወደድኳቸው። እንዲህ በማለት ጽሁፋቸውን ይጀምራሉ።

“ስለዚህ ይህንን ፅሁፍ ከሚያነቡ ሰዎች ሊንፀባረቅ ከሚችለው ኣስተያዬትና ግንዛቤ ለሞጋች መድረክ ማደግ የራሱ የሆነ ኣስተዋፅኦ ይኖረዋል ብየም ኣምናሎህ። ሃሳቦችን በተለያዬ መልኩ ማንሸራሸር ከተቻለ ደግሞ እውነቱን ሊንፀባረቅ ይችላል ብዬ ኣምናሎህ ። እውነትን ማንፀባረቅ ከታቸለ ደግሞ በኣንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚታለለውን ሰው መቀነስ ይቻላል ማለት ነው።

በዚህ መልኩ የሃሳብ ልውውጥ ከተደረገ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ህዝቦች (ብሄር ብሄረ ሰቦች ) በኣንድ ኣገር ጥላ ስር ሁነን ከኣድልዎ ነፃ የሆነ፣ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት ማእቀፍ ተከባብረንና ሰርተን መኖር የምንችልበት ስርዓት እንሻለን እላሎህ። ነገር ግን የስልጣን ሱስ ያለባቸው ጥቂት ግለ ሰቦች ኣይጨምርም ። ስለዚህ ወደ ዋናው ሃሳብ ልውሰዳችሁ።”

በውይይት ችግራችንን መፍታት አለብን ማለታቸው በመሆኑ ከዚህ የበለጠ የሚያስማማ መንደርደሪያ ከየት ይመጣል? ብዬም አሰብኩ። ጽሑፋቸውን ገባ እያልኩ ሳነብ ግን ብዙ በግል የማልስማማበት ነጥቦች ሲያነሱ አየኋቸው። የዋለልኝን በብሔር ትግል ላይ ያለ አመለካከት የአቤ ጉበኛን አልወለድም መጽሃፍ የሚጠቅሱት ዶክተር የሌላውን የተማሪ ንቅናቄ አባላት ትግል ቦታ ላለመስጠት የወሰኑ ለመሆኑ ካባባላቸው ለመረዳትም ቻልኩ።

“በሶሻሊስት ርእዮትም የብሄር ብሄረሰቦች መብትና ጥቅም ታትተዋል። እንዲሁም በኣለም ኣካባቢ ጭምር የማይኖሪቲ ራይት የሚል ሃሳብም በብዙ መልኩ ታትተዋል።” ብለው የኢትዮጵያን ተማሪዎች ትግል የብሔርና የመሬት ላራሹ ትግል መሆኑን አለባብሰው ሊያልፉ ሲሞክሩ ታዘብኩ። ሌላ ሰው ቢል ዝም ባልኩ። ዶክተር ግን ሲሉት ዝም ማለት አልወደድኩም። “ምሑር” ናቸውና። ለምን ቢባል ወደዱም ጠሉም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ያጠነጥን የነበረው በብሔር ጭቆናና በመሬት ላራሹ ትግል ዙሪያ ስለነበረ። ልዩነቱ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አቋም በወቅቱ የሶሻሊስት አብዮት አማራጭ የሌለው ሳይንሳዊ የትግል መርህ ነው የሚል መሆኑ፣ ቀደምት ቅራኔው የመደብ ትግል እንጂ የብሔር ትግል አይደለም ማለቱ ላይ ነው። ስለሆነም የወጣቱ ትግል የብሔር ጭቆናን እስከ መገንጠል ተቀብሎ የዲሞክራሲ ጥያቄ በመሆኑ ሌሎች የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ሲፈቱ የብሔር ጥያቄም አብሮ እንደሚፈታ ማመኑን አለማንሳታቸው ነው የገረመኝ። ለነገሩ TPLF ጭምር የማርክሲስት ሌኒኒስት እርእዮተ ዓለም ተከታይ ነን ይል እንደ ነበር እንዴት ዘነጉት? በወቅቱ ተራማጅ ነኝ የሚል ቡድን ደርግን ጨምሮ የማርክሲስት ንድፈ ሃሳብ ተከታይ ነን ማለቱ እውነታ አልነበረምን?

ደርግ ፋሽስት እንደነበር እየተስማማን የነበረውን የፊውዳል ሥርዓት መገርሰሱን እንዴት እንጣላበታለን? የመሬት ላራሹ አዋጅ የፊውዳል ስርአቱ የመጨረሻው መቃብር እንደ ነበረስ እንዴት እንካካዳለን? ሌላው ዶክተር ሓጎስን ልጠይቃቸው የምወደው ነገር ቢኖር ስለኦሮሞ ሕዝብ መጨቆን ሲያነሱ ሕዝቡ የደርግ የቀይ ሽብር ሰለባ መሆኑን የማንሳታቸውን ጉዳይ ነው። አባባሉ ትክክል ሆኖ እያለ ይህንን አባባል ለምን እንዳነሱት ብጠረጥርም አይፍረዱብኝ ብዬ እገምታለሁ። ለምን ቢባል በደርግ የሞቱት የኦሮሞ ብሔረሰቦች ብቻ ናቸው ሊሉን ስለመሰለኝ? ያ ከሆነ በታሪክ አምላክ ልለዎት ነው። በወቅቱ በደርግ የተጨፈጨፉትን አማራዎች፣ ትግራውያን፣ ጉራጌዎች፣ አደሬዎች፣ ሲዳማዎች፣ ወላይታዎች ሶማሌዎች ወዘተ ደም ደመ ከልብ ማድረግ ይመስልብዎታልና ቢያስቡበት መልካም ነው ብዬ የተሰማኝን ልንገረዎ።

“በሽምቅ ውግያ የተደራጀ የመንግስትን ሃይል ማሽነፍ መቻል የሚያሳየው ስርዓቱ በጣም ኣስከፊና በህዝብ የተጠላ እንደንበር በግልፅ ያሳያል።”

የሚሉንን ዶክተር በአባባላቸው እየተስማማሁ መንግሥት ሊወድቅ የቻለው በሕዝቡ ትግል መሆኑን ካመኑበትና ከተቀበሉት ተስማምተን መጓዝ እንደምንችል ነው። ካልሆነ የተወሰነ ድርጅት ትግል እንጂ የሕዝቡን ትግል አያካትትም ማለታቸው ከሆነ አብረን መጓዝ እንደማንችል እንዲያውቁት ለማድረግ ነው። ጽሑፋቸውን በመቀጠል በትግራይ ሕዝብ ላይ የተሸረበ ሴራ ሊያሳዩን ሲሞክሩ እንዲህ ይላሉ። “ከጣልያን በመስማማት የትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ለሁለት መክፈል ነበር (ኤርትራና ትግራይ)። ይህን ያደረጉበት ምክንያት የትግርኛ ተናጋሪዎች የሃይል ሚዛን ለመከፋፈል እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ።

አባባላቸው አፄ ምኒልክን የሚነካ መሰለኝ። ከሆነ አፄ ምኒልክ እውን ጣልያንን አባረው ከኤርትራ ማስወጣት ሳይፈልጉ ቀርተው ነው ወይስ የተዳከመ ጦር ይዤ ያገኘሁትን ድል አላከሽፍም ብለው ውጊያውን ያቆሙት? ካልሆነ እርስዎ እንዳሉት በወቅቱ ንጉሱ ከነበራቸው የትግራይ ሕዝብ ጥላቻ የትግራይን ሕዝብ ለመከፋፈል አስበው ያደረጉት ተንኮል ነበር? አዎ ተንኮል ነበር ብለው ካሰቡ ከብዙ የታሪክ ምሑራን ጋር ሊጣሉ መሆኑን ይወቁ ከእኔ ጋርማ ከተለያየን ቆየ።

ትምህርታዊ ጽሁፋቸውን በመቀጠል የአማራው ”የገዠ መደብ ደርግም“ በትግራይ ላይ ያደረሰውን በደል ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ። “ደርግ በሃውዜን ገበያ ላይ የተሰብሰበውን ሀዝብ በሰኔ 15/1981 ዓ/ም ከ 2500 ንፁሃን ሰዎች በኣየር ገድለዋል (ህዝቡ እየተገበያዬ በነበረበት ወቅት ነው ጭፍጨፋቸው የተካሄደው እንጂ የመቃወም፥ ድንጋይ የመወረወር የሚባል ነገር በወቅቱ ኣልነበረም )።” ይህንን የጭፍጨፋ ወንጀል እንዲወሰድ ትእዛዝ ያስተላለፈው በወቅቱ የአካባቢው የደርግ አባልና ባለስልጣን የነበረው የሃምሳ አለቃ ለገሰ አስፋው ለመሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጅ ነበር እንዴ? አሁንስ ያለው የት ይሆን? ማ ከተፈረደበት ወንጀል በምህረት እንዲለቀቅ አደረገው?ቢመልሱልኝ ደስ ባለኝ።

ለማለት የፈለኩት በጽሑፍዎ ላይ ሊነግሩን የፈለጉትን ለምን እንዳነሷቸው ለመጠቆም እንጂ እርስዎ አስበውበት የተነሱበት ደርግም የአማራ መንግሥት ነበር ሊሉን እንደሆነ ሳይገባኝ ቀርቶ አይምሰለዎ። ደርግ የአማራው መንግሥት ነበር ብለው ሲሉ ግን ፍስሃ ደስታ እንዳይስቅብዎ ፈራሁ።

በነገራችን ላይ በየትኛውም መንግሥት የሚደረጉ ግድያዎችን ጭፍጨፋዎችን የምቃወም መሆኔን አስቀድሜ ልናገር። አንድም ሰው መሞት እንደሌለበት፣ እንዳልነበረበት አምናለሁ ነገር ግን የሚከተለውን አረፍተ ነገር ሳነብ ተገረምኩ። “በኦሮሞ ተወላጆች በተለያዩ ኣከባቢዎች ለተነሱት የገበሬዎች ኣመፅ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ መጨፍጨፋችው ታሪክ ዘግቦታል። ለምሳሌ ጭካኔው በኣሩሲና ሃረርጌ ኣከባቢ (ኣኖሌ) የውላጅ እናቶች ጡት እስከ መቁጥ ያጠቃልላል”

ለምን ቢባል ይህንን መቃወም አግባብ ሆኖ እያለ ኢህአደግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በአማራው ተወላጅ ላይ የተፈጸመውን መንግሥት ከተደረገ ከዓመት በኋላ ይፋ ያወጣውን የግፍ ግድያ ለምን ሳያነሱት ቀረ? ለምን ለራሳችን ክርክር የሚፈለጉ ምሳሌዎችን ብቻ እያነሳን ለክርክራችን አይጠቅምም የምንለውን እውነታና ታሪክ እንዳላየ እናልፋለን? በመቀጠል ጸሐፊው ስለቅማንት መብት እየተናገሩ ስለወልቃይት ግን ሃሳቡን የሚገፋው ውጭ አገር ያለ ቡድን እና ጎንደር ያለ ሕዝብ እንጂ የወልቃይት ሕዝብ አይደለም ብለው የወልቃይት ወንዝና ቦታዎች በትግርኛ የተሰየሙ መሆናቸውን በመረጃ መልክ በማቅረብ ወልቃይት ትግራይ ነበር ነውም ብለው ይነግሩናል። እዚህ ላይ ከዚህ ቀደም ያልኩትን እንዲያነቡ ከመጠቆም ውጭ ምንም ማለት አልፈልግም። ለምን ቢሉ የሚነሱት ነገሮች መጥፎ ትርጉም ይሰጣቸዋል ብዬ በማሰብ ነው። ማንም ያንሳው ምን ጥያቄው መነሳቱ ግን አልቀረምና ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታው ጥያቄውን ለሕዝቡ እንተውለት እንጂ እሳቱን አናራግብ ለማለትም ፈልጌ ነው። የኛ ውሳኔ በወንዝ ስም የተደገፍ በመሆኑ ነው ካልን ወሎ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች ሐረር ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች ሲዳማ የሚነሱ ጥያቄዎች ሊኖሩ ነውና እዛ ውስጥ ባንገባ መልካም ይመስለኛል። ትግራይ ውስጥ ያሉ አናሳ ብሔሮችም የራሳቸው ችግር እያነሱ መሆኑንም አንርሳ። ደጋግሜ እንዳልኩት የትግራይ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ እንደሆነ ሁሉ የአማራውም ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ እንደሆነ እንቀበል።

በመደምደሚያ መሪዎችን ሲጠሩ ምነው አፄ ዮሐንስን ሳያነሱ ቀሩ? ትግራይን ያስተዳደሩ የአማራ መሪዎች እነማን ነበሩ? የመንግሥት ድርጅት ንብረት የሆኑ ድርጅቶች እየጎለበቱ መምጣት የግለሰቦችን ድርጅት አቅም አይገድልም ብለው ያስባሉን? በ monopoly ላይ ያለዎት አመለካከት ምንድነው? ብዬ በመጠየቅ መደምደሚያ ሃሳብዎን ግን ሙሉ በሙሉ እንደወደድኩት ነግሬ ውይይታችን ለመግባባት በር ይክፈት ብዬ በመናገር በሚያግባባን ዙሪያ ተነስተን የማያግባባንን ለመቅረፍ እንነሳ እያልኩ ልለይዎ።

ሰላሙን እየተመኘሁ ላብቃ ፡፡

                          ኢትዮጵያም ለዘላለም ትኑር

  1. dad says

    I read a comment about triblism written by ሓጎስ ኣረጋይ (PhD). I think the writter had not a title PhD unless the title is manufactured from dedebet .What push me to go to such conclusion are so many things from his document ,
    PhD is given for person which have universal truth that can able to change the living condition of human being. you are always writting about certain group of persons not socity you are supporting poltical leaders and opposing innocent cetizen.

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy