Artcles

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን

By Admin

June 06, 2017

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን

                                                       ታዬ ከበደ

የኢትዮጵያ ህዝብ ‘ድህነት አሻፈረኝ’ ብሎ የተነሳ ነው። ህዝቡ አስከፊዎቹን ቀደምት ስርዓቶች አሽቀንጥሮ ከአስወገዳቸው በኋላ፤ በሀገሪቱ የነበረው መጠነ ሰፊ ችግር በአመዛኙ ሊቀየር ችሏል፡፡ እንደሚታወቀው በፈጣን ዕድገት ላይ ባሉት ታዳጊ ሀገር ለሚገኙ ዜጎች ኤሌክትሪክ ብርሃንማ ጉልበትም ነው፡፡ እናም ከከተሞች ዳርቻ ፈቅ ሳይል ዘመናትን ያስቆጠረው የሀገራችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተደራሽነት ወሰኑን ከቀን ወደ ቀን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡

መላ ህይወቱን ከኩራዝ ጋር አቆራኝቶ “መብራት አይንሳችሁ” በሚል ብሂል የኤሌክትሪክ ብርሃንን ከሩቅ ይናፈቅ ለነበረው አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ምኞቱን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በመከናወን ላይም ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ለልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለአቅርቦቱ የተሰጠው ትኩረትም ድርሻው የጎላ ነው፡፡ ኃይል ለማቅረብ የየወቅቱን የልማት ጥያቄዎች ከመመለስ ባለፈ የዘርፉን ሥራ በማስፋትና በማቀላጠፍ ከድህነት ነፃ የሚያወጣ የሀገሪቱን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተቃኘ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም የሀገሪቱ ኢነርጂ ፖሊሲ ከመጋቢት 1986 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡

የፖሊሲው ዓላማ የሀገሪቱን የኢነርጂ ሀብት ከአጠቃላይ የመንግሥት የልማት ስትራቴጂ አኳያ ማጎልበትና ሥራ ላይ ማዋል፣ ሌሎች የየአካዳሚ ዘርፎች የዘረጉትን የልማት አቅጣጫ የሚደግፍ ግልጽና ውጤታማ የኢነርጂ ኃይል እንዲኖር ማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል ውጤታማ የኢነርጂ አጠቃቀም እንዲኖር ማስቻል ብሎም ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ መዋዠቅ ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት በመፍጠር ኢኮኖሚውን መታደግ የሚሉ ዓላማዎችንም ጭምር በማንገብፉ ሥራውን ጀምሯል፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ለማካት የኢነርጂ ፖሊሲው ቀጣይነትና አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲሁም ዘርፉን የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት ፈጣን ኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር እንዲኖር መመሪያዎችን ለመዘርጋት ከፍ ሲልም ሀገር በቀል የሆኑና የአየር ንብረት ብክለትን የሚያስወግዱ የኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ፖሊሲው ለውሃ ኃይል ልማትን እንዲሁም የኢነርጂ አጠቃቀም ስብጥር በማበረታታት ለታዳሽ የኢነርጂ አጠቃቀም፣ ለፀሐይ ኃይል፣ ለንፋስ እና ጂኦተርማል ልማትና ዋጋ ተወዳዳሪነት ትኩረት የሰጠ ነው፡፡

ተስማሚ የፖሊሲ ርምጃዎችን ለመውሰድ ደረጃ በደረጃ የህዝቡን ተለምዷዊ የኢነርጂ አጠቃቀም ወደ ዘመናዊውና ለአየር ንብረት ጥበቃ አጋዥ የሆነ አጠቃቀም የመቀየር ዓላማን አንግቧል፡፡

እንደሚታወቀው የኢፈረዴሪ መንግስት በሀገራችን ለሚገኝ ሁሉም ነዋሪ ዓለም አቀፍ ጥራትና ብቃት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠትና ተወዳዳሪ የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ኢንዱስትሪ የመሆን ትልሙን ለማሳት በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ የመሠረተ ልማት አካል ኢነርጂ ሲሆን ባለፉት ዓመታት ሥራ ላይ የዋለውን ፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል ሀገሪቱ ባላት የውሃ ሀብት በመጠቀም የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማነቃቃት ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድም አዳዲስ የኃይል ማመንጫዎች በመገንባት ነባሮቹን በማደስና የኃይል ማመንጨትና ማሠራጨት ተግባሩን ለማሳደግ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁለንተናዊ አገልግሎት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ ባለፉት 23 ዓመታት በተለይም ደግሞ ካለፉት 13 የስኬት ዓመታት ወዲህ በርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ከውሃ፣ ከንፋስና ጂኦተርማል በመገንባት ላይ ሲሆን የኃይል ማስተላለፊያ ማከፋፈያ ጣቢያዎችንም ጎን ለጎን ለመገንባት ከሚመረተው ኃይል ጋር በማጣጣም በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

በዋናነትም ከሚጠቀሱት ግንባታዎች መካከል የጢስ አባይ 2 ውሃ ኃይል ማመንጫ— 73 ሜጋዋት ፣ የጊቤ1 የውሃ ኃይል ማመንጫ— 184 ሜጋ ዋት፣ የተከዜ ውሃ ኃይል ማመንጫ— 300 ሜጋ ዋት፣ የግልገል ጊቤ 2 ውሃ ኃይል ማመንጫ— 420 ሜጋ ዋት እንዲሁም ከበለስ ውሃ ኃይል ማመንጫ— 460 ሜጋዋት እና ከፊንጫ አመርቲነሽ ውሃ ኃይል ማመንጫ— 97 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ማግኘት ተችሏል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በተለይም ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበሩ የኃይል አቅርቦት አማራጮች ፈቅ ብሎ ሌሎች አማራጮችም ለሀገሪቱ የኃይል እጥረት መቀረፉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚያችሉ የታየበትም ነው፡፡

ይህም ሲባል ኢትዮጵያ በነፋስ ኃይል ከአዳማ አንድ የኃይል ማመንጫ 51 ሜጋ ዋት እንዲሁም በትግራይ ክልል የአሸጎዳ ንፋስ ኃይል ማመንጫ በመገንባት 120 ሜጋ ዋት ለማግኘት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጊቤ ሶስት የሃይል ማመንጫ ግድብ እየተናወነ ሲሆን፤ 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው። ይህ አቅም ሙሉ ለሙሉ ወደ ማምረት ሲገባ የሀገራችንን ኤሌክትሪክ ሃይል አቅም ይጨምራል። ለጎረቤት ሀገሮችም ጥቅም ይሰጣል።

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት መሃንዲሶቹም ግንበኞቹም የፋይናንስ ምንጮችም እራሳችን ሆነን እየገነባነው ያለ የህዳሴያችን ታላቅ ፕሮጀክት ነው እንዳሉት ህዝቡ የራሱ ብሎም ብቸኛው ጠላታችን ድህነት ነው የሚለውን አጀንዳ በማንገብ ህብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደለት ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት እየተጋ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን አንድነትን ከአሳየበት ትይንት ባሻገር፤ የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ የማጥላላት ዘመቻ በማድረግ ላይ የሚገኙት የውጭ ኃይሎችና የሀገር ውስጥ ተላላኪዎችንም ምን ያህል ከህዝብ ያፈነገጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ያጋለጠ ታላቅ ፕሮጀክት ሆኗል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሆነ ሌሎች ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲገነቡ ልማቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረውንም ትስስር ያመላከተ ነው፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ወደ ጎረቤት ሀገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል በመላክ ሀገራቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት እነርሱንም ጭምር የሚጠቅም መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡ ሀገሪቱም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሀገራችን ለቀጣይ ዕድገት ተጨማሪ አቀም እንድታገኝ የሚያደርጉ የህዳሴያችንን ሁነኛ መሠረቶችንንም ይጥላሉ፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሀገራችን እና በቀጣናው ሀገራት መካከል መተማመን ላይ የተመሰረተ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት የሚሰጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠርም ያስችላል፡፡ የእነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች ድምር ውጤት ሀገራችን ከራሷ አልፋ ሌሎች ሀገሮችን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚጠቅማቸው ነው።