Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምርኳችንን እንጠብቅ

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምርኳችንን እንጠብቅ

                                                            አሜን ተፈሪ

የኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹ልዩ አብሮ የመኖር ችሎታ ወይም ደመ ነፍስ›› ያለው ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ለዘመናት የዘለቀውን የኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላም አብሮ የመኖር፣ የመከባበር እና የመቻቻል አኩሪ ባህል ወይም ታሪክ የሚጎዳ አንድ ወቅታዊ ፈተና ሆኖ የመጣው የጥላቻ ንግግር ነው፡፡ ህዝብን በህዝብ ላይ የማነሳሳት ግብ ያላቸው የጥላቻ ንግግሮች በሐገራችን ከንግግር እና ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት መከበር ጋር የአደባባይ ሥፍራ ማግኘት መቻላቸው የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሐገራችን ከተስፋፋው የኢንተርኔት አገልግሎት እና ከማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር መበራከት ጋር ተያይዞ፤ የጥላቻ ንግግር ተጽዕኖ መጠናከሩ ይታያል፡፡ በሐገራችን፤ የጥላቻ ንግግር እና ሕዝብን ከህዝብ ሊያጋጩ የሚችሉ መልዕክቶች በሰፊው የሚታዩ መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

እንደሚታወቀው፤ የፕሬስ ነጻነት መብት በተከበረ ማግስት የግል ፕሬስ ባለቤቶች የመሆን ዕድል ያገኙት የደርግ ስርዓት የሳንሱር ክፍል ሹሞች እና አፈ ቀላጤዎች፤ የሐገራችንን የግል ፕሬስ ሥነ ምግባራዊ እና ሙያዊ አሰራር የሚጎዳ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደራቸውም በላይ፤ በጥላቻ ንግግር ቀለም በተሞላ እና በተሸናፊነት ስሜት በታመመ ብዕራቸው፤ በአንዳንድ ወገኖች ላይ የተዛባ አመለካከት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ጥረት አድርገዋል፡፡

የጋዜጠኛነት ካባ አጥልቀው ብቅ ያሉት እኒያ የአፋኙ ስርዓት የሳንሱር ክፍል ሹሞች፤  አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በነጻነት የማሰር፣ የመግደል፣ የመዝረፍ ወዘተ መብት ስለነፈጋቸው በስርዓቱ ላይ የከረረ ጥላቻ ነበራቸው፡፡ ለስርዓቱ ያላቸውን ይህን ጥላቻ ሲገልጹም፤ ከአዲሱ ሥርዓት ጋር የተለየ ቁርኝት አላቸው ብለው በሚያስቧቸው ህወሓት እና በትግራይ ህዝብ ላይ በማትኮር ነው፡፡

በ17ቱ የደርግ የስልጣን ዘመናት ሲያደርጉት የቆዩት እና በፕሬስ ነጻነት ማግስት የቅርጽ ለውጥ አድርገው ያስቀጠሉት የጥላቻ ንግግር በትግራይ ህዝብ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ጥርሳቸውን የነቀሉት እና የዘወትር የፕሮፓጋንዳ ፊደላቸው ይታላቻ ንግግር ነው፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የተገለጸ እና ከአርባ ዓመታት በላይ የቆየ ዕድሜ ያለው በሰፊው የሚታወቅ ችግር ነው፡፡ ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማህበራዊ ሚዲያ ልዩ ባህርያት ለችግሩ መጠናከር የበኩሉን ድርሻ ተጫውቷል ማለት ይቻላል፡፡

ታዲያ ይህ የጥላቻ ንግግር በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የተዛባ አመለካከት ሊጥር የሚችል መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎችን የሚያሳስብ መልክ ይዞ የተከሰተውና የሐገሪቱን አንድነት እንዲሁም የህዝቦችን ነባር የመከባበር ወይም የወንድማማችነት ስሜት ከሚሸረሽር ደረጃ የደረሰው  የጥላቻ ንግግር በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡

ታዲያ አሳሳቢ የሚሆነው፤ በፖለቲካ አቋማቸው እና በትግል ስልት ምርጫቸው የተነሳ በጥላቻ ኢንዱስትሪው ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ጉዳይ ሳይሆን፤ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ በተለየ ተጠቃሚ ሆኗል በሚል ስሜት የተዛባ አመለካከት የሚይዙ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ የተዛባ አመለካከት የተጠለፉ ወገኖች፤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሚታዩ ነዳያንን በመቸገር ከሰው ፊት የቆሙ መሆናቸውን መቀበል የሚቸግራቸው እና መንግስት በስለላ ተልዕኮ ያሰማራቸው ሰዎች አድርጎ ማየት የሚመርጡ ናቸው፡፡ የትግራይ ህዝብ ለመንግስት ሙሉ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ፤ ህዝቡን በጠላትነት የሚፈርጁ ወገኖች (ባህር ማዶ ሆነ በሐገር ቤት ሆነው) ህዝቡን ከሌሎች ወገኖቹ ሊነጥሉት ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ መንግስት በሚከተለው የልማት ፖሊሲ አማካይነት የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት እንዳልተለወጠ የሚናገሩት እና የሚከራከሩት እነዚህ ሰዎች፤ በትግራይ ክልል የሚሰልል እንጂ የሚቸገር መኖሩን መቀበል አይፈልጉም፡፡ ይህ የተዛባ አመለካከት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡

‹‹የህዳሴውን ግድብ መቀሌ ወሰዱት›› ሲባል፤ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ አዕምሮ የተዛባ አመለካከት ሰለባ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡ የህወሓትን ስም እየጠሩ በኪራይ ሰብሳቢነት የተሰማሩ ወገኖችን፤ የክልል ፕሬዚዳንት ሥሞችን ወይም ሌሎች የፌዴራል ወይም የክልል ባለስልጣናትን ሥም እያነሱ ለመነገድ ከሚሞክሩ የሌላ ክልል ተወላጆች ጋር አስተያይቶ ሚዛናዊ ዳኝነት ለመስጠጥ የሚቸገር እና የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ መሆኑን የሚቀበል የተዛባ አመለካከት ሰለባ መሆኑን መቀበል ይኖርበታል፡፡ ገና ከማለዳው ‹‹ትግራይ እስክትለማ፤ ሌላው ሐገር ይድማ›› የሚል የጥላቻ መዝሙር የጀመሩት ሰዎች፤ ዛሬም አድማጭ እና አንባቢ ሊሸምተው ይችላል ብለው የሚያስቡትን የጥላቻ ሸቀጥ ማምረታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የሐገሪቱ ግዛት በተደጋጋሚ ሲጠብ እና ሲሰፋ ቢቆይም፤ ኢትዮጵያ የተባለች ሐገር ዘመናትን መሻገር የቻለችው በሕዝቦች መካከል ባለው ልዩ የአብሮ መኖር ባህል የተነሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ጸሐፊ – በአንድ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ግዛት ሲጠብ እና ሲሰፋ ቢታይም ህልውናዋ ሳይከስም ለረጅም ዘመን የመዝለቋ ነገር አስገራሚ መሆኑን፤ ግራ ቀኝ እየተመላለሰ የብዙዎችን ህይወት ባጠፋ የፈረንሳይ አብዮት ሰይፍ ሳይበላ በተአምር ከተረፈ አንድ ፖለቲከኛ ህይወት ጋር አነጻጽሮ ገልጾት ነበር፡፡ ከዚያ ሁሉ መከራ በተአምር ተርፎ ታሪክ ለመናገር እንደበቃው የፈረንሳይ ፖለቲከኛ፤ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎችን በማለፍ፤ ግራ ቀኝ እየተምዘገዘገ ብዙ የአፍሪካ ሐገራትን የቅኝ ግዛት ሰለባ ካደረገው ‹‹የበርሊኑ ሰይፍ›› ያመለጠችው ኢትዮጵያ፤ እንደ ፈረንሳዩ ፖለቲከኛ ብዙ አደጋዎችን ተሻግራ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን መድረሷ አስገራሚ መሆኑ አይቀርም፡፡ ታዲያ ይህ እንቆቅልሽ ሊፈታ የሚችለው ‹‹ግፍ ቻይ›› በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ የአብሮ መኖር ባህል ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሺህ ዘመናትን ባስቆጠረ የመንግስትነት ታሪክ የታለፈው ውጣ ውረድ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ሂደት በኢትዮጵያ የዳበረ ልዩ የብሔራዊ ማንነት (ብሔርተኝነት ስሜት) ተፈጥሯል፡፡ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንዳለው፤ ኢትየጵያዊነት ተረት እና ስሜት አይደለም፡፡ በራሱ ምክንያት ጸንቶ የሚቆም እና በቀላሉ በነፋስ የማይወሰድ ማህበራዊ እውነታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በየጊዜው እየተፈተነ፤ በበርካታ ምዕተ ዓመታት ጉዞ የተለያዩ ተግዳሮቶችን እያለፈ የተጓዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ህልውና የሚፈታተን ከባድ ችግር በተከሰተ ቁጥር ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ስሜት አደጋውን ለመከላከል ሲነሱ ታይቷል፡፡ በግዛት ወረራ ፍላጎት በተደጋጋሚ የገጠማቸውን የውጭ ኃይል ጥቃት በብቃት በመመለስ ድንቅ ገድል የተገነባ በኢትዮጵያዊነት የመኩራት ጥልቅ ስሜት ተፈጥሯል፡፡ ለዘመናት የዘለቀ እና በአይበገሬነት ስሜት ላይ የታነጸ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አለ፡፡

ብሔርተኝነት፤ እሙናዊ ወይም ምናባዊ በሆነ ባህል እና ታሪክ ላይ የሚመሠረት፤ የርዕዮተ ዓለማዊ እና የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወይም እምነት መገለጫ ነው፡፡ ብሔርተኝነት ዓለም ዓቀፍ ክስተት ሲሆን ከተለያዩ ወገኖች የተናጠል ልምድ እና ገጠመኝ ውህደት የሚፈጠር የቡድን ማንነት መገለጫ ነው፡፡ የተለያዩ ህዝቦች የወል ህሊና ወይም አስተሳሰብ የሚፈጥሩበት እና ልዩ መገለጫ የሚሆን ባህርይ ያለው ህሊናዊ ሁኔታ ነው፡፡ አካባቢያዊ፣ ብሔረሰባዊ እና ክልላዊ ቁርኝትን ተሻግሮ የሚሄድ የጋራ ማንነት ነው፡፡ ብሔራዊ ስሜት ከኔሽን-ስቴት ጋር የተቆራኘ እና የጋራ ማንነት አስተሳሰብ ማዳወሪያ እና የሁሉንም ዜጎች ፍጹም ታማኝነትን የሚጠይቅ ክስተት ነው፡፡

ሆኖም ማቅመማማትን የማይፈቅድ ፍጹም ታማኝነትን የመፍጠር ፍላጎት ሲኖር፤ ልዩነቶችን ጨፍልቆ በኃይል አንድ የማድረግ ስህተትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከብሔራዊ ስሜት ጉያ ሊደበቅ የሚችል፤ ሁሉንም አንድ የማድረግ ጠንካራ ምኞት ከባህል ብዙነት ጋር ግጭት እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ አንድነት የመፍጠር ፍላጎቱ፤ አንድ ወጥ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ የያዘን ፖሊሲ የመከተል ዝንባሌን ሊስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ የሚነሳው ግጭትም የፖለቲካ ህብረቱን አደጋ ላይ ከሚጥል ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ ችግሩ ከዚህ ደረጃ ሲደርስ ‹‹በጠቅላይ ግዛቱ›› መጨፍለቅ የማይሹ ቡድኖችን ሊፈጥር እና ይህን ድምጽ በኃይል የማፈን እርምጃን ሊጋብዝ ይችላል፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚከሰተው የፖለቲካ ግጭትም ለብሔራዊ ስሜት ግንባታ መሠረታዊ ስንቅ ሊሆን የሚችለውን ሐብት እየሸረሸረ፤ በመጨረሻ የብሔርተኝነት ስሜቱን አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡  በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ችግር ታይቷል፡፡ ዘመናዊውን የኢትዮጵያ የሐገረ-መንግስት (nation-state) ግንባታ ታሪክን መመልከት፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ህብረት ውስብስብነት ለመረዳት ከማስቻሉም በላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህብረት አፈጣጠር የሐገሪቱ የጥንካሬ እና የችግር ምንጭ መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡

ይህ ፈተና በኢትዮጵያ ብቻ የወደቀ ፈተና አይደለም፡፡ የመንግስት እና የብሄር ቡድኖች ውስብስብ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ የብሔር ቡድኖች፣ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ማንነታቸውን የሚጎዳ ሲመስላቸው በተለያየ መንገድ ተቃውሞአቸውን ይገልጻሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ያየነው ማንነትን ለማስከበር የተደረገ ትግል ምንጩ ይኸው ነው፡፡ በመሆኑም፤ በሐገር ግንባታ ጥረቶች ላይ ሁሌም የሚደቀነው ችግር፤ የብሔር ማንነትን ሳያጠፉ አንድነትን መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያ በውስጧ የሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ልዩነት በመዘንጋት ወይም እንደ ነገሩ በመያዝ ለችግር ብትዳረግም፤ የዳር እና የመሐል ሥፍራ የተሰጠው ባህል ይዛ ባደረገችው ያልተሳካ ጉዞ ውስጣዊ ሰላም ብታጣም፤ እንደ ሐገር የመቆየት ጥበብን ማዳበር እና አሁን ለተፈጠረው ፌዴራል ህብረት መሠረት ሊሆን የቻለ የህዝቦች ግንኙነትን መፍጠር ችላለች፡፡ ፈተናዋ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡ አሁን የተጋረጠባት ፈተና የጥላቻ ንግግር ነው፡፡ ይህን ችግር ተረድተን ምርኳችንን እንጠብቅ፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy