Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላም ለኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ

0 444

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላም ለኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ

ኢዛና ዘመንፈስ

ሰላም የነገሮች ሁሉ ቁልፍ ጉዳይ ስለመሆኑ ብዙ ተብሏል፡፡ በእርግጥ ደግሞ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር ምንም ዓይነት ተግባር መከወን አይቻልም፡፡ እንደኛ አገር ድህነት ለመላቀቅ ቆርጦ የተነሳ ህዝብና መንግስት ባለበት ሁኔታ ቀርቶ፣ መቼም ይሁን የትም የተሟላ ሰላም የማይሻ ህብረተሰብ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡

ከዚህ እጅግ ወሳኝ የጋራ መግባባትን የሚጠይቅ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ጋር በተያያዘም፣ ከትላንት እስከ ዛሬ ወይም ከጥንት ጊዜ ጀምሮ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በምድራችን ላይ እንዲሰፍን የማድረግ ጥረት መኖሩን መካድ አይቻልም፡፡

ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቆጠረውም በተለይ የምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁ ሀገራትን የሚመሩ አምባገነን መንግስታት፣ አልያም የፖለቲካ ቡድኖችና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን የሚከተሉ ግለሰቦች፣ በዜጎቻቸው ላይ ጭምር ሆነ ብለው የሚፈጥሩት ስነልቦናዊ ሁከት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ማህበራዊ ህይወቱ እንዳይረጋጋና ኑሮው እንዲመሰቃቀል በተደረገ ቁጥር፣ ውስጣዊ ሰላም ሊሰማው ስለማይችል ወይም መንፈሱ ስለሚታወክ፣ ከራሱ አልፎ የሌሎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ዕኩይ ተግባር ለመፈፀም ይገፋፋል ፡፡

   በአካባቢያቸው የሚያደርግ አዎንታዊ የህይወት እንቅስቃሴ ሁሉ የነሱን ውድቀት ለማፋጠን ሲባል የሚከናወን እንጂ የባለ ጉዳዩን ህብረተሰብ ጥቅም ለማረጋገጥ ያለመ መስሎ ስለማይታያቸው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ አጥፍቶ – መጥፋትን አማራጭ መፍትሔ አድርገው እስከመውሰድ የሚደርሱ ሰዎች ቁጥር የሚበራከተውም ሰላም ሲጠፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦችም ዓለም አቀፍ አድናቆትና ከበሬታ ለተቸረው አስተማማኝ ሰላማችን እንደ ህብረተሰብ ዘብ የማንቆምበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ በእርግጥም ደግሞ የትኛውም ልዑላዊ ሀገር ውስጥ የሚኖረው እያንዳንዱ ዜጋ እየዘራ የሚያጭደው ድምር ውጤት እንጂ በተአምር የሚፈጠር አይደለም፡፡

አንድ አገር እንደ ሀገር የምትቆመው ሁሉም ህዝቦቿ ወይም ዜጎቿ  በሚገነቡት የጋራ ዕሴት እንደመሆኑ መጠን፤ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም እቺ ሀገር የጋራ ቤታችን ናትና እያንዳንዳችን ዘብ ልንቆምላት እንደሚገባ የሚያከራክር ጉዳይ አይመስለኝም፡፡

  የጥንታዊቷ ቻይና ስመጥር ፈላስፋ ላኦ ቱዝ በዋነኛነት ከሚታወቅበት የሞራላዊ ዕሴት አስተምህሮ የምንረዳው እውነትም ቢሆንም፤ የአንድ አገር ህዝብ ታላቅነት የሚለካው ካለፈው ታሪኩ ሒደት ለገነባቸው ሀገራዊ የጋራ ዕሴቶቹ በሚሰጠው ክብርና በሚኖረው ፍቅር እንጂ በቁሳዊ ሀብት ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ማንኛውም የታላቅ ማንነት ባለቤት መሆን የሚችል ህብረተሰብ ከጽኑ ሀገራዊ መንፈስ የመነጩ የጋራ ኩራቶቹን እንደየዓይኑ ብሌን በጥንቃቄ የሚይዝና የማይገሰስ የነፃነት ታሪኩን ለምንም ይሁን ለማንም አሳልፎ የማይሰጥ ወይም  ለድርድር የማያቀረብ፤ ማህበራዊ መሰረት ይኖረው ዘንድ ግድ ነው፡፡

በዚህ ረገድ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ከራሳችን አልፎ ለመላው አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን የነፃነት ፋና የወጋንበት ሀገራዊ የድል አድራጊነት ባህል እንዳለንም ድፍን የዓለም ህብረተሰብ የሚስማማበት ታሪካዊ እውነታ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ጉዞ ስንልም ሺህ ዘመናትን ባስቆጠረው የነፃነት ታሪካችን ያካበትናቸውን የታላቅነታችን መገለጫ የሆኑ ሀገራዊ ትውፊቶችና የጋራ ዕሴቶች፤ ደምቀው እንዳይታዩ አድርጓቸው የቆየው ውስጣዊና ውጫዊ ችግራችንን ፈትተን ወደ ቀደመው የገናናነት ታሪክ የመመለስ ጥረት ማድረግ ማለታችን እንደሆነ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡

ስለሆነም የዛሬው ትውልድም ሀገራችን በድህነት ምክንያት የረሃብና የተመጽዋችነት ተምሳሌት ተደርጋ እስከመቆጠር የደረሰችበትን የአንድ ወቅት አሳፋሪ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ የመቀየር ኃላፊነት እንደተሸከመ ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ ትውልዱ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ጉዞ፤ በአንድም ወይም በሌላ መንገድ ለመተናኮልና ከተቻለም ለመቀልበስ የሚሹ ኃይሎችን ሁሉ ሊታገላቸው እንደሚገባም የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡

እያንዳንዱ ዜጋ ከአባት ከአያቶቹ በወረሰው ጽኑ የሀገር ፍቅር ወኔ ተነሳስቶ፤ የአዲሲቷን ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ህዝቦች የማይገሰስ ነፃነት ለመጋፋትና ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚቃጣቸው የሩቅም የቅርብም ጠላቶቻችን፤ የሚያደርጉትን ስውር እንቅስቃሴ ሁሉ በንቃት እየተከታተለ ዕኩይ ተልዕኳቸውን በማክሸፍ ረገድ ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ሰላም ወደዱ ህዝባችን እንደተለመደው ሥርዓት አልበኞችን ከታገላቸው የሽብርተኝነት ጉዳይ አስፈፃሚዎቹ ራሳቸውን ችለው ይሞቷታል እንጂ ሌላ አማራጭ አያገኙም፡፡

ስለዚህ ለመላው አፍሪካውያን ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ሀገራችን  በዘመናት ታሪኳ ለምትታወቅባቸው የታላቅነት መገለጫ ዕሴቶቻችን ተገቢ ክብር የምንሰጥ ዜጎች ሁሉ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደጋግሞ ሲፈታተነን የሚስተዋለውን አክራሪነትና የእርሱ ድምር ውጤት የሆነውን የሽብር ፈጠራ ተግባር በፍጹም ልባችን ከማውገዝና አምርሮ ከመታገል መቦዘን አይኖርብንም፡፡

አለበለዚያ ግን በአቋራጭ በትረ ስልጣን የመጨበጥ ቅዠት የሚያናውዛቸው ኃይሎች ከሻዕቢያ መሪዎች ጋር የሚዶልቱትን ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ለማስፈፀም ሲባል በሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የሽብር ፈጠራ እንቅስቃሴ ውስጥ ለርካሽ ጊዜያዊ ጥቅም ተገዝቶም ይሁን፤ በጭፍን ጥላቻ ፖለቲካቸው ተገፋፍቶ እጁን ያስገባ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ፤ ከሕግ ተጠያቂነት በላይ ታሪክ ይቅር የማይለው የሀገር ክህደት እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡  የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሕገ መንግስታዊ የቃል ኪዳን ሰነዳቸው ላይ የተስማሙበትን አንድ ጠንካራ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ሂደትን ከማስቀጠል የተሻለ ሌላ አንገብጋቢ አጀንዳ ይኖራቸዋል ተብሎ አይታመንም፡፡

ይህን ነባራዊ እውነታ የሚጠራጠር ወገን ካለም ደግሞ ሀገራችን በዓባይ ወንዝ የውሃ ሀብቷ አማካኝነት ጉባ ሸለቆ ላይ የምትገነባውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሲባል ህዝቡ ከመንግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የሚያደርገውን ፈርጀ ብዙ ጥረት ማስታወስ ብቻ በቂ ማረጋገጫ ይመስለኛል፡፡  የዛሬዋ ኢትዮጵያና የህዝቦቿ ይዋል ይደር የማይባል ወቅታዊ የጋራ አጀንዳ ስለመሆኑ የሚታመንበትን ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ፤ ይበልጥ አጠናክረን ማስቀጠልም ሆነ ዳር ማድረስ እንችል ዘንድ መሟላት ከሚኖርባቸው ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ፤ ዋነኛው አስተማማኝ ሰላምን የመሳፈን ቁልፍ ተግባር ስለመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም መጪው ጊዜ ለህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆንልን እየተመኘሁ ልሰናበት፡፡      

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy