Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬታማ ድሎቻችን ይጠናከሩ!

0 225

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬታማ ድሎቻችን ይጠናከሩ!

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ግጭትና ስር የሰደደ ድህነት ተምሳሌት ተደርጋ ትታወቅ እንደነበር የትላንት ትውስታችን ነው፡፡ ግና በዚህ መጥፎ ምሳሌነት የተሳለችው ሀገራችን ገጽታዋን እየለወጠች ትገኛለች፡፡ መንግስትና መላው ህዝቦቿ አንድነት ፈጥረው ባለፉት 26 ዓመታት ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በዓለም አቀፉ መድረክ በአዲስ ገጽታ መታየት ጀምራለች፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ያላሰለሰ ጥረት ጠንካራና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ከመሆኑም በተጨማሪ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ሀገሪቱ እነዚህን ስኬታማ የሆኑትን ድሎች ለመቀዳጀት የቻለችው ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በተለያዩ ዘርፎች ተቀርጸው ተግባራዊ በተደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካኝነት ነው፡፡

በሀገሪቱ ውጤታማ ከሆኑት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አንዱ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 86 ላይ የተዘረዘሩትን የውጭ ግንኙነት መርሆዎች መሰረት በማድረግ ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ፤ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም፣ ህልውናና ደህንነት ከአደጋ ለመከላከል፣ ገጽታዋን በበጎ ለመገንባትና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማስቀጠል እንዲሁም የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሥርዓትን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ ተቀርጾ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በስራ ላይ ውሏል፡፡

እርግጥ የየሀገሮች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባህሪ፣ ይዘትና ቅርጽ እንደየ ሀገሮቹ ርዕዮተ ዓላማዊ መስመርና እንደሚከተሉት የዕድገት አቅጣጫ ይለያያል፡፡ ከዚህ አኳያ የቅርብ ጊዜ የሀገራችንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ስንመለከት የአለፉት ሥርዓቶች በተለይም የደርግ የውጭ ግንኙነት ከሥርዓቱ አምባገነናዊ ባህሪይ የሚመነጩና በርካታ ጉድለቶችም የነበሩበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ሀገሪቷን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ድቀትና ለማያባራ ጦርነት ዳርጓታል፡፡ ከሰላም ታገኝ የነበረውን ጥቅምም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ ደርግ ይከተለው በነበረው አምባገነናዊ ሥርዓት ሳቢያ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከጎሮቤት ሀገሮች ጋር በጥርጣሬ ከመተያየታቸውም በላይ ግንኙነታቸው ወታደራዊ አቅምን በማፈርጠምና በጠብ መፈላለግ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ በዓይነቱ ሆነ በይዘቱም ተለወጧል፡፡ በጋራ ጥቅምና ህልውናን በማስከበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡  

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሠላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገራችን በሠላምና በዕድገት መጓዝ በጀመረችባቸው ሁለት አስርት ዓመታት ፖሊሲውና ስትራቴጂው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ያስገኛቸው ስኬቶችን እንደሚከተለው መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡

የፖሊሲውና የስትራቴጂው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ነው። በዚህ ስራም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከርም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 22 ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡

በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሠላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረትም በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ የቀጣናው አዋኪ ከሆነው ከኤርትራው ገዥ ፓርቲ በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ሲል ሀገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በጽንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡ ይኸውም የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ጽኑ እና ቁርጠኛ እምነት መያዙ መቻሉ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነጻ ልትሆን የምትችለው፤ ፈጣን የምጣኔ ሃብት ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄዱና ህዝቡም በየደረጃው የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን እንደሆነ በጥብቅ ያምናል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ካሁን በፊት ዘላቂ የልማትና ድህነት ቅነሳና ፈጣን ዘላቂ ልማት ድህነትን የመቀነስ ብሎም የማጥፋት ዕቅድ እንዲሁም ሌሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራሞች በሚገባ ለማሳካት ተችሏል፡፡ ስለሆነም እነዚህን ለመተግበር ከፍተኛ ገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ሰፊ  የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በሀገር ውስጥ የሚገኙት የገንዘብ ምንጮች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው። በፖሊሲው አማካኝነት በዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥረቶች ከለጋሽ ሀገሮችና ድርጅቶች እንዲሁም ከልማት አጋር ድርጅቶች ለፈጣን ልማታችን የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ተችሏል፡፡

በዚህም ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ይህን ማስፈጸምና መፈጸም የሚችል የሰው ኃይል በዲፕሎማሲው ዓለም የሚጠይቀውን ግብዓት ማግኘት የግድ ይላል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ፖሊሲውና ስትራቴጂው ምቹ መሰረት ጥሏል፡፡ በሌላም በኩል በፖሊሲውና ስትራቴጂው በመታገዝ ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል በዓለም መድረክ የአፍሪካውያን ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ ማድረግ የቻለች ሀገር ናት፡፡

ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሀገራት፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተሰሚነት እንዲኖራት አድርጓል፡፡ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአስተማማኝነት መመረጧ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባል መሆኗ፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በተለዋጭ አባልነት መወከሏ እንዲሁም በቅርቡ የቀድሞው የሀገራችን ጤና ጥበቃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸው የሀገራችንን ተቀባይነት ያሳያል። እነዚህ ስኬታማ ድሎቻችን ሊጠናከሩ ይገባል፡፡   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy