Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስደትና ተመላሾች

0 265

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስደትና ተመላሾች

                                                         ይነበብ ይግለጡ

ሳኡዲ አረቢያ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ሰዎች ከሀገሬ ይውጡ ብላ አዋጅ ካስነገረች እነሆ ቀናቱ ተገባደው ሊያልቁ አስራ አንድ ቀናት ብቻ ቀሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም እንደተፈጠሩት ክስተቶች ከመቶ ሺዎች በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በተመሳሳይ ሁኔታ በቀን በርካታ በረራዎችን በማድረግ ዜጎቻችንን በክብር ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ የቻለ ሲሆን ዛሬም ዜጎቹን ለመታደግ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

መንግስት ለዜጎቹ ያለውን ትልቅ ተቆርቋነት አሳይቷል፡፡ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከቀሩት አስራ አንድ ቀናት በኋላ ምን ክስተት ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም፡፡በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገብተን ይህን አድርጉ የማለት መብቱም ስልጣኑም ማንም ሊኖረው አይችልም፡፡

አንድ ሉዐላዊ ሀገር በነጻነት የምትመራበት የምታስተዳድርበት የራስዋ የተከበሩ ሕጎች አሏት፡፡ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነቶች  ችግሮችን ለመፍታት የሚቻለው በወዳጅነት መንገድ በመነጋገርና በመደራደር በዲፕሎማሲ ብስለት ብቻ ነው፡፡ያውም በሕገወጥ ስደተኝነት የአንድን ሉዐላዊ ሀገር ድንበር  በሕገወጥነት ጥሶ በመግባት መኖር የከበደ ወንጀል ነው፡፡በእኛም ሀገር ተመሳሳይ ሁኔታ ቢፈጠር ልናስተናግደው ልንቀበለውም አንፈቅድም፡፡ያውም ለበርካታ አመታት፡፡

ዛሬ አሜሪካንን እያመሳት ያለውም የትራምፕ ፖሊሲ ሕገወጥ ስደተኞች ሀገሬን ለቀው ይውጡ የሚለው ነው፡፡ ስደተኞች አብዛኞቹ ስራና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ  ሀገራቸውን ለቀው ወደሌላ ሀገር በአገኙት ቀዳዳና መንገድ የሕይወት መስዋእትነትም ጭምር ከፍለው በአውሬና በባሕር ላይ ጉዞ ሰምጠው የሚቀሩትን ሳይጨምር እድላቸው ፈቅዶ በሰላም ለመግባት የቻሉትን መኖርና መስራት ይጀምራሉ፡፡

ሰርተው መለወጥና ማደግ የሚፈልጉ የመኖራቸውን ያህል በሰው ሀገርም ገብተው ዘራፊዎች ነፍሰ ገዳዮች ከዚያም በላይ በአሸባሪነት ስራ ተሰማርተው የተለየ አጀንዳ በማራመድ የሚኖሩም አሉ፡፡ ይህንን በርና ቀዳዳ አክራሪ አሸባሪ ኃይሎችም በስፋት ሲጠቀሙበት ታይተዋል፡፡

በሀገሩ በሰላም ሰርቶ የሚኖረው ሕዝብ ስደተኞችን ባስጠለለ የሚዘረፍበት የሚገደልበት ክስተት በሳኡዲ አረቢያ ሲታይ ነበረ፡፡በሕገወጥ መንገድ ሰው ሀገር ተገብቶ እንደገናም ወንጀል ስራ ላይ ተሰማርቶ በመኖር መቀጠል ሕዝብና መንግስትን የከፋ አለመተማመንና ንትርክ ውስጥ አስገብቷቸው ኖሯል፡፡

ይህ ሁኔታ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገሪቱ በገቡት ላይ ከተከሰተ  መንግስት ከመንግስት ጋር በሚያደርገው ሕጋዊ ንግግር ችግሩ ሊፈታ ይችላል፡፡ሰዎቹን አስሮ ወደሀገራቸው ይመልሳል፡፡በሕገወጥ መንገድ የገቡት ሰዎች ማንነት ዜግነት ተለይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የሀገሩ መንግስት የሚወስደው እርምጃ እጅግ የከፋ ነው ፡፡

የሳኡዲ አረቢያ የ90 ቀናት የምሕረት የጊዜ ገደብ ሰጥታ ውጡልኝ ካለችበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቻችንን ቦታው ድረስ ሄዶ በማነጋገር መታወቂያ ሊሴ ፓሴ እዚያው በውጭ ጉዳይ ሰራተኞች አማካኝነት ተሰርቶ እየተሰጣቸው የተመዘገቡት  የውጭ ጉዳይ ቃለአቀባይ አቶ መለስ አለም  በገለጹት መሰረት  በአጠቃላይ 82 ሺህ 343 ብቻ ናቸው፡፡

ከ400 ሺህ በላይ  ከሚገመቱ ኢትዮጵያውያን መካከል እስከአሁን የተመዘገበው ቁጥር ሲታይ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ይህ ጉዳይ አሁንም እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ወገኖቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ ሕጻናቱም ልጆቻችን ሁሉም የእኛው ስለሆኑ ከልብ ያስጨንቀናል፡፡ ያሳስበናል፡፡

በአጠቃላይ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የጉዞ ሰነድ የወሰዱት 82 ሺህ 343 የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጾል፡፡ ከሠላሳ ሺህ በላይ የሚሆኑት አገራቸው ገብተዋል ፡፡ ስደተኞችን ከመመለሱ ስራ ጎን ለጎን ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የማድረጉም ስራ ከክልል መንግስታት ጋር እየተሰራበት እንደሆነም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

የሜድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እና እህት ካምፓኒዎቹ ለተመላሾቹ የአስር ሚሊዮን ብር የገንዘብ እርዳታ ለግሰዋል፡፡ካምፓኒው ነጻ ስኮላር ሽፕ  ለ100 ተመላሾች ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚገኙ 100 ሕጻናትን ለማስተማር እንዲሁም ለ100 ተመላሾች የስራ እድል እንደሚሰጥ ገልጾአል፡፡ይህም ትልቅ ወገናዊ አጋርነትን መግለጫ ነው፡፡ድርጅቱ ባለው አቅም ለወገኖቻችን የበለጠ የስራ መሰክ መፍጠርም ይችላል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በሰኔ 28 /2009 እንደሚከበር አስታውቋል፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ ከ850 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን አለም አቀፉ የስደተኞች ቀን የሚታሰብበትና የሚከበርበት ዋናው ምክንያት ሀገራችን እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ለበርካታ አመታት አስጠግታ በማኖርዋ ያደረገቸውን አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ነው፡፡

ከሰደት ተመላሾቹ ለዋልታ ኮርፖሬት በገለጹት መሰረት ሳዑዲ አረቢያ የሰጠችው  የምሕረት ቀናት ከተጠናቀቀ በኋላ ሊከሰት የሚችለውን ችግርና መጉላላት ለመቀነስ እንዲቻል ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተሰጠው ጊዜ ወደ ሀገራቸው እንደገቡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

አየለች ሸዋረጋ እንደገለጸችው የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የአውሮፕላን በረራ ዋጋን በሀምሳ በመቶ በመቀነስ እቃዎችም ከቀረጥ ነፃ በሆነ መልኩ እንዲያስገቡ መፍቀዱ ለዜጎቹ ያለውን ድጋፍ ያሳያል በማለት ለመንግስት ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡ አየለች አያይዛም በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህን መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ገልጻለች፡፡  

ኢትዮጵያውያን ከአገር ውጪ ሲወጡ እንደሚሰሩት በጥንካሬ አገራቸው ላይ መስራት ቢችሉ ውጤታማ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች በብዛት በመኖራቸው በሀገራቸው ሰርተው ለመለውጥ መጣር አለባቸው ስትል አስተያየትዋን ሰጥታለች፡፡

በሳዑዲ ኑሮ ቀላል አይደለም፤ የትምህርት፣ የእውቀት ወይም የክሕሎት አቅም ሊኖር ይገባል፡፡ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሰርተው ሕይወትን መቀየር እንደሚቻል በማመን መስራት ይገባቸዋል ወይም ሕጋዊ በሆነ መልኩ ራሳቸውን ለሥራ መስኮች ብቁና ተወዳዳሪ በማድረግ በሌሎች አገራት መስራት የሚያስችላቸውን አቅም ማጎልበት ይኖርባቸዋል ሲል ጀማል አሕመድ ገልጾል፡፡

ቅድስት አዳል በበኩልዋ በሳዑዲ አረቢያ ለአምስት ዓመታት ያህል ስትሰራ እንደነበርና አሁን ግን ተወልዳ ባደገችበት ከተማ ምንጃር ሸንኮራ ከእህቷ ጋር በመሆን በአነስተኛ ኢንቨስትመንት ሥራ ለመጀመር ማቀድዋን ተናግራለች፡፡

በሕገወጥ መንገድ ወጥተው ለመመለስ ያልተመዘገቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ350 ሺህ በላይ ሊገመት የሚችል መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለው ሰፊ ጥረት የቀጠለ ቢሆንም እስከ አሁን የተመለሱትና ለመመለስ የተመዘገቡት ዜጎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ቢሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ በመንግስት በኩል ጥረቱ በከፍተኛ ትኩረት ቀጥሏል፡፡

በነዚህ አስራ አንድ ቀናት ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ቤተሰብ ጓደኛ ዘመድ ወዳጅ የሆነ ሁሉ በሳኡዲ አረቢያ በሕገወጥ መንገድ ገብተው የሚኖሩ ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከፍተኛ ውትወታ በማድረግ ሊያነቋቸው ይገባል፡፡ የሚፈጠረው አይታወቅምና በኋላ ከመጸጸት ወደሀገራቸው ፈቃደና ሆነው እንዲመለሱ ማድረጉ የተሻለ ነው፡፡መቼም በሰው ሀገር ሕግን ጥሼ ልኑር ማለት የማይሞከርና የማይቻል መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy