Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሕገወጥ ስደት ተጠቃሚ የለም !!

0 530

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሕገወጥ ስደት ተጠቃሚ የለም !!

                                                    ይነበብ ይግለጡ

 

በሕገወጥ ስደት ከሀገር መውጣት ዜጎቻችን ብዙ የከፉ ችግሮችን፣ መከራዎችንና ፈተናዎችን እንዲጋፈጡ ከማድረጉም በላይ በዋነኛነት ሰብአዊ ክብራቸውና መብታቸው የሚጣስበት የሚረገጥበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ተፈጥሮ ታይቷል፡፡ለሕገወጥ ስደቱ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ሕገወጥ የሰው ንግድና ዝውውርን መደበኛ ስራቸው አድርገው  የሚገኙ ግለሰቦች ስለሆኑ እነዚህን በተለያየ ጊዜና ደረጃ ሕብረተሰቡ እያጋለጠ መንግስትም በሚያደርገው ክትትል የተያዙ ለህግና ለፍትሕ የቀረቡ የተቀጡም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ይህን በተመለከተም ብዙ ያልተሄደበት ስለሆነ አሁንም ብዙ ስራ ይቀረናል፡፡

 

በሕገወጥ ስደት ግለሰብ ፣ቤተሰብም ሆነ ሀገር ለዘለቄታዊ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ትርፉ ታላቅ ጉዳትና ውርደት ብቻ ነው ፡፡ሰሞኑን በአለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኖ የከረመው የሳኡዲ መንግስት ያወጣው አዋጅ ከሕገወጥ የውጭ ሀገራት ስደተኞች ነጻ የሆነች ሳኡዲ አረቢያን ማየት በሚለው እሳቤያቸው መሰረት በሕገወጥ መንገድ ወደሳኡዲ አረቢያ ገብተው የሚኖሩ ሰዎች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን በተሰጣቸው የምሕረት ጊዜ ገደብ ለቀው እንዲወጡ አዘዋል፡፡

 

ይህ ከሀገሬ ውጡልኝ በሚል የተሰጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ሃያ ያህል ቀናት ብቻ ይቀሩታል፡፡32.7 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ 9 ሚሊዮን ያህሉ በሕጋዊነት ገብተው የሚሰሩ የውጭ ዜጎች ሲሆኑ 2 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ገብቶ የሚኖር ነው፡፡ከዚህ ተጠቃሽ ቁጥር ውስጥ ከሁለት መቶ እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚደርሱት ደግሞ የእኛው ዜጎች መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

አስገራሚው ነገር ይህን ያህል የገዘፈ ቁጥር ያለው ሕዝብ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የተለያዩ ዘዴና መንገዶችን እየተጠቀሙ ከሀገር እንዲወጡ ሲያደርጉ የዛኑም ያህል በሕገወጥ የሰው ዝውውርና ንግድ ተሰማርተው ሕብረተሰቡን ሲገፉትና ከአቅሙ በላይ እያስከፈሉ ሲጫወቱበት ይሄንን ጉዳይ የሚከላከልና ለሕግ የሚያቀርብ መንግስታዊ አካል ምን ሲሰራ ኖረ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የለም፡፡ከዚህ ቀደም ከዚህችው ሀገር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በሕገወጥ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው የነበሩ ዜጎቻችንን የኢትዮጵያ መንግሰት ከሳኡዲ መንግስት ጋር በመነጋገር በተደጋጋሚ የአውሮፕላን በረራ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አደርጓል፡፡ስልጠና ወስደው በፈለጉት መስክ የመንግስትም የገንዘብ ድጋፍ ታክሎበት የየራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡አስገራሚው ነገር በአብዛኛው በተለያየ መንገድና ዘዴ ተመልስው ከሀገር መውጣታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች አሉ፡፡በሀገራቸው ሰርተው የተለወጡ ያደጉም አሉ፡፡

 

የስደትና የሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ጉዳይ ቋሚ መፍትሄ የሚያገኘው ሙሉ በሙሉ ከድሕነት መውጣት ስንችል ብቻ ነው፡፡እየሰራንም ከድህነት ለመውጣት ትግል እየተደረገም ይህንን ችግር መከላከል ግድ ይላል፡፡አቅም በፈቀደ እልባት ሊበጅለት ይገባል፡፡አሁንም ችግሩ ተመልሶ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንደሚሆን ልብ ልንለው ይገባል፡፡ሳኡዲ አረቢያ በሀገርዋ ማንም ሰው በሕገወጥ መንገድ መኖር የለበትም ብላ መወሰንዋ ከራስዋ የውስጥ ደህንነት ጋር የተያያዘ ጉዳይ በመሆኑ ማንም በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ይህን አድርጊ ይህንን አታደርጊ ማለት አይችልም፡፡እኛም ቢሆን ልናደርገው የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ መንግስት በሳኡዲ የሚገኙት ዜጎቹ በምሕረት አዋጁ የተሰጠው ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት በተቻለ መጠን ወደሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡በሳኡዲ እስካሁን ወደሀገራቸው የተመለሱት 20 ሺህ ያህል የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ይህ ቁጥር እጅግ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር ያሳስባል፡፡ያስጨንቃል፡፡ለምን ቢባል የሳኡዲ መንግስት የሰጠው የጊዜ ገደብ ካለፈ በኃላ ማንኛውንም እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ለምን ተብሎ ሊከሰስ ሊወቀስ አይችልም፡፡ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ለዚሁ በመሆኑ ነው፡፡

 

ዜጎቻችን ነገ የአዋጁ ቀን ካለፈ በኃላ ምን ይገጥማቸዋል የሚለውን ጉዳይ  በእጅጉ አሳሳቢ አስጨናቂም ነው፡፡ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ዜጎች ወደሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ የወተወቱት፡፡እባካችሁ ወደ ሀገራችሁ በሰላም ተመለሱ የሚል ጥሪ ያስተላለፉት፡፡

 

በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ይህንኑ በሳኡዲ በሕገወጥ መንገድ ገብተው የሚኖሩትን ዜጎቻችንን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ቡድን ይዘው ሳኡዲ አረቢያ በመግባት ከባለስልጣናቱም ጋር በመነጋገር በዜጎቻችን ላይ ችግረ ሳይፈጠር ወደ ሀገራቸው መመለስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረዋል፡፡እዛው የሚኖሩ ዜጎችን ተዘዋውረው አነጋግረዋል፡፡

በሀገር ውስጥም ከተመለሱ በኃላ ወደስራ የሚሰማሩበትን መንገድ በመፈለግ ረገድ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቡድን ሚኒስትሩ በመሩት ስብሰባ ላይ በመሳተፍ የተለያዩ ሀሳቦችን ተወያይቶአል፡፡፡አቅም ያላቸው ካምፓኒዎችና ድርጅቶች ተመላሽ ዜጎችን ተቀብለው በቀጥታ ወደስራ የሚሰማሩበትን መንገድ እንዲያመቻቹ መግባባት ላይ ተደርሶአል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy