Artcles

በመከላከል ላይ የተመሰረተውን የጤና ፖሊሲ ትክክለኛነት ያረጋገጠ ድል

By Admin

June 05, 2017

በመከላከል ላይ የተመሰረተውን የጤና ፖሊሲ

ትክክለኛነት ያረጋገጠ ድል

ስሜነህ

በሃገራችን ባለፉት ሥርዓቶች ለረዥም አመታት ተንሰራፍቶ በቆየው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድህነት ኋላቀርነት ጋር በተያያዘ እንደ ሌላዉ የልማት ዘርፍ ሁሉ ህዝባችን በጤናው ዘርፍም ተጠቃሚ ያልነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡የደርግ መንግስት በሃይል በተገረሰሰ ማግስት በኢህአዴግ የሚመራው የሽግግር መንግስት በጦርነት የፈራረሱ የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባት፣ በየአካባቢው የተዘጉ የጤና ተቋማትን ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የማድረግን ሥራ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ በፍጥነት አከናውኗል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐንም የህዝቡን የጤና ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል፣ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ፣ በሽታን መከላከል ላይ የሚያተኩር የጤና ፖሊሲ እንዲሁም እስትራቴጂ የዘርፉን ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላትን በስፋት ባሳተፈ ሁኔታ በ1986 ዓ.ም ተነድፎ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡

የጤና ፖሊሲያችን በዋናነት በሽታን በመከላከል ላይ የሚያተኮር ቢሆንም ከዚሁ ጐን ለጐን መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን የማስፋፋቱም ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በ1996 ዓ.ም ተቀርፆ ሥራ ላይ የዋለው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻልና በሽታን በመከላከሉ ስራ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክቷል፡፡ በመላ ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ የተሰማሩ ከ39ሺ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ባለቤትነት በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጐችን ለመፍጠር የተነደፈውን ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፤ በመጫወትም ላይ ናቸው።  በዚህም በወባ ምክንያት የሚከሰት ሞት ከ60 በመቶ በላይ ቀንሷል፡፡ የቲቢ በሽታ ስርጭት እየቀነሰ ከመሆኑም በላይ በሽታውን በአግባቡ አክሞ የማዳን መጠን ከ80 በመቶ በላይ ስለመድረሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡

የእናቶችና ህፃናት ጤና ቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው የጤናው ዘርፍ ልማት አጀንዳዎች ናቸዉ፡፡ በ1982 ዓ.ም በሀገራችን ከ100ሺ በህይወት ከሚወልዱ እናቶች መካከል 1200 የሚሆኑት ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ ወቅት እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ከሆኑ 1000 ህፃናት መካከል ከ200 በላይ ይሞቱ ነበር፡፡ የእናቶችን እና ህፃናትን ሞትን ለመቀነስ የተቀመጠውን የምዕተ አመቱን ግብ ለማሳከት በሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ሥራ በመሰራቱ ዛሬ ከ100ሺ እናቶች የሞት መጠኑ 350 በታች ወርዷል። ከ5 አመት በታች ዕድሜ ከ1ሺ ህፃናት ውስጥ የሞት ቁጥሩ 68 በታች ዝቅ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከ5 ዓመት ዕድሜ በታች ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የተያዘውን የምዕተ ዓመቱን ግብ ከተያዘው ጊዜ በሶስት አመት አስቀድማ አሳክታለች። የእናቶች ሞትንም በ69 በመቶ ዝቅ በማድረግ እቅዱን ቀድማ አሳክታለች። በአጠቃላይ ሲታይ በጤናው ዘርፍ የተቀመጡ የምዕተ አመቱን ግቦችን ሀገራችን በአብዛኛው ከተቀመጠው ጊዜ በፊት ማሳካት ችላለች፡፡

በተለይም የህዳሴው መስመር ተግባራዊ መደረግ ከጀመረባቸው 15 አመታት ወዲህ በሃገራችን በጤናው ዘርፍ ልማት በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸው በርካታ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በተለይ በማህበረሰብ ደረጃ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምና በጤና ልማት ሰራዊት አደረጃጀቶች የተሰሩ ሥራዎችና የተገኙ ምርጥ ልምዶች ከሃገራችን አልፎ በርካታ የአፍርካና ሌችም ታዳጊ አገሮች በመቅዳት ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የሴቶች የጤና ልማት አደረጃጀት በዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂያችን ደግሞ ለመላው አፍሪካ ተሞክሮ ከመሆንም አልፎ የአለም የጤና ድርጅትም ትኩረት በመሆን ፖሊሲውን በማስፈጸም በኩል ሰፊ ድርሻ የነበራቸውን ግለሰብ የድርጅቱ ዳይሬክተር አድርጎ በመምረጥ የፖሊሲያችንን ትክክለኛነት አረጋግጦልናል።

ጤናውም መስክ የተመዘገበው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ መከላከልን ማዕከል ባደረገውና ከዚህ በተጨማሪ በህክምና የሚፈወሱ በሽታዎችን ለማከም የሚያግዙ የተለያዩ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ላይ ያነጣጠረው የጤና ልማት እንቅስቃሴያችን የምዕተ ዓመቱን ግቦች ከማሳካትም በላይ የህዝባችንን መሰረተ ሰፊ ተጠቃሚነት ያረጋገጥንበት ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ በማስፈጸም በኩል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የነበራቸው ትጋትና ድርሻ ከፍተኛ ነበር። አገራችን ለረጅም ዘመናት በቀላሉ ሊፈወሱ ይችሉ በነበሩ በሽታዎች ስትጠቃ የቆየች አገር ነች፡፡ የዚህ ጥቃት ዋነኛ ሰለባዎች ደግሞ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ እንዲሁም የከተማው ሰፊ ህዝብ ነበሩ፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ በሳይንሳዊ አኳኋን በመመራት ሊወገዱ ይችሉ በነበሩ ተዛማች በሽታዎች የሚጠቁ ስለነበሩ ከጤና እክል ጀምሮ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና ድረስ ለሚዘልቅ ጉዳት ሲዳረጉ ኖረዋል፡፡

ይህ ሂደት መቋረጥ የጀመረው ልማታዊ መንግስቱ መከላከልን ማዕከል ያደረገ የጤና ፖሊሲ ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ እና ዶ/ር ቴዎድሮስ በመሪነት ፖሊሲውን ማስፈጸም ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ ነድፋ በመስራት የሚሊኒየሙን የልማት ግብ አስቀድማ ማሳካት እንድትችል የእርሳቸው አስተዋጽኦ ጉልህ የነበረ ለመሆኑ አሁን በአለም መድረክ ፊት የተሰጣቸው ድምጽ ያረጋግጣል።

70ኛው የአለም ጤና ድርጅት መደበኛ ስብሰባ በተካሄደበት ቀን ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት በእጩነት ከቀረቡት ከብሪታንያዊው ዴቪድ ናባሮ እና ከፓኪስታናዊቷ ሳኒያ ኒሽታር ጋር ብርቱ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን ፤ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከላይ በተመለከተው የጤና ፖሊሲ ላይ ተመስርተው ባከናወኗቸው አመርቂ ውጤቶች በመመረጥ በመከላከል ላይ የተመሰረተው የጤና ፖሊሲያችንን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ችለዋል።  

በምርጫው ቀን ኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በመልበስና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ዶ/ር ቴዎድሮስን ደግፈው በጄኔቫ አደባባይ ላይ መታየታቸውን በማህበራዊ ድረ-ገፆቹ ላይ ተመልክተናል። እነዚህ ደጋፊዎች ታዲያ በድጋፍ ሰልፋቸው ላይ ሲያሳዩ የነበሩት መፈክሮች ዶክተሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የእናቶችና ህጻናትን ሞት በመቀነስ ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ቀድማ እንድታሳካ ማስቻላቸውን የሚያመላክቱ ናቸው ።  

ዶ/ር ቴዎድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከአለም አገሮች ጋር ያላት የዴፕሎማሲ ግንኙነት እንዲጠናከርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የጀርመንና አሜሪካ ድምጽ ሬዲዮን ጨምሮ የተለያዩ ድረ ገፆች ዘግበዋል።

የ52 ዓመቱ ጎልማሳ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከትግራይ ብሄራዊ ክልል ጤና ቢሮ የጀመረው የአመራርነት ስኬታቸው ለአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት አብቅቷቸዋል።ከእነዚህ ስኬቶቻቸው መካከል የህጻናትና እናቶች ጤና መሻሻል እንዲሁም በልጅነት ልምሻና የወባ በሽታ ቅነሳን የተመለከተው ዋነኛው እንደሆነ ድምጽ የሰጧቸውን ሃገራት ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የጤና ተቋማትም መስክረዋል። ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ በተካሄደው የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ፣  194 አገሮች ድምፅ የሰጡበት የምርጫ ሥነ ሥርዓት ለእኛ የነበረው ትርጉም የተለየ ነው። ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ በመጀመሪያው ዙር 95 ድምፅ፣ እንግሊዛዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ 52 ድምፅ፣ ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ደግሞ 38 ድምፅ በማግኘታቸው፣ ዶ/ር ቴዎድሮስና ዶ/ር ናባሮ ወደ ሁለተኛው ዙር አልፈዋል፡፡ፓኪስታናዊቷ ሳኒያ ኒሽታር በመጀመርያው ዙር ከውድድሩ ውጪ ሲሆኑ፣ በሁለተኛው ዙር በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓትም ዶ/ር ቴድሮስ 121 ድምፅ፣ እንግሊዛዊው ዶ/ር ናባሮ ደግሞ 62 ድምፅ በማግኘት ሁለት – ሦስተኛ በሚባለው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት መሠረት ወደ ሦስተኛ ዙር ተሸጋግረዋል፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ በሦስተኛው ዙር 138 ድምፅ በማግኘት ሲያሸንፉ፣ እንግሊዛዊው ዶ/ር ናባሮ 50 ድምፅ በማግኘት ከፉክክሩ ተሰናብተዋል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ ከአፍሪካ፣ ከካረቢያንና ፓስፊክ አገሮች ቀድሞውኑ ሙሉ ድጋፍ አግኝተዋል። በዚህም በድርጅቱ ኢትዮጵያንም አፍሪካንም የወከሉ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ለመሆን በቅተዋል።የአለም የጤና ድርጅት ከተመሰረተ 70 ዓመታት ያስቆጠረ  ቢሆንም፤ በአፍሪካዊ ዋና ዳይሬክተር ሲመራ የመጀመሪያው ነው።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመስራት የጤና ሽፋንን ማሳደግና በሽታን መከላከል እንደቻለ መሪ እንጂ የአፍሪካ ብቸኛ ተወካይ በመሆናቸው የመራጮችን ድጋፍ ማግኘት እንደማይፈልጉ ዶ/ር ቴዎድሮስ በዚያኑ ቀን ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል። በእርግጥም ዶ/ርን ያስመረጣቸው የአፍሪካ ተወካይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በመከላከል ላይ የተመሰረተው የጤና ፖሊሲያችን እና የማስፈጸም ብቃታቸው መሆኑን ያጠይቃል ።

ዶክተር ቴዎድሮስ ለሰው ልጅ ቅድሚያ በመስጠት የአለም የጤና ሽፋንን አሁን ካለበት የተሻለ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ የመጨረሻ ዙር በሆነው ንግግራቸው ላይ አረጋግጠዋል።የሴቶች፣ የህጻናትና የወጣቶች የጤና ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ከዚህ ሌላ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመቀነስ ቁርጠኛ መሆናቸውንም በዚሁ ዙር አረጋግጠዋል።

የ194 አገሮች የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በ70ኛው የጄኔቫ የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ በተካሄደው የዋና ዳይሬክተርነት የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ ለሰው ልጆች የጤና ችግር የሆኑትን ተላላፊ በሽታዎች ማለትም እስከ ኢቦላ ድረስ ያሉትን ለመዋጋት፣ ለመከላከልና ብሎም ለማጥፋት ቃል ገብተዋል፡፡ በሁለት ዓመታት የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትም በዓለም ጤና ድርጅት የተለየ ሐሳብና አተያይ በማምጣት አሁን ያለውን የዓለም ጤና ሥርዓት እንደሚለውጡት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል፡፡  በአፍሪካ ኅብረትና በኢትዮጵያ መንግሥት አማካይነት ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ግብፅን ጨምሮ የተለያዩ የእስያና የፓስፊክ አገሮችን ድጋፍ በማግኘት ለአሸናፊነት መብቃታቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡በስድስት ተፎካካሪ ግለሰቦች ተጀምሮ የነበረው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የምርጫ ቅስቀሳ በመጨረሻ ሦስት ተፎካካሪዎችን አስቀርቶ፣  ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ላይ በመከላከል ላይ የተመሰረተውን የጤና ፖሊሲ ትክክለኛነት ባረጋገጠ ድል  ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡