Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሰጥቶ መቀበል መርህ ተመሩ

0 404

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሰጥቶ መቀበል መርህ ተመሩ

ኢብሳ ነመራ

በመንግስት የስራ ዘመን አቆጣጣር 2009 ሊያበቃ ከአንድ ወር በታች ጊዜ ቀርቶታል። በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት የሃገሪቱ ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2010 የመንግስት ባጀት የማጽደቅ ሂደት ላይ ይገኛል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 30፣ የ2010ን ባጀት አጽድቆ ለእረፍት ይበተናል፣ በቀጣይ ዓመት ጥቅምት ተገናኝቶ የስልጣን ዘመኑን ሶስተኛ የስራ ዓመት ሊጀምር።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2009 የስራ ዘመኑን ጥቅምት ላይ ሲጀምር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ባካሄደው የጋራ ስብሰባ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት የስራ ዓመት የመክፈቻ ንግግር የዓመቱን የስራ ክንውን ዝርዝር ገልጸው ነበር። ከእነዚህ በፕሬዝዳንቱ ንግግር ከተዘረዘሩ ተግባራት መሃከል፣ ምን ያህሉ ተከናወነ? የሚለውን በየጉዳዩ እያነሱ መመለከት አስፈላጊ ነው። በዚህ ጽሁፍ የሃገሪቱን ዴሞከራሲ ወይም የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ከማስፋት ጋር በተያያዘ ተገልጾ የነበረውን የተግባር እቅድ ለመመለከተ እሞክራለሁ።

በምክር ቤቶች የስራ ዓመት መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር ካነሷቸው ጉዳዮች መሃከል አንዱ የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር የሚመለከት እንደነበረ ይታወሳል። ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ፤  

. . . ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ከማበልፀግ አኳያ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ በሃገራችን የፍላጐት ብዙህነት እንዳለ ተገንዝቦ፣ እነዚህን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለፅ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የምክር ቤቶቻችንን ተዋፅኦ የማጐልበት ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ሃገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርዓት በመመራት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት በድምሩ  ለአስር ጊዜ ሃገራዊ፣ ክልላዊና ከባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ  የህዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ በሃገራችን ወሳኙ የስልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል። በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በህግ ማእቀፍ በተደገፈ አኳኋን የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል።

ብለው ነበር።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ይህ ዴሞክራሲውን ስርአቱን የማበልጸግ እቅድ ተግባራዊ የሚሆንበትንም መንገድ አስመልክተው የገለጹት ነገር ነበር። ይህን አስመልከተው ሲናገሩ፤

የሃገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል። ሃገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ ሃገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል። ስለሆነም የምርጫ ህጋችን የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል። ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና ሃገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት የሚፈፀም ይሆናል።

ነበር ያሉት

ይህ በ2009 የመንግስት የስራ ዘመን ይካሄዳል የተባለ የሃገሪቱን ዴሞክራሲ የማበልጸግ ጉዳይ በመንግስት ወይም በገዢው ፓርቲ የተሰጠ ችሮታ አይደለም። ይልቁንም ነባራዊው ሁኔታ የግድ ያለው የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ወቅቱ በሚጠየቀው ልክ የማጎልበት እርምጃ ነው። ነባራዊው ሁኔታ የወለደው የዴሞክራሲው መጎልበት ሂደት ውጤት በመሆኑ ምላሽ ከመስጠት ውጭ አማራጭ የለም።

ይህን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ በፕሬዝዳንቱ ንግግር እንደተገለጸው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ድርድር ለማካሄድ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጥር ወር መግቢያ ላይ በሃገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አስተላልፏል። ኢህአዴግ ጥር 6፣ 2009 ዓ/ም ባስተላለፈው ጥሪ፣ በሃገር ውስጥ እውቅና ካገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመከራከርና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ፣ ድርጅቱ እንደ ገዢ ፓርቲ በጋራ ከመስራት አኳያ የነበረበትን ውስጣዊ ክፍተት በመለየት በሃገራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት መዘጋጀቱንም በጥሪው አስታውቆ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ ቀደም ሲልም አብሮ ለመስራት ፍላጎቱ ካላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት መስርቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሶ፣ ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ማናቸውም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነትም ባስተላለፈው ጥሪ አስታውቆ ነበር። ኢህአዴግ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ውይይትና ድርድር ያደርጋል፤ በሚለያዩባቸው ጉዳዮች ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ክርክር ያካሂል ሲልም ገልጿል።

ኢህአዴግ ጥሪውን ባስተላለፈ ማግስት በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ሂደት ለመጀመር በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባሰቡ። በውይይታቸው መጀመሪያ በሀገር ጉዳይ ላይ መወያየት፣ መከራከርና መደራደር አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም?  ኢህአዴግ በተነሳሽነት የጠራው ውይይት አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነበር የተነጋጋሩት። በአነዚህ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል፤ ሁሉም በውይየቱ አስፈላጊነት ላይ ተስማምተው ነበር። በማያያዝ፤ የስብሰባ ስነስርአት፣ የመድረክ መሪነት አካሄድ፣ የፕሬስ መግለጫ  አሰጣጥ፣ የውይይት ታዛቢ ማንነት ላይ ተወያይተዋል።

ከዚህ በኋላ አንድ የጋራ የድርድር ረቂቅ ደንብ ወደማዘጋጀት ተሸጋገሩ። በዚህ መሰረት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም፣ ፍላጎትና ሃሳብ መሰረት ያደረገ የፓርቲዎች ክርክርና ድርድር ረቂቅ ደንብ እንዲያዘጋጅ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁመው፣ ኮሚቴው አዘጋጅቶ ያቀረበውን ደንብ አጽድቀዋል። በዚህ የሃገሪቱን ዴሞክራሲ የማበልጸግ የድርድር ሂደት ላይ የሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ነበር። በመጀመሪያ ከኢህአዴግ በስተቀር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ያስፈልገናል የሚል አቋም ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ በቀጣይ ስብሰባ አስራ አንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ያሰፈልጋል የሚለውን አቋማቸውን ቀየሩ። ስድስት ፓርቲዎችን የያዘው ሌላው ቡድን ደግሞ ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ያስፈልጋል የሚለውን አቋምን ባይቀይርም፣ ይህ አቋሙን በልዩነት አስመዝግቦ በድርድሩ ለመቀጠል ተስማማ። ከዚህ በኋላ ድርድሩን ከመሃከላቸው በሚመረጥ አደራዳሪ ወይም አወያይ ለመምራት ተስማሙ። እዚህ ላይ ሁለት ፓርቲዎች ራሳቸውን ከድርድሩ ውጭ አድርገዋል፤ መደረክና ሰማያዊ ፓርቲ።

በድርድሩ ለመቀጠል የተስማሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመሃከላቸው አደራዳሪ ወደመምረጥ ሂደት ተሸጋገሩ። የአደራዳሪዎቹ ቁጥርም ሶስት እንዲሆን ተስማሙ። ለአደራዳሪነት የተመረጡት አቶ አሰፋ ሀብተወለድ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የአደራዳሪው ሰብሳቢ፣ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ከኢዴፓ (የኢትዮጵያውያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) የአደራዳሪው ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ አለማየሁ ደነቀ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) የአደራዳሪው ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል። በአደራዳሪነት የተመረጡት ግለሰቦች በድርድሩ ሂደት የአደራዳሪነት ሚና ብቻ እንዲኖራቸው የፖለቲካ ፓርቲያቸውን በመወከል በተደራዳሪነት የማይቀርቡ መሆኑ ላይ ተስማምተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአጀንዳ አደራጅና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ አባላትንም መርጠዋል። በምርጫው ወቅትም ፓርቲዎቹ ኢህአዴግ ድርድሩን የጠራ በመሆኑ፣ በአጀንዳ አደራጅና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፍ ተስማምተዋል። ቀሪዎቹ የኮሚቴው አባላት፣ አቶ ገብሩ በርሄ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (አዴህ) የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ አቶ መላኩ መሰለ ከኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) የኮሚቴው አባላት ሆነው ተመርጠዋል። ኢህአዴግ በኮሚቴው ውስጥ በአቶ አስመላሽ ገብረስላሴ ተወክሏል።

በመቀጠል በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት ፓርቲዎች ላቋቋሙት የአጀንዳ አደራጅ ኮሚቴ መደራደሪያ አጀንዳቸውን አቀረቡ። የአጀንዳና የሚዲያ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ (ኢዴህ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ እንደገለጹት፣  የአጀንዳ ኮሚቴው ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ከ17 ፓርቲዎች የመወያያ አጀንዳዎችን ተቀብሏል። ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው ከ1 እስከ 34 የሚደርሱ የመወያያና የመደራደሪያ አጀንዳዎች ማቅረባቸውን፤ የአጀንዳዎቹ ይዘትም ከፖለቲካ ምህዳር መጥበብ እስከ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ድረስ የሚሸፍኑ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘው የድርድር ታዛቢዎች ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳልፈዋል። በዚህ ውሳኔ መሰረት ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው ሁለት ታዛቢዎች እንዲያቀርቡ ተስማምተዋል። በራሳቸው ከሚያመጧቸው ታዛቢዎች በተጨማሪ፣ በሁሉም ፓርቲ ስምምነት መሰረት ገለልተኛ የሆኑ 12 የውጭና የአገር ውስጥ ድርጅቶች በታዛቢነት እንዲሳተፉም ተስማምተዋል። ታዛቢ ድርጅቶቹ ከኢምባሲዎች፣ ከሲቪክና ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች የተውጣጡ ይሆናሉ ተብሏል። እንደታዛቢ ድርጅቶቹ ባህሪ ከአንድ እስከ አምስት ተወካዮች ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህን ተከትሎ ፓርቲዎቹ የታዛቢዎች የስነምግባር ደንብ አጽድቀዋል። ፓርቲዎቹ ያጸደቁት የታዛቢዎች የስነ ምግባር ደንብ ዘጠኝ አንቀፆችን የያዘ ነው። ይህም የታዛቢዎችን ተግባር የሚወስንና ድርድሩን ስለሚታዘቡበት ስርአት እንዲሁም ታዛቢዎች ከሚዲያ ጋር የሚኖራቸውን መስተጋብር የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘ ነው። ታዛቢዎች አንድ የድርድር አጀንዳ ከተጠናቀቀ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ መስጠት እንደሚችሉ፣ በሌላ በኩል ባልተቋጨ አጀንዳ ዙሪያ መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ በደንቡ ላይ ተደንግጓል። እንዲሁም ታዛቢዎች ከመታዘብ ውጭ አስተያየትና ሐሳብ ማቅረብ እንደማይችሉ ይገልጻል። አሁን ፓርቲዎቹ በድርድር ታዛቢዎች ፊት የመደራደሪያ አጀንዳቸውን አጽድቀው ወደድርድር ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው፤ ምናልባት የቀናት ጊዜ ነው የቀራቸው።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል የሚካሄደው ድርድር የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ወይም የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠየቀው ልክ ለማጎለበትና ለማስፋት በ2009 በጀት ዓመት እንዲከናወን የተያዘ ተገባር ነው። ድርድር ለማካሄድ ተይዞ የነበረው እቅድ ተሳክቷል ማለት ይቻላል።

እንግዲህ የድርድሩ መድረሻ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሳይሆኑ ህዝቡ ነው። የድርድሩ ግብ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምጽ የሚሰማበት፣ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎቶቹ በሙሉ የሚጠበቁበት የላቀ ዴሞክራሲን መገንባት ነው። እናም ተደራዳሪዎቹ የሚይዙት አቋም  ትክክለኛ፣ ተጨባጭና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይጠበቃል። ድርድሩ እኔ ያልኩት ተቀባይነት ካላገኘ ሞቼ እገኛለሁ በሚል መንፈስ መካሄድ እንደሌለበትም ማስታወስ አለባቸው። በድርደሩ ላይ የሚሳተፉት ሁሉም ፓርቲዎች ለህዝብ ይጠቅማል የሚሉትን አቋም ይዘው ስለሚቀርቡ ድርድሩ በሰጥቶ መቀበል መርኸ መካሄድ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy