NEWS

በስሚንቶ ስር የተደበቀ ሺሻ ተያዘ

By Admin

June 11, 2017

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዳማ ቅርንጫፍ ስሚንቶ በጫነ ተሽከርካሪ ተደብቆ ሊያልፍ የነበረ 215 ሺህ ብር ግምት ያለው ሺሻ መያዙን አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ የህግ ማስከበር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ለታ እንደገለፁት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-45423 አ.አ በሆነ አይሱዙ የጭነት መኪና ከላይ ለሽፋን ከጫነው 40 ከረጢት ሲሚንቶ ስር ደብቆ ሊያሳልፍ የነበረው 2 ሺህ 156 ስቴካ ሺሻ ተይዟል።

ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ሽሻውን የጫነው ተሽከርካሪ ሰኔ 1/2009 ዓ. ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አዳማ ከተማ ውሰጥ በጉምሩክ ሰራተኞችና በፌደራል ፖሊስ አባላት አማካኝነት ሊያዝመቻሉም ተገልጿል።

በወቅቱ አሽከርካሪው ከቆመበት ስፍራ መኪናውን አስነስቶ በፍጥነት ለማመለጥ በመሞከሩ የተሽከርካሪውን ጎማ ለመመታት በተተኮሰ ጥይት ግራ ጎኑን ተመቶ በአዳማ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በአዳማና ቢሾፍቱ ከተሞች ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ 673 ሺህ 303 ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ መያዙን አመልክተዋል።

ለህዝብ ጤናና ለአገር ኢኮኖሚ ስጋት እየሆነ የመጣውን የኮንትሮባንድ እንቅሰቃሴ ለመግታት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን  ኢዜአ ዘግቧል። EBC