Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በትብብር የመልማት አብነት

0 1,102

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በትብብር የመልማት አብነት

ስሜነህ

ዓባይ ወይም ናይል ወንዝ 6 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት የዓለም ረጅሙን ጉዞ ያደርጋል:: በዚህ ጉዞው ውስጥም በቀጥታ ወሠናቸውን አቋርጦ  የሚያልፍባቸውም ሆኑ ወሠናቸውን ሣይነካ ግብር የሚከፍሉለት አነሥተኛወንዞች ያላቸው 11 አገራት አሉት:: የሚገርመው ሁሉም አገራት ዝናውን እና ጉልበተኛነቱን ከመመሥከር ያለፈ ተጠቅመውበታል አይባልም:: በግዛቱ ውስጥ ከሚገኙት መካከል የግብጽን ያህል አቅሙን አሟጦ የተጠቀመበት አገር አይገኝም:: ከእሷ በመቀጠል ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የተሻለ ተጠቃሚ ናት:: ከዚያ ባለፈ 85 በመቶ የሚሆነውን የውሀ መጠን የሚመግበውን ዓባይን ከአብራኳ የምትወልደው ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ምንም አልተጠቀመችበትም:: ለታችኛው የተፋሠሡ አገራት ለእርሻ ሥራ የሚሆነው ለም አፈርም የሚሄደው በአብዛኛው ከዓባይ ወንዝ ነው:: ናይል እንዲያው ሥሙ ብቻ እንጂ በተለይ ለላይኛው የተፋሠሡ አባል አገራት ምንም ፋይዳ አልሠጠም:: በናይል ላይ የተገነቡት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንኳ ከአንድ እጅ ጣቶች ቁጥር አይበልጡም:: የላይኛው የተፋሠሡ አገራት አቅም ማነሥ እና የታችኞቹ የተፋሠሡ አገራት የላይኞቹን አንድም የልማት እንቅስቃሴ እንዳያከናውኑበት ተፅዕኖ ሲያደርጉ መቆየታቸው ከናይል ጋር የማይመጣጠን ተግባር እንዲያከናውኑ አድርጐ ቆይቷል::

እንኳን በግዙፉ ናይል ይቅርና የቀናነትና የትብብር መንፈስ ካለ እጅግ በበዛ እጅ ከእርሱ በሚያንሱት ላይም በርካታ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን መገንባት ከተቻለባቸው አብነቶች ይህ ትርክት የዳኑብን ወንዝ በማንሳት በትብብር ከመልማት ተቃራኒ ለተሰለፉቱ በጎውን ይመክራል።

ከናይል ወንዝ በርዝመቱ ሦስት እጥፍ አካባቢ ከሚያንሠው የአውሮፓውያን የትብብር መገለጫ ነው  ዳኑብ ወንዝ። ዳኑብ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ የመጠቀም ትልቅ ማሣያ እንደሆነም ይነገርለታል:: ዳኑብ የምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አገራትን የሚያሥተሣሥር ወንዝ ነው:: በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኙት ወንዞች መካከል በርዝመቱ በሁለተኛ ነው። የሚቀድመው ቮልጋ ወንዝ ብቻ ነው:: ዳኑብ ወንዝ ሁለት ሺህ 850 ኪሎ ሜትር ርቀት ይጓዛል:: በዓለም በርዝመቱ በ21 ደረጃ ላይ ለሚገኘው ዳኑብ ከ300 በላይ ወንዞች ግብር ይከፍሉታል:: በዳኑብ ወንዝ ተፋሠሥ ውስጥ ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚገኝ መሆኑን የሚዘረዝሩት የሃይድሮሎጂ መዛግብቶች አጠቃላይ የዳኑብ ወንዝ ተፋሠስ 817 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዌር የሚሸፍን መሆኑንም ይጠቅሳሉ:: እነዚሁ መረጃዎች በዳኑብ ወንዝ ሃተታቸው የምሥራቅናምዕራብ አውሮፓ አገራት በወንዙ ግዛት ውስጥ የሚገኙ እንደሆነ ገልጸው ከነዚህ መካከልም  ሀንጋሪ፣ ሮማንያ፣ ኦስትሪያ፣ ሶሎቬኒያ፣ ክሮሽያ፣ ስሎቫኪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ጀርመን፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሞልዶቫ፣ ዩክሪዬን፣ ሰርቢያ፣ በሶኒያ እና ሄርዞጐቪና፣ ጣሊያን፣ ስዊዘርላንድ፣ አልባኒያ እና ፖላንድ የዳኑብ ወንዝ ተጋሪ አገራት ስለመሆናቸው ይጠቅሳሉ::

ወደናይልና የተፋሰስ ሃገራቱ መጥተን የዳኑብን አብነት ስናወሳ ፤ዳኑብ ወንዝ እንደየአገራቱ ተፈጥሯዊ አቀማመጥና ባህሪ ጥቅም ላይ በመዋል በምሣሌነቱ የሚጠቀስ መሆኑ የመጀመሪያውና ቀዳሚው ጉዳያችን ይሆናል:: ዳኑብ  በተራራ ሠንሠለቶች ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ ለኃይል ሀንጋሪ ሙሉ ለሙሉ በተፋሰሱ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ቢሆንም የገነባችው 28 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ብቻ ነው:: ኦስትሪያ በዳኑብ ወንዝ ላይ 78 ትልልቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ገንብታለች:: 70 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የኃይል አቅርቦትም የምትሸፍነው በዳኑብ ወንዝ ላይ ከገንባቻቸው የኃይል ማመንጫ ግድቦች ነው – 14 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ያመነጫሉ::

የዳኑብ ወንዝ የላይኛው ተፋሠሥ ለኃይል ማመንጫ የታደለ የቦታ አቀማመጥ የተቸረው በመሆኑ ምክንያት  የአውሮፓ አገራት የትብብር መገለጫ ለመሆን አብቅቶታል። በወንዙ የመጀመሪያው አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመቱ ላይ 59 ግድቦች ገንብተውበታል::  የሃይድሮሎጂ መዛግብቶች እንደሚያትቱት የዳኑብ ወንዝ በአማካኝ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አንድ ግድብ ተገንብቶበታል:: በተለይ ኦስትሪያ በዓመት ከምትጠቀመው የኃይል አቅርቦት መካከል 60 በመቶ የሚሆነው ከውሀ የሚገኝ ነው:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ 20 በመቶው በዳኑብ ወንዝ ላይ ከገነባቻቸው ግድቦች የሚገኝ መሆኑን  መዛግብቱ አስፍረዋል። ስሎቫኪያም ከውሀ ኃይል የምታገኘው ኃይል 16 በመቶ አቅርቦት የሚሸፈነው ከውሃ ሲሆን 11 በመቶው ደግሞ ከዳኑብ ወንዝ የሚመነጭ ነው::

በዚህ ወንዝ ላይ ከተገነቡት ግድቦች መካከል አይረን ጌት አንድ እና ሁለትን በግዙፍነቱ የሚሥተካከለው የለም:: ግድቡ ድንበር ተሻጋሪ መንዞችን በጋራ የመጠቀም ትልቅ ማሣያ እንደሆነም በውሃ ድርሳናቱ ተመዝግቧል:: በሰርቢያ እና ሮማኒያ የሚተዳደር ሆኖ ሁለት ግድቦች ያሉት ነው:: ሰርቢያ 37 በመቶ ኃይል ሥትጠቀምበት ሮማኒያ ደግሞ 27 በመቶ ድርሻ አላት::

ሌላኛው አብነት ደግሞ የዳኑብ ወንዝ ተፋሰሥ አገራት ዛሬ የደረሡበት ውጤት በቀላሉ ያልተገኘ መሆኑን የተመለከተው ነው:: በብዙ የጥቅም ግጭቶች የታጀበ፣ በፅንፈኛ ብሔርተኞች እክል የገጠመው ነበር:: በ1989 (እ.ኤ.አ) የሶሻሊዝም ጐራው ሲፈራርስ ከቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት የተገነጠሉት አገራት በተፋሠሡ አባል አገራት ላይ መረጋጋት እንዳይኖርና መጠራጠር እንዲሠፍን ወንዙን ተጠቅመውበት እንደነበር የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድቦችን እና የውሃ ፖለቲካን የተመለከቱ ድርሳናት ያወሳሉ::

በዳኑብ ወንዝ ላይ የመጀመሪያው ሥምምነት የሚባለው በ1856 (እ.ኤ.አ) በፓሪስ የተደረገው መሆኑን የሚያወሱት እነዚህ ድርሳናት  እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድረሥም ይህ የፓሪሱ ስምምነት ትኩረት አድረጐ የነበረው የውሃ መጓጓዣ አገልግሎት እንዲሠጥ የነበረ መሆኑን ያትታሉ:: ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1948 (እ.ኤ.አ) በቤልግሬድ የተካሄደው ጉባኤ በምሥራቅ አውሮፓ የነበሩትን የሶሻሊስት አገራት እያንዳንዳቸው ግዛታቸው ውሥጥ የሚካሄደውን የማጓጓዣ ሥራ እንዲቆጣጠሩ ሥልጣን ሠጣቸው:: በወንዙ ላይ ለሚደረግ ማንኛውም የመጓጓዣ አገልግሎት የተቆጣጣሪነቱ ሥልጣን በአውሮፓ የዳኑብ ወንዝ ኮሚሽን ሥር ሆነ:: 1980 አጋማሽ ጀምሮ ሥለውሃው ደህንነትም መጨነቅ ጀመሩ:: ወንዙ በከፍተኛ ደረጃ መበከሉ ሥጋት ውስጥ ከተታቸው:: አራት ታላላቅ ዋና ከተሞችን አቋርጦ የሚጓዝ መሆኑ (ቬና፣ ብራስላቪያ፣ ቡዳፒስት እና ቤልግሬድ) በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኗሪዎች ነፃ ንክኪ ውስጥ በመውደቁ ንፅህናው እና ህልውናው አደጋ ውስጥ ወደቀ:: ያለገደብና ከልካይ ለእርሻ ሥራ አገልግሎት እንዲሁም ከፋብሪካዎቻቸው ጋር መነካካቱ ለብክለት ሥጋት የፈጠሩ ችግሮች ሆኑ:: ከዚህ ባሻገር 13ቱ የተፋሠሡ አባል አገራት በከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የሚጠቀሡ ናቸው:: የሶቭዬት ህብረት መፈራረሥም የወንዙ ክትትልና ቁጥጥር እንዲዘነጋ ያደረጉ ክስተቶች ሆኑ:: ይህ የወንዙ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያሣሠባቸው ስምንት የተፋሠሡ አባል አገራት በ1985 የቡካሪስት ስምምነትን ተፈራረሙ:: ሥምምነቱ በውሀው ንፅህና፣ በደህንነቱ እና ክትትልና ቁጥጥሩ ላይ የሚያተኩር ነው:: ከዚህ በኋላ በ1994 የ”ዳኑብ ወንዝ ጥበቃ መግባቢያ” የሚል ስምምነት በመፈራረም አውሮፓውያን የበለጠ ትብብራቸውን አሣዩ::

መረጃዎቹ እንደሚያትቱት  የተፋሠሡ አባል አገራት እንደተፈጥሯዊ አቀማመጣቸውና አቅማቸው ወንዙን በፍትሐዊነት ለመጠቀም የሚያሥችል በጋራ የመልማት ህብረት ፈጥረዋል:: የላይኞቹ የተፋሠሡ አባል አገራት በውሀ ኃይል ማመንጨት ላይ ሲያተኩሩ የታችኞቹ ደግሞ ለአሳ ሀብት እና ለመሥኖ ልማት ትኩረት ሠጥተው ይሰራሉ:: ከዚህ ባሻገር ሁሉም የተፋሠሡ አባል አገራት ለደረቅ ጭነት ማጓጓዣነት ያውሉታል:: ልክ እንደ ስዊዝ ቦይ ሁሉ በዳኑብ ወንዝ ውሥጥ የሚገኙ አገራትን በቦይ በማገናኘት የውሀ ማጓጓዣ ሥራውን አጠናክረው እየተገበሩት ይገኛሉ:: የሁሉም የተፋሠሡ አባል አገራት ዋና ወደቦች ከወንዙ ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው ተደርጓል:: በዚህም የፋብሪካ ዕቃዎችን እና የግብርና ምርቶችን ከባልካን አካባቢ ለማሥገባት ትልቅ አሥትዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል:: በተለይ ከጀርመን የፋብሪካ ውጤቶችን ወደ ጥቁር ባህር አካባቢ ለማድረሥ ትልቅ የመሠረተ ልማት መዘርጋት ያስቻላቸውን ትብብር ፈጥረዋል:: በቬና፣ በቡዳፒስት እና ቤልግሬድ ውሀውን ለፋብሪካ የመጠቀም ዕድል ሠጥቷል:: በሀንጋሪ፣ ቡልጋሪያ እና በሌሎች በእርሻ ላይ ለተሠማሩ የተፋሠሡ አባል አገራት ደግሞ ትልቅ የመሥኖ ልማት አማራጭ ፈጥሮላቸዋል:: በተለይ የእርሻው ሥራ የሚከናወነው ከወንዙ ከመነሻ ግማሽ ርቀት ከተጓዘ በኋላ መሆኑ ወንዙን በአግባቡ ለመጠቀም ከፈጠሩት ትብብር የመነጨ መሆኑን “የዳኑብ ወንዝ ጠቀሜታ አውሮፓን ከሜዲትራኒያን ባህር ጋር በማገናኘት እረገድ” በሚል የተካሄደ ጥናት ፅሁፍ አሥፍሯል:: በወንዙ መጨረሻ አካባቢ የሚገኙት አገራት ደግሞ በሥፋት በአሣ ሀብት ልማት ላይ ተሠማርተዋል:: ወንዙንም ከ100 በላይ ለሚሆኑ የአሣ ዝርያዎች መገኛ አድርገውታል:: ይሄው ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚያሥረዳው ከ300 የዳኑብ ወንዝ ገባሮች መካከል 60ዎቹ ለመጓጓዣ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው:: በአውሮፓ የሚያደርገውን የውሀ መጓጓዣ አገልግሎትም ወደ 35 ሺህ ኪሎ ሜትር እንዲደርሥ አሥችለውታል:: በርካታ ሰው ሠራሽ ቦዮችን በመፍጠርም ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ማገናኘት ችለዋል::

በዳኑብ ወንዝ ላይ የአውሮፓ አገራትን ምጣኔ ኃብት በትልቁ ማሣደግ የቻሉ ግንባታዎች ተካሂደውበታል:: በ1992 (እ.ኤ.አ) በቼኮዝሎቫኪያ የተገነባው ጋቢችኮብ ግድብን ለመገንባት የዳኑብን ወንዝ 24 ኪሎ ሜትር ከተፈጥሯዊ ፍሠቱ ማሥቀየር ግድ ብሏል:: በተፈሠሡ አባል አገራትም በኃይል ማመንጫነቱ በትልቅነቱ ተመድቧል:: የራሄን ሜን- ዳኑብ – ቦይ ደግሞ ጥቁር ባህርን ከሰሜኑ ባህር ጋር በመገናኘት የአህጉሩን ምጣኔ ኃብት ዕድገት በእጅጉ አፍጥኗል:: በሰርብያ የተገነባው የዳኑብ – ቲሳ- ዳኑብ ቦይ ደግሞ ትልልቅ መርከቦችን ማንቀሣቀሥ ከማሥቻሉም በላይ በአውሮፓ 12 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ካሬ ስፋት ያለው ለም የእርሻ መሬት መሸፈን እና ማልማት ችሏል::

በአጠቃላይ ዳኑብ ከረጅሙ ናይል ወንዝ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጥቅም ለተፋሰሱ አገራት የሰጠ ነው:: ከ11 የማይበልጡት የረጅሙ የናይል ወንዝ ተፋሠሥ አባል አገራት ምንም ሣይሠሩበት ዘመናት ነጉደዋል:: (ከግብጽ እና ሱዳን በስተቀር) በርዝመትም በመጠንም ብዙ የሚያንሠው የአውሮፓው ዳኑብ ወንዝ ግን 13 አባል አገራቱን በሚገባ ተጠቃሚ በማድረግ የትብብር አብነትነቱን አሥመስክሯል:: የናይል ተፋሠሥ አባል አገራትም የዳኑብን ተሞክሮ ለመውሠድ እንደየተፈጥሯዊ አቀማመጣቸው እና የአገራቱ ምጣኔ ሀብት አቅም ኢኮኖሚያቸውን ሊያሣድጉ በሚችሉበት ሥራ ላይ በመሣተፍ ለትብብር ቦታ መሥጠት ቢችሉ የዓባይን ልጅ ውሀ እንዳይጠማው ማድረግ በቻሉ ነበር::

የዳኑብ ወንዝ ሁሉም የናይል ተፋሠስ አባል አገራት የጋራ ሀብታቸው መሆኑን ተገንዝበው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለማልማት ትብብራቸውን እያሣደጉ መሄድ እንደሚገባቸው ያሣያል:: እንደአለፉት ረጅም ዓመታት አንዱ በይ ሌላው ተመልካች መሆኑ ቀርቶ በጋራ የማደግ መንፈሥ ሊያጠናክሩ ይገባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy