Artcles

በትግል ሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎችን በግንቦት20 ድል ማስወገድ ይገባል!!

By Admin

June 05, 2017

በትግል ሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎችን  በግንቦት20 ድል ማስወገድ ይገባል!!

ዮናስ

ፌደራላዊ ስርዓቱ እውን ከሆነ በኋላ የሃገሪቷ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው ባህልና ቋንቋ እንዲተዳደሩ፣ በማንነታቸውም እንዲኮሩ በመደረጉ አያሌ ለውጦች የታዩ ቢሆንም አልፈታ ብለው የተቋጠሩብንም ጉዳዮች መኖራቸው እሙን ነው።በግንቦት 20 ድል የተመሰረተው እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ እውን መሆን መሰረት የሆነው የፌደራል ስርዓት የብሔር ብሄረሰቦችን እኩልነት በማስፈኑ ሁሉም የራሱን ማንነት እንዲያስተዋውቅ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል።ግንቦት 20 በሃያ ስድስት አመታት እድሜው ለኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያመጣላቸውን እና ያስቀረባቸውን ጉዳዮች በየአመቱ ማስታወስም ድሉን ከማጣጣም በላይ ድሉን ለመጠበቅና ያስቀረንብንንም እንዲያሟላልን ይጠቅመናልና ማስታወስ ግድ ይላል።

በግንቦት 20 ድል የተመሰረተው የፌደራል ስርአት ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲተዋወቁና እንዲቀራረቡ  በማድረግ  የአመለካከት ችግሮችን እየቀረፈ በመከባበር ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት እንዲኖር ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል።የፌዴራል ስርአቱ ክልሎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ መፈቀዱ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በማሳደግ በፖለቲካው መስክም በሀገራቸው ጉዳይ ወሳኝ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ 

 ከዚህ ቀደም ሀገሪቷ ስትተዳደርበት የነበረው  አሀዳዊ  የመንግስት ስርአት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያሳትፍ የሚያስችል ሁኔታን ባለመፍጠሩ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች በመሆን የተዛባ ግንኙነት  ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሁሉንም ከግምት ያስገባ የመንግስት  ስርአት በማስፈለጉ ረጅም ጊዜ የወሰደ ትግል ተካሄዶ አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ስርአት መገንባት ተችሏል፡፡

 

በኢትዮጵያ የኩሽ፣ ሴም፣ ኦሞና ናይሎቲክ ሰሃራ የቋንቋ ቤተሰብ ስብስብ የሆኑ የራሳቸው ባህል፣ ማንነትና ቋንቋ ያላቸው 76 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዳሉ ድርሳናት ያወሳሉ። ሁሉም ባህልና ቋንቋቸውን እንዲያበለፅጉና እንዲጠቀሙበት በሕገ-መንግስቱ ሙሉ መብት መሰጠቱም በማንነታቸው እንዲኮሩ ከማድረግ ባሻገር አንድነታቸው ጤናማ እንዲሆን አስችሏል።ሃገራት ብዙ ጊዜ አንድነታቸውና አብሮነታቸው በተለያየ ምክንያት አደጋ ውስጥ ከሆነ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ፌደራሊዝም ሁነኛው አማራጭ ስለመሆኑ የሚመሰክሩ የታሪክና የፖለቲካ ልሂቃን ፤በግንቦት 20 ድል በተመሰረተው የፌደራል ስርአት በአሁኑ ወቅት በልዩነት ውስጥ አንድ ሆኖ በእኩልነት መኖር እንደሚቻል የሚያምን ህብረተሰብ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ መሆኑን በአስረጂነት ይጠቅሳሉ።

 ሆኖም ግን የፌደራል ስርዓቱ መዋቅሩን ምክንያት በማድረግ ግለሰቦችና ቡድኖች አገራዊ አንድነትን ትተው ወደ አላስፈላጊ  ብሔርተኝነት  እየሳቡ የግጭት ምክንያት ሲያደርጉ ይስተዋላል የሚሉት ምሁራን ይህን አስተሳሰብ ማረቅ የሚቻለውም በዚሁ ፌደራላዊ ማእቀፍ ውስጥ ሆነው ብቻ መሆኑንም ያሰምራሉ።  

 በሃገራችን በ1983 ዓ.ም የመጣውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በ1987 ዓ.ም የጸደቀውን ሕገ-መንግስት መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓት ተዋቅሯል። ይህ ስርአት በህዝቦች አሰፋፈር፣ ቋንቋንና ማንነትእና ፈቃድን መሰረት በማድረግ በዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ተዋቅሮ 26 ዓመታትን አስቆጥሯል። በዚሁ ድል ሃገሪቱ እንድትመራበት የተዘጋጀው ህገ መንግስትም ለሁሉም ብሄሮች ቋንቋ፤ ባህልና ማንነት እውቅና መስጠት የሚችል፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግና ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል ስርአትን መዘርጋት ዋናው አላማው ያደረገ ነው፡፡ ይሄ ያልተማከለ ስርአት በአንዳንድ ክልሎች  በዞንና በወረዳም ደረጃ  ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ስልጣን የተሰጠበት አግባብ  በመኖሩ ስርአቱ ራስን የማስተዳደር ስልጣኑን ለሁሉም ተደራሽ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ያሳያል።  ይሄ እንዳለ ሆኖ መንግስቱን ያቋቋሙት ክልሎች  በጋራ የሚያስተዳድሩት የጋራ ስልጣን ለራሳቸው የሚያስቀምጡበትና ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት የፌደራል ስርአት የያዘ  መሆኑ ደግሞ ሀገሪቷ አንዲት ሉአላዊ ሀገር ሆና እንድትቀጥል የሚያስችላት ነው ።   

በኢኮኖሚውም ረገድ የፌደራሊዝም አስተዳደር ሲገነባ አዳዲስ የአስተዳደር መዋቅሮችን መዘርጋት የሚያስፈልግ በመሆኑ ከፍተኛ በጀት  የሚጠይቅ  ቢሆንም፤ ህዝብን በሩቅ ሆኖ ከማስተዳደር የተሻለ  አማራጭ ነው፡፡ ወደ ህዝቡና አካባቢው ወዳለው ሀብት ቀርቦ ማስተዳደር ክልሉ በራሱ ስለሚሰራ የተፋጠነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግና  ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር አስችሏል። አሁን ባለውም ነባራዊ ሁኔታ ክልሎች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም እየፈጠሩት ያለው የስራ እድል ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡

 

26 ዓመታት ያስቆጠረው ግንቦት 20 የሃገሪቱን የድህነትና የኋልዮሽ የዓመታት ጉዞ በልማት እንዲቀየር ያደረገ ታሪካዊ ዕለት መሆኑ አሁን በሚገባ ተረጋግጧል።በግንቦት 20 የተመዘገበው ድል በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ለአገሪቱ ሕዝቦች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው።እለቱ በሃገሪቷ ለዘመናት የቆየው አሀዳዊ ሥርዓት ተቋጭቶ የህዝቦች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ያሰፈነ  የፌዴራል ሥርዓት የተረጋገጠበት ነው።

ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ በኃይል አቅርቦት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና በመንገድ ልማት ዘርፍ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች መከናወናቸውና ህዝቡም የእነዚሁ ልማቶች ተጠቃሚ መሆኑ ተረጋግጧል።ግንቦት 20 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የተጎናፀፉበት እለት ነው።እለቱ የሃገሪቷ ሕዝቦች በራስ ቋንቋ የመማር፣ የመዳኘት፣ የመስራት፣ ባህላቸውን የማልማትና የማሳደግ መብት የተጎናጸፉበት ነው።

በሃገራችን ሁለት ብቻ የነበሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአሁኑ ወቅት ወደ 34 ማደጋቸውንና የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት የድሉ አንድ ማሳያ ነው ። የህዝቦች ንቃተህሊና ማደግ እንዲሁም በልማትና በዴሞክራሲ ጥያቄ ሞጋች ሕብረተሰብ መፈጠሩ የድሉ ሌላኛው ማሳያ ነው።

ድሉን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት በሃገሪቷ የኋልዮሽ ጉዞ ቀርቶ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ተመዝግበዋል።ከቀጥታ የውጪ ኢንቨስትመንት ፍሰት ጀምሮ በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ግንቦት 20 ያስገኛቸው ውጤቶች ናቸው።

ያም ሆኖ ግን ግንቦት 20 ያስቀረብን እና ያልፈታው ቋጠሮ መኖሩንም ማስታወስ እና ድሉን ከመዘከር በላይ የግንቦት 20 የድል በዓል አከባበር አጀንዳ ሊሆን ይገባል።   ይኸውም የመልካም አስተዳደር ቋጠሮ ነው።

በየጊዜው የተካሄዱ ተሃድሶዎች በመልካም አስተዳደር ረገድ ያመጡት ለውጥ እንደሌለ እየተነገረ እና በተግባርም በተለይ ታችኛው መዋቅር አካባቢ እየከፋ የመጣ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች መጥቀስ ስለሚቻል።

ስለሆነም 26 ዓመታትን ያስቀጠረው ግንቦት 20 ሲዘከር ኅብረተሰቡ ስለሃገሩ ታሪክ፣ ሕግና ስርዓት በየጊዜው መነጋገር የሚችልበትን እድል ከማመቻቸት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይገባዋል ፡፡ይህ ብቻ አይደለም፤ በሃገሪቷ በየጊዜው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል በሚካሄደው ትግል ወጣቶችና ሴቶች ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን መላም መዘየድን ቁልፍ አጀንዳ በማድረግ ሊሆን ይገባዋል።

ግንቦት 20 ያስገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብትና እንዲዳብር ፤የህገ መንግስቱ መርሆችና ድንጋጌዎችን መተግበር መልካም አስተዳደር የህልውናችን ጉዳይ የማይሆንበትን ቀን ለመፍጠር ዜጎች ቃላቸውን የሚያድሱበት እንጂ ለይስሙላ ተነጋግረው እና መፈክር አሰምተው የሚለያዩበት ሊሆን አይገባም። በዓሉ ሲከበር ሁሉም የየራሱን ድርሻ በመውሰድ ህገ መንግስቱ ላይ ያሉ መርሆችንና ድንጋጌዎችን ለመተግበር ቁርጠኝነቱን በማሳየት ሊሆን ይገባዋል።

ሁሉም በያለበት እና እንደስራ ድርሻው ኀብረተሰቡ የሚያነሳውን ችግር ለመፍታት በቅንነት ለማገልገልና በተሃድሶው የገባውን ቃል ለመተግበር ቃል ኪዳን የሚገባበትን እና የገባውን ቃል ስለመፈጸሙ መትጋት የሚገባው እንጂ የዛሬ አመት ፎክሮ የሄደውን ዛሬም ይዞ በሚመጣበት አድሮ ቃሪያ መንገድ ሊሆን አይገባም ።

ለህዝቦች የይቻላል መንፈስን በማላበስ  እና የዜጎችን አቅም በመገንባት ለሃገሪቷ የልማት ጉዞ ቀጣይነት ዋስትና የሆነው ቀን በብልሹ አሰራሮች እና በኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ቅርብ አዳሪ እንዳይሆን የሚያስችለንን ስንቅ የምንሰንቅበት እንጂ ከበርቻቻ ብለን የምንወጣበት የበአል አከባበር ሊያበቃ ይገባል።

በዓሉን ስናከብር አገሪቷ የጀመረችው ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መትጋት የሚችሉበትን መንገድ በማሳየትና በመምራት ሊሆን ይገባዋል።

ስለሆነም የየበአል አከባበር መድረኮቹ የስርዓቱ ፈተና የሆኑትን ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ በሚደረገው ርብርብ ልክ የመልካም  አስተዳደር ትግሉንም ለማድረግ ቁርጠኝነታችንን የምናሳይበትና የተቆጠረና ለመጪውም አመት ተቆጥሮ በተሰጠን ልክ ቆጥረን የምናስረክበው ተልእኮ ይዘን የምንወጣባቸው እንጂ አጨብጭበንና ተሞጋግሰን ወይም በተገኘውና ከላይ በተመለከቱ ድሎች ተኩራርተን የምንወጣበት ዘመን አሁን አብቅቷል ።