Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጥልቅ አለመታደስ ክህደት ይሆናል

0 1,000

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በጥልቅ አለመታደስ ክህደት ይሆናል

                                                   አሜን ተፈሪ

በያዝነው ዓመት በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የሚሰማ ቃል ‹‹ተሃድሶ›› ነው፡፡ ቃሉ አዲስ አይደለም፡፡ ሆኖም ዛሬ ‹‹ተሃድሶ›› ሲባል እንደ ትናንቱ በአንድ ተልዕኮ ማጠቃለያ የሚደረግን የመዝናኛ ዝግጅት ለመግለጽ አይደለም፡፡ አሁን ‹‹ተሃድሶ›› ስንል የሞት – የሽረት ትግልን ለማመልከት ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄውን ሳያሳካ፤ በቀደመ ትርጉሙ አግባብ ‹‹ተሃድሶ›› ሊያደርግ አይገባም፡፡ ገዢው ፓርቲ ድርጅቱን የማስተካከል ከባድ የቤት ሥራ የተሸከመ በመሆኑ ለተሃድሶ ጊዜ እና ምክንያት የለውም፡፡

 

ኢህአዴግ በውስጡ የሚታዩ ድክመቶችን ለማረም፤ ያሉበትን ጉድለቶች ለመሙላትና የፖለቲካ ቁመናውን ለማጠናከር ሌት ተቀን መሥራት የሚጠበቅበት ድርጅት እንጂ ስኬቶቹን ምክንያት አድርጎ የተሃድሶ ፕሮግራም ለማዘጋጀት የሚችል ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ ኢህአዴግ ‹‹ተሃድሶ›› ሲል፤ ለመታረም፣ ጠርቶ ለመውጣትና ለመጠናከር የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን ለመግለጽ ካልሆነ፤ ስኬትን ለማክበር እና ለቀጣይ ተልዕኮ የስሜት ስንቅ ለመያዝ የመዝናኛ ሁነት ሊያዘጋጅ አይችልም፡፡ ድርጅቱ፤ የመታረም፣ ራስን የማጥራት እና የማጠናከር ፋታ የማይሰጥ ‹‹የጥልቅ ተሃድሶ›› ተልዕኮ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ በመሆኑ ለዋዛ ጊዜ የለውም፡፡

 

ማናቸውም ሰው ስህተት እንደሚፈፅመው ሁሉ ድርጅትም ስህተት የሚሰራበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ኢህአዴግ ስህተት መስራቱን አምኗል፡፡ ስህተት መስራቱን ማመን ብቻ ሳይሆን፤ የሰራውን ስህተት ለማረም ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ለማድረግ ወስኖ ከያዝነው ዓመት መባቻ ጀምሮ ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡

 

በርግጥ አንዳችም ስህተት ሳይሰራ መላ የድርጅት ህይወቱን የሚኖር ድርጅት እንዲኖር አይታሰብም፡፡ የአንድ ድርጅት ብቃት የሚገለፀው ስህተት ባለመስራቱ ሳይሆን፤ ስህተቱን ፈጥኖ በመረዳት፤ ያን ስህተቱን ሳይውል ሳያድር ለማረም በቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስ በመቻሉ ነው፡፡ የአንድ ድርጅት ብቃት የሚለካው የፈጸመው ስህተት ምን እንደሆነ በትክክል በመረዳት ችሎታው እና የፈፀመውን ስህተት ለማረም በሚከተለው አሰራር ነው፡፡

 

ኢህአዴግ የችግሩን ምንነት የተረዳው የህዝባዊ ቁጣ ወላፈን ሲለበልበው አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት የታየው እሣት ሳይከሰት በፊት፤ ኢህአዴግ በጉዞው የሚገጥመው አደጋ የት አካባቢ እንዳለ ያውቀው ነበር፡፡ አስቀድሞ በትንታኔ ደረጃ ችግሩን ተረድቶታል፡፡ ሆኖም ስኬቶቹ ከድክመቶቹ ጋር አብረው ሲርመሰመሱ እየተመለከተ፤ አልቃሽ እና ዘፋኝ ሲያንጎራጉሩ እየሰማ ልቡ በዜማው ተወስዶ ‹‹በቆይ ነገ›› ሲያቅማማ፤ በፍጥነት ሊቀድመው የሚያስበው ናዳ እየተምዘገዘገ ዱብ ዱብ ማለት ጀመረ፡፡

 

ኢህአዴግ ስህተት መፈጸሙን አምኗል፡፡ ‹‹የማህበራዊ መሠረቶቼን ጥቅም እና ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል ብዬ የቀረጽኩትን ኘሮግራም ለማስፈጸም ስታገል ሰህተት ሠርቻለሁ፡፡ ነገር ግን የሚፈፅምኩት ስህተት መሠረታዊ ኘሮግራሜን የሚጻረር አይደለም›› ይላል፡፡ እንደ ኢህአዴግ ሐሳብ፤ አንድ ድርጅት ማህበራዊ መሠረቱ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም እና ፍላጎት የሚጻረር ጥፋት ከፈጸመ፤ ችግሩ ስህተት ሳይሆን ክህደት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ችግሩ ወደዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መስተካከል ካልቻለ ድርጅቱን ተሃድሶ አያድነውም፡፡ ችግሩ የሰልፍ ለውጥ የሚያስከትል በመሆኑ፤ እንዲህ ዓይነት ጥፋት ወደ መስራት ከተገባ ጥያቄው የተሃድሶ ጉዳይ አይሆንም፡፡

 

ኢህአዴግ፤ መሠረታዊና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ስህተት ያለመስራት፣ መሠረታዊ ያልሆኑ ስህተቶች ሲፈፀሙም ቀልጥፎ የማረም፣ አንዴ የተፈፀመና የታረመ ስህተትም መልሶ የማይደገምበትን ሁኔታ የማረጋገጥ መርህ የሚከተል ድርጅት ነው፡፡ ሆኖም መሠረታዊ ያልሆኑት ስህተቶች ተደራርበው ሲከሰቱ ውጤታቸው የመሠረታዊ ስህተትን ያህል ከባድ ሆኗል፡፡  

 

ኢህአዴግ የተጠቀሱትን መርሆዎች ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥር የቆየ ቢሆንም፤ አስቀድሞ የሚያውቀውን አደጋ ለመከላከል ወይም መሠረታዊ ያልሆኑ ስህተቶቹን ቀልጥፎ ለማረም ባለመቻሉ ችግሩ አደገኛ መልክ ይዞ ሊከሰት በቅቷል፡፡ አሁን የኢህአዴግ ጥንካሬ የሚገለጠው ለስህተት የሚዳርጉ ችግሮችን አስቀድሞ በማየቱ እና ስህተቱን አምኖ በመቀበል ረገድ አይደለም፡፡ ስህተትን ቀልጥፎ ከማረም አኳያ የታየው ችግር በኢህአዴግ ውድቀት የሚመዘን ብቻ ሳይሆን፤ አክራሪ የገበያ ኢኮኖሚ ሊያስከትል የሚችለውን ጦስን በብቃት ለመከላከል ያስቻለውን ርዕዮተ ዓለም ለሽንፈት በመዳረግ ሒሳብም ሊታይ የሚገባው ችግር ነው፡፡

 

ታዲያ ከዚህ ችግር ለመውጣት ከሁሉ አስቀድሞ ስህተት መሰራቱን አምኖ መቀበል  ያስፈልጋል፡፡ እናም ኢህአዴግ ተሃድሶ አካሂዳለሁ ሲል የመጀመሪያው ጉዳይ አገራዊ የመሪነት ሃላፊነቴን በመወጣት በኩል ላደርገው ሲገባኝ ሳላደርገው የቀረሁት፣ ማድረግ ሳይጠበቅብኝ በማድረግ የፈፀምኩት ስህተት አለ ብሎ በማመን ነው፡፡ አሁን ጥልቅ የተሃድሶ ንቅናቄ ውስጥ የገባው ለዚህ ነው፡፡

 

እናም የተሰራውን ስህተት በትክክል ነቅሶ በማውጣትና መሳሳቱን ሳይግደረደር በማመን እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ስህተቶቹን አንድ ሁለት ብሎ ቆጥሮ፤ ለምንና እንዴት እንደተፈጸሙ በቂ ማብራሪያ አቅርቦ፤ ስህተቶቹ በቀጣይ እንዴት እንደሚታረሙ በተብራራ አኳኋን ገልጾ ግለ ሂስ አድርጓል፡፡

 

ድርጅቱ ግለ ሂስ ሲያደርግ ስህተቶቹን ለማረም ዝግጁ በመሆን እና ስህተቶቹን ለማረም የሚያስችል ድርጅታዊ ሁኔታ ለመፍጠር በመወሰን ነው፡፡ ይህን ውሳኔ ሲያደርግም የተፈጸመው ስህተት ዳግም እንዳይከሰት ርግጠኛ በሚያደርግ አግባብ ለመስራት ቃል በመግባት ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደሚለው፤ ‹‹ለመታረም የሚያስችል ድርጅታዊ ሁኔታ በሌለበት ወይም እንዲህ ዓይነት ድርጅታዊ ሁኔታ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆን በማይቻልበት ሁኔታ ስህተትን አርማለሁ፣ ተሃድሶ አካሄዳለሁ ብሎ መነሳት›› አይቻልም፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ሲል፤ ባለፋት ዓመታት በነበረው የአመራር ሂደት ስህተት መሰራቱን በማመን ብቻ ሣይሆን ስህተቱ ዳግም  እንዳይከሰት የሚያደርግ ድርጅታዊ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ ጭምር ነው፡፡

 

ድርጅቱ፤ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን አስፈላጊነት ሲያትት፣ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ውስጥ ለመግባት ግድ ያሉት ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ነው፡፡ የመጀመሪያው በሃያ አምስት ዓመታት ሂደት (በተለይ ደግሞ በአስራ አምስቱ የተሃድሶ ዓመታት ጉዞ) ያስመዘገባቸውን መልካም ውጤቶች ማስጠበቅ እና ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ከዕድገታችን ጋር ተያይዘው የተነሱ አዳዲስ የህዝብ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶችን በዳበረ አስተሳሰብ በመመለስ የህዝብን ፍላጎት ማርካት እና አዳዲስ ጥያቄዎች እንዲነሱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስቱና ድርጅቱ በመንግስት ስልጣን አተያይና አጠቃቀም ዙሪያ ካጋጠማቸው አደጋና ድክመት በማላቀቅ ለተልዕኮአቸው ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ነው፡፡ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውን ማወጅ ያስፈለገባቸው ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው፡፡

 

የተሃድሶ ንቅናቄው የታወጀው ድንገተኛ የሆነ ችግር በመፈጠሩ ወይም ፈጦ የወጣ ወቅታዊ ችግር ስላጋጠመ ያንን ለመሻገር አይደለም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ የተሃድሶው መሠረታዊ ግብ፤ ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ድሎች በማስጠበቅ፣ በማስፋት እና ይህንን በማድረግ ረገድም እንቅፋት የሚሆኑ ድክመቶችን እና ተግዳሮቶችን የማስወገድ እና የመፍታት ጉዳይ ነው፡፡

 

በአጠቃላይ ኢህአዴግ አገሪቱን የመምራት ሃላፊነት ከተከረበበት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እንደ ድርጅት እና እንደ ህብረተሰብ ወደፊት ለመራመድ እክል የሚሆኑ የአስተሳሰብና የተግባር ችግሮችን በመፍታት ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በአገራችን የተመዘገበውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል የተሃድሶው ተልዕኮ ነው፡፡

 

በእስካሁኑ ትግል የተገኙት ውጤቶች ሁሉንም የአገራችንን ችግሮች የፈቱ ባይሆኑም፤ ገና መፈታት ያለባቸውና ያልተሻገርናቸው ብዙ ችግሮች እንዳሉብን ቢታወቅም፤ የተገኙት ውጤቶች እንዳይከስሙ አለመጠበቅ፣ እንዲጎለብቱ እና እንዲሰፉ አለማድረግ፤ ክህደት እንጂ ስህተት ተደርጎ የሚቆጠር አይደለም፡፡ በመሆኑም የጥልቅ ተሐድሶ ንቅናቄው ግለቱን ጠብቆ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ቀደም ሲል የተቀየሱት የለውጥ አቅጣጫዎች፣ የተበጁት የለውጥ መሳሪያዎች፣ የእንቅስቃሴው ፍጥነት እና ጉልበት ለአዲሱ የሁኔታዎች እድገት በትክክል የሚያገለግሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ፤ ለአዳዲስ ሁኔታዎች ራስን ዝግጁ በማድረግ የለውጡን እንቅስቃሴ ማስቀጠል የሚያስችል የታደሰ አመለካከት፣ አደረጃጀትና አሰራር ያለው የዳበረ አመራር በመገንባት፤ የተሃድሶ ንቅናቄው በማያቋርጥ አኳኋን እየታደሰ፣ ይበልጥ ጥልቀትና ጥንካሬ እያገኘ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy