NEWS

ባለስልጣኑ የክረምቱን መግባት ተከትሎ ከግንቦት 30 ጀምሮ የመንገድ ቁፋሮ እንዳይከናወን ከለከለ

By Admin

June 02, 2017

የክረምት ወር መግባትን ተከትሎ ከግንቦት 30  ቀን 2009 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ድረስ ማንኛውም አካል የመንገድ ቁፋሮ ማከናወን እንደማይችል የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በተለይም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በተፈቀደለት የጊዜ ገደብ መሰረት ግንባታዎችን አለማከናወኑ በነዋሪዎቹ ዘንድ ቅሬታን እያስከተለ መሆኑን ገልጿል፡፡

ቅሬታ ከሚነሳባቸው መንገዶች መካከል በተለምዶ ሰሜን ማዘጋጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፥ በተለይም በሰሜን ጤና ጣቢያ በኩል በሚያልፈው መንገድ የፍሳሽ ማስወገጃ ቁፋሮ እየተከናወነ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መታዘብ ችሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም የመንገድ ዳር የፍሳሽ ማስወገጃው ቢሰራ የሚፈልጉት ቢሆንም ግንባታው እየተከናወነበት ያለው ጊዜ ግን የዝናብ ወቅት በመሆኑ ለችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ስራው ከተጀመረ አንድ ወር ቢያስቆጥርም ባለመጠናቀቁ ከመኖሪያቸው ለመውጣት እና ለመግባት አመቺ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው አቅመ ደካሞች እና ህጻናትን ጨምሮ ወደ ጤና ጣቢያው ለህክምና የሚመጡ ተገልጋዮች መንገዱ ምቹ ሁኔታን አልፈጠረላቸውም፡፡

በሌላ በኩል ላዛሪስት ትምህርት ቤት አቅራቢያ በሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤት የፍሳሽ ማስወገጃ ቁፋሮ ቢጀመርም የክረምት ወቅት በመሆኑ ተገቢነት እንደሌለው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር ደመላሽ ገብረማርያም፥ በክረምት ወቅት የሚደረጉ ቁፋሮዎች ነዋሪዎች መንገዱን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ እያደረገ መሆኑን መስሪያ ቤታቸው ማረጋገጡን ነው የተናገሩት።

ለአብነት የቀረበው የሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የውሃ እና ፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ እንዲጠናቀቅ የተቀመጠለት ቀነ ገደብ ከህዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡

አሁን ላለው ቁፋሮና ግንባታ ባለስልጣኑ ፈቃድ እንዳልሰጠ የጠቀሱት ኢንጅነር ደመላሽ፥ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በላይ መጓተቱ ለችግር እየዳረገ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ መስሪያ ቤታቸው በከተማዋ ማንኛውም የመንገድ ቁፋሮና ግንባታ ከግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ድረስ እንዳይከናወን ከልክሏል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ብስራት በበኩላቸው ለግንባታው መጓተት የግንባታው ስፍራ አለታማ መሆን እና ግንባታውን የሚያከናውኑት በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች አቅም ውስንነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ መንዶች ባለስልጣን ከዚህ በኋላ ባስቀመጠው የክልከላ ቀነ ገደብ ውስጥ፥ ማንኛውም ግንባታ እንዳይከናወን እና የተጀመሩትንም ራሱ ተረክቦ እንደሚያጠናቅቃቸው ጠቁሟል፡፡

 

በአልዓዛር ታደለ