Artcles

ባለ ተስፋዋ አገር!

By Admin

June 29, 2017

ባለ ተስፋዋ አገር!

                                                      ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ በህገ መንግስት የምትመራ ሀገር በመሆኗ መፃዒ ተስፋዋ የተመሰረተው በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጡት ግቦች አማካኝነት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ መግባባቱ እየዳበረ መምጣት፣ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ መግባት ችላለች።

ህገ መንግሥቱ አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል። ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የመቀየስ ኃላፊነት ወድቆበታል።

በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ ደንግጓል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና እድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበትም እንዲሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል። በደርግ ሥርዓት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ሃብት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ ተንዷል። ዛሬ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተረጋግጦለታል። ነገም ባለ ተስፋ ነው።

በኢትዮጵያ የመሬት ስሪት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል አስችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል። ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  ተደርሷል። ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል። እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል።

የሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው። የህዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ቀዳሚ ዓላማዎች በመሆናቸው ህዝቦችንና ሀገራችንን ባለ ተስፋ አድርገዋታል።

ዛሬ የልማት አጀንዳ ለአገራችን እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ “የሞት ሽረት” ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ርብርብ እያደረገ ነው። ከአንዴም ሁለቴ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን በመንደፍ “የሞት ሽረቱን” ጉዳይ ወደ መሬት አውርዶ እየሰራ ነው።

በዚህም አብዛኛውን ህዝብ መሰረት ያደረገ ዕቅድ ነድፎ የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በማሳለጥ ላይ ይገኛል። በሀገራችን በተዘረጋውና በተመረጡ ጉዳዩች የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለበት የነፃ ገበያ ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓትም፤ የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ አገሪቱን ከነበረችበት ፈታኝ የድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማው አድርጎ እየሰራ ነው።

ገበያ መሩን የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ተከትሎ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሥራ ሥምሪት ፖሊሲዎች ተነድፈው በሥራ ላይ ውለው ውጤት እያስገኙ ነው። እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የሚያሳዩ የውጭ ባለሃብቶች በምን ዓይነት የስኬት መንገድ ላይ እየተረማመድን መሆኑን ጠቋሚዎች ይመስሉኛል።

እርግጥ በምጣኔ ሃብቱ ውስጥ ውስጥ የመንግሥት ዋና ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት ነው። መሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሃብት ልማት ማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎቶችን በመስጠት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ዕውን ሆነዋል። በአንፃሩም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ተግባራትን እንዲከናወኑ እየተደረጉ ነው።

እንደሚታወቀው ልቅ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት፤ ፈጣን፣ ዘላቂና ሰፊ መሠረት ያለው እድገት የማምጣት አቅም የሌለውና ብቻ አይደለም። ከዚህ በላይ የህዝብና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ጎራ እንዲሰማሩ እንደሚያደርግ ይታመናል። እናም በልማቱ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግዳሮት ለመፍታት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው።ይህ ጥረትም ሀገራችንንና ህዝቦቿን ባለ ተስፋ ያደረገ ነው።

ታዲያ እነዚህ ለማሳያነት ያነሳኋቸው የባለተስፋነታችን እውነታዎች ቢኖሩም ተግዳሮቶች የሉም ማለት አይደለም። እንኳንስ በታዳጊ ሀገር ውስጥ ቀርቶ ባደጉት አገራት ውስጥም  ቢሆን ችግሮች መኖራቸው አይቀርም። ዳሩ ግን የሀገራችን መንግስት የሚከተለው ስርዓት ራሱን በራሱ እያረመ የሚሄድ በመሆኑ ተግዳሮቶቹ የሚፈቱ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሳለጠ በሚገኘው ልማታዊ ስርዓት ችግሮች ዘላቂ እንዳይሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ በባለ ተስፋነታችን ላይ እምብዛም አሉታዊ ጫና አያሳርፉም። በመሆኑም የተገኘውን ሁለንተናዊ ለውጥ በማቀብ ባለ ተስፋነታችንን ነገም አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።