NEWS

ቦርዱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሰራጩት ወሬ የተሳሳተ መሆኑን አስታወቀ

By Admin

June 19, 2017

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች «በአገሪቱ ህጋዊ እውቅና አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፓርቲዎች ቁጥር 10 ብቻ ናቸው» በሚል እያሰራጩት ያለው ወሬ ፍፁም የተሳሳተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ቦርዱ እውቅና ሰጥቷቸው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 62 መሆናቸው እየታወቀ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች «ቦርዱ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ህጋዊ ናቸው ብሏል፤ ሌሎቹ ህጋዊ አይደሉም» በሚል ሆን ብለው ከሚያሰራጩት የተሳሳተ ወሬ ሊቆጠቡ ይገባል። ቦርዱ 62ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህገ ደንባቸው መሰረት ጉባዔ ማካሄድ አለማካሄዳቸውን በውስጠ ደንባቸው እየተመሩ ነው ወይስ አይደለም የሚሉትን እና በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2000 መሰረት የተደነገጉ ህጎችንም ጭምር አሟልተው የሚተገብሩና የማይተገብሩትን የመከታተል ስልጣን እንዳለው ተናግረዋል። እንደ ፕሮፌሰር መርጋ ገለፃ ቦርዱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ህጋዊ እውቅና ከተሰጣቸው 62 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 10 ፓርቲዎች ከላይ የተጠቀሱትን ህጎች እና ደንቦች ሙሉ በሙሉ ጠብቀው ተጉዘዋል፤ አብዛኞቹ ደግሞ ደንቦቹን እና ህጎቹን በከፊል የተገበሩና ያሟሉ ሲሆን፣ ጥቂት የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ደንቦቹን እና ህግጋቶቹን ሳይጠብቁና ተግባራዊ ሳያደርጉ የቀሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ለተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወር ሪፖርት በቀረበበት ወቅት በቅጡ ባለመረዳት አሊያም ሆን ተብሎ የሪፖርቱን መልዕክት በማዛባት የተሰራጨ ወሬ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ይሁን እንጂ ህጎችን እና መመሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ጠብቀው ከተጓዙት 10 ፓርቲዎች ውጪ ያሉትም ቢሆኑ አጓድላችኋል የተባሉትን ህግጋቶችና ደንቦች ደረጃ በደረጃ እያሟሉ መሆኑን አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ ሙሉ ህጋዊ እውቅና አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፓርቲዎች ብዛት 62 መሆናቸው ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ያሉት ፕሮፌሰሩ ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ አገራዊ ሲሆኑ 40 የሚሆኑት ደግሞ ክልላዊ ናቸው።   ሀብታሙ ስጦታው – See more at: