Artcles

ተመራጭ ያደረገን ፖሊሲ

By Admin

June 20, 2017

ተመራጭ ያደረገን ፖሊሲ

                                                      ታዬ ከበደ

የሀገራችን የዕድገት ተስፋ ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ብቻ ነው፡፡ ይህን ዕውነታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለዘመናት የህዝባችንን አንገት ያሰደፋውን ድህነት አሸንፈን ለድል ለመብቃት እየተደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ሊሆን የሚችለው የአካባቢያችን ቀጣና ያለመረጋጋት ችግር አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከአካባቢያችን ሀገራት የሚመነጨው የሽብርተኝነት አደጋንና የእርስ በርስ ጦርነትን መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥም ይህ አደጋ ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍለ አህጉሩ አካባቢ ለሚገኙ እንዲሁም ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምን ያህል አስጊና አስከፊ እንደሆነ በተጨባጭ በዓይናችን እያየን ያለነው ዕውነታ ነው፡፡

እናም አካባቢያችን ሁኔታ ምን ጊዜም በትኩረት በመከታተል በአንድ በኩል በጎ ተፅዕኖዎችን ለማስፋፋትና ለማጎልበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ ጎጂ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረቡ የአማራጮች ሁሉ አማራጭ መሆኑ አይታበይም፡፡ በቀጣናችን ካሉት ሀገሮች መካከል ጎረቤት ሀገር የሆነችው ሶማሊያ የአሸባሪዎች መፍለቂያና መናኸሪያ በመሆን ለአካባቢው ሀገራት በተለይም ለሀገራችን ስጋት ሆና መቆየቷ ከማንም የተሰወረ ዕውነታ አይመስለኝም፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት መንግስት አልባ በነበረችው ሶማሊያ የመሸጉ የተለያዩ የጦር አበጋዞችና አሸባሪ አክራሪ ቡድኖች፣ የገዛ ሀገራቸውን ህዝብ ሠላምና መረጋጋት ከመንሳት አልፈው የቀጣናውን ሀገራት በሽብር የማመስ ዓላማን አንግበው ሲሯሯጡ ነበር። ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች በሀገራችንና በጎረቤት ሀገሮች ያደረሷቸው የሽብር ጥቃቶች ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው።

መንግስት አልባ በነበረችው በያኔዋ ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት አጥታ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች— ምንም እንኳን ከጥቂት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ መረጋጋት ቢታይባትም፡፡ በዚህች ሀገር የመሸጉና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ አክራሪዎችና  አሸባሪ ቡድኖች የሶማሊያ ህዝብን ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናውን በማተረማመስ ጭምርም በርካታ የሽብር አደጋዎችን ማድረሳቸው አይዘነጋም፡፡ አሸባሪ ኃይሎቹ በኬንያ፣ በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳና በኢትዮጵያ ያደረሷቸው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች ምንኛ አሰቃቂ እንደነበሩም እንዲሁ።

በዚህም ሳቢያ ሶማሊያውያን በገዛ ሀገራቸው ለደህንነታቸው ዋስትና አጥተው፣ በየጎራው ያኮረፉ የጦር አበጋዞች ህገ-ጠብመንጃን ብቸኛው አማራጭ አድርገውባቸው እንዲሁም በጎሰኝነት የመከፋፈል ጣጣ ተጭኖባቸው ለሞት፣ ለእንግልትና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የያኔዋ ሶማሊያ ለአሸባሪ አክራሪ ቡድኖች ምቹ ምድር በመሆን የጦር መሳሪያዎች እንደ አሸን የሚለዋወጡባትና የሚቸበቸቡባት፣ አደንዛዥ እፆች ያለ ገደብ የሚዘዋወሩባት እንዲሁም ዋነኛ የኮንትሮባንዲስቶች መናኸሪያ ሆና ዘልቃለች፡፡

እርግጥ በቀድሞዋ ሶማሊያ በሀገሪቱ የመሸጉ አሸባሪ ኃይሎች የእስልምና አክራሪነትን ብሎም ሃይማኖታዊ መንግስትን ለማስፋፋት በአፍሪካ ቀንድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ ባይሳካላቸውም፡፡ ዛሬ ግን በሀገራችን መከላከያ ሰራዊት ያላሰለሰ ጥረትና በአሚሶም ኃይል የተቀናጀ እርምጃ ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ በአንፃራዊነት የሰላምን አየር እየተነፈሰ ነው። ይህ ሁኔታ ሀገራችን ለቀጣናው ሰላም ያላትን ቁርጠኝነትና በጋራ አብሮ የማደግ ፍላጎትን የሚያንፀባርቅ ነው።

በሌላ በኩልም ሰራዊታችን የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርዓታችን በአስተማማኝ እንዲጠብቅ ከተሰጠው ተልዕኮ ባሻገር፤ የጎረቤቶቻችንና የአካባቢያችንን ሠላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲጫወት ከተባበሩት መንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ተደጋጋሚ ጥሪዎች ይቀርቡለታል፡፡ ይህን ተልዕኮውን በዓለምና በአህጉር አቀፍ የሰላም ማስከበር ጥበቃዎችን በንቃት በመሳተፍ እየተወጣ ነው፡፡

መከላከያ ሰራዊታችን ለአብዬ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ በሁሉም ወገኖች አመኔታ ያገኘው ያለ ምክንያት አይደለም። የመንግሥታችን ሰላም ወዳድነት፣ የሚመራባቸው የሰላም ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የሚያከናውናቸው ተግባራት ለማንም ያልወገኑና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ውጤት ስለሆኑ ነው፡፡

ህዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ተቀብሎ በተሰማራባቸው የግዳጅ  አካባቢዎች ሁሉ በጠንካራ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባሩን በብቃት፣ በጀግንነትና በሚያኮራ ሁኔታ መፈጸሙ በመንግሥታቱ ድርጅትም ይሁን በሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ፅኑ እምነትንና አክብሮትን ያጐናፀፈውና ብቸኛው ተመራጭ ሠራዊት ሊያደርገው ችሏል። ይህ የሰራዊታችን ማንነትም የሀገራችንን ሰላም ወዳድነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና የተጫወተ ይገኛል።

እርግጥ እንደ ደቡብ ሱዳን ያሉ ሀገራት በዘር እና በአካባቢ ተወስነው በሚያደርጉት የእርስ በርስ ጦርነት ምን ያክል ንፁህ ዜጋዎችን ሰለባ እያደረገ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይህም ለሚደረገው የሰላም ጥረት የበኩሉን አሉታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱ አልቀረም። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ጋር ያለት የድንበር ማካለል ስራዎች ላይ ያለመረጋጋት ሁኔታዎች መፈጠራቸው የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ጭምር የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ማስገደዱም ሌላኛው ሁነት ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመታደግም ሀገራችን ከአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀረበላትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለማዋጣት ተስማምታለች። የተወሰኑትም ወደ ስፍራው በማቅናት የጎረቤት ደቡብ ሱዳን ህዝብን ሰላም በመታደግ ላይ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ያላትን ቀናዒ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

እርግጥ የምስራቅ አፍሪካን ቀውስ ለማርገብ የቀጣናው ሀገራት በሚያደርጉት ርብርብ እንደ ኤርትራ አይነቱ ፀብ ጫሪ ሀገር ጉዳዩን ይበልጥ በማወሳሰብ፣ የሃይልና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ ቀውሱን ለማብረድ የሚደረገውን ርብርብ አድካሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ያም ሆኖ ሀገራት በጎረቤት ሀገራትም ሆነ በተለያዩ ሀገራት ለሚፈጠሩ ችግሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ አኩሪ ተግባራትን ከውናለች፡፡ ይህም በአንድ ወገን እንደ ኤርትራ ዓይነት መንግስታት ቀጣናውን ለማወክ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር ያጋለጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችንን ሰላም ወዳድነት ያረጋገጠ ክስተት ሆኗል።

ሆኖም በእነዚህ በተባበሩት መንግስታትም ሆነ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ስር ብቻ ያሉ የሠላም ማስከበር ኃላፊነቶች አህጉሩ ለሚፈልገው የሠላምና የፀጥታ የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመፍጠር በቂ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ጎረቤት ሀገራት የራሳቸው የሆነ እና የጋራ የፀጥታ ሃይል በማቆቆም በድንበሮቻቸው እና በሀገራቸው ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ቀድመው መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአፍሪካ በአሁኑ ወቅት ይህን በመረዳት በአምስት ቀጣናዎች የሠላም እና የፀጥታ ሃይሎችን በማቋቋም ወደ ስራ ለመግባት የዝግጁነት ስራዎችን እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡ በዚህ በኩልም ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም የጋራ የሠላም እና የፀጥታ ሃይል “የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል” የሚል አካል እንዲቋቋም በማድረግ የበኩሏን ሚና ተጫውታለች፡፡ እነዚህ ሃቆች ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ተመራጭ እንድትሆን ያደረጓት ናቸው፡፡ ይህ ፖሊሲ ተመራጭና ተደማጭ እንድንሆን ያደረገን ነው፡፡