ተምሳሌት ይሁን
ይነበብ ይግለጡ
ብዙ ሀገራዊ ራእዮች አሉን፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃም ፈጣንና ስር ነቀል የኢኮኖሚ ለውጥና እምርታ በማምጣት ላይ ያለች ታላቅ ተስፋን የሰነቀች አብዛኛውን ማሳካት የቻለች የተቀሩትን ደግሞ ከድክመታቸው በተግባር ከተከሰቱት ፈተናዎች በመማርና የተሻለ ዘዴና መንገድ በመፈለግ በተሳካ ሁኔታ ለውጤት የሚያበቃትን ስራ በትጋት እየሰራች ያለች ሀገር ናት፡፡
በአብዛኛው አስደናቂና አስደማሚ የልማትና የእድገት ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ የእነዚህ ስኬታማ ውጤቶች ቁልፍ ያለው በቀረጸቻቸው የልማትና የእድገት ፖሊሲዎች ውስጥ ነው፡፡ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ እጅግ የገዘፉ ታላላቅ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ለቀጣዩ ኢትዮጵያ ትውልድ ታላቅ መሰረት የተጣለበት ሀገራዊ ፍቅርና ኩራቱን የሚያሳድግበት ስራዎች በስፋት ተሰርተዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ ከሰሞኑ የሚመረቀው የአዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ነው፡፡ የአዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ በአፍሪካ አህጉር በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው በቅርብ ቀናት ሙሉ በሙሉ ስራ ይጀምራል፡፡
የፓርኩ ግንባታ ሪከርድ ባስመዘገበ ሁኔታ ስራው የተጠናቀቀው በ9 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ሰኔ ወር ላይ ይመረቃል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የያዘውን ቁርጠኛ አቋም መሰረት በማድረግ እቅድ ተነድፎ ዲዛይኑ የወጣውም የተገነባውም የሚሰራውም የአየር ንብረትን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡
እጅግ ዘመናዊ የሆነ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በፓርኩ ውስጥ የሚጠቀማቸውን 90 በመቶ ውሃዎች በማከም እንደገናም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፡፡ፓርኩ በአፍሪካ የመጀመሪያው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትርያል ፓርክ ነው፡፡የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በቀጣይ ሊዘልቅ የሚችለው በመዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ መሆኑን አርከበ እቁባይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ገልጸዋል፡፡
በ2025 ሀገሪቱን በአፍሪካ መሪ የማኑፋክቸሪንግ ማእከል ለማድረግ የማይናወጥ ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን ይህም በበኩሉ ከፍተኛ የሆነና ተወዳዳሪ የኢንዱስትሪ መሰረትን ማስፋትን ይጠይቃል፡፡አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ልዩ በሁሉም አቅጣጫ ውሕድነት ያለው ወደ ውጭ ምርትን የሚልክ ኢንዱስትሪል ፓርክ የራእያችን ዋነኛው መሪና ማእከላዊ አካል ነው ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና ሽግግርን ለማረጋጋጥ እየሰራች ሲሆን ወደ ውጭ ምርቶችን የመላክ አቅሟን በማሳድግ በተመሳሳይ የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩን አቅም በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡የአዋሳው ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለሌሎችም በሀገሪቱ ውስጥ ለሚሰሩ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ሞዴል ይሆናል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርክ እድገት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሳይ ገመቹ በበኩላቸው መንግስት በመላው ሀገሪቱ በአጠቃላይ 10 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እቅድ የያዘ ሲሆን አላማው የስራ እድሎችን ማስፋት ገቢ ማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርኩን በሞዴልነት በመውሰድ መንግስት ተመሳሳይ ፓርኮቸን በኮምቦልቻ፤መቀሌ፤ቂሊንጦ ፤ቦሌ ለሚ2፤ ድሬዳዋና አዳማ በመገንባት ላይ ሲሆን የመቀሌና የኮምቦልቻው በቅርቡ ይመረቃሉ፡፡
ፓርኮቹን የያዙት 18 አለምአቀፍ መሪ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾችና ካምፓኒዎቻቸው እንዲሁም 8 የውስጥ ባለሀብቶች ናቸው ፡፡ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ያጋጠማቸውን ፈተናዎች በመጋፈጥ ልክ እንደ አዋሳው ኢንዱስትሪያል ፓርክ ፈጣን አፈጻጸም በመከተል በጀት፣ የሰው ኃይልና ገንዘብ ሳይባክን ወደ ሙስናና መዝረክረክ ሳይገባ ሰበብም ሳይደረደር ሀገራዊ የአፈጻጸም ውጤታቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡
ትልቁ ችግር መንግስት እቅዱን ለተሻለ የሀገር ልማትና እድገት ውጤት ቢያወጣም አስፈጻሚ ሆነው የሚቀመጡት ወገኖች ቃልና ተግባራቸው ሊገናኝ ባለመቻሉ ለእቅዱ መሰናከልና መጓተት ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው ችግሩ እየባሰና እየጎለበተ የሚሄድበት መሆኑ ነው፡፡በስራው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችል ችግሮች መሰናክሎች የሚጠበቁ ቢሆን በቅድሚያ በጥናቱ ውስጥ ተለይተው የሚቀመጡት ከነመፍትሔያቸው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት በስኬት ደረጃ ከነችግሮቻቸው የባቡር ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ጁቡቲ የተዘረጋው 765 ኪሎሜትር መስመር በ4ዓመት ተኩል ውስጥ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ መፈጸሙ በዓለም ደረጃ በጥቂቶች አገሮች ብቻ የሚከናወን ውጤታማ አፈጻጸም በመሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የከተማ ውስጥ ባቡር ሲሆን ውስብስብ ፈተናዎችን በመራመድ በአጭር ጊዜ መፈጸሙ እሰየው የሚያሠኝ ነው፡፡ በሀገራችን የተከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችም 82 በመቶ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸውና ቀሪው 18 በመቶ የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተለያዩ የአፈጻጸም ችግሮች ምክንያት መጓተታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ዛሬ ላይ ስራዎች በተሻለ ፍጥነት የመገስገስ ምልክቶች እያሣዩ ነው፡፡
ዛሬ ላይ በሀገር ደረጃ የመስኖ ስራውና የተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች በገዘፈና በፈጣን መልኩ በመሰራት ላይ መገኘታቸው ተስፋ ሰጪ ሀገራዊ ጉዞና እድገት ነው፡፡ከተሀድሶው እርምጃ ወዲህ የተመዘገቡ ለውጦች ናቸው፡፡
ባንጻሩ በቻይናና በመከላከያ ብረታብረትና እንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተያዙ ኩራዝ ቁጥር አንድና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፕሮጀክቶች በድፍረት የሚሰሩና በቅርቡ የሚጠናቀቁ ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡በአጠቃላይ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ያለባቸውን ፈተና በመቋቋም ወደ ተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እየደረሱ በመሆናቸው መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያከናውናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቀደም ሲል መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ለሁሉም ፕሮጀክቶቻችን የአዋሳው ኢንዱስትሪያል ፓርክ ስራ አጀማመሩና ስኬቱ ተምሳሌት እንዲሆን እንሻለን፡፡ይህች ሀገር አድጋና በልጽጋ ሰላምዋ ተጠብቆ ተከብራ ከመኖርዋ ለዜጎቿም የተመቸች ከመሆንዋ በላይ ማየት የምንፈልገው ምንም ነገር የለም፡፡