Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተምችን በህዝባዊ ንቅናቄ

0 775

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተምችን በህዝባዊ ንቅናቄ

ኢብሳ ነመራ

መጽሃፍ ቅዱስ  ተምች ቸነፈር የሚያስከትል የእግዚአብሄር ቁጣ መሆኑን  በተለየዩ መጽሃፍቱ ውስጥ ይጠቅሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ ቸነፈር ያስከተለ የተምች ወረርሽኝ ስለመኖሩ የተመዘገበ መረጃ ባላገኝም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተምች ወረርሽኝ በሰብል ላይ አስከፊ ውድመት ማድረሱን የሚያመለክቱ ወሬዎች  ግን ይሰማሉ። ተምች ዘንቧል የሚባልበት ዘመን እንደነበረም ሰምቻለሁ። ተምች የዘነበበትን ዘመንና ስፍራ ማወቅ አልቻልኩም እንጂ። የሩፋኤል ጸበል እንደሆነ የሚታመንበት ጷግሜ 3 የሚዘንበው ዝናብ እጅግ የሚፈለገው ተምች ያጠፋል በሚል እምነት መሆኑም ይታወቃል። እነዚህ ብጥስጣሽ እውነታዎች የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከተምች ጋር ያለውን ትውውቅ ያመለክታል። ተምች ለኢትዮጵያውያን ፈጽሞ ባዕድ የሆነ ጸረ ሰብል ተባይ አይደለም።

እንግዲህ ተምች የተለያየ ዝርያ ያለው ሲሆን፣ ከቢራቢሮ እንቁላል የሚፈለፈል ትል (አባ ጨጓሬ) ነው። ይህ ትል ኩብኩባ ሆኖ እድገቱን ሲጨርስ ክንፍ አውጥቶ ይበራል። ታዲያ ይህ የቢራቢሮ ውላጅ የሆነ ተምች እንደየዝርያው የተለያየ መጠን ያለው የሰብል ጥቃት ያደርሳል። በተለይ በወረርሽኝ መልክ ሲከሰት በማሳ ላይ ያለ ሰብልን ክፉኛ ይጎዳል። ይህም የምግብ እጥረት በማስከተል የቸነፈር ምክንያት ይሆናል።

ዘንድሮ ከሳህራ በታች ባሉ ከ20 በላይ የአፍሪካ ሃገራት የተምች ወረርሽኝ ተከስቷል። በኢትዮጵያም እንዲሁ። ይህ ተምች በሳይንስ ስሙ ስፖዶፔትራ ፍሩጊፔራ ወይም ፎል ይባላል። የትውልድ ሃገሩ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ደቡብ አሜሪካዋ አርጀንቲና የሚገኙ ምእራባዊ እርጥበታማ ሞቃት አካባቢዎች ናቸው። ይህ ተምች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ወደአፍሪካ ዘምቷል። አፍሪካ ውስጥ በመጀመሪያ የታየው ጥር ወር 2008 ዓ/ም ላይ ነበር፤ በምእራብ አፍሪካ ሃገራት፣ በተለይ በናይጄሪያ። ከአሜሪካ ወደምእራብ አፍሪካ የተጓዘው ከበቆሎ ጋር ተጭኖ ነው የሚል መላ ምት አለ። ቢራቢሮው በንፋስ እየተገፋ አትላንቲክን አቋርጦ ነው ወደምእራብ አፍሪካ የደረሰው የሚል መላ ምት የሚያስቀምጡም አሉ። የተጓጓዘው በምንም ይሁን ምን አሜሪካዊው ተምች አሁን ሃያ ያህል የአፍሪካ ሃገራት ላይ ወረራ ፈጽሞ ጥቃት እያደረሰ ነው።

ተምቹ በምእራብ የአህጉሪቱ አካባቢ ከታየ ከአንድ ዓመት በኋላ ጥር 2009 ዓ/ም ላይ ደቡብ አፍሪካ ደርሷል። ቢራቢሮው በቀን ከ100 እስከ 500 ኪሎ ሜትሮች የመጓዝ አቅም ያለው ይህ ተምች እስከ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ሊጓዝ እንደሚችል በአሜሪካ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ። ተመቹ ከአርጀንቲና እስከ ካናዳ የተጓዘባቸው ወቅቶች ተመዝግበዋል። አሁን ጥር ላይ ደቡብ አፍሪካ የነበረው ይህ ፎል የተባለ ተምች ወደሰሜን ጉዞውን ጀምሮ በሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ደርሷል። በዚህ ጉዞው ሃያ የአፍሪካ ሃገራትን ወሯል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ገደማ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ነበር።

ፎል የተባለው አሜሪካዊ ተምች ከ100 በላይ የተለያዩ ሰብሎችን ያጠቃል። በተለይ የሚያጠቃው ግን በቆሎና ማሽላን ነው። የሸንኮራ አገዳንም በተለየ ያጠቃል። በቆሎና ማሽላ ከ200 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ከሳህራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት ህዝቦች ዋና የምግብ ምንጭ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም በተለይ በስምጥ ሸለቆ ቆላማና ወይና ደጋ አካባቢዎች፣ በምእራብ እርጥበታማና በምስራቅ ደረቃማ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ ዋና የምግብ ሰብል በቆሎና ማሽላ መሆኑ ይታወቃል። ተምቹ በቆሎና ማሽላን በተለይ ያጠቃል ይባል እንጂ ሌሎች የሰብል ምርቶችንም አይምርም። ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ አኩሪ አተር፣ ድንች፣ ጥጥ፣ አትክልትና የተለያዩ ቅጠለ ሰፋፊ ሰብሎችንም ያጠቃል። በመሆኑም በአስቸኳይ ቁጥጥር ካልተደረገበት በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል። እስከዛሬ የተከሰቱት ድርቆች እንኳን መላውን የሃገሪቱን አካባቢዎች አጥቅተው እንደማያውቁ ልብ በሉ። ይህ ተምቹ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ያመለክታል።

ከአራት ወራት በፊት በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል የተከሰተው የተምች ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የጥቃት አካበቢውን በማስፋፋት ስድስት ክልሎችን አዳርሷል። በደቡብ ክልል ሁሉም ዞኖች፣ በአሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች፣ በአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ በጋምቤላ እና ቤንሻጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይ ተዛምቷል። በአጠቃለይ በእነዚህ ክልሎች በ35 ዞኖች በ235 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኝ በ146 ሺህ 320 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ሰሞኑን ደግሞ ወደ ትግራይ መዝለቁ ተሰምቷል።

በዚህ ምክንያት አሜሪካዊው ተምች በቁጥጥር ስር ካልዋለ የከፋ የምግብ እጥረት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። በዚሁ ጉዳይ ላይ በናይሮቢ ተካሂዶ የነበረ ስብሰባ ላይ የዓለም አቀፍ የበቆሎና ስንዴ ማሻሻያ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ቦዱፓሊ ፕራሳና የተምቹን አስፊነት ሲገልጹ “ሁኔታው የሳይንስ ልቦለድ ወደእውነትነት የመቀየር ያህል ሆኖ ይሰማኛል። ይህን ተባይ መቆጣጣር የሚቻል አይመስለኝም። በመሆኑም ጥቃቱ ከሁሉም ጸረሰብል ተባዮች ሁሉ የከፋ ነው የሚሆነው። የመቆጣጠሪያ መንገዶቹ ውስን ከመሆናቸው ባሻገር ውድ ናቸው” ብለዋል።

ተምቹ ካጠቃቸው የአፍሪካ ሃገራት መሃከል አንዷ የሆነችው ኡጋንዳ ብሄራዊ የግብርና ምርምር ተቋም ተመራማሪ የሆነው ሚቼል ኦትዊ ስለሁኔታው ሲገልጽ፣ “ተምቹ አብዛቻዎቹን መድሃኒቶች የተለማመደ በመሆኑ የአፍሪካ አርሶ አደሮችን ተስፋ እያስቆረጠ ነው። ተምቹን ለመከላከል የሚታዘዘው የመድሃኒት መጠን በቂ አልሆን እያለ በሁለትና ሶስት እጥፍ እየጨመሩ እየተጠቀሙ ነው። ይህም በአብዛኛው ውጤት እያስገኘ አይደለም። በመሆኑም መድሃኒቱን የሚረጩ አርሶ አደሮችና አካባቢው ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።” ብላል።

የዓለም አቀፍ የእርሻና ስነህይወት ሳይንስ ማዕከል ባለሞያ የሆነው ሮገር ዴይ የተባለ ተመራማሪ “ተመቹ በቀጣይ 12 ወራት ከሳህራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት በቆሎ ላይ በሚያደርሰው ጥቃት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ ያስከትላል” ብሏል። በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት የሰብል ተመራማሪ የሆነው ልዊስ ሆቭ ስለተምቹ ጥቃት ሲያብራራ፣ “ተምቹ ከቦታ ቦታ በፍጥነት ከመዛመቱ ባሻገር የሚያደርሰው ጥቃት የከፋ ነው። ተምቹ በሚከሰትበት አካባቢ የሚገኝ ሰብልን እስከ 80 በመቶ ማጥቃት ይችላል። ይህ ጥቃት በአንዳንድ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሊሆን ይችላል።” ብሏል።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ተምቹ አሁን በኢትዮጵያ በአብዛኛው አካባቢ ተከስቷል። የተምቹን መራባት በመከላከል በሰብል ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ማስቀረት ካልተቻለ በሃገሪቱ በከፋ የድርቅ ወቅት ከሚያጋጥመው የባሰ የምግብ እጥረት ሊከሰት የሚችልበት እድል አለ። በመሆኑም የተምቹን ጥቃትና መዛመት የመከላከሉ ተግባር ከአዘቦት የግብርና ስራ ባለፈ በዘመቻ መልክ ህዝባዊ ንቅናቄ መፈጠርን ይሻል። በተለይ ተምቹ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል በሚችልባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች – የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት፣ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች የህብረተሰብ አደረጃጀቶች ጸረ ተምች ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈልጋል።

የእርሻና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ተምቹን መከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች ብሎ ያስቀመጣቸው ርምጃዎች አሉ። ቀዳሚው ባህላዊ ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ተምቹን በእጅ እየለቀሙ በመግደል የሚከናወን ነው። አንድ የተምች ቢራቢሮ እስከ ሁለት ሺህ እንቁላሎችን በቅጠል ላይ ትጥላለች። በመሆኑም አንድ ተምች መገደል ከቀናት በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁለት ሺህ ተምቾች እንዳይፈጠሩ የማድረግ እርምጃ መሆኑ መታወስ አለበት። የሳይንስ ጥናት እንደሚያመለክተው ፎል የተባለው የተምች ዝርያ በአንድ የተክል ግንድ ላይ ከሁለትና ሶስት በላይ አይኖርም። ከዚህ በላይ ከሆነ እርስ በርስ ይበላላል። በመሆኑም እያንዳንዱ የበቆሎ ወይም የማሽላ ግንድ ላይ ያለ ተምች በመልቀም ተምቹን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይቻላል።

ተምቹን በእጅ ከመልቀም ጋር የሚከናወነው ሌላው ባህላዊ የመከላከያ ዘዴ፣ በሰብሉ ዙሪያ የሚገኙ ያለፈ እርሻ ቃርሚያን፣ አረሞችን፣ የሰብል ቅሪቶችን፣ በማረስ መገልበጥ ነው። መሬቱ ታርሶ ሲገለበጥ  በማሳው ላይ የነበረው ተምች መሬት ውስጥ ተቀብሮ በስብሶ ይጠፋል።

በባህላዊ ዘዴ የሚገኘወን ውጤት መነሻ በማደረግ ሳይንሳዊ ዘዴን የመጠቀም አማራጭም ተይዟል። ይህ የኬሚካል ርጭትን የሚመለከት ነው። ይህ በበቆሎ ወይም በማሽላ አገዳ ሙሽራ ውስጥ የሚደበቀውን ተምች የመግደል እድሉ አነስተኛ በመሆኑ፣ ውጤታማነቱ አስተማማኝ እንዳልሆነ ባለሞያዎች የናገራሉ። ዓለም አቀፍ መረጃዎች ደግሞ ተምቹ አብዛኛዎቹን የመከላከያ መደሃኒቶች ተለማምዷል። በዚህ ምክንያት ውጤታማነቱ አስተማማኝ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢና መድሃኒቱን በሚረጩ አርሶ አደሮች ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ አለ። ያም ሆነ ይህ የተምቹን ጥቃትና መዛመት ለመከላከል እንደአማራጭ የሚወሰድ እርምጃ ነው። የእርሻና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር በቂ ጸረ ተምች ኬሚካል መዘጋጀቱን አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ፎል የተሰኘው አሜሪካዊ ተምች ወረርሽኝ የአንድ አሀጉር፣ ወይም ሃገር ችግር ሳይሆን ዓለም አቀፍ አደጋ ነው። የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ ባወጣው ሪፖርት፣ አሁን በአፍሪካ የሚገኘው የተምቹ መዛመት ካልተገታ በሜድተራኒያን ባህር በኩል ወደአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ በኩል ወደተቀረው ኢሲያ መዛመቱ አይቀሬ ነው ሲል አስጠንቅቋል። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታትና በአጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተምቹን ጥቃትና መዛመት የመከላከል ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በሚገባ የማሳወቅ የፖለቲካ ስራ ሊከናወን ይገባል።

በአጠቃላይ አሁን በሃገሪቱ አብዛኛው አካባቢዎች የተከሰተውንና ጥቃት በማደረስ ላይ የሚገኘውን እስከ መቶ የሚደርሱ የሰብል አይነቶችን የሚያጠቃውን አደገኛ ተምች መከላከል ካልተቻለ የምግብ እጥረት መፈጠሩ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ይህን አደገኛ ተምች ለመከላከል ህዝባዊ ንቅናቄ ሊፈጠር ይገባል። ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ማደረግም ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy