Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተስፋ የሰነቀች ዘላይ – አርያት ዲቦ

0 532

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጊዜው 2003 ዓ.ም ነው በጋምቤላ ክልል የዞን የስፖርት ውድድሮች እየተካሄዱ ነው። ከተሳታፊ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዲት ረጅም ቀጭን ወጣት ሴት ከርቀት ታየች። ልጅቷ ከሌሎች ሴቶች የተለየ የአረማመድ ስልት አላት። በረጃጅም ቅልጥሞችዋ የጋምቤላ ለም አፈር በኃይል እየረገጠች ወደ ፊት ትስፈ ነጠራለች። በውል ለተመለከታት ሰው አረማመድዋና ወኔዋ  ለመዝለል የምትንደረደር ይመስላል። እርሷ ግን ገና ወደ ውድድር ስፍራ እየሄደች ነው።

በውድድር ስፍራም ተሰየመች፤ ወረፋዋ ደርሶ ተጠራች። ከርቀት እንደ ጀት እየተምዘገዘገች መጥታ በከፈታ ዝላይ 1 ሜትር ከ30 ሴንቲ ሜትር ከፍታ በመዝለል ተመልካቹን አስደመመች። ያን ዕለት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ባሰማራቸው ባለሙያዎች ዓይን ውስጥም ገባች፤ ድንቋ ዘላይ አርያት ዲቦ።

በጋምቤላ ክልል የተወለደችው የ21 ዓመቷ አርያት በ2003 ዓ.ም በክልሉ በተደረገው የዞን ውድድር በከፍታ ዝላይ የተሻለ ብቃት በማሳየትዋ ለጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ተመለመለች። በማሰልጠኛ ማዕከሉም ለአንድ ዓመት ያህል ከሰለጠነች በኋላ ለብሄራዊ ቡድን ተመረጠች።

ብሄራዊ ቡድኑን በመወከል በአፍሪካ የአዋቂዎች ውድድር በከፈታ ዝላይ የነሐስ  ሜዳሊያ አስገኘታለች፤ በአፍሪካ የታዳጊዎች ውድድርም  ሜዳሊያ ውስጥ መግባት ችላለች – አርያት።

ይህንን ስኬት ስታስመዘግብ አይናአፋር በመሆንዋ ምክንያት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋ አታውቅም። “ተስፋ የሰነቀች ብቅርዬ ዘላይ” ብትሆንም ስሟን አንሰቶ ተስፋዋን ያበሰረ፤ ስለእርሷ የመሰከረ የለም። አሁንም ቢሆን ከመገናኛ ብዙሃን ተቀራርባ ስለራሷ ለመግለጽ ድፍረት እንደሌላትና  ቋንቋ እንደሚያስቸግራት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር አውገታዋለች። ኢዜአ የዘላይዋን ታሪክና ልምድ ለማወቅ አሰልጣኝዋን ለማ ደበሌ እንደ ምንጭ ተጠቅሟል።

አርያት በ2006 ዓ.ም ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ወጥታ አሁን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ በከፍታ፣ በስሉስና በርዝመት ዝላይ እየሰለጠነች ነው። ከግንቦት ስምንት እስከ ግንቦት 13 ቀን 2009 ዓ.ም ለተከታታይ ስድስት ቀናት በአዲስ አበባ በተደረገው የ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ክለብዋን በመወከል ሁለት ክብረወሰን እና ሶስት የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የሻምፒዮናው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።

ስሉስና ከፍታ ዝላይ ክብረወሰን ያስመዘገበችባቸው የውድድር ዓይነቶች ሲሆኑ በምርኩዝ ዝላይ ደግሞ ወርቅ ያመጣችበት የውድድር ዓይነት ነው። በስሉስ ዝላይ በ2006 ዓ.ም በቻኑ ዳቪድ ተይዞ የነበረውን የስሉስ ዝላይ ክብረ ወሰን አርያት በስሟ ቀይረዋለች።

12 ነጥብ 79 ሜትር በመዝለል በቻኑ ዳቪድ ተይዞ የነበረው ክብረወሰን አርያት 12 ነጥብ 94 ሜትር በመዝለል ነው የግልዋን ማድረግ የቻለችው።

በከፍታ ዝላይ በ2008 ዓም ያስመዘገበችውን የ1 ሜትር ከ73 ሴንት ሜትር ከፍታ ዝላይ በዘንድሮ ውድድር  ዜሮ ነጥብ አንድ በማሻሻል ሁለተኛ ክብረወሰን አስመዝግባለች። በሶስት የውድድር ዓይነቶች ሶስት ወርቅ በማግኘት ኮከብ ሆና የተመረጠችው አርያት በተመሳሳይ ውድደር በአገር ውስጥ ከ42 ሺ ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት ያገኘች ብቸኛ አትሌት ለመሆን በቅታለች።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዝላይ አሰልጣኝ ለማ ደበሌ እንደሚሉት፤ አርያት በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም በአፍሪካና በዓለም ሻምፒዮናዋች ውጤታማ የመሆን ዕድልዋ ከፍተኛ ነው።

እንደ አሰልጣኙ ገለጻ፤ አንድ ስፖርተኛ በዝላይ ስፖርት ውጤታማ ለመሆን የስልጠና ዕድሜ ወሳኝ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዝላይ ውጤታማ ለመሆን በተከታታይ ከአስር ዓመታት በላይ በዚህ ስፖርት ስልጠና መውሰድ  አስፈላጊ ነው።

አርያትም በዚህ ስልጠና ውስጥ ከገባች ገና ስድስት ዓምቷ ነው። “ስለዚህ በቀጣይ ዓመታት በአፍሪካም ሆነ በዓለም ውጤታማ የመሆን ዕድል አላት” ብለዋል።

“ብቃትዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው” የሚሉት አሰልጣኝ ለማ፤ አሁን ላይ እስከ 1 ሜትር ከ80 ከፍታ የመዝለል ብቃት እንዳላት ነው የሚገልጹት።

“በዝላይ ውድድር ቁመት ወሳኝ ነው፤ አርያት 1 ሜትር ከ76 ቁመት አላት፤ በዓለም ሻምፒዮና ደግሞ  1 ሜትር ከ85 በላይ የሆኑ ስፖርተኞች ናቸው ውጤታማ የሚሆኑት” ይህም አርያትን ሊፈትን እንደሚችለ ነው የሚናገሩት አሰልጣኙ።

እንደዚያም ሆኖ ግን አርያት እስከ  1 ሜትር ከ90 ከፍታ የመዝለል አቅም እንዳላት ይናገራሉ። ይህን ለማሳካት ግን ድጋፍ አስፈላጊ ነው።

በተለይም “ምቹ ሜዳና ዘመናዊ መሳሪያዎች መሟላት ይኖርባቸዋል” ብለዋል አሰልጣኝ ለማ። ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ የራሱ የሆነ ሜዳም ሆነ የዝላይ ቁሳቁሶች የሉትም። ይህም በዕቅዳቸው ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ያስጠሩና ዝነኛ የሆኑ አትሌቶች ለመጥራት በጣም ቀላል ነው። “ዝነኛ ለመሆን እየተንደረደሩ” ያሉት አትሌቶች ለማግኘትም እንዲሁ። በ”ዝላይ ውጤታማ የሆኑና ለመሆን እየታገሉ” ያሉት ስፖርተኞች ለማግኘት ግን የዝላይ ስፖርተኞች አሳሽ ከመሆን በተጨማሪ ዕድለኝነምትን ይጠይቃል።

ይህን ስል ግን “ዘላይ የለም” ማለቴ አይደለም። በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አስገራሚ ባህላዊ ዘላዮች እንዳሉ ይታወቃል።

ነገር ግን እነዚህ በባህላዊ መንገድ የሚዘሉት ሰብስቦ በዘመናዊ መንገድ አሰልጥኖ ውጤታማ የሚያደርግ አሰልጣኝ የለም።

አርያት ዲቦ ግን ይህን ዕድል አግኝታ ከጋምቤላ የዞን ውድድር በኢትዮጵያ ደረጃ ደምቃ በአፍሪካና በዓለም ሻምፒዮናዋች ለመደመቅ እየጣረች ያለች ተስፋ የሰነቀች ዘላይ ናት።

በኢትዮጵያ ዕድሉን ያላገኙና ተስፋ ያላቸው ዘላዮች እንዳሉ የማይካድ ሀቅ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጯዎች ባለፈ ለሜዳ ላይ ተግባራት ትኩረት ሰጠቶ ቢሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ መሆን ይቻላል። በዝላይና በውርወራ ውጤት ለማምጣት እየጣሩ ላሉ ክለቦችም ዘመናዊ የመለማመጃና ማወዳደሪያ ቁሳቁስ እንዲኖራቸው ማገዝ ተገቢ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy