Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ታሞ የተነሳ እግዚአብሄርን ረሳ

0 269

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ታሞ የተነሳ እግዚአብሄርን ረሳ

ብ. ነጋሽ

ባለፈው ዓመት  ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረንም ። በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው  የአደባባይ ተቃውሞዎች በረደ ስንል እያገረሸ፣ አዚያ ነው ሲባል እየተዛመተ በአቀጣጫው እየተስፋፋ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። አውራ መንገዶች በድንጋይ ክምር እየተዘጉ የሰዎች የመንቀሳቀስ መብቶች ተገትተው ነበር። ሱቆች ተዘግተው፣ ገበያዎች ሳይቆሙ የዋለቡቻው ቀናት በርካቶች ነበሩ። ለማህበራዊ ጉዳይ መንቀሳቀስ የሚያስፈራበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።  ይህ ሁኔታ በብዙ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ስጋት አሳድሮ ነበር። በተለይ ይህ የአደባባይ ተቀውሞ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወደ ለየለት ሁከትነት ከተሻገረ ሊፈጠር የሚችለውን ውድመትና ሃገራዊ ቀውስ ለተገነዘቡ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነበር።

በሌላ በኩል፤ ስርአቱን የማፍረስ ፍላጎት የነበራቸው ወይም በይፈርሳል ምኞት ውስጥ የነበሩ “ተስፋ ለደርግ” ወገኖች፣ ሁከቱ በሃገሪቱ ዘላቂ ህልውና ላይ ሊያስከትል ይችል የነበረውን አይቀለበሴ (irrevesible) ቀውስ ማየት እስኪሳናቸው በስሜት እየተነዱ “ግፋ በለው” ሲሉ ነበር። ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማንኛውም መንገድ – በጦርነት፣ በሽብር ጥቃት፣ በከተማ ሁከት . . . ለማፍረስ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ደግሞ፣ ምንም ሳይለፉ ውጭ ሃገር ተወዝፈው ያገኙትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከሰማይ እንደወረደ ሲሳይ ነበር የቆጠሩት። የበርጩማ ላይ አዋጊ ኮማንደሮቻቸው ኮምፒዩተሮቻቻውን ከፍተው በማህበራዊ ሚዲያ ማዋጋታቸውን ተያያዙት። አንድ ከተማ ላይ በተደረገ ተቃውሞ አምስት ጥይት ከተተኮሰ፣ ሃያ ሰው ሞተ ብለው ያወራሉ። የአስከሬን ፎቶ፣ በዱላ ተደብድቦ የቆሰለ ሰው ፎቶ ከየትም ሃገር፣ በማንኛውም ጊዜ የተፈጸመ እየፈለጉ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ በሃገሪቱ መአት የወረደ አስመሰሉ። እዚሁ ሃገር ቤት ያሉ የስርአት ለውጥ ተስፈኞችም በስልክ ይህን ያህል ተገደለ፣ ይህን ያህል ታሰረ እያሉ እውነታውን በመቶ እጥፍ አያዛቡ የፈጠራ መረጃ ያቀብሉ ነበር።

እነዚህን የበርጩማ ኮማንደሮች በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቁትን፣ እንዲሁም በውጭ ያሉ የፅንፈኞች መደበኛ ሚዲያዎች (የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራምን ጨምሮ) የሚያሰራጩትን ያለወጉ የተጋነነና የፈጠራ ወሬ የሚከታተሉ ሃገር ቤት ያሉ ወጣቶች ደግሞ ሌላ የተቃውሞ አጀንዳ አገኙ። በመጀመሪያ ለተቃውሞ ያወጣቸው የስራ እድል እጦት፣ የማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ መሆን አለመቻል ወዘተ ነበሩ። በኋላ በበርጩማ ኮማንደሮቹና በጽንፈኛ ሚዲያዎቹ ውዥንብር ውስጥ ገብተው “በመንግስት የሚፈጸም ግፍ” የመቃወም አዝማሚያ እየያዙ መጡ። ውዥንብሩ ለዚህ ነበር የሚፈለገው።

እያደረ የበርጩማ ኮማንደሮቹ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ የኦሮሚያ ወጣቶችን ወደማዘዝ ተሻገሩ። ጃዋር መሃመድ የተባለው የበርጩማ ትግል ዋና ኮማንደር የተፈጠረው ይሄኔ ነበር። አሜሪካ በርጩማ ላይ ተቀምጦ እዚህ ወጣቶች ማንን መግደል እንዳለባቸው፣ የትኛውን ተቋም ማውደም እንዳለባቸው፣ ምን ይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው . . . ያዛል። ወጣቶቹ ይህን ተከትለው ለማውደም ይወጣሉ። በኋላ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎችም ወጣቱን ከለላ አድርገው አደባባይ መውጣት ጀመሩ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልልም የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ሁኔታው አልዋጥ ያላቸው ትምክህተኞች ግጭት ቀሰቀሱ። የበርጩማ ትግል ኮማንደሮችና ጥቂት መደበኛ ሚዲያዎቻቸው፣ ይህንንም ጉዳይ “አንድነት ፈረሰ፣ ጎጥ ተበራከተ፣ ምንትስ ቅብጥርስ”  ብለው ግጭቱ ወደስርአት ተቃውሞ ሁከትነት እድዲያድግ ለማድረግ ሞከሩ። ይህን ማድረጉ ባይሳካላቸውም፣ ከአማራም ከቅማንቴዎችም የንጹሃን ህይወት እንዲያልፍ አድርገዋል። የሚገርመው እነዚሁ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ለምን ተመለሰ በሚል “አንድነት ፈረሰ፣ መልካው ደፈረሰ” ሲሉ የነበሩ ትምክህተኞች፣ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” እንዲሉ፣ ትግራይ ውስጥ የሚኖረው የወልቃይት ህዝብ ምንም ጥያቄ ሳያነሳ ጎንደርና አሜሪካ ተቀምጠው “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ” በሚል መጨበጫ የሌለው ሰበብ ወጣቱን ቀስቅሰው ለሁከት ጎዳና እንዲወጣ አደረጉ።

በዚህ አኳኋን ወደአውዳሚ ሁከትነት የተሸጋገሩት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አልመጋገብ ብለው ሃገር አቀፍ መልክ አልይዝ አልችል አሉ። የሄኔ አንዱ ለሌላው አጥፊው የሆኑት የትምክህትህትና የጠባብ አመለካከት ቡድኖች ፍጥምጥም ፈጸሙ። የኦሮሞ ህዝብ በፌደራላዊ ስርአት ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ የእግር ውስጥ እሳት የሆነባቸው ትምክህተኞች፣ ኦሮሚያን እገነጥላለሁ ብሎ ከሚንቀሳቀሰው ኦነግ ጋር ተጋቡ። የጋብቻው መደረሻ ኢትዮጵያን ሃገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ ማፍረስ ነበር። የሃገር ማፍረስ ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽመው መሳሪያቸው ደግሞ በስራ አጥነት፣ በመልካም አስተዳደር መጓደል፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ አለመስተካካል የመረረ ቅሬታ ያደረበት ወጣት ኢትዮጵያዊ ነበር።

ይህን በትምክህተኞችና በጠባቦች ሃገር የማፍረስ ፍላጎት የሚመራ ሁከት ለመግታት አይነተኛው መንገድ መሳሪያቸውን ማስጣል ነበር። መሳሪያቸው በመንግስት ላይ ጫን ያለ ቅሬታ ያደረበት ወጣት ነበር። ወጣቱን ከትምክህተኞችና ጠባቦች ለመነጠል ፍላጎቶቹን ማሟላት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር። የወጣቶች ቀዳሚና መሰረታዊ ፍላጎት ደግሞ የስራ እድል ማግኘት ነበር። መንግስት በተለይ ወጣቱ የሰራ አጥነት ችግር እንዳለበት፣ በዚህ መክንያት ያደረበት ቅሬታና ወደተቃውሞ መሸጋገሩም ተገቢ መሆኑን ተቀብሎ ችግሩን ለመፍታት አቅዶ ተነሳ። በተለይ አሁን ሊያበቃ ከአንድ ወር በታች ጊዜ የቀረው የ2009 በጀት ዓመት ወይም የመንግስት የስራ ዓመት ሲከፈት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ያዘጋጀውን እቅድ በይፋ አሳወቀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዓመቱ የስራ መክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር ይህን በይፋ አሳውቀዋል። ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በምክር ቤቶቹ የስራ ዓመት መጀመሪያ የጋራ ስብሰባ ላይ የሚከተለውን ነበር የተናገሩት።

የሃገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል። በዚህ መሰረት፣ መንግስት በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል። ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። ለወጣቶች የስራ መነሻ ይሆን ዘንድ ከተመደበው ፈንድ ጐን ለጐን የስራ ፈጠራው የሚያተኩርባቸው መስኮች ተለይተውና ከወጣቶች ጋር ተመክሮባቸው መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው ይደረጋል።

እንግዲህ ይህ ከላይ የተገለጸ የወጣቶች የስራ ፈጠራ እቅድ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለበት የ2009 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ቀናት ነው የቀሩት። አሁን ጥያቄው ይህ ለወጣቶች ቃል የተገባ የስራ እድል ፈጠራ ምን ያህል ተሳክቷል የሚል ነው።

የ2009 በጀት ዓመት ያለፉ ዘጠኝ ወራት ወጣቶችን ከሃገሪቱ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸው አይካድም። ከእነዚህ ተግባራት መሃከል የወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቷል። የ10 ቢሊየን ብር የወጣቶች ስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። በአዋጁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈንዱን በፌደራል መንግስት ስም እንዲያስተዳድር ሃላፊነት ተሰጥቶታል። በአዋጁ መሰረትም ብድሩ በአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት አማካኝነት የሚፈጸም ይሆናል። ተቋማቱ በማይገኙበት ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቋማቱን ተክቶ እንዲሰራ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ18 ቢሊየን ብር የ2009 ተጨማሪ የመንግስት ባጀት ሲያጸድቅ፣ ከዚህ ውስጥ 5 ቢሊየኑ ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲሆን ወስኗል። ይህ ባጀት ለእያንዳንዱ ክልል ባላቸው የስራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር ልክ ተከፋፍሏል። ክልሎቹም ይህን ከፌደራል መንግስት የተመደበላቸውን ተዘወዋሪ ፈንድ ለዚሁ ዓላማ ራሳቸው ከመደቡት ባጀት ጋር አዳምረው ለስራ ፈጠራ የሚውል ባጀት በእጃቸው ይዘዋል። ወጣቶች ሊሰማሩባቸው ይችላሉ ተብለው የታሰቡ የስራ መስኮችም የተለዩበት ሁኔታ አለ። ይህ ብቻ አይደለም በቅርቡ ደግሞ ለወጣቶች የአጭር ጊዜ የሞያ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

አሁን ትልቁ ጥያቄ ተንቀሳቃሽ ፈንዱን በመጠቀም ምን ያህል ወጣቶች የስራ እድል ተፈጠረላቸው? የሚለው ነው። በኦሮሚያ አበረታች እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የሚያመለክቱ እውነታዎች አሉ። ክልሉ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ወደ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለወጣቶች የስራ ፈጠራ በብድር ሰጥቷል። የኦሮሚያ ክልል ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ በህገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ መሬት በማስመለስ ለወጣቶች እንዲሰሩበት ሰጥቷል። በዚህም ከ197 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል አግኝተዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ በህገወጥ መንገድ የተያዙ የማእድን ማውጫዎችን ለወጣቶች የሰጠበት ሁኔታ አለ። በሊዝ ፋይናኒስንግ የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ የተለያዩ ማሺነሪዎች ለወጣቶች ተሰጥተዋል።

በሌሎች ክልሎች ግን አዲስ አበባን ጨምሮ ከዝግጅት ያለፈ ይህ ነው የሚባል ተግባር መከናወኑን የሚያመለክት ይፋ መረጃ የለም። ወይም በተጨባጭ ያከናወኑትን ተግባር አላሳወቁም። ያም ሆነ ይህ በያዝነው ዓመት በወጣቶች የስራ ፈጠራ ሊከናወን የነበረው ተግባር ከዝግጅት ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሳይታይ ዓመቱ ተገባዷል። በበዙ አካባቢዎች ተስፋ አድሮባቸው የነበሩት ወጣቶች አሁን አሁን ተስፋ ወደመቁረጥ እየሄዱ መሆኑን የሚያመለከቱ ሁኔታዎች አሉ። በዚህ ሳቢያ ወጣቶች መንግስት ላይ አመኔታ እያጡ ነው። ይህ ደግሞ አደጋ አለው፤ አምና ያለፍንበት አደጋ። እናም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች ተስፋ ወደመቁረጥ እየተሸጋገረ፣ በመንግስቱ ላይ ያለው አመኔታ እየተሸረሸረ የመጣው ወጣት ድንገት ከመቆጣቱ በፊት ሊፈጥኑ ይገባል። አያያዛቸው የአምናውን የወጣት ቁጣ የረሱ ይመስላል፤ “ታሞ የተነሳ እግዚአብሄርን ረሳ” እንዲሉ።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy